Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Wednesday, 04 April 2012 08:52

እውነተኛ ‘ኑሮ’ና ልብ ወለድ ‘ፊልም’ …

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ለጿሚዎች…ጾሙ ተጋመሰ አይደል! ‘እውነተኛው ጾማችን’ ከጀመረ የከራረመ ቢሆንም… እንዲሁ ለአእምሯችን ‘ተጋመሰ’ ማለት አሪፍ አይደል! (በየኃይማኖት ተቋማቶቻችን ገብቶ ወገን ከወገን የሚያናከሰውን ጋኔን አንድዬ እስከወዲያኛው ያስወግድልንማ! ኽረ… በዚህ በሰለጠነ ዘመን፣ ስንት ራስ ምታት ጠፍሮ በያዘን ዘመን እንዲህ አይነት መካረሮች ደስ አይሉም!)
ስሙኝማ… ዘንድሮ ‘ቦተሊካው’… አለ አይደል… ‘ኮሜዲ’ ነገር አልሆነባቸሁም! ልክ ነዋ….በቃ፣ ወላ ጅራት፣ ወላ ምናምን የሌለው ነገር!.. (በእርግጥ ለምን ይዋሻል፣ ሲብስበት ቀንድ ነገር የሚያበቅል የሚመስለንም አለን!) አንዳንዴ እኮ “ማን ምን እንደሚል” ግራ ይገባችኋል፡፡ በፊት በሶሺሌ ዘመን እኮ… ‘ቦተሊካ’ ላይ “አጠቃቀስኩ፣” “ግንባር አሳይቶ አገጭ” ምናምን ነገር የለም፡፡ በቃ… ፊት ለፊት ነው፡፡ “ዓለም የወዛደሮች ትሆናለች”… አለቀ፣ ትሆናለች፡፡ (ምን እንዳናመጣ ነው!) “የምታጣው ሰንሰለትህን ነው…” አለቀ፣ ሰንሰለትህን ነው፡፡ (እኔ የምለው… “በሊዝ ምናምን የምታጣው ጓሮና፣ የኩችና ቦታ ምናምን የለም” ማለታቸው ነበር እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…)  እናላችሁ…ያኔ “መሀረቤን አያችሁ ወይ!” “አላየንም…” ምናምን ነገር የለም፡፡
ዘንድሮ፣ ነገርዬው ሁሉ የ‘ከት ኤንድ ፔስት’ ዘመን ሆነና፣ አንደኛ “ዓለም የማን እንደሆነች” ግራ ገብቶናል፤ ሁለተኛ እንደ ሰንሰለቱ የምናጣው ሳይሆን የማናጣውና “የቀረን ነገር” መኖር አለመኖሩን የሚነግረን አጥተናል፡፡ (እግረ መንገዴን…‘ከት ኤንድ ፔስት’ ከጠቀስን አይቀር… ተዉት ‘ድንቅ ፊልም’ ምናምን የተባሉ ማስታወቂያዎቻቸውን የምንሰማቸው ቀርቶ ‘ሬጉሌሽኑ’ ምናምኑ ሁሉ “ቆርጦ ለጥፍ” እየሆነ ግራ ገብቶናል፡፡)
እናላችሁ ‘ቦተሊካ’ የሆነ ኮሜዲ ነገር እየሆነብን ተቸግረናል፡፡
ደግሞላችሁ…በፊልም ‘ልብ አንጠልጣይ’ ምናምን የሚሉት ነገር አለ አይደል… እኛም በጣም ሰፋፊ ወንበሮች ላይ ያሉ ‘የቦሶቻችን’ ነገር ‘ልብ አንጠልጣይ’ ሆኖብናል፡፡ (ለመረጃ ያህል… ብዙም የማናንጋጥጠው “አንገታችን ሊቀጭ ይችላል” ብለን ስለምንፈራ መሆኑ በሀርድዌርና በሶፍትዌር ተመዝግቦ ይያዝልንማ!)  እናላችሁ…ጧት የተባለው ያልተመቸን ነገር አመሻሽ ላይ በምን መልክ ‘ማሻሻያ’ ተደርጎበት እንደሚብስበት ስለማናውቅ… ነገርዬው ሁሉ ‘ልብ አንጠልጣይ’ ሆኖብናል! ስሙኝማ…በተከለሱ፣ በተከላለሱ ነገሮች ዓለምን ሳንመራ እንቀራለን፡፡ የዘንድሮ ዋና ምክር…  “ነገ ምን እንደሚሉ ስለማይታወቅ ቶሎ በል…” ምናምን ነው፡፡ ከዚህ የባሰ ‘ሰስፔንስ’ አለ!
እኔ የምለው…አንዳንዴ ሳስበው የቦሶቻችን’ ነገር ለራሳቸውም… አለ አይደል… ‘ልብ አንጠልጣይ’ የሚሆንባቸው ይመስለኛል፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…ደግሞ ለሳቅ ‘የጀርባ ትርጉም’ እስኪሰጠው ድረስ ቂ…ቂ…እንበል እንጂ!) ልጄ…ከ‘ናይት ኦን ዘ ታውን’ መልስ ጠዋት ቢሮ ሲገቡ ጠረጴዛ ላይ ምን አይነት ደብዳቤ እንደሚጠብቃቸው አያውቁማ፡፡ የዘንድሮ ብዙዎቹ የ“ደህና ሰንብት” ደብዳቤዎች ደግሞ ካልቾ ከመቅመስ አይተናነሱም ሲባል ሰማሁ ልበል? (የናፍቆት ጥያቄ አለን…የለመድናቸው ‘ፊቶች’ ከአደባባይ ሲጠፉብን ሆዳችንን ባር፣ ባር ስለሚለን…አትጥፉብንማ! የውጪ ሬደዮ ጣቢያ መጎርጎር ሰለቸና!)
ስሙኝማ… ‘ሆረር’ ፊልም ማየት የማትወዱ… ብትለማመዱ አሪፍ ነው፡፡ አሀ…ሆረር ከሲኒማ ስክሪን ወደየጓዳችን ገብቷላ! ልጄ ዘንድሮ… የአቅምን ቋጥሮ ገበያ ወጥቶ መመለስ ‘ሆረር’ ሆኖላችኋል! እንደውም ዘንድሮ ድንጋጤ ማማተብ ከቤተክርስትያን ይልቅ በየገበያው በዝቶላችኋል!  የምር… ጫማ እግር ላይ እያለ ድርድር ከሚካሄድበት ሰፈር… ገና ከህንጻው በር ስትገቡ ከዘቡሌ ጀምሮ ጫማችሁ የሚገመገምበት መገበያያ ስፍራ ሁሉ…የሚጠራው ዋጋ ‘ሆረር’ ሆኗል፡፡  አለ አይደል… ዋጋ ሲነገረን ፊታችን ላይ የሚታየው ‘ድንጋጤ’  የ‘ትዋይላይት’ ፊልሞች የሚሠሩባቸው ጫካዎች ውስጥ በግዴታ የተወረወርን ነው የሚያስመስለው፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… እውነተኛው ኑሯችን ውስጥ ‘አክሽን’ ፊልም ነገር የሆነው ምን መሰላችሁ…እንትናዬዎችን ያለመግባቢያ ሰነድ መንጠቅ! ቀላል መነጣጠቅ ነው እንዴ ያለው! ምን ይገርምሀል አትሉኝም… ዘንድሮ መነጠቅና መንጠቅ መልሱ “ሶ ኋት!” ነገር ሆኖ ይረፍ! እኔ የምለው… “በእናት አገርና በሚስት የለም ዋዛ!” አይነት ነገር ቀረ እንዴ!
(ስሙኝማ… በፊት ጠርጣሪ ባሎች “ይሄ ዕቁብ፣ ማህበር እያልሽ በየመንደሩ የምትዞሪውን ነገር ተይ ብያለሁ!” ምናምን ይሉ ነበር፡፡ ዘንድሮ ተለውጦ ምን ሆኗል መሰላችሁ… “አሁን አንቺ ጂም የምትገቢው የትኛው ክብደትሽን ልትቀንሺ ነው! ወንድ ፍለጋ ነው እንጂ!” እናላችሁ…‘ውሽሜነት’ በማህበር የብርጭቆ ጠላ ሳይሆን በጂም የጠርሙስ ውህ እየሆነላችሁ ነው! እናላችሁ… እንትናዬዎችን በተመለከተ የቀለጠ ‘አክሽን’ እንዳለ አያችሁልኝ አይደል!)
ደግሞላችሁ… አሁን፣ አሁን ብዙ የምትሰሟቸውና የምታነቧቸው ‘ዜናዎች’፣ የሆነ ‘ታሪካዊ ልብ ወለድ’ ነገር አይመስሏችሁም! ልክ ነዋ… ‘ታሪካዊ ልብ ወለድ’ ሲጻፍ መነሻውን ይዞ አይደል ‘ክሬቲቪቲ’ የሚጦፈው!… የዘንድሮ ብዙ ‘ዜና’ም መነሻውን ይዞ ‘ክሬቲቪቲው እየጦፈላችሁ ነው፡፡ ዕድሜ ለዓረብሳት እንጂ ‘ጦጣ’ ሆነን ቀርተን ነበር እኮ!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… በደህናው ዘመን እኮ ‘ሮማንስ’ ፊልም ለማየት ሰኒማ ቤቱ ግጥም ይል ነበር፡፡ ዘንድሮ ‘ሮማንሱ’ ወደሌላ ቦታ ሄዶላችኋል፡፡ (ያልገባን ነገር አለ… የአገራችን ፈልም ሁሉ ‘ሮማንቲክ ኮሜዲ’ ካልተባለ ግብሩ የገቢውን ዘጠና በመቶ ይሆናል የሚል መመሪያ ነገር አለ እንዴ! ግራ ገባና! ወይስ ‘ሮማንቲክ ኮሜዲ’ ማለት በፊልሙ ዓለም እንደ ‘ጆከርነት’ እያገለገለ ነው?) እናላችሁ…ዘንድሮ የስልጣንና የፍራንክ ነገር የእነ “ላቭ ስቶሪ”ን ታሪክ የሚያስንቅ ‘ሮማንስ’ ሆኗላችኋል፡፡ ልክ ነዋ… አገር ሁሉ ከስልጣንና ከገንዘብ ጋር ‘አሪፍ ሮማንስ’ ይዞታላ! ምን እናድርግ… የዕቁብ ጸሀፊ እንኳን ወንበሯ ላይ ሙጭጭ “አርፌ የተኛሁትን በሬ አታድርጉኝ አውሬ!” አይነት ነገር ሲል ከዚህ የባሰ ‘ሮማንስ’ አለ እንዴ!
የቢዝነስ ነገር ደግሞ ምን ሆኗል መሰላችሁ… ‘ሳይለንት ፊልም’፡፡ ቀላል እረጭ ብሏል እንዴ! የምር… ልክ ነዋ… እንደ ዘንድሮ ቢዝነስ ደንዝዞ የሚያውቅም አይመስል!  ለነገሩ…ቦርሳችንም፣ የእህል ጆንያና ማዳበሪያችንም እኩል ተራግፈው ኪሳችን እየነተበ ሲሆን ጆንያና ማዳበሪያዋ በቅርቡ ወደ መረብ ኳስ መረብነት መለወጣቸው አይቀርም፡፡ ሀሳበ አለንማ…የእግር ኳስ ክለቦች ሁሉ የመረብ ኳስ ቡድን እንዲያቋቁሙ የሚያስገድድ ህግ ይውጣልንማ! ‘ሺህ ቀዳዳ’ ጆንያና ማዳበሪያዎቻችንን ቸብችበን ቢያንስ ፌጦና ድንገተኛ እንገዛበታለን! (በቀደም በመንገድ ላይ ሊመዘን የነበረውን ጓደኛውን “ለምን ገንዘብህን ታጠፋለህ፣ እኔ በአንድ እጄ አንጠልጥዬ ልመዝንህ እችላለሁ፣” ያለው ሰው የምር ተመችቶኛል፡፡ ልክ ነዋ…በአንድ እጅ ‘ተንጠልጥሎ’ መመዘን እየተቻለ ስሙኒና ሽልንግ ለምን አለአግባብ ይውጣ!
ጥርጣሬ አለኝ…ባለሚኒባስ ታክሲዎች በራሳቸው ውስጥ ለውስጥ ያልተጻፈ ሰርኩላር ነገር ያስተላለፉ ይመስለኛል፡፡ አለ አይደል…“የሀበሻ ክብደት ላባ እየሆነ ስለሄደ በሰው ቁጥር ስንጭን ታክሲዎች የአቅማቸውን ግማሽ ስለማይጠቀሙ ቁጥሩ ቀርቶ በክብደት እንጫን፣…” የተባባሉ ይመስለኛል፡፡ አሀ… በየወንበሩ ሦስት እየሆንን ‘ዘና’ ብለን እየተጓዝን ነዋ! በቀን ሦስቴ የምንበላበት ‘ዘመን’ ገና በከፍተኛ ናፍቆት እየተጠበቀ እያለ… ክብደቱን ከየት እናምጣ! ክፋቱ የክብደት ኮፒራይት ምንተፋ የለ!
እኔ የምለው… የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… በቀደም “ጤፍ ሺ ሁለት መቶ ምናምን…” ምናምን የሚል ‘ታሪካዊ ልብ ወለድ’ ዜና ነበር አሉ፡፡ አንድ ጥያቄ አለን… እንዲህ የሚሸጥበት አገሩ ይነገረንና በእግርም ቢሆን ሄደን እንገዛለን! ነው ወይስ… “አድማጮቻችንን ዘና ለማድረግ…” ተብሎ  የቀረበ የ‘ሾርኒ ጆክ’ ነው! አሁን እኮ…አይደለም ነፋስ የሚያወዛውዘው ነገር ያጣበት ጓዳችንን… ‘ወዛችንም’ መመስከር ጀምሯል፡፡ስሙኝማ የወዝ ነገር ካነሳን አይቀር… ከተማው እንደሁ እየለየለት ነው፡፡ አቋራጭ ፈልጋችሁ ወይም መንገድ ጠፍቷችሁ በሆነ አሪፍ የመኖሪያ አካባቢ መሀል ስታልፉ ዘበኞች የሚያፈጡባችሁ ሰፈሮች እየበዙ ነዋ! ‘ወዛችን’ ከዚህ በላይ ምን ያጋልጠን! (እነ እንትና… “የአራት ኪሎ አራዳ፣” “የገዳም ሰፈር ጮሌ” “የውቤ በርሀ ፋስት” ምናምን ስትሉ በረሀ ላይ ቀራችኋት! እስቲ ሁለት እጃችሁን ኪሳችሁ ከታችሁ በእንትን ሰፈር መሀል እለፉ! ድሮ እኮ…አለ አይደል… የ‘ሀብታም ግቢ’ ምናምን ስለምናውቅ አጥሩን እንኳን እንዳንነካ ራቅ ብለን እናልፍ ነበር፡፡ ዘንድሮ እኮ ጭራሽ… ‘የሀብታም መንገድ’ አይነት ነገር እየተፈጠረ “እግረኝነት” እንኳን ችግር መጣባት!)እናላችሁ… ነገርዬው ሁሉ የት ጀምሮ በየት በኩል ወደየት እንደሚሄድ ግራ እየገባን ስለሆነ… የዘመን አቆጣጠር እንደ ዓመተ ዓለም ወደኋላ ይሁንልን፡፡ በቃ…መንሸራተታችን ካልቀረ ከዜሮ ይጀምርና አንደኛውን ጭልጥ ብለን ወደ ኔጌቲቩ እንገባለና! (ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…‘የዕድሜ እኩያነት’ ዘንድሮ የሚመጣበት መንገድ የሆነ አሪፍ ነገር ነው፡፡ እንዴት መሰላችሁ…እንትና ከ‘ትዌንቲ ምናምን’ ይነሳና ሁለትና ሁለት ተኩሏን ወደ አንድ እያጣፋ  ወደ ላይ ይንፏቀቃል፤ ሌላኛው ደግሞ ከ‘ፎርቲ ምናምን’ ሁለትና ሁለት ተኩሏን እየሸረፈ በኋላ ማርሽ ይንደረደርና ምን ላይ ይገናኙ መሰላችሁ… ‘ሠርቲ’ ላይ! እና አብሮ አደግ ሆኑ ማለትም አይደል! ቂ…ቂ…ቂ…)
እናማ…ይኸው ‘እውነተኛው ኑሯችን’…አለ አይደል… የ‘ልብ ወለድ ፊልሞችን’ መጠሪያዎች  ተውሶ አረፈላችሁ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 2397 times Last modified on Friday, 06 April 2012 11:16