Saturday, 15 April 2017 13:23

ዝክረ ጃጋማ ኬሎ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  ከአዘጋጁ ፡-
    ታላቁ አርበኛ ሌተናል ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው፣ ባለፈው መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም በተወለዱ በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን የቀብር ስነ ስርዓታቸውም ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞችና በርካታ የአዲስ አበባ ከተማ
ነዋሪዎች በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ባለፈው እሁድ ሚያዝያ 1 ቀን መከናወኑ
ይታወሳል፡፡

                 ኦፈን ያ ጃጋማ!!
ኦፈን ያ ጃጋማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
ጣሊያን ግራ ገባው መብረቅ አይጨበጥ
ሲያስገመግም እንጂ አይታይ ሲያደፍጥ
ከቶ ምን ፍጥረት ነው እንዲህ የሚያራውጥ!!
ደንዲ አፋፉ ላይ ታይቷል ሲባል ጀግናው
ግንደበረት ወርዶ ጣልያንን አጨደው።
በቡሳ አቋርጦ… በሺ ላይ አድፍጦ
ዱከኖፍቱ አድሮ ጨሊያ ላይ ማልዶ…
ቦዳ አቦን ተሳልሞ ጊንጪ ላይ ብቅ አለ
በጠራራ ፀሐይ መብረቁን ነደለ።
‘ካፒቴኖ ጃጋማ… ካፒቴኖ’ ጣሊያን ቢማፀነው
አገሬን ሳትለቅ ሰላም የለም አለው።
ተመለስ ጃጋማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
ባንዳ ተልከስክሶ ለጠላት ሊሸጣት
አገሬን ሲያስማማት
ክብሬን ሊያዋርዳት
‘ኢንተኡ ፣ ዲዴ’ ብሎ ጃጋማ ካለበት
በቁጣ ገንፍሎ መብረቁን ጣለበት።
ጠላትሽ ኢትዮጵያ ማደሪያ የለውም
የጃጋማ መብረቅ ምቾት አይሰጠውም።
የጠላት ጦር ሰፈር በጭንቅ ተሽመድምዶ
በጠራራ ፀሐይ መብረቅ መጣል ለምዶ
ጃጋማ ጃጋማ ጃጋማ ተወልዶ!!!
ኦፈን ያ ጃጋማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
         (ከታሪኩ አባዳማ ሚያዝያ 1 ቀን2009)
(ምንጭ፡- ጃጋማ ኬሎ - የበጋው መብረቅ/ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ)

Read 2771 times