Monday, 10 April 2017 11:00

የኢትዮጵያ ቴአትርና ተስፋዎቹ!?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  አርቲስት ደበበ እሸቱ ምን ይላል?

         አርቲስት ደበበ እሸቱ ባለፈው ሳምንት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተከበረው 55ኛው የዓለም የቴአትር ቀን ላይ ከተሳተፉትና በበዓሉ ላይ በተለያየ መልኩ ጉልህ ሚና ከነበራቸው አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች አንዱና ግንባር ቀደሙ ነበር፡፡ ከሚናዎቹ መካከል ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያን ወክሎ የአለም የቴአትር ተቋም አባል እንዲሆን የድርድሩንና መሰል ሂደቶች በማካሄድ ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ አርቲስቱ በተጨማሪም ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ
ባዘጋጀውና በ1905 ዓ.ም በጅሮንድ ተክለሀዋሪያት ተ/ማሪያም በፃፉት ‹‹የአውሬዎች መሳለቂያ ኮሜዲ›› (ፋቡላ) ቴአትር ላይ በመሪ ተዋናይነት ተጫውቷል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ አርቲስት ደበበ እሸቱን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አግኝታው በቅርቡ በቤተ እስራኤላዊያን ላይ በሚያጠነጥነው ‹‹ቀያይ ቀንበጦች” (Red Leaves) በተሰኘውና በመሪ ተዋናይነት ስለተወነበት ፊልም፣ ኢትዮጵያ የአለም የቴአትር ተቋም አባል እንድትሆን ስላደረገው ጥረት፣በወቅቱ የአገራችን የቴአትር ሁኔታና ስለ ወደፊት ሀሳቡ እንደሚከተለው አነጋግራዋለች፡፡

     ከሁለተኛው የ”ጉማ ሽልማት” የህይወት ዘመን ሽልማትህ በኋላ ትንሽ ጠፍተሀል፡፡ የጠፋኸው ደግሞ እስራኤል ውስጥ እየሰራህ በነበረው ፊልም ምክንያት ነው ይባላል፡፡ እውነት ነው?
እውነት ነው፡፡ አሜሪካዊያንና እስራኤሎች የሚሰሩት በቤተ እስራኤላዊያን ላይ የሚያጠነጥን ፊልም ነበር፡፡ እሱን በዋና ገፀባህሪነት ለመስራት ተመርጬ፣ ወደ እስራኤል አቅንቼ ለስድስት ወራት ቆይቼ፣ ፊልሙ ተሰርቶ ካለቀ በኋላ ወደ አገሬ ተመልሼ ነበር፡፡ ፊልሙ ለእይታ ሲከፈት እንደገና ተመልሼ ሄድኩኝ፡፡ እዛም ፊልሙ ተሸለመ፡፡
ምን አይነት ሽልማት አገኘ? የፊልሙስ ጭብጥ ምንድን ነው?
በታጨበት ዘርፍ ብልጫ ያለውና አዲስ አቀራረብ የታየበት በሚል ተሸለመ፤ ለእኔም እውቅና ሰጥተው አመስግነውኛል፤ ይበቃኛል፡፡ የፊልሙ ጭብጥ በዓለም ዙሪያ የተበታተኑ ቤተ እስራኤላዊያን ተመልሰው ወደ እስራኤል ይካተታሉ የሚልና ኢትዮጵያን እንደ ምሳሌ የወሰዱበት ነው፡፡ ፊልሙ ሁሉንም ዓለም የሚመለከትና በፍልሰት ምክንያት የሚያጋጥምን ፈተና በተለይ ቤቴ እስራኤላዊያን ላይ የደረሰን ችግር በጉልህ የሚያሳይ ነው፡፡ እውነት ለመናገር በፊልሙ ላይ እኔ ስለተወንኩ አይደለም፤ ግን በጣም በጥሩ ሁኔታ የተሰራ በመሆኑ ቫንኮቨር ላይም ለፌስቲቫል ቀርቦ ከታየ በኋላ ከቀረቡት 36 ፊልሞች ጥቂት ተመርጠው ሲያልፉ 10ኛ ሆኖ አልፎ ነበር፡፡ ከዚያ የመጨረሻው ሶስት ፊልሞች ውስጥ ገብቶ፣ ‹‹The Best leading Actor Golden Leopold Award›› የሚል ሽልማት ተሸልሜበታለሁ፡፡ የተሰራበት ቋንቋ አማርኛና ሂብሩ ሲሆን እንግሊዝኛ ሰብታይትል ተሰርቶለታል፡፡
ጋሽ ደበበ --- በአሁኑ ወቅት ቴአትሩ አካባቢ ምን እየሰራህ ነው ?
እኔ እንግዲህ መፅሐፎች እተረጉማለሁ፤ በቅርቡ የተረጎምኩት ‹‹ኢትዮጵያ የባሩድ በርሜል›› የተሰኘ መፅሐፌ፣አሜሪካ በፀሐይ አሳታሚ ታትሞ ለገበያ ቀርቦ ነበር፡፡ በድጋሚ ኢትዮጵያ ታትሞ ለገበያ ውሏል፡፡
መፅሐፉ በጣም የቆየና ስለ አንድ ኦስትሪያዊ የኢትዮጵያ ጥላቻ የሚያወሳ ነው፡፡ ይህን የቆየ መፅሐፍ የተረጎምክበት ዓላማ ምንድን ነው?
እንዳልሽው መፅሐፉ አንድ ኦስትሪያዊ ፋሽስት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥላቻ ስለነበረው ኢትዮጵያ የአለም መንግስታት ማህበር (league of Nations) አባል እንዳትሆን ሽንጡን ገትሮ ሲሟገት የነበረ ነው። ይህንን መፅሀፍ አግኝቼ ሳነበው፣ በሰውየው ስራ በጣም ስለተናደደኩ፣ ተርጉሜው ለኢትዮጵያ ህዝብ ይቅረብና ህዝቡም እንደኔው ይናደድ ብዬ ነው፡፡ መፅሐፉ ለንባብ ከበቃ በኋላ ያንን ውጤት እያየሁ ነው፡፡ አሁንም እየተረጎምኳቸው ያሉ መፅሐፍት አሉ፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም የቴአትር ተቋም አባል እንድትሆን ያንተ ከፍተኛ ጥረት እንደነበረበት ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ስለዚህ ሂደትና በተቋሙ የአፍሪካ ተወካይ ሆነህ ስለሰራህበት ዘመን ንገረኝ?
እ.ኤ.አ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ባህል ሚኒስቴር በአንድ አጋጣሚ በኢንተርናሽናል ቴአትር ኢንስቲትዩት ስብሰባ ላይ እንድካፈል ልኮኝ፣ ምስራቅ ጀርመን ውስጥ በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ ተካፍዬ ነበር፡፡ በዛን ጊዜ ስለ ተቋሙ ብዙ እውቀት አልነበረኝም፡፡ እዚያ ከደረስኩ በኋላ መፅሐፍት ፈልጌ አንብቤ ነው የዩኔስኮ የባህል ምዕራፍ እንደሆነ የገባኝ፡፡ በወቅቱ በዚህ ስብሰባ ላይ የተሳተፉት በጣም ጥቂት የአፍሪካ ተወካዮች ነበሩ፤ ነገር ግን ብዙ አይናገሩም ነበር፡፡
እኔ አንድም ብዙ ካለማወቅ የተነሳ፣ሁለተኛ እንደ አፍሪካዊነቴ አፍሪካ ልትወከል ይገባታል በሚል ደጋግሜ ብዙ ጥያቄዎችን አንስቼ ነበር፡፡ በጊዜው የነበረው የITI ዋና ፀሀፊ የአፍሪካ የITI ተወካይ ሆነህ እንድትሰራ መርጠንሀል አለኝ፡፡ እግዜር ይስጥልኝ ብዬ ተቀበልኩት፡፡ ከዚያ እንደተመለስኩኝ ዚምባብዌ ውስጥ ‹‹Theatre for Development and Non Formal Education›› የሚል ወርክሾፕ ይካሄድ ነበር:: እዚያ ላይ እንደ ባለሙያ ሄጄ እንድሳተፍ ሆነ፡፡ እዚያ እያለን ስመለከት ከሌላው አገር ሀላፊነት ወስደው የመጡትና ስለ ቴአትር የሚናገሩት (የአፍሪካን ጭምር የወከሉት)፣ ስለ አፍሪካ ባህል አስተያየት የሚሰጡት ጀርመኖች፣ እንግሊዞች፣ ከፈረንሳይ የመጡት ናቸው፡፡ እኛን ባለቤቶቹን አንዳንዴ እስኪ ተናገሩ እያሉ እያናገሩን ለካ እነሱ ዶክትሬታቸውን ነው የሚሰሩት፡፡
ይሄ ጉዳይ በምን ታወቀ?
በቃ ታወቀ፤ መቼስ ፍንጭ አይጠፋም፡፡ እኔ ይሄን ነገር በግልፅ ተቃወምኩ፡፡ ከታዛኒያ የመጣች ዶ/ር ፔኒና ምላማ፣ አሁን የዳሬሰላም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆናለች፤ እሷና እኔ ሌሎችንም አስተባብረን፣ እኛ የተጎዳነው አንድ አፍሪካን የሚወክል ማህበር ስለሌለን ነው፤ ለምን ማህበር አናቋቁምም በሚል የውስጥ ለውስጥ እንቅስቃሴ ጀመርን፡፡ ከዚያ እንግሊዞቹ፣ ጀርመኖቹና ፈረንሳዮቹ ኑና አስረዱ ሲሉን፣ አይ እናንተው አስረዱ እኛ ልንረዳ ነው የመጣነው፤ እናንተ ራሳችሁን ቻሉ በሚል አለመግባባት ተፈጠረና ማህበሩን እንድንፈጥር አንድ ምክንያት ሆነን፡፡ በሌሎች አገሮች ሞክረን አልተሳካልንም ነበር፤እዚያ ተሳካልን፡፡
ማህበሩ ሲመሰረት የትኞቹ የአፍሪካ አገራት መስራችና አባል ሆኑ?
19 የአፍሪካ አገሮች መስራች ሆነው ነበር፡፡ ከፈረንሳይ ተናጋሪዎቹና እንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹ፣ ወደ ደቡብ ያሉት አንድ ላይ ሆነው ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ጋምቢያ፣ ዚምባብዌ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ኢትዮጵያና ሌሎችም በግለሰብ ደረጃ ተሰባስበን ያቋቋምነው ማህበር ነው፡፡ “The African Union of African Performing Artists” ይባላል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1985 ዓ.ም ነው የተቋቋመው፡፡ ይህ ማህበር ሲቋቋም እኔ አንዱ የአስመራጭ ኮሚቴ አባል አድርገውኝ ገባሁ፡፡ በነጋታው ሊመረጡ የተጠቆሙት ሰዎች ሲመጡ፣ ከዚምባብዌ የመጡት ተጠቋሚዎች ነጮች ናቸው፤ እኔ እንደ አስመራጭ ኮሚቴ አባልነቴ ነጮቹን አልቀበልም አልኩኝ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ቅኝ ገዢዎች ናቸው፤ ዚምባብዌ ውስጥ ገንዘቡ የነሱ ነው፤ ከ7 በላይ ቴአትር ቤት አላቸው፡፡ የዚምባብዌ የቴአትር ባለሙያዎች ግን ከነዚህ ነጮች ቴአትር ቤት የመከራየት መብት ተነፍጓቸው ዛፍ ስር ነው የሚሰሩት፤ ስለዚህ ከተጠቋሚዎቹ ውስጥ ትክክለኛ ዚምባብዌያውያን መሆን አለባቸው አልኩኝ። ከዚምባብዌ የተወከለው ሰው ግን የኔን ውሳኔ ባለመቀበል ከነጮቹ ጋር ወግኖ ወጣ፡፡ በኋላ ይሄ ጥቁር የዚምባብዌ ዜጋ ለምን እንዲህ እንዳደረገ ሳጣራ፣ መንግስት የተቀበለውን እኛ እምቢ ለማለት ምን መብት አለን ብሎ በፍርሃት እነሱን መደገፉን ሰማሁ፡፡ በወቅቱ የተሰበሰብንበት አዳራሽ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመጡ ሰዎች እንጂ የዚምባብዌ አይደለም፤ ስለዚህ አንተን መምረጥ ነበር የፈለግነው አልነው፤ እሱ እሺ ለማለት ትንሽ ዘመም ቢልም ሌሎች ሰዎች ግን እሱን አንፈልግም አሉ፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ ሌላ አስመራጭ ኮሚቴ ምረጡ ብለን ከመድረክ ልንወርድ ስንል፤ ‹‹በቃ ደበበን ፕሬዚዳንት አድርገን መርጠናል፤ ሌላ ምንም ስብሰባና ቀጠሮ አንፈልግም›› አሉና የመግቢያ ሰነድ ተፈራርመው ለዩኔስኮ ላኩ፡፡ የዛን ጊዜ መጀመሪያ የ ITI የአፍሪካ አስተባባሪ ነበርኩኝ፤ በኋላም በአፍሪካ የተቋቋመው ማህበር ፕሬዚዳንት ሆኜ በመመረጤ ከኢንተርናሽናል ቴአትር ኢንስቲትዩት ጋር ለብዙ አመት አብረን ሰርተናል፡፡ ዩኔስኮ ‹‹ኢንሳይክሎፒዲያ ኮንቴምፖራሪ ቴአትር››ን ሲያሳትም፣ የአፍሪካው ክፍል ላይ የኤዲቶሪያል ቦርድ አባልም ነበርኩኝ፡፡
እስቲ ኢትዮጵያ የITI አባል እንድትሆን ስላደረግኸው ጥረት አውጋኝ?
እንግዲህ የዛሬ ሁለት ዓመት 53ኛውን የአለም የቴአትር ቀን ይህ አዲስ የተቋቋመ ዩኒቨርሲቲ፣ ያውም የተቋሙ አባል ሳይሆን ለማክበር ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩት የዩኒቨርሲቲው የቴአትር መምህራንና ተማሪዎች ጋበዙኝ፡፡ በእውነት ያንን የወጣቶቹን ጥረትና ጥሩና ያማረ ዝግጅት ስመለከት እንባ ተናነቀኝ፤ እናም ያን ቀን አንድ ነገር ወሰንኩ፡፡
በቃ ከITI ጋር ሰፊ ቆይታ ስለነበረኝ የማውቃቸውን ሰዎች ለምኜም ቢሆን፣ የኢትዮጵያ የቴአትር ኢንስቲትዩት ማህፀን፣ ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ መሆን አለበት የሚል ውሳኔ ላይ ደረስኩ፡፡ ማንም ለምን አደረግህ ሊለኝ አይችልም፤ መብቴ ነው። ከዚያ በኋላ ዘንድሮ እነዚህ ልጆች በበዓሉ ላይ ሊጋብዙኝ እንደሚችሉ ገምቻለሁ፤ እርግጠኛ ግን አይደለሁም፤ከጋበዙኝና ከጠሩኝ ግን አንድ ነገር ይዤ መሄድ አለብኝ ብዬ፣ ከITI ሰዎች ጋር ስፃፃፍ ነበር። በመጨረሻም እሺታቸውን ገለፁልኝ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ አሜሪካ ሎስ አንጀለስ የሚኖር አንድ መልካም ኢትዮጵያዊ ነበር የእኔን መፅሐፍ ያሳተመው፣ በአስቸኳይ መልዕክት አንድ መቶ ኮፒ ለወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ልኮ አስረክቤያቸዋለሁ። ሁለተኛ ደግሞ ለሁለት ዓመት የአባልነት ክፍያ የሚከፍልላቸውም አግኝቻለሁ፡፡ ፀሀይ አሳታሚ ነው መፅሐፌን ያሳተመው፡፡ አሳታሚው ሎያላ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚገኝ ነው፤ ስለዚህ ሎያላ ዩኒቨርሲቲና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የእህትማማችነት ግንኙነት እንዲኖራቸው እየሰራ ይገኛል፡፡
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር መምህራንና ተማሪዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ቴአትርን በተመለከተ ምን ተስፋ ፈጠረብህ?
በጣም የሚገርምሽ በዚህ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ያሉ መምህራን በሌሎቹ ቦታዎችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚታየውን የተማሪና አስተማሪ እንደ ጌታና ሎሌ መተያየትን አላስፈላጊ ግንኙነት የሰበሩ ናቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲው ትልልቅ ስልጣን ላይ ተቀምጠው ሙያውን አልተውትም። ሙያው ውስጥ ሲገቡ ከተማሪዎቻቸው እኩል መድረክ ላይ ለመሰለፍ፣ እኩል የሙያ አስተዋፅኦ ለማድረግ በጣም ፈቃደኛ ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ ይሄ በሙያው ላይ የሚታየኝ ትልቁ ተስፋና ለውጥ ነው፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ለወደፊት ተማሪና አስተማሪ በመምህርና በደቀ መዝሙር ደረጃ እየተወያዩና ስህተታቸውን እየተራረሙ አብረው እያደጉ፣ ሙያውንም የሚያሳድጉት ይመስለኛል፤ ይሄ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡
በመምህራንና ተማሪዎች መካከል ለምንድን ነው የጌታና ሎሌ ዓይነት ግንኙነት የሚኖረው?
ቀደም ሲል መምህሩ የተናገረውን ያለ ጥያቄ መቀበል ግድ ነበር፡፡ መምህሩ ይፈራል። አሁንም በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ይሄ ሁኔታ የሚታይበትና የቀጠለበት አሰራር አለ፡፡ ተማሪዎቹ አስተማሪን ጥያቄ መጠየቅ የሚፈሩበት ሁኔታ ሁሉ አለ። አንዳንዱ መምህር ልከበር ከሚል አኳያ ነው፡፡ አንዳንድ መምህራን ደግሞ ከተማሪው የሚሰነዘረው ጥያቄ ስለሚከብዳቸው ተማሪዎቹን ማግለል ነው የሚፈልጉት፡፡ የወልቂጤዎቹ በእውነቱ እንደዚህ አይደሉም፤ ከተማሪው ጋር አብረው ይውላሉ፤ ከክፍል ውጭ ይወያያሉ፡፡ ከተማሪው ጋር መድረክ ላይ በሙያ ደረጃ አብረው ይሰለፋሉ። የሚታሙበት እንከን የሚገኝባቸው አይደሉም፤ ስለዚህ እነዚህ የመጪው ዘመን የቴአትር ተስፋዎች ናቸው፡፡
ጋሽ ደበበ አንተ በመሪ ተዋናይነት ስለተወንክበት በ1905 ስለተፃፈው የበጅሮንድ ተክለሀዋሪያት ተ/ማሪያም “አውሬዎቹ ኮሜዲ መሳለቂያ (ፋቡላ)” ቴአትር አጫውተኝ፡፡ በመተወንህ ምን ተሰማህ? አዲስ ስለመጣው “መልቲ ሚዲያ ቴአትር” ጥበብስ ምን ትላለህ?
በመጀመሪያ የዚህ ፕሮዳክሽን አካል ያደረጉኝን የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል መምህራንን በጣም አመሰግናቸዋለሁ፡፡ በጣም ነው የተደሰትኩት፣ በጣም ነው የኮራሁትና የረካሁት በነዚህ ወጣቶች፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮዳክሽኑ ሲሰራ ነበር ያየሁት፤ ከዚያ በኋላ ከተመልካቹ እኩል ነው ያየሁት። እነሱ ያቀረቡት በጅሮንድ ተክለሀዋሪያት እንዴት አድርገው ይሄን ቴአትር ፃፉት የሚለውን ነው፤ በጣም ምሉዕ ነው፡፡
እነዚህ ወጣቶች ፊልምንና እውን የሆነውን ቴአትር- ትወና አስተሳስረው ነው ያመጡት። “መልቲ ሚዲያ ቴአትር” በሚል ደራሲው እንዴት ፃፉት የሚለውን ወደፊት ለተማሪዎችም በሚያገለግል መልኩ ነው የሰሩት፡፡ አየሽ በፊልም በመድረክ በፅሁፍ መልክ ታግዞ የቀረበ ነው፡፡ ይህ አዲስ አሰራርና አስተሳሰብ በጣም የሚያስደስት ነው፡፡ በዚህ ቴአትር ላይ ከነዚህ ወጣቶች ጋር በመተወኔ በጣም ተደስቻለሁ፤ ወጣቶቹን አመሰግናለሁ፡፡
በዩኒቨርስቲው 55ኛው የአለም የቴአትር ቀን ላይ ከቀረቡ 8 ጥናታዊ ፅሁፎች መካከል በመቀሌ ዩኒቨርሲቲው ተካልኝ ገ/ሚካኤል የቀረበው ‹‹የቴአትር ትምህርት በኢትዮጵያ›› የተሰኘው ጥናታዊ ፅሁፍ፤ቴአትሩ ላይ የተጋረጡትን ዘርፈ ብዙ ችግሮችና  ፈተናዎች  ያመላከተ ነው፡፡ ብዙ መሠረት ልማት ባልተሟላበት፣ ባልፀደቀ ሥርዓት ትምህርት እያስተማሩ እንደሚገኙ ተጠቅሷል። ተባባሪ ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬም የውጭው አገር ተሞክሮ በአገራችን እንዲተገበር በጥናታቸው ጠቁመዋል። ከሁለቱ የትኛው መቅደምና መከተል አለበት ትላለህ?
የአቦነህ ጥናት ምክር አዘል አስተዋፅኦ ያለው ነው ለምን? መንግስት ለስነ ትበቡ ለኪነ ትበቡ ለቴአትር ትምህርት ሊያደርግ የሚገባውን ነገር ነው ያስቀመጠው በሌላው አለም እየተደረገ ስለሆነ እዚህም ዘርፍ መደገፍ አለበት መንግስት ዘርፉን ቢደግፍ ይጠቀማል እንጂ ምን የሚጎዳው ነገር አለ ነው፡፡
ለምሳሌ ቀረጥን በተመለከተ ከቴአትር የሚወስደው ቀረጥ የመንግስትን የትኛውንም ቀዳዳ አይሞላም አንድን የመንግስት ሰራተኛ የአመት ደሞዝ እንኳን አይሸፍንም። ሰዎች ተነቃቅተው ለጥበቡ ልግስና በሚያደርጉበት ጊዜ ያ ገንዘብ ከቀረጡ ላየ የሚቀነስላቸው መሆኑን ቢያውቁ ማንንም ሳያስቸግሩ እነዚህ ሰዎች በሚሰጡት ድጋፍ ብቻ ትልቅ ደረጃ መድረስ ይቻል ነበር፡፡ ይሄንን ነው አቦነህ ያስቀመጠው የተካልኝ ጥናት በበኩሌ በጣም ያስደነገጠኝና ያሸማቀቀኝ ጥናት ነው፡፡ አንድ ቡና ቤት እኮ መፀዳጃ ክፍልህ ንፁህ አይደለም ተብሎ ይዘጋል፤ አንድ ሆስፒታል የሚያቀርበው የህክምና እርዳታ በህብረተሰቡ ላይ ትንሽ ህፀፅ ሲገኝበት ያንን አላሟላህም ተብሎ ይዘጋል፡፡ እነዚህ የተቋቋሙ ስምንት የቴአትር ጥበብ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪችን የሚያስተምሩበት እውቅና ባላገኘ ስርዓተ ትምህርት ነው፡፡ ነገ ይህንን ፈቃድ የሚሰጠው ተቋም ያገኛችሁት ዲግሪ ባልፀደቀ ካሪኩለም ነውና አላውቃችሁም ቢል እነዚህ ልጆች የት ነው የሚወድቁት ትምህርት ሚኒስቴር አይመለከተኝም ካለ ለሌላ ለሚመለከተው አካል አሳፎ ይሰጥ። እንዴትስ ነው ለሳምንት ዩኒቨርሲቲ ሶስት አራት አይነት ካሪኩለም የሚወጣው፡፡ ዩኒቨርስቲዎቹ በአንድ ኤኔት ሰርዓት ትምህርት በአንድ አይነት መንገድ ተማሪዎቹን ማሰልጠንና ማስመረቅ ይገባቸዋል፡፡ ያለበለዚያ ምስቅልቅሉ የወጣ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ ይሄ እንግዲህ ተመልካች የማጣት ጉዳይ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለጥበቡ ምን አገባኝ የማለት ነገር ይመስለኛል፡፡
ግን እኮ እንደ ቴአትር ያሉ ጥበባትን መንግስት ለተለያዩ ጉዳዩች ይጠቀማል አይደለም እንዴ?
ለመጠቀሙማ በደንብ ይጠቀምባቸዋል ጥበቡን መጥቀም ነው እንጂ የተሳነው፡፡ እንደሚጠቀምበት ሁሉ ጥበቡ እንዲያድግና ጥበበኛው እንዲጠቀም ቢያደርግ ኖሮ መልካም ነበር፡፡ የተካልኝም ጥናት የሚያመላክተው ይሄንኑ ነው ባልተሟላ የሰው ሀይል ባልተሟላ መሰረት ልማትና ባለፀደቀ ካሪኩለም ተማሪዎችን እስተማርን ነው ያለው ይሄ ትክክል አይመስለኝም፡፡
በሌላው አለም የኪነ-ጥበብ መማክርት አለ ሙያውን ለማስከበር አርቲስቱን ይተባበራል መብቱን ያስከብራል እየተባለ ነው ለመሆኑ በአገራችን አርቲስቱ እርስ በእርስ የመተባበርና የመከባበር ባህል አለው ወይ ይህ ባልኖረበት ሁኔታ መብታችንን ይከበር ማለት ያስኬዳል ወይ? ሌላው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ አርቲስቱን በሰበሰቡበት ወቅት ቤተ መንግስትና ኤርፖርት ገብተን እንድንቀርፅ ይፈቀድልን የሚልና ከጥበቡ ጋር ግንኙነት የሌለው ጥያቄ ከማንሰትና ትዝብት ውስጥ ከመግባት ባለፈ ለኪነ-ጥበቡ የሚበጅ ጥያቄ ሳያነሳ መበተኑ አሁን አልተከበርንም ለማለት ሙያው አልተከበረም ማለት አግባብ ነው ትላለህ?
በነገራችን ላይ ስለዚህ ስብሰባ ካነሳሽ አይቀር ስሜቴን ልናገር፡፡ እኔ ስብሰባውን እቤቴ ቁጭ ብ እንደ ማንኛውም ተመልካች ነበር በቴሌቪዥን ያየሁት፡፡
እንዴት? አልተጋበዝክም ነበር?
አልተጋበዝኩም፡፡ በዕለቱ በውስጤ የመጣው የመጀመሪያው ጥያቄ ማን ነው ይህን ስብሰባ ያዘጋጀው? እነማን ናቸው አርቲስቱን ወክለው የተገኙትና ጥሪ የተደረጉት? እማንስ ናቸው እየመሩት ያሉት የሚለው ነበር፡፡ በኋላ ሳየው በሙያው ምንም ብቃት የሌላቸው ሰዎች ነበሩ እንደ ቁንጮ ባለሙያ ሆነው ሲያጋፍሩት የነበሩት ስለ ሙያው ስለኪነ ጥበቡ ሊጠየቅ የሚገባው በርካታ ጥያቄ ምልቶ ነበርኮ አንድ የቴአትር ባለሙያ ካሜራ በነፃ ይግባልን ብሎ አይጠይቅም ይህን መጠየቅ ያለበት ነጋዴው ነው ምክንቱም ቴአትሩን እሰራው ያለው ነጋዴው አይደለም እንዴ ነጋዴ ስል በጅምላ መናገሬ አይደለም፡፡ አሁን ቴአትር እየሰራ ያለው ባለሃብቱ ነው ለማለት ነው። በጥበቡ ላይ የሚነግዱ ሰዎች ስላሉ ነው ነጋዴ እያልኩ ያለሁት፡፡ ቴአትረኛው ምን ሊደርግበት ነው ካሜራ በነፃ ይግባልኝ የሚለው? የጥበቡ ባለሙያ ካሜራ ከቀረፅ ነፃ ቢገባ የሚጠቀመው ምንድ ነው? ይልቅ የሚጠቅመው መብት ቢከበርለት ነበር፡፡ ለእሱ የሚጠቅመው የስራው ስራ እውቅና ቢያገኝለት ከብዙ ፈተናዎች ነፃ ቢሆንለት ነው። ስለዚህ ስብሰባውም በስብሰባውም ላይ የተነሳው ጥያቄ ትክክል አይደለም። በስብሰባውም አፍሬያለሁ በስብሰባው ባለመካፈሌም እግዛብሄርን አመስግኘዋለሁ። መጠየቅ አለበት ብሎ የጠበቀው ጥያቄ ባለመጠየቁ ጠቅላ ሚኒስትሩም ጥሏቸው ወጣ እኮ! ሙያተኛው ራሱ አልተሰባሰበም በተለያየ ምዕራፍ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሙያተኛውን ተከፋፍለውታል፡፡
ኪነ ጥበቡና ጥበበኛው እንዲከበር ምን መደረግ አለበት ትላለህ?
አሁን ባነሳሺው ጥያቄ ላይ በምሰጠው ምላሽ ብዙዎች ሊጠሉኝ ይችላሉ፡፡ ባለቤቴና ሙያዬ እስካልጠሉኝ ድረስ ሌላው ቢጠላኝ ጉዳዬ አይደለም። የሆነ ሆኖ ሙያውን ከሸቀጥነት ወደ ጥበብነት ለመለወጥ ባለሙያው ፈቃደኛ መሆን አለበት፡፡ ምንም የሞያ ክህሎት የሌለው በሞያው ስልጠና የሌሎው ገንዘብ ስላለው ብቻ ፊልም ዳይሬክት ላደረግ ነው ብሎ ቢጠራን አልሄድም በበኩሌ፡፡ የፈለገው ገንዘብ ሊቀር ይችላል። በሙያው ሰልጥኖ ብቃት አግኝቶ የወጣ ከኔ በጣም በዕድሜ የሚያንስና ልጄ ሊሆን የሚችል ባለሙያ ግን ቢጠራኝ በነፃም ቢሆን እሰራለሁ ምክንቱመ እሱ አድጎ እንዲተካኝ ስምፈልግ፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ገንዘብ ስላለው ናና ስራ ቢለኝ ያኔ አልቃስ አይደለሁም፡፡ አላደረግውም ስለዚህ ችግሩን የፈጠረው ሁሉ ባለሙያው ስለሆነ ከዚያ ችግር ውስጥ ራሱን ማውጣት አለበት እንጂ ጣቱን ወደሌላው እየቀሰረ እንዲህ አደረገኝ እከሌ ይህን አላደረገልኝም የሚባል ነገር አይሰራም፡፡ ባለሙያው ችግሩን ያውቀዋል መፍትሄው ራሱ እንደሆነ ያውቀዋል ባለሙያው መብቱን ማስከበርና በመብቱ መጠቀም አለበት ስለዚህ ባለሙያው ከዚያ ችግር ራሱን ካላወጣ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ቁጭ ብሎ ሲያማርርና እዬዬ ሲል ከመኖር በስተቀር ቆይ እኔ እምለው ጦርነቱን ማን እንደዋጋለት ነው ባለሙያው የሚጠብቀው፡፡ በሙያው ላይ የተቃጣውን ጦርነት ሁሉ ባለሙያው በሰላማዊ መንገድ ታግሎ ማሸነፍ አለበት፡፡ እንደገናም በችግራቸው ላይ ተሰብስበው ተነጋግረው አንድ ሆነው መቅረብ ነው ያለባቸው፡፡ ተበታትነው ተለያይተው በየአቅጣጫው ሲሯሯጡ መንግስትም እኮ ግራ ይገባዋል፡፡ እዚህ አንድ ማህበር እዚያ ሌላ ማህበር ሌላ ቦታም እንዲሁ አነንደኛውን የፅዋ ማህበር አድርገውታልኮ የማሪያም የገብርኤል የጊዮርጊስና ፅዋ አይነት የእነዚህ አባላት እንኳን ከአንዱ ወደ አንዱ አይሄዱም ተከባብረው ነው የሚኖሩት ሀይማኖታዊ ሰርዓት ስላለው፡፡ እንዴ ሙያም እኮ የራሱ ሰርዓት አለው በስርዓት መሄድ አለበት፡፡ ለስንቱ ማህበር ነው ድጋፍ የሚያደርገው አካል ድጋፉን ሚሰጠው?

Read 1539 times