Saturday, 15 April 2017 13:21

አዙሪት

Written by  በግርማ ይ. ጌታኹን
Rate this item
(6 votes)

(ደራሲ - ነገሪ ዘበርቲ፣ ኅትመት - ዐዲስ አበባ፣ 2008 ዓ.ም) ቋንቋ-ነክ ሒሳዊ ዳሰሳ
                       
     «አዙሪት»ን ያነበብኩት በቅርብ ሰሞን ነው። ልቦለዱ ታትሞ ገበያ ከወጣ ግን አንድ መንፈቅ ዐልፏል፤ (መጽሐፉ ውስጥ በተጠቀሰው የኅትመት ጊዜ ሲሰላ)። ልቦለዱን የሚመለከቱ ዳሰሳዎች አላነበብኩም፤ የታተሙ ሊኖሩ እንደሚችሉ ግን እገምታለኹ። የኔው ከሌሎች ቀዳሚ ዳሰሳዎች ቢዘገይም የተለየ አተያይ - ቋንቋ-ተኰር በመኾኑ - ሊቀርብ ይችላልና እነሆ። ወዲህም ዳሰሳ በባሕሪው ግለኛ ነውና በመቼቱ አማላይነት፣  በታሪኩ ጭብጦች ጕልሕነት መጽሐፉ እንዲስበኝ ያደረጋቸውን ስሜቶች እግረ-መንገዴን ለአንባቢ ማጋራት  መልካም ይመስለኛል።
አጠቃላይ አስተውሎዎች
አካሉ፣ የልቦለዱ ዋናው ገድለኛ፣ ከደርግ የወጣት ጭፍጨፋ ተርፎ በምሕንድስና ትምህርት የተመረቀ ባለሙያ ነው። የአሰላ ልጅ ነው። ታሪኩ የርሱን ሕይወት ዋናው ሐመልማል (ሽብልል ንድፍ ጥጥ)፣ የፍቅረኛውን እና የጓደኞቹን ደግሞ ማከያ አድርጎ እየፈተለ ያጠንጥናል። ከወጣቱ ጋር የሚተሳሰሩ ዐብሮ-አደጎች እንዲሁም የሙያና የፍቅር ጓደኞች ይብዛም ይነስ የዚያ የጭፍጨፋና ጭካኔ ዘመን ሰለባዎች ናቸው። እነርሱም እንደ አካሉ ሕያውያን (survivers) ከመኾናቸው በላይ ወይ ተምረው ሙያተኛ ለመኾን የበቁ አሊያም በዩኒቨርስቲ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ናቸው። እነዚህ ትግልና መራራ የሕይወት ተመክሮ ያበሰላቸው ኅሩያን (elites) በሚኖራቸው የሐሳብና የጓደኝነት መስተጋብር ትልልቅ አርእስተ-ነገር ይዳሰሳሉ፤ እንደ ነጻነት እና ፍትሕ፣ ማንነት እና ሀገር ወዳድነት፣ ታሪክ እና እውነት ያሉ አርእስተ-ነገር። አርእስቱ ንድፈ-ሐሳባዊና ፍልስፍናዊ ቃና ያላቸው አስተያየቶች የሚደመጡባቸው ተዋሥኦዎች ናቸው።
አካሉ በሙያው የውሃ ልማት መሐንዲስ ቢኾንም በአስተሳሰቡና በምግባሩ የፈላስፋነት ዝንባሌ ጐልቶ ይታይበታል። ለሙያው ያለው ትጋት፣ ለአለቃው አእምሮዊ ብቃትና ታላቅ ሰብእና ያለው አክብሮት፣ ለጓደኞቹና ዐብሮ-አደጎቹ ያለው በጎነት፣ ለሥልጣንና ሀብት የሚያሳየው ግድየለሽነት፣ ለሚያፈቅራት ሴት ያለው ግልጽነትና ሥሡነት በሚሰነዝራቸው ጥልቅና ምጡቅ አስተያየቶች ላይ ታክለው ቢሰሉ ድምራቸው ከጠቢባን ወገን እንዲፈረጅ የሚያበቃው ይመስላል።
ለምሳሌ በአንድ ጭውውት ላይ ስለ ዕጣ ፋንታ ወሬ ይነሣል። ርእሰ-ነገሩ አካሉን ያሳስበዋል። ምሥጢሩን ግን የሚደርስበት አይመስለውም። እንዲያም ኾኖ ግን ዕጣ ፋንታን ከችሎታና ነፃ ፍቃድ ጋር አያይዞ የሚከተለውን ጠለቅ ያለ ፍልስፍናዊ አስተያየት ሲሰነዝር እናስተውላለን።
“... የተፈጠርነው እንድናውቅ፣ እንድንበለፅግ፣ እንድንደሰት ይመስለኛል። ይህን ለማድረግ ችሎታውም ተሰጥቶናል። ...
በችሎታ ላይ ደግሞ ነጻ ፍቃድ ታክሎበታል። ... የሰው ልጅ ዕጣ ፋንታ ችሎታውን ከተለገሰው ነፃ ፈቃድ ጋር በአግባቡ መሸመን ላይ የተንጠለጠለ ይመስለኛል ...”
እንዲህ ዐይነት ረቀቅ ያሉ ሐሳቦችን በተለያዩ አርእስተ-ነገር ላይ ይናገራል። ምግባሩና ጨዋ አንደበቱ ደግሞ ክብርና መወደድን ሲያስገኙለት እንታዘባለን፤ ከታላቆቹም ሳይቀር። የብዙ ጓደኞቹና ዘመድ-አዝማዱ ገጸ-ባሕሪያትም የሚታመኑና የሚወደዱ ናቸው። ልጅ-እግሮቹ ከትምህርት በተጨማሪ ከመራራ ሕይወት በተገኘ ምዕዳን (lesson) ዕድሜያቸው ከሚፈቅደው በላይ የበሰሉ ወጣቶች ናቸው። ከአካሉ ዐብሮ-አደጎች አንዱ በኾነ አጋጣሚ እንዲህ ያሰላስላል፤ “በስጋ መወለድ እንጂ በስጋ መነሳት እርግማን ነው፤ መወለድ ወደማያውቁት አለም ትንሳኤም ወደ ማያውቁት አለም ነው፤ ወደኖሩበት አለም ትንሳኤ ህግ ያፈርሳል። ሥርዐት ያጠፋል፤ ረብሻ ነው”
በአንድ ውይይት ላይ ደግሞ ስለ መሬትና ስለ ፍትሕ ሕዝብ ያነሣቸው ጥያቄዎች ዘመን ተሻግረንም አለመመለሳቸውን እያነጠበ እንዲህ ይላል፤ “... የዘመኑን ጥያቄ በዘመነ መልኩ ማስተናገድ የሚችል ባህል አልፈጠርንምና ገና ብዙ የምን[ን]ፏቀቅ፣ የምንጓተት ይመስለኛል።” (ገ. 421)
ለአካሉ ሚስትም፣ እኅትም፣ ፍቅረኛም፣ ጓደኛም የኾነችው መሠረት  በበኩሏ የአንድ ተዋሥኦን ጭራ ይዛ እንዲህ ታነበንባለች፤ “ማንም ሰው ምርጫ ተሰጥቶት ወደዚህ ዓለም አልመጣም [።] እኛ ግን የምንከባከበው ከጊዜ በ[ኋ]ላ ያጠለቅነውን ጥብቆ ነው [።] ስለለበስነው ጥብቆ ስንከራከር ከላያችን ላይ ነትቦ ያልቃል [።] ... ደሞ ሌላ ጥብቆ እናጠልቃለን [።] ንትርኩ ይቀጥላል” (ገ. 427)
በጥብቆ የመሰለችው ዘውጌ ማንነትን (ethnic identity) እንደኾን ልብ ይሏል። የነዚህ ወጣቶች ወላጆችም እጅግ የሚወደዱና አንጀትን የሚያንሰፈስፉ ገጸ-ባሕሪያት ናቸው፤ የዐይኖቻቸው ማረፊያ የነበሩ ወጣት ልጆቻቸውን መቅሰፍታዊው ደርግ ነጥቋቸው፣ በሐዘንና የጧሪ ዕጦት የተጐሳቈለ ሕይወት ሲገፉ እናያለን።
የአካሉ እናት ደርግ የገደለውን የበኵር ልጃቸውን እያሰቡ፤ “ልጅማ ወልደን ነበር” ይላሉ።
“ልጅማ ወልደን ነበር [።] “ምን ያደርጋል እንደ ዝንብ የትም ጣ[ሉት]። ይሄው የአካሉ አባት እህ እንዳለ አለ፤ ... ሁሌ እህህ ነው።” (ገ. 362)
ደግሞ በሌላ ወቅት በትንሽ ችግር ሆድ የሚብሳትን ሰላማዊት እንዲህ በማለት ይገሥጻሉ፤ “እኛ የልጆቻችንን ሬሳ ከበራችን ላይ ማንሳት ያቃተን ምን እንበል? ... እኛ እናልቅስ! የወለድናቸው ልጆች፣ ለፍተን ያሳደግናቸው ልጆች የትም ሲቀሩ ... ለቅሶን ለእኛ።” (ገ. 356)
ልቦለዱ አጕልቶ ያወጣቸው ታሪካዊና ማኅበረሰባዊ ሐቆች አሉ። ከነዚህ አንዱ የደርግ ጭፍጨፋ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብና በሀገር ደረጃ ያደረሰው ጥፋትና ሥቃይ ነው። በጭፍጨፋው ልጆቻቸውን ፣ምንዝሮቻቸውን፣ ጓደኞቻቸውን ያጡ ወጣቶችና አዛውንት የልብ ስብራታቸው ሳይጠገን፣ ብሶታቸው በቅጡ አደባባይ ሳይወጣ፣ ቍስሎቻቸው በደንብ ሳይድኑ ይኖራሉ። ትንንሽ አጋጣሚዎች እኒህን ከየተደበቁበት እያወጡ “እህህ” ሲያሰኟቸው እንድናይ ያደርገናል።
የመሠረት እናት ሴት ልጃቸው ያለ ሰርግ ድግስ፣ ያለ ወግ ማዕረግ ማግባቷ እያብከነከናቸው እንዲህ ይላሉ፤ “መቼም ቤቱ አላደለውም በለቅሶውም ቀን ለቅሶ፣ በሠርግም ቀን ለቅሶ ነው። የዘር ማንዘር እርግማን ሳይኖርብን አይቀርም።” (ገ. 242)
የዘር-ማንዘር ርግማን እንደሌለባቸው ግን እኚህ ደርባባ እናት ያውቃሉ። ለበኵር ልጃቸው ሞት፣ ለሴት ልጃቸው መጥፋት ተጠያቂው ደርግ እንደኾን አይረሱም። ባለቤታቸውንም ለሞት የዳረጋቸው መሪር ሐዘን ያደረሰባቸው የልብ ስብራት  እንደኾነ ያውቃሉ። እንዲህ ዐይነቱን መንግሥታዊ ጭካኔ መረዳትም ኾነ ማመን ከአእምሮ በላይ ኾኖባቸው ይመስላል “የዘር ርግማን” ይኾን ብለው እንዲጠረጥሩ የሚያደርጋቸው።
ሌላው «አዙሪት» አጕልቶ ያሳየው ሐቅ፣ የደርግ “ምርጥ መኰንኖች”፣ የከተማ ተቃዋሚዎቻቸውን ጨፍጭፈው ሥልጣናቸውን ካደላደሉ በኋላ ለቀማኛ ካድሬዎች የፈጠሩት የሥልጣን ክፍተት ነው።
ወጣቶችና ገበሬዎች ያለ ፍቃዳቸው እየታፈሱ በጥቂት ሳምንታት የውትድርና ሥልጠና ወደ ጦር ግንባር ይላካሉ።
በየጦርነቱ ዐውድማ የመድፍ መኖ (canon fodder) ይደረጋሉ። ካድሬ መኰንኖቹና የፖለቲካ ኮሚሳሮቹ ግን ከተሞች ውስጥ ከስግብግብ ነጋዴዎች ጋር ተመሳጥረው የመንግሥት ካዝና እና መጋዘን እየዘረፉ ሕገወጥ ንግድ ያካኺዳሉ። በየመሸታ ቤቱ የሚሠሩ የዐማፂያን ጆሮ ጠቢዎችን ውሽምነት ይዘው የጦርና የመንግሥት ምስጢር ያዝረከርካሉ። በውጊያ ላይ የሞቱ መኰንኖችን ሚስቶች ሳይቀር እያማገጡ ይሴስናሉ። ይህን ስጽፍ የሚታሰበኝ አንድ ትዝብት አለ። እኒህ እልፍ አእላፍ ኢትዮጵያውያንን የወላድ መካን ያደረጉ፣ በመንግሥታዊ ሽብራቸው የሕዝብን ሀገራዊ ኵሩ መንፈስ የሰበሩ፣ በከሰረ ፖለቲካቸውና ወታደራዊ ወንጀላቸው የጀግናውን ሰራዊት ወኔ የሰለቡ፣ ለሥልጣናቸው ሲሉ ኢትዮጵያን በማያባራ የጦርነት ማጥ ውስጥ የዘፈቁ፣ ሕዝቧን ለአሠቃቂ ርኃብና ድኽነት አጋልጠው ሀገሪቱን ውርደት ያከናነቡ “ምርጥ መኰንኖች” ዛሬም “ትግላችን”፣ “እኛና አብዮቱ”፣ ... እያሉ ራሳቸውን ማወደሳቸው፣ “ከደሙ ንጹሕ ነኝ” ማለታቸው ነው።
«አዙሪት» አድምቆ ካሳያቸው ማኅበራዊ ሐቆች ገዝፎ የሚታየኝ ታላቅ ምግባሩና ኵሩ መንፈሱ የተሰበረ ሕዝብ ግዴለሽ እንደሚኾን የሚያስገነዝበው ሐቅ ነው። ልቦለዱ ይህን ሐቅ በሙና ታሪክና ሰብእና የሥጋ ግዘፍ ሰጥቶ፣ የውበት ልዕልና አጐናጽፎ፣ የአፍራሽነትና የሥርዐት - አልበኛነት አእምሯዊ ዝንባሌ አሲዞ ያሳየናል። ይህን በመለበሙ ይመስላል ዋናው ገጸ-ባሕሪ እንዲህ የሚለን፤ “ማህበረሰብ ሲያምፅ ግድ የለሽ ይሆናል። አያገባኝም ይላል። አድርግ ያሉትን ያደርጋል። አታድርግ ሲሉትም እሺ ይላል። ባህሉን ይንቃል። ወጉን ያፈርሳል። ለማንነቱ አክብሮት ይነፍጋል። እፍረተ ቢስ ይሆናል። ...” (ገ. 149)
በመጨረሻ፣ ግን ከሌሎች በማይተናነስ ደረጃ፣ ልቦለዱ ስለ ማኅበራዊ ዕርቅ አስፈላጊነት የሚያስተላልፈውን መልእክት እለብማለኹ። ይህን አለማንሣት የአስተውሎ ሕጸጽ ይኾናል። ከታሪኩ ዐበይት ኹነቶች አንዱ ትርሓስ፣ አካሉና መሠረት ላይ ባደረሰችው ከፍተኛ አደጋ ተጸጽታ ይቅርታ የምትጠይቅበት አጋጣሚ መኾኑ ለዚህ አጕራ (claim) ማስረጃ ይኾናል። ከዋናው ባለገድል ጀምሮ አብዛኞቹ ገጸ-ባሕሪያት፣ የደርግ አገዛዝ ያደረሰባቸውን ግፍ እስከ ዕለተ-ሞት የማይረሱ ሰለባዎች ኾነውም፣ ያ አገዛዝ ከወደቀ በኋላ የበቀል መንፈስ አይታይባቸውም። እንዲያውም በዳዮቻቸው የፈጸሙትን የፖለቲካ ወንጀል አምነው ይቅርታ ቢጠይቋቸው ዕርቅ ለማውረድ ፍቃደኛ ኾነው ይታያሉ። ለምሳሌ የአካሉ አባት፤ “የልጄ ገዳይ ከልቡ ይቅርታ ቢጠይቀኝ ሀዘኔን ይከፍለው ነበር።” (ገ. 384) ሲሉ ይደመጣሉ። በዚህ ፍሬ ቃላቸው  (statement) የሌሎቹን ተበዳዮችም ስሜት የገለጹ ይመስለኛል። ቀጠል አድርገውም በተባ የፈላስፋ አንደበት እንዲህ ይላሉ፤ “ይቅርታ መጠየቅ መሸነፍ፣ ይቅር ማለት መበለጥ አይደለም። ይቅር መባባል የአሸናፊነት ጎዳና ነው። ... የይቅርታ ስርዓት ለበዳይም ለተበዳይም ሽልማት ነው።” (ገ. 385)
እንዲህ ዐይነት አስተዋይነትንና ይቅር-ባይነትን ከተበዳይ የሚጠይቅ ማኅበራዊ ዕርቅ ግን በበዳዮቹ ዘንድ እስከ ዛሬ ተቀባይነት ያለው ሐሳብ አይደለም። “ምርጦቹ መኰንኖች” እና ግብር-ዐበሮቻቸው ለዚህ ዕርቅ የሚያስፈልጉትን የሥነ-ምግባርና የሰብእና ብቃቶች ከ40 ዓመታት በኋላም ያዳበሩ አይመስሉም።
ከላይ በገደምዳማ እንደጠቈምኩት፤ የ«አዙሪት» ተዋሥኦዎች በጥልቅና ምጡቅ አስተውሎዎች የጐለበቱ ናቸው። እንዲህ የምለው ግን ወዝ-የለሽ ሐተታ የታጨቀበት ድርሰት በአንባቢ አእምሮ አሠር (impression) ኾኖ እንዲቀረጽ አይደለም። በልቦለዱ ውስጥ ከቁምነገረኛ ተዋሥኦዎች ጋር “ድሪያ-ቀመስ” ምልልሶችንም እናነባለን (ይመልከቱ ገገ. 136-37፣ 155፣ 200-01፣ 295)። እኒህ ደግሞ ቅልጥፍጥፍ እና ጥፍጥ ያሉ ናቸው። በአግቦና በተረብ ተዋዝተው፣ ወሲብ-ነክ አንድምታዊ ፍቺ (connotation) ባሏቸው ግልጸቶች (expressions) ተከሽነው ይነበባሉ።
ልቦለዱ በኔ አተያይ የተአማኒነት ጥያቄ ሊያስነሡ የሚችሉ በርከት ያሉ የኹነት ግጥምጥምሾች አሉት። ገጸ-ባሕሪያቱ በሕይወት አውራ መንገድ ላይ እንዲገናኙ ከሚያደርጓቸው አጋጣሚዎች በተጨማሪ ሌሎች የሚያስተሳስሯቸው ያለፈ ዘመን ኹነቶች ይገጥሟቸዋል። እኒህ አንድ-ኹለት ብቻ ቢኾኑ የተአማኒነት ችግር አያመጡም። በርካቶቹን ባሕሪያት የሚያስተሳስሩ ያለፉና ዘመነኛ ኹነቶች መኖራቸው (ለምሳሌ የተሻለ እና የአካሉ ታላቅ ወንድም ጓደኛነት፣ የሰላማዊት እና የፈንታው ወንድም ድርጅታዊ ግንኙነት) የታሪኩን ተአማኒነት የሚቀንሰው ይኾንን እላለኹ።
ቋንቋ-ነክ ትዝብቶች
ስለ «አዙሪት» ታሪክና የዘመን ምሰላ ይህን ያኽል መንደርደሪያ አስተያየት ከሰነዘርኩ፣ አሁን በቀጥታ  ዋና ትኵረቴን ወደ ልቦለዱ ቋንቋና ሥርዐተ-ጽሕፈት አዞራለኹ። በቋንቋ ረገድ ኹለት ዐበይት ነገሮች ምቾት የሚነሡ ኾነውብኛል። አንደኛው መጽሐፉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ገጾቹ በጕራማይሌ ቃላትና ጽሒፍ (script) የተዘጋጀ መኾኑ ነው። ኹለተኛው የአገባብና አገላለጽ ችግሮችን ይመለከታል። በሥርዐተ-ጽሕፈቱ ዘርፍ ደግሞ የብሂል-መር (pronunciation led) አጻጻፍ ችግሮች፣ የከተባ ስሕተቶች (typos) እንዲሁም  ከነጥብና እምሮች አጠቃቀም ጋር የሚዛመዱ ችግሮች ጐልተው ስለሚታዩ፣ ተማግቦው በነዚህ ላይ ጠቅለል ያሉ ነጥቦችን ያቀርባል፤ (ዝርዝር አርትዖታዊ አስተያየቶችን ለደራሲው እንዲቀርቡ በመተው)።
ጕራማይሌ ቋንቋ
መጽሐፉ ውስጥ ከ145 በላይ የተውሶ ቃላትና ሐረጎች በዐማርኛ ጽሒፍ ጥቅም ላይ ውለዋል። ከነዚህ አንዳንዶቹ በርካታ ጊዜ መደጋገማቸው ሳይቈጠር ይህን ያኽል መብዛታቸው በአንባቢ አእምሮ ጥያቄዎች ያስነሣል። ይህ አልበቃ ብሎ ከነአካቴው በላቲን እንግሊዝኛ ጽሒፍ የተሰጡ ቃላትና ምልልሶች ብዙ ናቸው። አንድ የደርግ መንግሥት መሥሪያ ቤት ደግሞ በእንግሊዝኛ መጠሪያው ስመ-ስም (acronym) መጠቀሱ ሳይበቃ፣ በቅይጥ ጽሒፎች ተደጋግሞ ተጽፏል (የEDDCው እየተባለ)።
የመሥሪያ ቤቱ ሙሉ የዐማርኛ ስም በኅዳግ ማስታወሻ ተሰጥቷል፤ «የኢትዮጵያ ሀገር ውስጥ ማከፋፈያ ኮርፖሬሽን» ተብሎ (ገ. 23)። ከዚህ ስም “ኢሀውማኮ” የሚል ስመ-ስም ማውጣት እየተቻለ ለምን የእንግሊዝኛ አቻውን መጠቀም እንዳስፈለገ ግልጽ አይደለም፤ ከላይ የጠቈምኩትን አጕል ፈሊጥ በጣም ተነቃፊ በኾነ ቅርጹ ለማሳየት ካልኾነ በቀር። ወዲህም የዐማርኛውን ስመ-ስም መጠቀም በልቦለድ ሥራ ውስጥ እምብዛም ጥቅም ላይ የማይውለውን ኅዳግ ማስታወሻ ለማቅረብ ከመገደድ ያድን ነበር።
በርግጥ የተወሶ ቃላቱ ኹሉ አላግባብ ወይም ሳያስፈልጉ ሥራ ላይ የዋሉ አይደሉም። አንዳንዶቹ የቴክኒክ ቃላት በዐማርኛ አቻ የሌላቸው ሊኾኑ ይችላሉ። እኒህ በዐማርኛ አቻ ቃላት ቢኖሯቸውም በደራሲውና አንባቢያን ዘንድ የማይታወቁ መኾናቸው ለውሰታቸው አስገዳጅ ምክንያት ሊኾን ይችላል። ከተውሶዎቹ ቃላት ውስጥ አብዛኞቹ ግን አላስፈላጊ ይመስሉኛል፤ እነርሱን በቅጡ የሚገልጹ የዐማርኛ ቃላት በቋንቋው ተናጋሪዎች ዘንድ ይታወቃሉና።
ደራሲው የቃላት ውሰቱን ኾን ብለው እንዳደረጉት መጠርጠር ይቻላል። ከደርግ ዘመን ወዲህ እንግሊዝኛ ቃላትን እየደባለቁ መናገር የምሁርነትና የዘመናዊነት ማሳያ አጕል ፈሊጥ ነው። ፈሊጡ በዐፄው ዘመነ-መንግሥትም እንደነበረ ቢታወቅም እጅግ ገንኖ መታየት የጀመረው ግን ከ1960ዎቹ ወዲህ ይመስላል። በተለይ የዩኒቨርሲቲና የቴክኒክ ኮሌጅ ተመራቂዎች እንዲያ መኾናቸውን የሚያሳውቁበት ዘዴ ለተራው ሰው ባይተዋር የኾኑ የጽንሰ-ሐሳብ ቃላትን በንግግር ውስጥ ማዥጐድገድ ነው። ደራሲው ይህን የምሁር-ተብዬ ማኅበረሰባዊ ቡድን ፈሊጥ አጕልቶ ለማሳየት በነርሱ ምልልሶች ውስጥ ዘወትር የሚደመጠውን ጕራማይሌ ቋንቋ ለአንባቢ አቅርበው ሊኾን ይችላል። እንዲያ ከኾነ ጕራማይሌ ቋንቋው በዘመናችን ኅሩያን ላይ ያነጣጠረ ሽሙጥ (satire) ነው። አንባቢ ከእንዲህ ዐይነት አብሻቂ ባህል ይላቀቅ ዘንድ ንቁ ጥረት እንዲያደርግ ያበረታታል።
በዐማርኛ ጽሒፍ የተሰጡ የተውሶ ቃላት ላይ አንዳንድ ብሂል-ነክ ስሕተቶች ተከሥተዋል፤ ለምሳሌ ሌጅትመንት (ገ.12 ሌጂትሜት ለማለት)፣ ኮንቬንቤልት (ገ.25 ኮንቬየርቤልት ለማለት)። ከነዚህ በርካታዎቹ ስሞች ናቸው፤ ለምሳሌ ማርክቲውን (ገ.180 ማርክ ትዌይን ለማለት)፣ በርትላን ካስተር (ገገ. 134፣ 166 በርት ላንካስተር ለማለት)። ዝነኛው የፈረንሳዩ “ባለቅኔ” አ’ቹኧ ራምቦ ደግሞ አክተር ራንቦ ተብሏል (ገ.223)። የስሙን ፈረንሳይኛ ንብበት በዐማርኛ ጽሒፍ መወከል አስቸጋሪ ቢኾንም በዐማርኛዊ አጠራሩ “አርተር ራምቦ” ማለት ይገባ ነበር። በላቲን ጽሒፍ የተሰጡትም ከከተባ ስሕተቶች የጸዱ አይደሉም፤ ግን ጥቂት ናቸው፤ (በገጾች 133 እና 141 ያሉትን ይመለከቷል)።
አገባብ እና አገላለጽ
የአገባብ እና አገላለጽ ችግሮች ብዙ አይደሉም። ከታዘብኳቸው ችግሮች ደግሞ አብዛኞቹ ለቋንቋ ጥራት በማይጨነቅ አንባቢ ዘንድ የሚስተዋሉ እንደማይኾኑ መገመት ይቻላል። በአኹኑ ጊዜ ታትመው ለንባብ በሚበቁ ብዙ ሥራዎች ውስጥ በገፍ የሚታዩ መሰል ችግሮች እዚህ ሥራ ውስጥ ጥቂት መኾናቸው የአርታዒውን - ባዩልኝ አያሌው - መልካም ተዋፅኦ ይመሰክራል። ዐልፎ ዐልፎ ከሚታዩት ችግሮች የሚከተሉትን በምሳሌነት እጠቅሳለኹ።
በገጽ 94 ላይ “ይህ አርዕስት አውሎ ያሳድራል።” የሚል ዐረፍተ-ነገር እናነባለን፣ “አርዕስት” ከዐረፍተ-ነገሩ ነጠላ ቍጥር ጋር የሚጣረስ ርባታ እንደኾነ ባለማስተዋል። በገጽ 301 ላይ “ብርጭቆዋቸውን አንስተው <ችርስ> ተባለ።” የሚለው እንከናም ዐረፍተ-ነገርም “ብርጭቆዎቻቸውን አንሥተው ‘ቺርስ!’ አሉ።” ቢባል መልካም ነበር፤ በዐረፍተ-ነገሩ ባለቤትና በግሱ መካከል ያለውን ያለመመጣጠን ችግር ያስወግዳልና። በገጽ 412 ላይ ያለው “የእግሬ ላይ ንቃቃት” ደግሞ “የተረከዜ ንቃቃት” ቢባል ዐማርኛው አይጐለድፍም።
ዐልፎ ዐልፎ የቃላት አጕል ምርጫ ወይም ውሱንነት ለውስብስብ ሐሳቦች ስብቅልናን ሲያሳጣ ይታያል።
ለምሳሌ በገጽ 214 ላይ፤ “መቀየጥ ጥሩ ነው፤ እኔነትን ያጠፋል፤ ትምክህትን ይሰብራል፤ ልዩነትን ያጠፋል፤ ልይዩነትን ያስተናግዳል።”
የሚል ፍሬ ቃል እናነባለን። ግን “እኔነት” በ“እኔታ” አሊያም በ“ግለኛነት/አግላይነት” ቢተካ የደራሲውን ሐሳብ ይበልጥ በትክክሉ የሚገልጹ ይመስለኛል። “እኔነት” በቁሙ ግለሰብ ስለራሱ ማንነት ያለውን ግንዛቤ የሚጠቍም ቃል ሲኾን፣ “እኔታ” ሌሎችን ከመጤፍ የማይቈጥር፣ “እኔ ብቻ” የማለት ዐባዜን ጠቋሚ ነው።
ፈረንጆቹ ኢጎ (ego) ለሚሉት ቃል ይመጥናል። በተጨማሪ በፍሬ ቃሉ ውስጥ ያሉት “ያጠፋል” እና “ይሰብራል” የሚሉት ግሳዊ ሐረጎች እቅጭ ውጤቶችን (exact results) ስለሚጠቍሙ ተቀባይነት ያላቸው አይመስሉም። ማኅበረሰብ በእቅጭ ሳይንስ ቀመር የሚገለጽ አይደለምና። በበኩሌ ደራሲውም ይህንን የሚስቱት አይመስለኝም። ካልሳቱት ደግሞ የፍሬ ቃሉ ችግር የቃላት ምርጫ ሳይኾን አይቀርም። እናም ፍሬ ቃሉ “መቀየጥ ጥሩ ነው፤ እኔታን/ግለኛነትን/አግላይነትን ይገድባል፤ ትምክሕትን ያዳክማል፤ ልዩነትን ያቀራርባል፤ ልይዩነትን ያስተናግዳል።” ቢል የደራሲውን ሐሳብ በቅጡ ይገልጸው ነበር ብዬ ዐስባለኹ።
በአገባብና አገላለጽ ረገድ የታዩኝ ችግሮች ብዙ አለመኾናቸው ተለባሚ (noteworthy) ነገር ነው፤ ልቦለዱ በርካታ ውስብስብ ወይም የርቃቄ ደረጃቸው (level of abstraction) ከፍ ያለ ጽንሰ-ሐሳቦችን በተዋሥኦ መልክ የሚያቀርብ ሥራ በመኾኑ። ይልቅ ሥራው ብዙ ችግሮች የሚታዩበት ሥርዐተ-ጽሕፈቱን በሚመለከቱ አርእስተ-ነገር ላይ ነው።
ሥርዐተ-ጽሕፈት
የ«አዙሪት» ሥርዐተ-ጽሕፈት ነክ ችግሮች ከሞላ-ጐደል በኹሉም የዐማርኛ ኅትመቶች ውስጥ - አንሰውም በዝተውም - የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው። ችግሮቹን በፈርጅ ከፋፍሎ ለማቅረብ ያኽል ሦስት ማወገኛ ነገሮችን (sorting factors) መጠቀም ይቻል ይመስለኛል። ማወገኛዎቹ ግን በቅጡ ያልታሰበባቸው (arbitrary) መኾናቸውን ልብ ይሏል። በመጀመሪያው ፈርጅ ብሂል-መር የአጻጻፍ ችግሮችን እንመልከት። እነዚህ አባባልን መሠረት ያደረጉ አጻጻፎች ሆሄያትን በገደፋ (deletion)፣ በእሒደት (assimilation)፣ በቦታ ቅይይር (metathesis)፣ ወዘተ. ስለሚለውጡ አንዳንዴ በጽሑፋዊ ቅርጻቸው ሌሎች ቃሎችን የሚወክሉ ይኾናሉ።
ለምሳሌ በገጽ 291 የሚገኘውን “ይፈሳል”፣ በገጽ 298 የሚገኘውን “አወከው” እና በገጽ 390 የሚታየውን “መቶ” እንመልከት። እኒህ ቃላት በቁማቸው እና በቅደም-ተከተላቸው “ፈስ”፣ “እውከት” እና “የዐሥር ጊዜ ዐሥር ብዜት” ያዘሏቸውን ፍቺዎች የሚገልጹ ናቸው። ከዐውደ-አገባባቸው የመፍሰስን፣ የማወቅን እና የመምጣትን ፍቺዎች እንደሚገልጹ ማወቅ ቢቻልም አላስፈላጊ ውዥንብር የሚፈጥሩ አጻጻፎች ናቸው።
በቅደም-ተከተላቸው “ይፈስሳል”፣ “አወቅከው” እና “መጥቶ” ተብለው ቢጻፉ ኖሮ ርባታቸው የቃላቱን ዐምዶች/ሥሮች የማሳየት ብቃት ያገኙ ነበር፣ ያውም የፍቺ አሻሚነትን አስወግደው። የቃላት ሆሄ ጥንቀቃ ሥርውቃላዊ ሲኾን ከቦታና ጊዜ ጋር የማይለዋወጥ ሥርዐተ-ጽሕፈት እድብ ይኾናል፤ መደበኛነቱም ይጸናል።
በኹለተኛው ፈርጅ ያሉት የከተባ ስሕተቶች ናቸው። በጽሕፈት ወይም ከተባ ተግባር ላይ የሚከሠቱ እንጂ አጕል ልማድ ወይም አጕል ግንዛቤ ያስከተላቸው ችግሮች አይደሉም። በ«አዙሪት» ውስጥ ያሉት የከተባ ስሕተቶች በቍጥር ጥቂት የሚባሉ ባይኾኑም በየገጹ ላይ የሚገኙ አይደሉም። እንደ “የምራል” (ገ. 52)፣ “እየቃታት” (ገ.77)፣ አንጋጭተው (ገ. 241)፣ ትህራስን (ገ.399) ያሉ ስሕተቶች ረቂቅ ጽሑፉ ለኅትመት ከመብቃቱ በፊት በናሙና ዕትም ዐራሚ ታይቶ ቢኾን በቀላሉ ሊወገዱ የሚችሉ ነበሩ።
ከኒህ ለየት ብለው የሚታዩ ሦስተኛ ወገን ችግሮች ሥርዐተ-ነጥብን የሚመለከቱ ናቸው። ልቦለዱ ብዙ ቦታዎች ላይ ነጥቦችን በአግባቡ ቢጠቀምም አንዳንድ ቦታዎች ላይ ትእምርተ ጥቅስ እና ሌሎች ነጥቦችን አጓጕል ጥቅም ላይ ያውላል አሊያም ይገድፋል። ለምሳሌ ገጽ 86 ላይ በጥቅስ ውስጥ ያለ ሌላ ጥቅስ እንደ ዋናው ጥቅስ በድርብ እምሮች ተመልክቷል፣ በነጠላ እምር ውስጥ መቀመጥ ሲገባው። በገጽ 120 ላይ ደግሞ የሙና ንግግር በአፋዊ ቋንቋ አባባሉ ይታይ ዘንድ የሚረዱ ነጥቦች ችላ ተብለዋል።
«አዎ ይባላል» አለች ሙና በሽሙጥ። [«]ወንድና ወይን ሲቆይ ነው [....።] ድንቄም መጣፈጥ እቴ[!] እሺ ቲቸር ምን አሉ?» አለች። (ገ. 120) በቅስር አቅናፍ ውስጥ ያሉት የሥርዐተ-ነጥብ ምልክቶች በኔ የተጨመሩ ናቸው። በሙና ንግግር ውስጥ በእንጥልጥል የተተወ ዐረፍተ-ነገርን፣ የተጋነነ አገላለጽን፣ ወዘተ. ለማመልከት አስፈላጊ ናቸው። «አዙሪት» ግን ገድፏቸዋል።
የሥርዐተ-ጽሕፈቱ ችግሮች እኒህ ብቻ አይደሉም። ይህ ዳሰሳ ችላ ያላቸው ጕዳዮች አሉ። ከነዚህ ዋነኛው «አዙሪት» ውስጥ የሚታየው በሥርውቃላዊ ሆሄ ጥንቀቃ (etymological orthography) ያልተመከረ የድምፀ-ሞክሼ ሆሄያት አጠቃቀም ጕዳይ ነው። ይህ ግን ሌሎች ልቦለዶችን በሚመለከቱ ሒሳዊ ተማግቦዎች ላይ ከዚህ ቀደም ትኵረት ስለተደረገበት (ለምሳሌ በዘነበ ወላ “ልጅነት”፣ በአስማማው ኀይሉ “ከደንቢያ ጎንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ”፣ በፋሲካ መለሰ “ከእኒያ ልጆች ጋር” የቀረቡ ተማግቦዎች) እዚህ ላይ መድገሙ አላስፈላጊ ነው።
መደምደሚያ
የ«አዙሪት» አማላይ ታሪክ እና ትረካ በበርካታ ተለባሚ ፍሬ ቃሎች የዳበረ ነው። አንዳንዶቹ ስብቅል እና ስንግል (polished) ኾነው አልቀረቡም እንጂ የዐማርኛ ብሂሎች ወይም ምሳሌያዊ ንግግሮች ሊኾኑ በቻሉ ነበር። ከነዚህ ጥቂቱን እነሆ፤ “መውደድ ውለታ አይደለም፤ ፀጋ ነው።” (ገ. 41)። “እኛ ሴቶች እንመረጣለን እንጂ ስንመርጥ ምርጫችን ብዙ ነው።” (ገ. 62)። “ሰው ልምዱን የሚያጠራቅምበት ቋት አይሞላም። እንኳን ሊሞላ ድር[በ]ብም አይሆን፤ እንዲሁ እንዳንቦጫቦጨው ይዞት ያልፋል።” (ገ. 309)።
ከኹሉም ይልቅ የአካሉ አለቃ የአባይ ወንዝን የማስገበር ምስጢር በምሳሌነት አቅርበው “ዝቅ ብሎ የሚያስገብር መሪ አልናፈቀህም?” (ገ. 271) የሚሉት አእምሮን የመደሰም ዐቅሙ ይሰባኛል። በአምባገነኖች የግፍ አገዛዝ ያመረሩ ሕዝቦችን የዘወትር ምኞት ቀንብቦ የሚያቀርብ ፍሬ ቃል ነው እላለኹ።
ይህ ሒሳዊ ዳሰሳ በሥነ-ጽሑፍ መመዘኛዎች ላይ የተመረኰዘ ምሁራዊ ዳሰሳ አይደለም። ልቦለዱን ከብጤ ዘመነኞቹ ወይም ከቀደምት ሥራዎች ጋር እያስተያየ አይዳኝም፤ በአተራረክ ስልት፣ በአቀራረብ ዘዴ፣ በጭብጥ ቅመራ፣ ወዘተ. ርባናዎቹን እና ሕጸጾቹን አይዘረዝርም። የገጸ-ባሕሪያቱን በግልጽ የሚታዩ ወይም በሐዪጾት የሚታወቁ (inferred) ሰብእናዊ ጭብጦችን በጥልቀት አይተነትንም። ባጭሩ እኒህን እና እኒህን በመሰሉ የልቦለዱ ኪነጥበባዊ ዕሴቶች ላይ የሐያሲ ዳሰሳ አያቀርብም።
«አዙሪት» ለነገሪ ዘበርቲ መራ መውጫ ሥራ ይመስለኛል። እንዲያም ኾኖ ከዘመነኛው የዐማርኛ ልቦለድ ዐበይት ቅርሶች ተርታ ለመግባት ጥሬ ዐቅምና ርባና ያለው ሥራ ነው እላለኹ። ግን ለዚህ ወግና ማዕረግ ይበቃ ዘንድ በስብቅልና ስንግል ዝግጅት እንደገና መታተም ያለበት ይመስለኛል።
(ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. __ማግኘት ይቻላል፡፡)

Read 6542 times