Saturday, 15 April 2017 12:35

የጋምቤላ ሀገረ ስብከት፤ ”የኪዳነ ምሕረት ጽላት ጠፋ” መባሉን አስተባበለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

• የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ “አዲስ አድማስ” ይቅርታ መጠየቅ አለበት አሉ
• በውሸት ወሬ ይነዛሉ ባሏቸው ወገኖች ላይ እርግማን አወረዱ

   የጋምቤላ ክልልና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ጽ/ቤት፥ መንበረ ጵጵስና በሆነችው የሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል፣ “የወርቅ ጽላት የገባበት ጠፋ” መባሉን ሀገረ ስብከቱ ያስተባበለ ሲሆን፤ ዋና ሥራ አስኪያጁ በበኩላቸው፤”ዘገባውን የሠራው የ”አዲስ አድማስ” ጋዜጠኛ፣ ይቅርታ ይጠይቀኝ” ብለዋል፡፡   
በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በኩል ለዝግጅት ክፍሉ የደረሰው የአህጉረ ስብከቱ ማስተባበያ፣ “ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተለበጠው የጋምቤላ ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል ታቦት የደረሰበት ጠፋ” በሚል ርእስ፣ባለፈው መጋቢት 23 የቀረበው የአዲስ አድማስ ዘገባ፤“በቤተ ክርስቲያኗ መልካም ስምና ዝና ላይ የተፈጸመ የሐሰት ውንጀላና ስም ማጥፋት ነው” በማለት ተቃውሟል፡፡የኪዳነ ምሕረት ጽላት ሳይጠፋ ጠፍቷል፤በማለት ውሸት መነዛቱን የጠቀሰው ማስተባበያው፤ ጽላት መኖሩን አረጋግጠዋል የተባሉት፦ የካቴድራሉ
ቄሰ ገበዝና አገልጋዮች እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ አባላት፣በእማኝነት የፈረሙበትን ሰነድ አያይዞ አቅርቧል፡፡የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት፣ ለአህጉረ ስብከቱ በጻፈው ደብዳቤ፣ የታቦቱን መኖር በዓይን እማኝነት አረጋግጠዋል ያላቸውን አራት የካቴድራሉን ሓላፊዎችና አንድ የሌላ ወረዳና ደብር ሓላፊ እንዲሁም 12 የሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ አባላትን በእማኝነት አካቷል፡፡
የጋምቤላ ከተማ ምእመናን ተወካዮች ጽላቱ ጠፍቷል በሚል ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤትና ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ባስገቡት አቤቱታ፤ አስቸኳይ ምርመራና ማጣራት እንዲካሔድ መማጸናቸው በዘገባው መጠቀሱን ያስታወሰው ማስተባበያው፤ “ምዕመናኑ ወደ
አዲስ አበባ ሳይሔዱ እንደሔዱ በማስመሰል የቀረበ የተሳሳተ መረጃ ነው” ብሏል፡፡ “መቀመጫቸውን አዲስ አበባ አድርገው፣ በሃይማኖት ሽፋን በክልሉ ሁከትና ትርምስ እንዲፈጠር በሚፈልጉ ግለሰቦች የታቀደ ሐሰት ነው” ሲልም ማስተባበያው ጠቁሟል።  ዘገባው በወጣበት ሳምንት፣ የአህጉረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት፣ እንደ አኮቦና ጂካዎ ባሉ ጠረፋማ
ወረዳዎች ቤተ ክርስቲያን በማሠራት ላይ እንደነበሩና በክልሉ 54 አብያተ ክርስቲያናትን እንዳሳነፁ ያወሳው ማስተባበያው፣ አንድም የተዘጋ ቤተ ክርስቲያን እንደሌለና ዋና ሥራ አስኪያጁም፣ ከሕዝብና ከመንግሥት ጋራ በፍቅርና በሰላም ተግተው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል፣ እንደ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ የካቴድራሉ ጽላት ጉዳይ የሚመለከተው ቄሰ ገበዙንና አስተዳዳሪውን እንጂ እርሳቸውን እንዳልሆነ ባለፈው እሑድ የሆሣዕና በዓል ላይ ለምእመናን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ 17 ካህናትን ይዘው ገብተው ጽላቱ በመንበሩ ላይ መኖሩን
እንዳረጋገጡና በቃለ ጉባኤም እንደተፈራረሙ ተናግረዋል፡፡ “ከ107 በላይ ታቦታትን ለክልላችሁ በነጻ የሰጠሁ ነኝ፤ በገንዘብ ቢተመን ስንት ብር ያወጣል?” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡  “ሃሰተኛ ወሬው የተነዛው ጋምቤላን በዚህ እናተረማምሳለን ብለው ባቀዱ ፀረ ሰላም ኃይሎች ነው” ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ሆኖም አልተሳካላቸውም ብለዋል፡፡ “የሚያተረማምሱት ስምንት ሰዎች ናቸው፤ ስምንቱንም እኔ ዐውቃቸዋለሁ” ያሉት መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት፤ ከስምንቱ ተፈላጊዎችም፣ ሁለቱ ተይዘው ቦንጋ እስር ቤት መግባታቸውን ጠቁመው፤ “አንዱ ትላንት ማተሚያ ቤት ገብቶ አምልጧል፤ ሲመጣ እጠይቀዋለሁ” ብለዋል፡፡ ጉዳዩን ለመንግሥት አሳልፈው መስጠታቸውንና የግለሰቦቹ ማንነትም ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ይፋ እንደሚሆን
ለምዕመናኑ አክለው ገልጸዋል፡፡  የአገረ ስብከቱ የማስተባበያ ደብዳቤ ለዝግጅት ክፍሉ ከደረሰ በኋላ ሥራ አስኪያጁ በሆሳዕና በዓል ላይ ለምዕመናን ባደረጉት በዚህ ንግግራቸው፤ ዘገባውን የሰራው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ይቅርታ ካልጠየቀ፣ሀገረ ስብከቱ ፍርድ ቤት እንደሚገትረው ዝተዋል፡፡ “በውሸት ወሬ
ይነዛሉ፤ሃይማኖትንና ቤተ ክርስቲያንን ለማንኳሰስ ተነሣስተዋል” ሲሉ በወነጀሏቸው ማንነታቸው በግልጽ ያልታወቀ ወገኖች ላይም እርግማን አውርደዋል- ሥራ አስኪያጁ፡፡ … በእኔ በአባ ተክለ ሃይማኖት ላይ ምንም አታገኙብኝም፤ አትድከሙ” ሲሉ በዐውደ ምሕረቱ ላይ ስለ ንጽሕናቸው መሟገታቸውን ለዝግጅት ክፍሉ የደረሰው የድምጽ ማስረጃ ይጠቁሟል፡፡ አዲስ አድማስ፣ በመጋቢት 23 እትሙ፣ የጋምቤላ ከተማ ምእመናን ተወካዮች፣ የኪዳነ ምሕረት ጽላት በመንበሯ ላይ አለመኖሯን በመጠቆም፣ ለመንበረ ፓትርያርኩ ያደረሱትን አቤቱታ ጠቅሶ፣ የጽላቱን መጥፋት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ የምእመናኑ ተወካዮች፥ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣
ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤትና ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አቤቱታቸውን አስፈርመው የሰጡበት ሰነድ ለዝግጅት ክፍሉ የደረሰው ሲሆን፤ ጽላቱ በመንበሩ ላይ አለመኖሩን የሚያሳይ የቪዲዮ ምስልም በማስረጃነት መቅረቡን መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ ለተፈጠረው አለመግባባት የዝግጅት ክፍሉ
ይቅርታ ይጠይቃል፡፡

Read 3703 times