Saturday, 15 April 2017 13:13

የሸገር ደርቢ በፋሲካ ዋዜማ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 · በደርቢው የመጀመሪያ ዙር ከትኬት ሽያጭ የተሰበሰበው ከ970 ሺ ብር በላይ ነው፡፡
               · የተመዘገቡ ደጋፊዎች በኢትዮጵያ ቡና ከ13 ሺ በላይ፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከ14 ሺ 700 በላይ
               · በተለያዩ የጥራት ደረጃዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 10 ሺ ማልያዎችና 1 ሺ እስካርፎች፤ ኢትዮጵያ ቡና ከ8 ሺ በላይ  ማልያዎች                         ሸጠዋል፡፡
               · የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በተናጠል ወይም በህብረት ለፊፋ የደጋፊ ሽልማት (FIFA FAN AWARD)                          ማመልከት አለባቸው፡፡

      በ2009 ኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሁለተኛ ዙር 23ኛ ሳምንት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ነገ በ10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታድዬም ይገናኛሉ። መጀመርያው ዙር 8ኛ ሳምንት ጨዋታ በተገናኙበት ወቅት   ኢትዮጵያ ቡና 1ለ0 እንዳሸነፈ ይታወሳል፡፡
ከዛሬው የሸገር ደርቢ  በፊት ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ  21 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን  12 ድል፤ 6 አቻ እንዲሁም  3 ሽንፈት አስመዝግቦ በ42 ነጥቦችና በ21 የግብ ክፍያ መሪነቱን እንደያዘ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡና   ደግሞ 22 ጨዋታዎች ያደረገ ሲሆን 9 ድል፤ 8 አቻ እንዲሁም  5 ሽንፈት በማስመዝገብ በ35 ነጥቦችና በ9 የግብ ክፍያ 4ኛ ደረጃ ይገኛል፡፡

በስታድዬም ገቢና በተለያዩ የስፖርት አልባሳትና ቁሳቁሶች  ሽያጭ…
የሸገር ደርቢ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት በሁለቱ ክለቦች ከሚሠሩ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጋር ስፖርት አድማስ ያደረጋቸው ውድድሮች ያመለክታሉ። በአዲስ አበባ ስታድዬም የሚደረገው የሁለቱ ክለቦች ፍልሚያ ማራኪ የድጋፍ አሰጣጦችን ይስተዋሉበታል። የደጋፊዎቻቸውን ልዩ ትኩረትና ድባብም ያስገኛል። በስፖርታዊ ጨዋነት አዳዲስ ተመክሮዎች ያጋጥሙታል። በተለያዩ የስፖርት አልባሳትና የድጋፍ ቁሳቁሶች  ገበያ ይደራል ከፍተኛ ሽያጭ ይመዘገባል፡፡ እንዲሁም ከትኬት ሽያጭ ባለሜዳው ክለብ ከፍተኛውን የስታድዬም ገቢ የሚያገኙበት እንደሆነም ይታወቃል፡፡
በመጀመርያ ዙር የ8ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ ሁለቱ ክለቦች በተገናኙበት ወቅት ባለሜዳው የነበረው ኢትዮጵያ ቡና ነው፡፡ በደጋፊዎች ማህበሩ አስተባባሪነት ባካሄደው የትኬት ሽያጭ ብቻ ከ970ሺ ብር በላይ መሰብሰቡን ለስፖርት አድማስ የገለፀው የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ደጋፊዎች ማህበር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ክፍሌ ወልዴ ነው፡፡  ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በተገኘው መረጃ መሰረት  የኢትዮጵያ ቡና ክለብ በመጀመርያ ዙር ብቻ ከስታድዬም የትኬት ሽያጭ ያገኘው የገቢ ድርሻ ከ1.9 ሚሊዮን ብር በላይ  ሲሆን ይህ በሊጉ ታሪክ ከፍተኛው እንደሆነ ይገለፃል፡፡ ለቡና ክለብ የሜዳ ገቢ መጠናከር የደጋፊዎች ማህበሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን  አቶ ክፍሌ ሲያስገነዝብ፤ ተመዝግበው የአባልነት መዋጮ የሚከፍሉ የክለቡ ደጋፊዎች ብዛት ከ13ሺ ማለፉን በመጥቀስ ነው ባለፉት 18 ወራት ብቻ ከ8ሺ በላይ ደጋፊዎች ተመዝግበዋል ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና የደጋፊዎች ማህበር በስፖርታዊ ጨዋነት  ከፍተኛ እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ መቆየቱ ውጤታማ ተግባራት ለማከናወን ማገዙን አቶ ክፍሌ ያብራራል ከሊጉ መጀመር በፊት በክረምት ወራት በደቡብ ክልል ከሚገኙት ወላይታ ዲቻ፤ ሲዳማ ቡና፤ አርባምንጭ ከነማ እና ሃዋሳ ከነማ ክለቦች አመራሮች እና የደጋፊ ማህበራት ጋር በስፖርታዊ ጨዋነት እና በማህበሩ እንቅስቃሴ የተደረጉት የውይይት እና የልምድ ልውውጥ መድረኮች ነበሩ፡፡ ከክልል ክለቦች በደጋፊ ማህበራት በኩል  ትስስር በመፍጠር የተካሄዱት መሰል እንቅስቃሴዎች ውጤታማ ነበሩ የሚለው ክፍሌ፤ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ደጋፊዎች በየክልሉ በሰላማዊ መንገድ ተዘዋውረው ጨዋታዎችን መመልከታቸው የየክለቦችን ገቢ እንደሚጨምር፤ በየሄዱበት ሁሉ በየስታድዬሙ ቦታዎች ኖሯቸው እና ፀጥታና ደህንነቱ አስተማማኝ ሆኖላቸው ለክለባቸው ድጋፍ እንዲሰጡ አድርጓል ብሏል፡፡ የደጋፊዎች ማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ እንደሚናገረው የሊጉ ውድድር ከተጀመረ በኋላ በመጀመርያው ዙር ከዚያም ሁለተኛው ዙር ከገባ በኋላ ከፋሲል ከነማ እና ከድሬዳዋ ከነማ ክለቦች ጋር የተደረጉ እንቅስቃሴዎችም ውጤታማ ነበሩ፡፡ ይህም በየክልሉ በሚደረጉ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ቡና ለመደገፍ ጉዞ የሚያደርጉት ደጋፊዎች እንደ አመቺነቱ ከ1 ሺ ጀምሮ እስከ 4ሺ አድርሶታል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ከሀበሻ ቢራ ጋር በፈረመው ውል መሰረት ዘንድሮ 10 ሺ ማልያዎችን በአዲዳስ ወይም በናይኪ ኩባንያዎች በጥራት በማሰራት ለደጋፊዎቹ ማቅረብ ቢፈልግም በወቅቱ አልደረሰለትም የሚለው አቶ ክፍሌ የደጋፊውን ፍላጎት ለማርካት በቻይና የተመረቱ 5 ሺ  ማልያዎችን  በ220 ብር ዋጋ ቀርበው ሙሉ ለሙሉ መሸጣቸውን፤ ክለቡ ደግሞ በተጨማሪ ያስመጣቸው ቡኒ እና ቢጫ 3ሺ ማልያዎችን በ230 ብር ዋጋ ተሸጠው ሊያልቁ መሆኑን ጠቅሶ  የደጋፊ ማህበሩ ከዚሁ የማልያዎቹ ሽያጭ 20% በማግኘቱ ተጠቃሚ መሆኑንም ገልጿል፡፡
የደርቢው ጨዋታ ከባድ ፉክክር ያለበት፤ በደጋፊዎቹ መካከል ውጥረት የነገሰበትና ብዙ ትኩረት የሚሰጠው ነው የሚለው አቶ ክፍሌ ዘውዴ፤  የኢትዮጵያ ቡና የደጋፊዎች ማህበር ደጋፊዎችን የሚያስተባብሩ፣ ሰላማዊ ድጋፍ አሰጣጥ እንዲፈጠር የሚሰሩ 60 የስታድዬም አስከባሪዎችን አዘጋጅቶ ያሰማራል ሲል ተናግሯል፡፡
በሌላ በኩል የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምኒልክ ግርማ ለስፖርት አድማስ እንደሚናገረው በማልያዎች ሽያጭ፣ በደጋፊ ብዛት መጨመር ፤ በአፍሪካ ደረጃ ያለውን ታሪክ በመቀየር እና አካዳሚውን በማስመረቅ ክለቡ ስኬታማ ሆኗል፡፡ በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ  የተለያዩ ደረጃ ያላቸውን የቅዱስ ጊዮርጊስ 5ሺ ማልያዎች አቅርቦ በሰባት ወር መሸጡ ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ባለዳማው ማልያ ዋጋው 400 ብር ሲሆን ከ1 ሺ በላይ ፤ማክሮን የተባለ ሌላ ማልያ በ220 ብር ዋጋ 5 ሺ ያህል ለገበያ ቀርቦ ሙለሙሉ ተሸጦ አልቋል ያለው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው የክለቡ ስፖንሰር ደርባ አርማ የተለጠፈበት ማልያም እየተሸጠ መሆኑን  ገልፆ፤ በሌላ በኩል “የክለቡ ስካርፍ ከ1000 በላይ መሸጡን ገልጿል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በተያዘው የውድድር ዘመን በሲቲ ካፕ፣ በጥሎ ማለፍ ውድድሮች ስኬታማ መሆኑን ተከትሎ እንዲሁም በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒየንስ ሊግ የምድብ ድልድል መግባቱና በስታድየም ህብረ ዝማሬ ልዩ ድባብ መፈጠሩ የደጋፊዎቹን ብዛት እንዲጨምር አድርጎታል ያለው ምኒልክ በአሁኑ ወቅት የተመዘገቡ የክለቡ ደጋፊዎች ብዛት ከ14ሺ 700 በላይ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
በርግጥም የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር በውድድር ዘመኑ በከፈታቸው አዳዲስ ምዕራፎች ሁለቱ ለመላው የአገሪቱ ክለቦች ፈርቀዳጅና ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር በደብረዘይት ፤ ቢሾፍቱ ከተማ ላይ በ60 ሚሊዮን ብር ወጭ በ24.000 ካሬ ሜትር ላይ ያስገነባው  ይድነቃቸው ተሰማ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ መመረቂ የመጀመሪያው ነው፡፡ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሚሆናቸውን 100 ታዳጊ እግር ኳስ ተጨዋቾች የሚያስተናግደው አካዳሚ ሁለት ኳስ ሜዳዎች፤ ዘመናዊ ጂምናዚየምና የህክምና ማዕከል፣ የስብሰባ አደራሽ፤ ካፍቴሪያ … እንዲሁም G+1 የተጨዋቾች መኖሪያ ቤት የተገነባለት  ነው፡፡ በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ የመጀመርያውን የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በመገንባት ፈርቀዳጅ የሆነው ክለቡ በአፍሪካ ደረጃም ከትልልቅ ክለቦች ተርታ የሚሰለፍበት የስፖርት መሰረተልማት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል በ2017 ቶታል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ  ኢትዮጵያን በመወከል በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የምድብ ፉክክር ውስጥ በመግባት ቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪክ ሰርቷል፡፡

ለፊፋ የደጋፊዎች አዋርድ በማመልከት
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፊፋ ከ2016 እኤአ ጀምሮ በየዓመቱ በሚያካሂደው የዓመቱ ኮከቦች ምርጫ የደጋፊዎች ልዩ ሽልማት መስጠት እንደጀመረ ይታወቃል፡፡ ስፖርት አድማስ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በተናጠል እና በህብረት በዚሁ ልዩ የሽልማት ዘርፍ መወዳደር እንደሚችሉ፤ ከመጨረሻዎቹ 3 እጩዎች ተርታ በመግባት ለማሸነፍ የሚፎካከሩበት እድልም እንዳላቸው ለመጠቆም ይፈልጋል፡፡
በ2016 የፊፋ ደጋፊ አዋርድ FIFA FAN AWARD ላይ የመጨረሻ እጩዎች ሆነው የቀረቡትን 3 የድጋፍ አሰጣጦች በመመልከት ሁለቱ የኢትዮጵያ ክለቦች  ለመወዳደር ብቁ መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል። 3ቱ የመጨረሻ እጩዎች በ2016 የአውሮፓ ዋንጫ ላይ የነበሩት የአይስላንድ ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች፤ የሆላንዱ አዶ ዴን ሃግ ክለብ ደጋፊዎች እና በዩሮፓ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በህብረት ልዩ ትእይንት  ያሳዩት የጀርመኑ ቦርስያ ዶርትመንድ እና የሊቨርፑል ደጋፊዎች ናቸው፡፡
የአይስላንድ  ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች  በመጨረሻ እጩነት የቀረቡት በጭብጨባ እና ህብረ ዝማሬያቸው ነበር፡፡ በዩሮ 2016 ላይ ብሄራዊ ቡድናቸው ለሩብ ፍፃሜ የደረሰበት አስደናቂ ታሪክ የሚዘነጋ አይደለም፡፡  በተለይ በሩብ ፍፃሜ ከአዘጋጇ ፈረንሳይ ጋር ተገናኝተው ባደረጉት ጨዋታ  ላይ የአይስላንድ ደጋፊዎች ከብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ጋር እጃቸውን ወደላይ አንስተው በማጨብጨብና ህብረዝማሬ በማሰማት ትኩረት ስበዋል፡፡ የሆላንዱ ክለብ አዶ ዴን ሃግ ደጋፊዎች ደግሞ የድጋፍ አሰጣጣቸውን ከበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ ጋር በማተሳሰር በመጨረሻ እጩነት ሊቀርቡ ችለዋል፡፡ በሆላንድ ኤርዲቪዜ ከአንጋፋው ክለብ ፋየኖርድ ጋር በተደረገ ጨዋታ የአዶ ዴን ሃግ ደጋፊዎች በዴኮውፕ ስታድዬም ለነበሩ ተቀናቃኝ ደጋፊዎች አሻንጉሊቶችን ከላይ ወደታች በመወርወር አስደናቂ ተግባራቸውን የፈፀሙ ሲሆን፤ በሮተርዳም የሚገኝ ሶፊያ የተባለ የህፃናት ማዕከልን ለመደገፍ በሚል ነበር፡፡  
በ2016 የፊፋ ደጋፊ አዋርድ FIFA FAN AWARD ላይ በታሪክ የመጀመርያዎቹ አሸናፊዎች ሊሆኑ የበቁት ግን የጀርመኑ ቦርስያ ዶርትመንድ እና የእንግሊዙ ሊቨርፑል ደጋፊዎች ናቸው፡፡ ሁለቱ ክለቦች በዩሮፓ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ የተገናኙበት ቀን በሂልስቦሮው የሊቨርፑል ደጋፊዎች በስታድዬም ግርግር ያለቁበት 27ኛ ዓመት መታሰቢያ  ነበር፡፡ ከጨዋታ በፊት የሁለቱ ክለቦች  ደጋፊዎች ስታድዬሙን በቢጫ እና ቀይ ቀለሞቻቸው አሸብርቀው በአንድነት ዘምረዋል። የሚያገርመው ህብረ ዝማሬያቸው የሊቨርፑል ደጋፊዎች ታዋቂ መዝሙር ‹‹ዩ ኔቨር ዎክ አሎን›› ነበር፡፡
በፊፋ ድረገፅ ስለ የፊፋ ደጋፊ አዋርድ FIFA FAN AWARD በቀረበው ዝርዝር መረጃ መሰረት በሽልማቱ ዘርፉ ለመወዳደር  በየትኛውም አገር፤ በማንኛውም የእግር ኳስ ውድድር ላይ ያሉ ደጋፊዎች ማመልከት ይችላሉ፡፡ ደጋፊዎች በስታድዬም በሚያሰሙት የተቀናጀ ህብረ ዝማሬ፤ በሚያሳዩት የተጠናና ማራኪ የድጋፍ እንቅስቃሴ  እንዲሁም በተለያዩ የስፖርታዊ ጨዋነት ተግባራት የታጀቡ ድጋፍ አሰጣጦቻቸው ለማመልከት ብቁ ያደርጋቸዋል፡፡ በቪድዮ ምስል ተዘጋጅተው በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለፊፋ የሚቀርቡት  እነዚህ ድጋፍ አሰጣጦች በተለይ በዓለም አቀፉ ማህበር ኦፊሴላዊ ፌስቡክ ገፅ የሚሰራጩ ናቸው፡፡ የመጨረሻ 3 እጩዎችን ለመለየት ደግሞ ፊፋ በስሩ ያቋቋመው ልዩ ፓናል ያለ ሲሆን ታዋቂዎቹ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ቦባን፤ ባቲስቱታ፤ ፔትኮቪች እንዲሁም ብራዚላዊቷ ማርታ የሚገኙበት ነው፡፡ በመላው ዓለም ትኩረት የሳቡ ተወዳዳሪ የድጋፍ አሰጣጦች የፊፋ ባለድርሻ አካላት እና ፓናሉ በሚያደርጉት ምክክር የመጨረሻ ሶስት እጩዎችን በመለየት በፊፋ ድረገፅ መላው ስፖርት አፍቃሪ ድምፅ እንዲሰጥባቸው ያቀርባሉ፡፡ ከዚያም አሸናፊው ተለይቶ ይታወቃል፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር  ፊፋ ለ2017 የፊፋ ደጋፊ አዋርድ አመልካቾችን መቀበል ከጀመረ 4 ወራት የተቆጠሩ ሲሆን ለማመልከት ቀሪ 6 ወራቶችም አሉ፡፡ ስለዚህም የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በዚሁ ሽልማት በየራሳቸው አቅጣጫ ወይንም በህብረት ተፎካካሪ ሆነው ለመቅረብ የተለየ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የሸገር ደርቢ ደግሞ ለዚህ አይነተኛ መድረክ ነው፡፡ በዚሁ ሽልማት በመወዳደር ሁለቱ ክለቦች የአገሪቱን እግር ኳስ፤ የየክለባቸውን ብራንድ እና የሊግ ውድድር በከፍተኛ ደረጃ ያስተዋውቁበታል፡፡

-------------------

                 ሸገር ደርቢ
         በ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ   ሁለተኛ ዙር  በፋሲካ በዓል ዋዜማ ሁለቱን ክለቦች የሚያገናኘው ሸገር ደርቢ በታሪክ 37ኛው  ነው፡፡ በሁለቱ ክለቦች መካከል በሁሉም ውድድሮች  36 ፍልሚያዎች መደረጋቸውን የሚጠቅሱ መረጃዎች፤  20 ጊዜ  ቅዱስ ጊዮርጊስ ማሸነፉን፤ ኢትዮጵያ ቡና  7 ጊዜ መርታቱን እንዲሁም በ9 ጨዋታዎች  አቻ መለያየታቸውን ያመለክታሉ፡፡ ባለፉት አምስት የውድድር ዘመናት በተገናኙባቸው የሸገር ደርቢ ጨዋታዎች የተመዘገቡት ውጤቶች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡
በ2004 ዓ.ም በመጀመርያ ዙር 0ለ0 ፤ በሁለተኛው ዙር ቡና 0 ጊዮርጊስ 3
በ2005 ዓ.ም በመጀመርያ ዙር ጊዮርጊስ 2 ቡና 0 ፤በሁለተኛው ዙር ቡና 1 ጊዮርጊስ 0
በ2006 ዓ.ም በመጀመርያ ዙር ጊዮርጊስ 0 ቡና 1፤ በሁለተኛ ዙር ቡና 1 ጊዮርጊስ 2
በ2007 ዓ.ም በመጀመርያ ዙር ቡና 0 ጊዮርጊስ፤ 2 በሁለተኛ ዙር ጊዮርጊስ 0 ቡና 1  
በ2008 ዓ.ም በመጀመርያ ዙር ቡና 1 ጊዮርጊስ 0፤ በሁለተኛው ዙር 0ለ0

Read 1874 times