Saturday, 15 April 2017 13:12

“ድብርት የሁሉም ችግር ቢሆንም Postpartum ግን...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

   ድብርት በእድሜ በጾታ ወይንም በተለየ ሁኔታ የሚከሰት ሳይሆን በሁሉም ሰው ላይ ሊደርስ የሚችል ከአእምሮ ጭንቀት ጋር የተያያዘ ችግር ነው። ነገር ግን Postpartum የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ከወሊድ በሁዋላ በሚለው ስለሚተረጎም (Postpartum Depression ) ይባላል።
 ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት
አንዲት ስሙዋ እንዳይገለጽ የፈለገች እናት የሚከተለውን ሀሳብ ነበር የላከችልን።
“እኔ እርጉዝ በነበርኩ ጊዜ በሚገርም ሁኔታ በአካባቢዬ ያሉ ሰዎች ሁሉ ስለእኔ እንዲያስቡ እፈልግ ነበር። ካለባበስ ከአመጋገብ ...ብቻ ከሁሉም አቅጣጫ... ዛሬ ይህን ትብላ... ዛሬ ይህን ትልበስ... እንድባል እፈልግ ነበር። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከባለቤቴ በስተቀር ከእኔ ጋር አብሮኝ የሚኖር ሰው አልነበረም። እናም የቢሮ ሰራተኛና የራስዋ ኑሮ ያላት ናት። እህቶቼም የየራሳቸው ኑሮ ያላቸው ስለሆኑ በሳምንት ወይንም በአስራ አምስት ቀን አንድ ቀን እንጂ በየጊዜው አያገኙኝም። እናቴም ብትሆን በሁለት ሶስት ቀን ልዩነት ነበር የምታገኘኝ። ታዲያ በምታገኘኝ ጊዜ ምንም ጥያቄ እንድትጠይቀኝ ወይንም አስተያየት እንድትሰጠኝ አልፈቅድላትም ነበር። ፀጉርሽ እንደዚህ ሆኖ... ወይንም ይህን ለምን ለበስሽ? ብትለኝ... በቃ አያገባሽም የሚል ነበር መልሴ። ምክንያቱም ከእኔ ጋር ሆነሽ አገልግሎት አልሰጠሸኝም የሚል ነው። ...
“...ከባለቤቴ ጋር ባለው ግንኙነት ልክ እንደ ጦር ተፈራርተን ነበር የምንውል የምናድረው። ...አንተማ ምን ቸገረህ... እኔ በእርግዝና ምክንያት እንደዚህ ስቸገር... ቅርጼ ተበላሽቶ... መልኬ ጠቁሮ... አንተ ግን እንዳማረብህ ትኖራለህ። ገና ልጁ ሲወለድ ደግሞ ከማጥባት ጀምሮ ብዙ ነገር ይጠብቀኛል። ለመሆኑ ስራዬን ትቼ ልጄን ላሳድግ ነው? ወይንስ ምን ላደርግ ነው? ሰራተኛ አይገኝ... ሌላም ሌላም ነገር እናገራለሁ። ባጠቃላይም ይህ ባህርይ የተወኝ ...ልጄን ወልጄ ክርስትና ካስነሳሁ በሁዋላ ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱ ደግሞ ለክርስትናው ባለቤቴም ሆነ ቤተሰቦቼ ከአቅም በላይ ስለደከሙና ባለቤቴም እኔን ለማስጌጥና ለመሸለም ብዙ ገንዘብ ስላወጣ... አሀ... ለካስ በመውለዴ ሙሉ ቤተሰቤ ተደስቶአል... ያከብሩኛል... የሚል ስሜት አደረብኝ። ከዚያም በላይ የባለቤቴ እናት...ሊጠይቁኝ ሲመጡ አስበው አብራኝ የምትኖር ልጅ ከገጠር ይዘውልኝ ስለመጡ ከምንም በላይ ተደሰትኩኝ። ይህንንም አስቀድሞ የነገራቸው ባለቤቴ መሆኑን ከእርሳቸው ስለሰማሁኝ ስሜ በሙሉ እየተለወጠ መጣ። ...
“...ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው በጣም ይገርመኛል። ምክንያቱም ልጅ በማርገዜ ምክንያት የመጣውን ነገር በጸጋ እንደመቀበል እና ልጅ ሊኖረኝ በመሆኑም መደሰት ሲገባኝ ነገር ግን በተቃራኒው ባሌን ተከሳሽ ቤተሰቤን ተወቃሽ ማድረጌ... ምን የሚሉት ነገር እንደሆነ ግራ ይገባኛል። የሆንኩትን ነገር ለጉዋደኞቼ ስናገር ግን በእርግዝናና በወሊድ ወቅት የሚከሰት ድብርት ሊሆን ይችላል አሉኝ። ለመሆኑ ይህ የደረሰብኝ ነገር እውነት ከድብርት የተነሳ ይሆን? እባካችሁ ለሌላውም ትምህርት ሊሆን ስለሚችል የባለሙያ ማብራሪያ አስነብቡን።”
በዚህ እትም በእርግዝናና ወሊድ ምክንያት የሚከሰትን ድብርት በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡን ዶ/ር ተባባሪ ፕሮፌሰር ባልካቸው ንጋቱ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ መምህር ሲሆኑ ከአሁን ቀደም ያናገርናቸው ዶ/ር አታላይ አለም የስነአእምሮ ሐኪም ሀሳብም ተካቶአል።
እንደ ዶ/ር ባልካቸው አገላለጽ ድብርት በማንኛውም ጊዜ በማንኛውም ሰው ላይ ሊያጋጥም የሚችል የአእምሮ ችግር ነው። ነገር ግን (Postpartum Depression) የሚባለው ድብርት ከወሊድ በሁዋላ እስከ አርባ ሁለት ቀን ባለው ጊዜ የሚያጋጥም ድብርት ነው። ይህም ከሌሎቹ የሚለይበት የራሱ የሆነ መለያ አለው። ለምሳሌም...አዲስ ከሚሆነው ነገር አንዱ ልጅ መኖሩ ነው። ከልጅ ጋር በተያያዘ የእናትየው ስሜት ምን ይመስላል? የሚለውን ለይቶ በማወቅ የድብርቱን መገለጫ ማወቅ ይቻላል። ይህም ካልወለዱ ሰዎች የሚለይበት አንዱ ነገር ነው። መገለጫዎቹም ከመውለድ ወይንም ከእርግዝና ጋር ካልተገናኙት ድብርቶች ይለያል።
በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ድብርት፡-
የድህረወሊድ ወይንም በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ድብርት መገለጫ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የአመጋገብ ልምድ መለወጥ ነው። ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመው የምግብ ፍላጎት ማጣት ሲሆን በሌላው አቅጣጫ ደግሞ በብዛት መመገብ ነው። እንዲሁም የአለባበስ የኢኮኖሚና ሌሎች የአኑዋኑዋር ሁኔታዎችን በጸጋ አለመቀበልም ሌላው መገላጫው ነው። ይህ ከሚሆንባቸው ምክንያቶችም አንዱ ለራስ የሚሰጠው ግምት መቀነሱ ነው። በተለይም በብዛት የመመገብ ሁኔታ የሰውነትን ግዝፈት የሚያመጣ ሲሆን በጣም በዝቅተኛ ደረጃ መመገብም እንደዚሁ በእናትየው ላይ የአቅም ውስንነትን ሊያስከትል ይችላል። ኢኮኖሚን በሚመለከት ከእርግዝና በፊት ሊታሰብበት የሚገባ ሆኖ ሳለ ልጁ ሲወለድ በምን ሊያድግ ነው? ከሚል እራስን ማስጨነቅ ተገቢ ባይሆንም ነገር ግን ብዙዎች ላይ የሚታይ ነው።
በእርግዝና ጊዜ ከቤተሰብ ትኩረት የመፈለግ ነገር አለ። ሁሉም ነብሰጡሮች ወይንም ወላዶች የሚጠበቁት እንክብካቤ መኖሩ ደግሞ በእያንዳንዱዋ እርጉዝ ሴት በግል የሚከሰት ፍላጎት ሆኖ ሳይሆን ይህ ተፈጥሮአዊ ነው። ስለዚህም ባልተለመደ ሁኔታ ሌላ ጊዜ የማያደርጉትን ነገር በመጠየቅ ከባል ወይንም ከቤተሰብ ጋር ንግግር ማድረጋቸው ለቤተሰቦቻቸው እርጉዝ የሆነችው ሴት ያለችበትን ሁኔታ እንዲረዱ ሊያደርጋቸው ይገባል። እናም በአጸፋውም ምላሹን በተቻለ መጠን ለመስጠት ጥረት ማድረግ ድብርቱን እንዳይኖር ሊያደርገው ይችላል።
ከወሊድ በሁዋ የሚፈጠር ድብርት፡-
ከወሊድ በሁወላ የሚፈጠረው ድብርት አንዳንድ ጊዜ የእናትየው ብቻ ሳይሆን አባትየውንም ሊጨምር ይችላል። ምክንያቱም እናትየው በድብርቱ ምክንያት ጥሩ ስሜት ካልተሰማት እና ባልተቤትየው የሚቻለውን ሁሉ አድርጎ ግን ጥሩ ምላሽ ካላገኘ እሱም ድብርቱ ሊይዘው ይችላል። ልጅ በመወለዱም ምክንያት ደስታውን እንዳጣ ሊያስብ ይችላል። ስለዚህም ወንዶች የልጅ አባት ከሆኑ በሁዋላ ከ1.2-25.5 ድረስ የሚሆኑት ለችግሩ ሊዳረጉ ይችላሉ።
(Postpartum Depression) በወሊድ ጊዜ የሚከሰት የአእምሮ ጭንቀት ሴቶች በወለዱ ከአራት ሳምንት ጀምሮ ሊከሰት የሚችል ሲሆን ማብቂያው ከተወሰኑ ወራት እስከ አንድ አመት ሊደርስ ይችላል። ምናልባትም በትክክል የህክምና እርዳታ ካላገኘ ለከፋ ሁኔታ ሊጋብዝ ይችላል። ልጅ መውለድ ተፈጥሮአዊ የሆነና እናትየውንም ሆነ አባትየውን የሚያስደስት መሆኑ የታመነበት ነው። እናቶች በእርግዝናቸው ወቅት ስለወደፊቱ ሁኔታ ማለትም በምን ሁኔታ ልጅ እወልድ ይሆን? እንዴትስ አሳድገዋለሁ የሚሉት እና ሌሎችም ተያያዥ የሆኑ ነገሮች የሚያስጨንቋቸው ሲሆን ልጃቸውን በሰላም ሲገላገሉ ግን የሚጠበቀው ደስተኛ እንዲሆኑ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን ስሜታቸው በተቃራኒው መንገድ ይሄድና ልጃቸውን ከወለዱ በሁዋላ ሊያሳዩ የሚገባቸውን የደስታ ስሜት ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ያጋጥማል። ብዙዎቹ እናቶች ልጃቸውን ከወለዱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ስሜታቸው መረበሽ፣ የሚያዩትና የሚሆነው ነገር አለመገናኛት፣ ስለራሳቸው፣ ስለቤታቸው፣ ስለቤተሰባቸው የሚያስቡት ሁኔታና እውነታው አልገናኝ ስለሚላቸው የሀዘን ስሜት በውስጣቸው ይፈጠርና ስሜታቸው ይረበሻል። እናቶች ከእርግዝናው ጋራ በተያያዘ የሆርሞኖች፣ የንጥረ ነገሮች እና የተለያዩ ነገሮች ለውጦች ስለሚኖሩ እነዚህ ለውጦች ከአስተሳሰብ ወይንም ከአእምሮ ጋር ስለሚገናኙ በድንገት በሚቋረጥበት ጊዜ የአእምሮ መረበሽንና መጨነቅን ሊያስከትል የሚችል ሲሆን ነገር ግን ይህ ስሜት ቀላልና በብዙዎች ዘንድ የሚታይ ሕክምናን የማይፈልግ እና በጥቂት ጊዜያት በራሱ የሚወገድ ነው።
 ዶ/ር አታላይ አለም የስነአእምሮ ሐኪም
በተለያዩ አገሮች በተደረገው ጥናት እንደተመዘገበው ከሆነ ከ 10-16 ከመቶ የሚሆኑ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ድብርት Depression በሚባለው የስሜት ለውጥን ያሳያሉ። ይህ ግን ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ሕክምናንም የሚፈልግ ነው። በእርግጥ ይህ ስሜት በመውለድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን አልፎ አልፎ እናቶች ቀደም ሲልም ጀምሮ አብሮአቸው የቆየ ሊሆን እንደሚችል ጥናቶች ያስረዳሉ።
ከወሊድ በሁዋላ ድብርት Depression የያዛቸው እናቶች የጥፋተኝነት ስሜት መጨመር፣ ጥልቅ የሆነ ብስጭት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ የደስተኝነት መጠን መቀነስ፣ የፍቅር ግንኙነት መቀነስ፣ በጣም ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት፣ የእፍረት ስሜት፣ የፀባይ መለዋወጥ፣ ከልጅ ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር አለመቻል፣ የመሳሰሉት ባህሪዎች ሊታዩባቸው ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ ሁኔታው በቸልታ ከታየ በእራስ ወይንም በተወለደው ልጅ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ መታወቅ አለበት።
ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚታየው ድብርት Depression የተለያዩ ምክንያቶች አሉት፡:
እርግዝናው በታቀደና በፕሮግራም በሚፈለግበት ሁኔታ ካልተከሰተ እናቶች እንደ ችግር ስለሚቆጥሩት ከመደሰት ይልቅ በተቃራኒው ድብርትን ሊያስከትልባቸው ይችላል።
ከትዳር ጉዋደኛ ጋር ከእርግዝናው በፊትም ይሁን ከእርግዝናው በሁዋላ የሚኖረው ግንኙነት ጤናማ መሆን ያለመሆንም ምክንያት ሊሆን ይችላል።
አንዳንድ ቤተሰብ ውስጥ እንደሚታየው ከሆነ የባል ቤተሰቦች በትዳር መሀል ጣልቃ በመግባት እንዲሁም ለወንድ ልጃቸው የበለጠ ትኩረት በመስጠት ያረገዘችውን ወይንም የወለደችውን ሚስቱን ችላ ካሉ ይህም ሌላው የድብርት ምክንያት ሊሆን ይችላል።
በትዳር መካከልም ይሁን ከቤተሰብ ድጋፍ ማጣት እና ስሜትን የሚጎዱ ችግሮች የደረሱባቸው ሴቶች ላይ በአብዛኛው ድብርት ይስተዋላል።
ባለፈው ሳምንት በወጣው ጽሁፍ ለተከሰተው የቃላት ግድፈት አንባቢን ይቅርታ እንጠይቃለን።

Read 2471 times