Saturday, 15 April 2017 12:40

በፋሲካ በዓል የጎንደር ከብቶች ገበያውን ተቆጣጥረውታል

Written by 
Rate this item
(10 votes)

የወለጋ፣ የሐረርና የቦረና ከብቶች ዘንድሮ ወደ አዲስ አበባ አልገቡም

በአቃቂ ለ12 ዓመታት በበሬና በበግ ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ አስቻለው ሽመልስ፤ ከዓምናው የትንሳኤ በዓል ገበያ አንፃር ሲታይ የዘንድሮው በከብቶች ጥራትም ሆነ በዋጋ የተሻለ ነው ይላሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ዓምና በሬ አምራች በሆኑ እንደ አርሲና ሐረር አካባቢዎች፣ ድርቅ በመከሰቱ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡  ማተሚያ ቤት እስገባንበት ሐሙስ ድረስ በአቃቂ ባደረግነው የገበያ ቅኝት፤ መካከለኛ በሬ ከ8 ሺህ - 11 ሺህ ብር፣ ትልቅ በሬ  እስከ 30 ሺህ ብር ሲሸጥ ሰንብቷል፡፡ የበግ ዋጋ ከወትሮው እምብዛም የዋጋ ጭማሪ ያላሳየ ሲሆን ትንሹ 1ሺ 200 ብር፣ሙክት የሚባለው እስከ 8 ሺህ ብር እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚሁ ገበያ ዶሮ ከ300 ብር እስከ 350 ብር ሲሸጥ ሰንብቷል፡፡ በሾላ ገበያ ደግሞ በግ ከ1800 ብር  - 3100 ብር
እየተሸጠ ሲሆን በበዓሉ ዋዜማ የከብቶች ዋጋ ሊጨምር እንደሚችል ነጋዴዎችና ሸማቾች ተናግረዋል፡፡
እዚያው ሾላ ሌሎች የበዓል ገበያዎችን እንመልከት፡- ቀይ ሽንኩርት በኪሎ፡- ከ10-12 ብር፣ ቲማቲም 15 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 60 ብር እየተሸጡ ሲሆን ቅቤ በኪሎ ከ160-250 ብር፣ ዶሮ ከ190-300 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ አይብ በኪሎ ከ45-55 ብር፣ እንቁላል ከ3.50 እስከ 3 ብር ከ75 የሚገኝ ሲሆን የተፈጨ በርበሬ በኪሎ፡- ከ140 ብር እስከ 155 ብር ይሸጣል፡፡ የዳቦ ዱቄት በመደበኛ ሱቆች 1ኛ ደረጃ የሚባለው ኪሎው 14 ብር
እየተሸጠ ሲሆን በተለያዩ የሸማች ማህበራት ሱቆች በኪሎ እስከ 8 ብር እንደሚሸጥ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ሆኖም በጉለሌ ክፍለ ከተማ በሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ፣ በአራዳ፣ በየካ፣ በቦሌ ክ/ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፤ በአብዛኛዎቹ የሸማች ማህበራት ሱቆች፣ የዘይትና የዱቄት አቅርቦት በመቋረጡ፣ በመደበኛ ሱቆች በውድ ዋጋ ለመሸመት ተገድደዋል፡፡   ፈረንሳይ ለጋሲዮን፣ በተለምዶ ብረት ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከአንድ ዓመት በፊት የተመሰረተው “ዳንኤል ኢዛናና ጓደኞቻቸው
የዶሮ እርባታ ሽርክና ማህበር” በበኩሉ፤ ለበዓሉ የምስራች አለኝ ይላል - እንቁላል በ2 ብር ከ50 እንደሚሸጡ በመግለጽ፡፡ ማህበሩ፤ከአንድ ሺህ በላይ ዶሮዎችን ለእንቁላል ምርት ብቻ በማዘጋጀት፣በቀን ከ900 በላይ እንቁላሎችን እንደሚያመርቱም አስታውቋል።  በከተማዋ የእንቁላል እጥረት እንዳለ በጥናት እንዳረጋገጡና ይህንን ክፍተት ለመሙላት ወደ ስራው እንደገቡ የሚገልጹት ወጣቶቹ፤ በበዓልም ሆነ በአዘቦት ቀናት ገበያ ላይ ከ3 ብር ከ50 እስከ 4 ብር የሚሸጠውን እንቁላል፣ በ2 ብር ከ50 እየሸጡ እንደሆነ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ
ተናግሯል፡፡ “እኛ የዶሮ እርባታችን ድረስ ለሚመጡ ግለሰቦችም ሆነ ለአከፋፋዮች በ2 ብር ከ50 እየሸጥን” ነው ያለው ስራ አስኪያጁ፤ በቅርቡ የዶሮዎቹን ብዛት ወደ ሁለት ሺህ በማድረስ፣ የእንቁላል ምርት በመጨመርና ዋጋውን አሁን ከሚሸጡበት በመቀነስ፣ ማህበረሰቡ እንዲጠቀም ለማድረግ ማሰባቸውንም ጠቁሟል። ለአዲስ ዓመትም ለስጋ ምርትነት የሚያገለግሉ ዶሮዎችን በማርባት 300 ብር እና ከዚያ በላይ የገባውን የዶሮ
ዋጋ ልክ እንደ እንቁላሉ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እንዳቀዱ የተናገረው አቶ ኢዛና፤ “አሁንም እንቁላል በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልግ ሰው የዶሮ እርባታ ቦታችን በሆነው ብረት ድልድይ አካባቢ በመምጣት፣ በ2 ብር ከ50 መግዛት ይችላል” ብሏል፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ምንጮቻችንን እንደጠቆሙን፤ በዘንድሮው የትንሳኤ በዓል ከወትሮው በተለየ የጎንደር ከብቶች ገበያውን የተቆጣጠሩት ሲሆን የወለጋ፣ ቦረና፣ ክብረ መንግስትና የሐረር ከብቶች ለበዓሉ ወደ አዲስ አበባ አልመጡም ተብሏል፡፡ በስጋቸው
ጣፋጭነት በእጅጉ የተወደዱትና የተለመዱት የሐረርና የቦረና ከብቶች በዘንድሮ በዓል የት እንደገቡ ከአስተማማኝ ወገን ማረጋገጥ ባይቻልም በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ፣ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን በግልና በመንግስት ለተቋቋሙ የከብት ማደለቢያ ማዕከላት በመሸጣቸው ሊሆን እንደሚችል የገለጹልን ምንጮቻችን፤ ብዙ ከብቶችም ወደ ውጪ ገበያ እየተላኩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ የንግድ ጽ/ቤት የቄራዎች የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተክኤ ግደይ፣ ለበዓሉ እስከ 2ሺ የሚደርሱ ከብቶች ወደ ገበያ ማዕከሉ እንደሚገቡ ጠቁመው፣ በዘንድሮው የፋሲካ በዓል በአብዛኛው የጎንደርና የሰሜን ሸዋ ከብቶች ለሽያጭ መቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡



Read 7624 times