Monday, 10 April 2017 11:09

አልማዝ

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(6 votes)

 ወደ አውሮፕላን ማረፍያው   የደረሰው   በጊዜ ነበር፡፡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በሙሉ አድርጓል፡፡ የደቡብ  አፍሪካው  አየር መንገድ  የበረራ  ቁጥር 892 አውሮፕላን፣ አዲስ አበባ የሚገባው  ልክ ከጠዋቱ  4 ሰዓት  ከ 15 ደቂቃ  መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በዚያ አውሮፕላን አንዲት ህጻን ልጅ  አቅፋ በምታመጣው አሻንጉሊት ውስጥ የተደበቀው ዕቃ፣ ዕድሜ ልኩን ቁጭ ብሎ እንዲበላ የሚያደርገው ሀብት ነው። ሰማያዊ ህብር ያለው፣ ሃምሳ ግራም የሚመዝን አልማዝ።
ሰለሞን ቀላል ሰው አይደለም፡፡ ዕድሜው ወደ 40ዎቹ መጀመሪያ የሚጠጋ፣ አዳዲስና ውጤታማ የንግድ ሀሳቦችን በማመንጨት አብረውት በሚሰሩት ላይ አድናቆትን በመፍጠር የሚታወቅ፣ ሲበዛ ጮሌ የሆነ፣ እሳት የላሰ ደላላ ነው፡፡ ቀጠን ብሎ ረዘም ያለ፣ ወሬ የሚያነፈንፍ የሚመስል ሾካካ አፍንጫ ያለው፣ ፀጉሩ ወደ ኋላ ገባ ያለ ነው፡፡ አራት ቋንቋዎችን አቀላጥፎ መናገር ይችላል፡፡ ጓደኞቹ በሙሉ የናጠጡ ሀብታሞች ናቸው፡፡ የግንኙነት መረቡ በጣም ሰፊ ሲሆን የቡና ነጋዴዎች፣ የጫት ቱጃሮች፣ የጅምላ ንግድ አከፋፋዮች፣ የሰራተኛና አሰሪ አገናኝ ወኪሎች--- ኪሱ ውስጥ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ በመገረም፣ በመደነቅና በጥላቻ ነው የሚመለከቱት፡፡ ምክንያቱም እነሱ ሊያዩት ያልቻሉትን የቢዝነስ ሐሳብ በቀላሉ እያመነጨ ከመዳፋቸው ውስጥ ገንዘብ መንጭቆ ስለሚወስድ ነው፡፡ እንደውም አንዱ ጓደኛው “..ለምን የሐሳብ መሸጫ ቢሮ አትከፍትም..” እስኪለው ድረስ አዳዲስ ሀሳቦችን በማመንጨት ተወዳዳሪ የለውም፡፡
እንደ አለመታደል ሆኖ ግን እንደሚመኘው ሃብታም መሆን አልቻለም፡፡ አብረውት የሚውሉት ቱጃር ጓደኞቹም፤ ሲበሉ ከማብላት፣ ሲጠጡ ከማጠጣትና አልፎ አልፎ ለእጁ ከሚሰጡት ገንዘብ ያለፈ ነገር ሊያደርጉለት አልቻሉም፡፡ በድለላውም ቢሆን እንደሱ አነጋገር፣ እስካሁን አሪፍ ዝግ ዘግቶ አያውቅም፡፡ ገንዘብ ባይቸግረውም ህይወቱን ከመሰረቱ የሚለውጥ ሀብት ግን ሊያገኝ አልቻለም፡፡  
አሁን ግን ይሄ ሁሉ ሊቀየር ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ይኖር የነበረው ሚስተር ኮፊ- በእናቱ ጋናዊ፣ በአባቱ ደቡብ አፍሪካዊ የሆነውና ጊዜ ያነሳው ቱጃር፣ ህይወቱን ሊቀይርለት ነው፡፡ ሚስተር ኮፊ ከወላጅ አባቱ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ካፒታል ያለው የአልማዝ መሸጫ ሱቅ የወረሰ የናጠጠ ቱጃር ነው፡፡ ከሁለት አመታት በፊት ግን አዲስ አበባ በሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ውስጥ ተራ የመዝገብ ቤት ሰራተኛ ነበር፡፡ የተዋወቁትም ሚስተር ኮፊ የሚኖርበትን ቤት ደልሎ ያገኘው ሰለሞን ስለነበረ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የቅርብ ጓደኛሞች ሆኑ። በርካታ ምሽቶችን አብረው ሲጠጡ አሳልፈዋል፡፡ ግዙፉና ውስጠ - ረጅሙ ሚስተር ኮፊ ከሚወዳቸው  ነገሮች መካከል  ዘወትር ከአፉ የማይለየው ፒፓው፣ በርበሬ የበዛበት የዶሮ ወጥና ትላልቅ ጡቶች ያላት የሐበሻ ሴት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሰለሞን ታዲያ መዓዛ የተባለችውንና በሰፈሩ በጡቷ ትልቅነት ምክንያት “.ሱቅ በደረቴ” የሚል ቅጽል ስም የወጣላትን  የአክስቱን ልጅ ያስተዋወቀው የዛሬ አመት ገደማ ነበር፡፡ ሚስተር ኮፊ ከመዓዛ ጋር በፍቅር ከነፈ፡፡ በመጨረሻም አገባት፡፡ ለዚህ ውለታውም ሰለሞን በሚስተር ኮፊ አይን እንደ ወንድም የሚታይ የልብ ጓደኛ ሆነ፡፡  የዛሬ ሶስት ወር የሚስተር ኮፊ ቱጃር አባት በጠና ታመው ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጠራ፣ በሁለት እጁ የሰለሞንን ትከሻ ይዞ በፍጹም እንደማይረሳው ቃል ገብቶለት ነበር፡፡ ይኸው እንዳለውም አልረሳውም፡፡ በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ዋጋ ያለው አልማዝ ልኮለታል፡፡
መታወቂያውን አሳይቶ ወደ ተርሚናሉ ገባ። የአውሮፕላን ማረፍያው ተርሚናል በሰው ብዛት ተጨናንቋል፡፡ አንዱን የመስተንግዶ ሰራተኛ፣ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 892 ፣ አዲስ አበባ ደርሶ እንደሆነ ሲጠይቀው፣ ከገባ አምስት ደቂቃ እንደአለፈው ነገረው፡፡ የለበሰው አመድማ ካፖርት እስኪውለበለብ ድረስ እየሮጠ፣ ወደ መንገደኞች መግቢያ በር አመራ፡፡ እንደ ደረሰም የተሰለፉ ሰዎች የጉዞ ሰነዶቻቸውን ለኃላፊዎች እያሳዩ ነበር። ልጅቷንም ከሩቁ ለያት፡፡ አንዲት ፀጉረ ረጅም፣ የሙሽራ ቀሚስ የለበሰች፣ አሻንጉሊት የያዘች፣ ከሐበሻ እናትዋ ጋር የተሰለፈች፣የስምንት አመት  ሀበሻ ሴት ልጅ፡፡ ሰለሞን እፎይ አለ፡፡ እሷ በያዘችው አሻንጉሊት ውስጥ ሃምሳ ግራም የሚመዝን፣ ሰማያዊ ህብር ያለው እጅግ በጣም ውድ የሆነ አልማዝ አለ፡፡  
በራሱ የብልጠት ሐሳብ እየተገረመ ልጅቷን በደንብ ተመለከተ፡፡ እናትዋንም በጥንቃቄ አያት፡፡ ነገረኛ ብጤ ትመስላለች፡፡ በሰከንድ አርባ ቃላት የምትናገር አይነት፡፡ አሁን በሷ ቤት ልጅዋ ከአንድ ደቡብ አፍሪካዊ የተበረከተላት የአሻንጉሊት ስጦታ፣ ተራ የመጫወቻ አሻንጉሊት ብቻ መስሏት ይሆናል፡፡
አልማዙን እንዴት እንደሚልክለት ግራ የገባው ሚስተር ኮፊ ሲያማክረው፣ ሰለሞን የፈጠረው ሃሳብ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ህፃናትን ማንም ውድ ዕቃ አስርጐ በማስገባት ሊጠረጥራቸው አይችልም። ሌላው ደግሞ የህፃናት የመጫወቻ አሻንጉሊቶች፣ ልክ እንደ ነጭ እርግብ የንፁህነትና የየዋህነት ምልክት ናቸው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ አሻንጉሊቱ በስጦታ ለራሷ ተሰጣት እንጂ ለሰለሞን አድርሺ ተብሎ አልተሰጣትም፡፡ እሱ ነው በራሱ መንገድና ዘዴ አሻንጉሊቱን እጁ ውስጥ ማስገባት የሚጠበቅበት። ይህ ደግሞ እሱን ከማንኛውም በፖሊስ የመጠርጠርና የመያዝ አደጋ የሚከላከል ዘዴ ነው፡፡ መቼም ይሄን ያህል ውድ ዋጋ ያለው የከበረ ድንጋይ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ ያለው ጣጣ ብዙ ነው። በህጋዊ መንገድ መግባት ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ጥያቄ ጭራሽ ባይነሳ እንኳን፣ አድርስ ተብሎ የሚላከው ሰው በምን ይታመናል? በአሁኑ ጊዜ ማን አይኑ እያየ በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ዋጋ ያለው ዕቃ አሳልፎ ይሰጣል? ስለዚህ አልማዙን አድራሹ እራሱ ሳያውቅ፣ ወደ አዲስ አበባ እንዲያደርስ ማድረግና ምንም በማይጠረጠር ሁኔታ እጅ ውስጥ ማስገባት አማራጭ የሌለው ዘዴ ነበር፡፡ ቢነቃም እንኳን ማን ማንን ያገኛል? አዲስ አበባ ሰፊ ከተማ ነው፡፡ ለዚህ ነበር ሰለሞን አልማዙን አንድ አሻንጉሊት ውስጥ ደብቆ ለአንድ ህፃን የመስጠት ሃሳብ ያመጣው፡፡ ከዚያ አሻንጉሊቱን በጣም የወደደው መስሎ በብዙ ገንዘብ ይገዛዋል፡፡ ወይም በሌላ የተሻለ አሻንጉሊት ይቀይረዋል፡፡ መቼም ማንም ቢሆን ይሄን ሃሳብ የሚቃወም የለም ግን እንደው የተረገመ ጠማማ ሰው እንኳን አጋጥሞት፣ በሁለቱም  መንገድ እምቢ ቢል በሐይል ነጥቆ ወይም ሰርቆ ይፈረጥጣል፡፡ ማንም ሰው አሻንጉሊት ተሰረቅኩኝ ብሎ እንደ ጅል  ከኋላው አይሮጥም፡፡ ወይም ለፖሊስ አያመለክትም፡፡
ከመንገደኞች መግቢያ ፊት ለፊት ካለ የእንግዶች ማረፊያ  ሄዶ ተቀመጠ፡፡ አንዲት ወፍራም ድብዬ ሴትዮ አጠገቡ አለች፡፡ ከጥጥ የተሠራ ወፍራም ቡናማ የድብ አሻንጉሊት ይዛለች፡፡ ከመንገደኞቹ አንድ ሰው እንደምትጠብቅ ጠርጥሯል፡፡ ይህች ሴት የያዘችውን አሻንጉሊት ቢያገኝ፣ ያለ ምንም ጥርጥር ከዚያች የሱን አልማዝ ያለበትን አሻንጉሊት ከያዘች ልጅ ጋር ሊቀያይር ይችላል፡፡ ምክንያቱም ይህቺ ዱብዬ ሴትዮ የያዘችው አሻንጉሊት በጣም ውድና የሚስብ፣ ህፃናት የሚወዱት አይነት ሲሆን አልማዙ ያለበት አሻንጉሊት ግን በዋጋውም ረከስ ያለ፣ ብዙ ዓይን የማይስብ ተራ አሻንጉሊት ስለሆነ ነው፡፡
ወሬ ለመፍጠር ሞከረ፡፡ ሴትየዋ ተግባቢ፣ ተጫዋችና ቅን ሴት ናት፡፡ ማንን ልትቀበል እንደመጣች  ሲጠይቃት፣ ልጇን  እንደሆነ ነገረችው። ከዚያ ድርቅ ብሎ አሻንጉሊቱን ትሸጥለት እንደሆነ ጠየቃት፡፡ ሴትየዋ በመገረም አየችው፡፡
«የልጄ የልደት በአሉ ዛሬ ነው፡፡ ልክ የዚህ ዓይነት አሻንጉሊት መርጦ ገዝቼለት ነበር፡፡ በታክሲ ስመጣ ታክሲ ውስጥ ረሳሁትና ወረድኩ፡፡  ልጄ ምን ያህል ልቡ እንደሚሰበር ይታይሽ..» አለ እየተቅለሰለሰ፡፡
ሴትዮዋ በሀዘኔታ ከንፈሯን መጠጠች፡፡ «ግን..» ... ብላ ንግግርዋን ስትጀምር፣ «ስምንት መቶ ብር እከፍላለሁ።» አለ፡፡ የብሩ መጠን አጓጉቷትም ይሁን በሌላ ምክንያት አይኖችዋ ፈጠጡ፡፡ ሰለሞን አሻንጉሊቱን ለመስጠት እያወላወለች መሆኑን ተረዳ፡፡ እግረ መንገዱን አልማዙ ያለበትን አሻንጉሊት የያዘችውን ህፃን አሻግሮ ተመለከተ፡፡ ከእናቷ ጋር ተሰልፋለች። እናቷ የጉዞ ሰነዶቿን ለማሳየት ተራዋ እንደደረሰ አስተዋለ፡፡ «እሺ ምን አሰብሽ?» አላት ሴትየዋን፡፡
«ግን ችግሩ ምን መሰለህ...» ... ብላ ሳትጨርስ «ይገርምሻል ልጄን የማሳድገው ያለ እናት ነው። እናቱ የዛሬ ዓመት በመኪና አደጋ ህይወትዋ አልፏል» አለና ፊቱን በሀዘን አኮማተረ፡፡
አሁን ሴትየዋ አልቻለችም፡፡ ተሸነፈች፡፡ በሀዘን ከንፈርዋን መጠጠችና አሻንጉሊቱን ሰጠችው። እያመሰገነ ስምንት መቶ ብር አውጥቶ ሲሰጣት፣ ሁለት መቶ ብር ብቻ ይበቃኛል ብላ ቀሪውን መለሰችለት፡፡ ወደ መንገደኞች ፊቱን ሲያዞር፣ እናትና ልጅ ተያይዘው የጉምሩክ ሠራተኞችን አልፈው በበሩ ሲወጡ ተመለከተ፡፡ ሴትየዋን ተሰናብቶ ተነሳና ቀስ ብሎ ተከተላቸው፡፡ እናትየዋ ሻንጣዋን እየጐተተች፣ ባንድ እጇ ልጇን ይዛለች፡፡ ልጅቷ ደግሞ አሻንጉሊቷን አቅፋ አብራት ትራመዳለች፡፡ ከእናትየዋ አጠገብ ደርሶ እየተራመደ «ላግዝሽ?» አላት፡፡
በለስ ቀናው፡፡ ልጅቷ ሰለሞን የያዘውን ትልቅ የሚያምር የድብ አሻንጉሊት ስታይ በጉጉት እየተናጠች፣ የእናቷን እጅ እየነቀነቀች «ካልገዛሽልኝ..» ብላ መወትወት ጀመረች፡፡ ሰለሞን እናቷን ለማገዝ ሻንጣዋን ይጐትታል፡፡ ሴትየዋ ልጇን ከተቆጣች በኋላ ሰለሞንን በእፍረት እያየች.» .ልጆች ሁሉም ነገር የሚሸጥ ይመስላቸዋል..» አለች፡፡ ልጅቷ ግን ማልቀስ ጀመረች፡፡
«ግድ የለም፡፡ በጣም ስለወደደችው ልሰጣት እችላለሁ። ለልጄ የልደት በዓል የገዛሁት ስጦታ ነበር።  አሁን ግን እሷ የያዘችውን አሻንጉሊት ልሰጠው እችላለሁ.. .  ከቀየረችልኝ..   «አለ  ለልጅቷ ያዘነ መስሎ፡፡
«.እውነት?» አለች ሴትየዋ፤ «በእውነት በጣም ጥሩ ሰው ነህ..» «በይ አንቺ አምጪ . . . እሱን አመሰግናለሁ በይ..» አለች እናትየዋ፤ ከሰለሞን የተቀበለችውን የድብ አሻንጉሊት ለልጅቷ እየሰጠችና ትንሹን አሻንጉሊት ከልጅዋ እየተቀበለች፡፡ ሰለሞን የሚሆነውን ማመን አልቻለም፡፡ የሚፈልገውን አሻንጉሊት እጁ አስገባ። «..መልካም ጊዜ.» አለችውና ተለየችው፡፡ መታገስ አልቻለም፡፡ በፍጥነት ወደ መጸዳጃ ቤት አመራና ገብቶ በሩን ቆለፈው፡፡ አሁን ሥራው አክትሟል፡፡ እሱም በፍጥነት ተሰውሯል፡፡ አዲስ አበባ እንደሆነ ሰፊ ከተማ ነው፡፡ ማን ማንን ፈልጐ ያገኛል!
መጸዳጃ ቤት ውስጥ ሆኖ ያቺን ከፕላስቲክ የተሠራች ምስኪን አሻንጉሊት፣ እንደ ዶሮ ለመገነጣጠል ደቂቃ አልፈጀበትም፡፡ ያገኘው ግን ሃምሳ ግራም የሚመዝን የከበረ ድንጋይ ሳይሆን ኤቨርሬዲ የሚል ጽሑፍ ያለበት ባትሪ ድንጋይ ነው፡፡ ቀዝቃዛ ላብ በጀርባው እየፈሰሰ፣ እንደገና ያንን አሻንጉሊት ብትንትኑ እስኪወጣ ድረስ ፈተሸው፡፡ ምንም ነገር የለም፡፡ ከሽንት ቤቱ እየሮጠ ወጣና መጀመሪያ እነሱን ወዳገኘበት ቦታ ሮጠ፡፡ ዱብዬዋ ሴትዮ ቆማ ወደ መንገደኞች መግቢያ ስትመለከት አገኛት። ቁና ቁና ይተነፍሳል፡፡ በዓይኖቹ እናትና ልጅን እየፈለገ እንደሆነ፣ ወፍራምዋ ሴትዮ እንዳታውቅበት ፈገግ አለ፡፡ «አሁንም እዚህ ነሽ?..» አለ መሮጡን እንዳታውቅበት ለመረጋጋት እየሞከረ፡፡ «..ምን ላድርግ ልጄን  እየጠበቅኩኝ  ነዋ፡፡  ፓስፖርትም  ላይ  ስህተት አለ ብለው እኔን አሰልፈው እሷን አቆይተዋት ነበር፡፡ አሁን መጣች--» አለች ሴትየዋ፤ ፈገግ ብላ ወደ መንገደኞች መግቢያ በር እያየች። ሰለሞን ዞር ብሎ ሲያይ ስምንት ዓመት ገደማ የሚሆናት ልጅ ወደ ሴትየዋ ስትመጣ ተመለከተ፡፡
«አንቺም ከዚያው ነው የመ-ጣ-ሽ-ው?» ድምጹ ተደናቀፈ፡፡ «ሁላችንም ከደቡብ አፍሪካ ነው የመጣነው ... ከጆሃንስበርግ..»
«..ታዲያ የሸጥሽልኝ አሻንጉሊት..» ብሎ ሳይጨርስ፤ «ሽሽ. . . እንዳትሰማ፡፡ አንድ ደቡብ አፍሪካዊ ነው ዛሬ ጠዋት ከዚያ ስንነሳ በስጦታ የሰጣት። ሐበሻ ሚስት አለችው፡፡ በጣም ነው ሀበሻ የሚወደው...» አለችና ወደሷ ሮጣ የመጣችውን ልጇን አቀፈቻት። ሰለሞን ዛሬ ጠዋት ሚስተር ኮፊ በስልክ ያለውን አስታወሰ፡፡ «አልማዙን ከእናትዋ ጋር የምትመጣ፣ በግምት የስምንት ዓመት ህፃን የምትሆን  የያዘችው አሻንጉሊት ውስጥ ልኬዋለሁ፡፡»
አልማዙ የነበረበትን ትልቁንና ውዱን አሻንጉሊት፣ በማይረባውና ባዶ በነበረው አሻንጉሊት ቀይሮታል፡፡ እንደ ዕብድ እየሮጠ አሻንጉሊቱን የቀየራቸውን እናትና ልጅ ለማግኘት ተቅበዘበዘ። በየጥጋጥጉ፣ በመውጫ መግቢያው፤ ውስጥም፤ ውጭም--- የትም አልቀረውም፡፡
ምን ዋጋ አለው፡፡ አዲስ አበባ ሰፊ ከተማ ነው፡፡ ማን ማንን ያገኛል!
 (ከጁላይ 31, 2011 አዲስ አድማስ ዕትም፣ በድጋሚ የወጣ)

Read 2912 times