Monday, 10 April 2017 11:03

የዘመናችን ገጣሚያን … ልዕልና!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(15 votes)

 ሰማይ ቤት እንዴት ነው … ዳዊትስ ደህና ነው፣
ዛሬም ይዘምራል …. ዛሬም ይፎክራል?
ሰላም ነው ጠጠሩ … ሰላም ናት ወንጭፉ፣
እዛስ አቅል ገዛ ጎልያድ ተራራው … ጎልያድ ግዙፉ …
ዘመን የማይሽረው ሥራ የሰሩ ሰዎች በአግባቡ ይነሳሉ፤ያላግባቡ ግን ሊረሱም ይችላሉ፡፡ … ምክንያቱም ዋናው ዘመን፣ ሰውየው በአፀደ ስጋ ያለበት፣ በጥበብ ምድጃ ላይ የተጣደበት ነውና! ከቀድሞዎቹ ገጣሚያን ይልቅ ቦታ ሊሰጣቸውና ስራቸው ሊታይ የሚገባቸው የዘመኑ ገጣሚያን/ ደራሲያን ሥራ መሆን አለበት የሚል እምነትም እውነትም አለኝ፡፡ ይህን ስል ግን የበቀሉበትን የቀደመ ዘመንና ትውልድ እንርሳው ማለቴ አይደለም! … ያ ፖለቲከኛ ፕሬዚዳንት ጀፈርሰን እንዳለው፤ … ህያዋን ይቀድማሉና ነው!
ታዲያ ስለ አሁኖቹ ዘመን ገጣሚያን ስናወሳ፣ ጥንካሬያቸው ምንድነው? ጉድለታቸውስ? … የሚለውን ማንሳት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ፡-  በጊዜው ጎላ ጎላ ያለ እንቅስቃሴ ያላቸው ገጣሚያንን ማለቴ ነው፡፡ በህትመት ውጤቶች፣ በፌስቡክ ላይ አንባቢን የያዙት ገጣሚያን እነማን ናቸው? … ጥቂቶቹን መጥቀስ እንችላለን፡፡
በለው ገበየሁ፣ ዮሐንስ ሞላ፣ አሌክስ አብርሃም፣ በላይ በቀለ ወያ፣ ትዕግስት ማሞ፣ ትዕግስት ዓለምነህ፣ ዮናስ ኪዳኔ፣መስፍን ወንድወሰን ወዘተ …. (የጉባዔ ገጣሚያንን ሳንጨምር ማለት ነው)፡፡
እስቲ ዋቢ ግጥሞችን እንመልከት-፡
መቅረጫ ሀገር ውስጥ - ገብቶ እየዞረ፣
“እቀረፃለሁ” ሲል - ያልቃል እያጠረ፡፡
ቢቀርፁት ቢቀርፁት - መዶልዶሙ ላይቀር
“መቅረጫ” በሚሏት - በእርሳሶች ሀገር
ማስተካከል ሳይሆን - መቅረፅ ነው ማሳጠር፡፡
ይህ የበላይ በቀለ ግጥም በእጅጉ ጥልቅ አተያይ ያለው ነው፡፡ እማሬውና ፍካሬው ሲሰነጠቅ ፣ጥልቅ የሆነ መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ … የስነ- ግጥም ምሁራን እንደሚሉት፤ “… ግጥም የነበረውን ነገር አዲስ አድርጎ፣ በሌላ አተያይ ማስደነቅ ነው፡፡” ይህ ገጣሚ በሁሉም ግጥሞቹ በእጅጉ የሚገርም ሀሳቦችን ይመዝዛል፣ አንገት ያስነቀንቃል፡፡ ብርታቱም እዚህ ላይ ነውና!
ግን ደግሞ ቃላቱ በለዛ የተነከሩና በሸጋ ዘይቤዎች ቀለም የረጠቡ አይደሉም፡፡ … የሙዚቃውም ጣዕም ብዙ መሳጭ ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ …ይሁንና አመታቱ ጥብቅ ነው፡፡ የቀደሙ ገጣሚዎቻችን ውስጥ የምናያቸው “ንቡር ጠቃሽ” ዘይቤዎች ብዙ አይታዩም፡፡ … ይህ ደግሞ የገጣሚውን ሁለገብ እውቀት መመዘኛ ስለሆነ የዚህ ዘመን ገጣሚያን ከንባብ መራቃቸውን ሊቀጥሉበት አይገባም ባይ ነኝ፡፡
ሌላው ገጣሚ አሌክስ አብርሃም ነው፡፡ … ይህ ገጣሚ የቋንቋ አጠቃቀሙና ለዛው፣ ከዚያም ባለፈ የትረካ ትንፋሹ ሸጋ የሚባል ነው፡፡ እስቲ አንድ ዋቢ እንውሰድ፡- ‹‹ለእግዜር የተላከ ደብዳቤ›› ከሚለው፡-
አባታችን ሙሴ እንዴት ነው ለክብሩ፣
ውቅያኖስ መክፈያው ደህና ናት ብትሩ?
እኛማ ይኸውልህ …
እንጀራ ፍለጋ ባህር ሥናቋርጥ፣
የትም ውሃ በላን የትም ዓሳ ላሰን፣
ንገርልንና ብትሩን ያውሰን …
    እናልህ እግዜር ሆይ …
ከተስፋዋ ምድር ወደሌላ ተስፋ አለን እየኳተን
መሄጃው ሲገርመን መመለሻ መንገድ መቆሚያ ቦታ አጥተን … !
…..
ሰማይ ቤት እንዴት ነው … ዳዊትስ ደህና ነው፣
ዛሬም ይዘምራል …. ዛሬም ይፎክራል?
ሰላም ነው ጠጠሩ … ሰላም ናት ወንጭፉ፣
እዛስ አቅል ገዛ ጎልያድ ተራራው … ጎልያድ ግዙፉ …
የአሌክስ አብርሃም ግጥም፣ በእንቶኔና በንቡር ጠቃሽ ዘይቤ የተሞላ ነው፡፡ በአንድ በኩል ውበት፣ በሌላ በኩል የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት - እንዳለው ያሣያል፡፡ የዚህ ወጣት ገጣሚ ግጥሞች ብዙዎቹ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጭብጦች ላይ ያተኮሩና ጠያቂ ናቸው፡፡
ግን ደግሞ የራሱ የሆኑ ችግሮች አሉበት፡፡…በአብዛኛው የዚህ ገጣሚ ችግሮች የአሰነኛኘት (versification) ነው፡፡ የስንኝ ቀርጽ ላይ ብዙ ጥንቃቄ አያደርግም፡፡…አንጓዊ መዋቅር አይጠቀምም፣ በስንኝ ድርደራ ስልቱ ደካማ ነው፡፡ … የስርዓተ ነጥብ ግድ የለሽነቱ ደግሞ አይጣል ነው፡፡ … ግጥም ሙዚቃ፣ የድምፀት ከፍታና ዝቅታ፣ የስሜት ማዕበል፣ መዋዠቅ ስለሆነ፣ ትርጉም ሊያስትና ዜማ ሊያበላሽ፤ ሀሳብ ሊያቆረፍድ ይችላል፡፡ … ግን እነዚህን  ችግሮች ማረም ቢችል እጅግ በጣም ከፍ ያለ ሥራ ሊሠራ የሚችልበት አቅም እንዳለው ያስታውቃል፡፡
በምት ላይ ያለ የአናባቢዎች ሃይልና ድምጽ ድክመት የአሁን ዘመንና ፣የብዙ የቀደሙ ገጣሚያንም ችግር ነው፡፡ እነ ጋሽ ፀጋዬም በማንቁርት ድምፆች ለዚያውም በሣድስ ቤት የሚመቱበት ጊዜ አለ፡፡ ይሁን እንጂ በምንም መለኪያ ይህ በጎ ነው ብሎ ማስተባበል  ይከብዳል፡፡ ምናልባት አልፎ አልፎ፤ በጉራማይሌነት ከሆነ ብቻ ልንታገሠው እንችላለን፡፡ አሊያ ግን ያንዳንዶቹ ትንሽ ዘግነን ይላል፡፡
ወደ ትዕግሥት ማሞ ግጥሞች ደግሞ እንምጣ፡፡ ››እንጉርጉሮ ፩ ›› የሚለውን እንመልከት፡-
ሰማዩ ሲጠቁር፤ ጽልመት ሲበረታ
በአውሬዎች ጩኸት በነፍስት ሲርሲርታ
ውሎና አዳርህን እያሰላሰልኩኝ
ተስፈኛውን ልቤን፤ ከጠባቧ ቤትህ
ሩቅ እያሻገርኩኝ፤
አንተን አስባለሁ፡፡
እዚህ ቤት አመታት ላይ ‹‹ሀሀ›› እና ‹‹ሀለ›› ተጠቅማለች፡፡… ምሠላዋም (Imagery) ጉልህ ነው፡፡ ለዓይነ ህሊና፤ ለእዝነ ልቡና ቅርብ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ስንኞች ደማቅ ድምፅ ያላቸው ናቸው፡፡ የታችኞቹ ግን የሠርን ድምፅና ሣድሥ ስለሆኑ ምታቸው መቀነሱ ግድ ነው፡፡.. ይሁንና የፍቅርን ሃይል፤… የነፍስን መባነን… ናፍቆትን የሚያሣይ ግዙፍ ምናብ ይታያል፡፡
ለምርቃት ያህል፡-
 ሕይወት ብሎ ተአብ ፍቅር ብሎ ወሬ
ገረመኝ ነገርህ፤ ገረመኝ ነገሬ
…የሚለውም የፍቅር ሀሳብ ከዚሁ ጋር ይተጋገዛል፡፡.. ገጣሚ ትዕግሥት ማሞ፣ ደማቅና ውብ ቃላት በመጠቀም በዘመኑ ከሚጠቀሱ በጣት የሚቆጠሩ ገጣሚያን አንዷ ናት፡፡ ይሁንና እርሷም እንደ ብዙዎቹ ያሁንና ቀደምት ገጣሚያን ሁሉ አሠነኛኘት ላይ፣ ችግሮች ይስተዋሉባታል፡፡ (በዚህ መቅደስ ጀንበሩ ትለያለች፡፡) ለምሳሌ ‹‹የጎደሉ ገፆች›› በተሰኘ አዲሱ የግጥም መጽሐፍዋ ውስጥ በቤት መምቻ ላይ ከፊል አናባቢን ከሣድሥ ጋር መጠቀምና የማንቁርት ድምፆችን ከሣድስ ጋር መጠቀም በተደጋጋሚ ታዝቤያለሁ፡፡
ሌላው ወጣት ገጣሚ ዮሐንስ ሞላ ነው፡፡ ዮሐንስ ሁለት መጻሕፍት አሉት፡፡
እኔ የመጽሐፍ ዳሠሣ የሰራሁበት የመጀመሪያውና ‹‹የብርሃን ልክፍት›› የተሰኘውን ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ የያዘው በጭብጥና በቅርፅ ልዩነታቸው ደማቅ ነበር፡፡
‹‹ከፍቅሬ ሙዚቃዬ›› ላይ አንድ ሁለት አንጓ እነሆ፡-
አካሌ በተንተን፣… ሰውነቴ ወዝወዝ፤…
አንዴ መለስ ቀለስ፤ ደግሞ ፈዘዝ፤ ተከዝ፤
አንቺ ሆዬ መርገፍ፤ በባቲ መንዘፍዘፍ፤
በአምባሰል መቆዘም፤ በትዝታ መቅዘፍ፤
ጎኔ ተቀምጠሽ፤ መላቅጥ አጣለሁ፤
ካንቺ ጋር አብዳለሁ!
በመውደድሽ ዜማ፤ በፍቅርሽ ዝማሬ፤
በቋንቋሽ ጥፍጥና፤ በሐሳብሽ ሰክሬ፤
በሱስሽ ታስሬ፤ በስሜት ታውሬ፤
ስትጠፊ ናፍቄ፤ ሳገኝሽ ደንብሬ፤
እኖራለሁ እንጂ …
የተቃራኒ ፆታ ፍቅር ነው፡፡… የፍቅር ስሜቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ ምሠላውም እንደዚሁ ደማቅ ነው፡፡ በተለይ የመጀመሪያው አንጓ፡፡.. ያ ብቻ አይደለም፤ የሀገራችንን የሙዚቃ ቅኝቶች ጥሩ አድርጎ ለምሠላ ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ይህም ማለት ተገቢውን ቃላት ቀለም ነክሮ ግጥሙን አሣምሮበታል፤ ሆኖም አሠነኛኘቱ ያን ያህል ውብ አይደለም፡፡
 የዮሀንስ ግጥሞች ብዙ ጊዜ አጥንታቸው ጠንካራ፤ ቋንቋቸውና ሀሳባቸው የቀደሙ ገጣሚያንን ዓይነት አካሄድ ያላቸው ናቸው፡፡… በአተያዩም ካሁኖቹና ከቀደሙት ዘመን ሰዎች የመቀላቀል አዝማሚያ አለው፡፡… ግን ስሜት ብቻ አይደለም፡፡
በአጠቃላይ ዛሬ በጨረፍታ ላነሣው የሞከርኩትን የዘመናችን ገጣሚያን ሥራና አዝማሚያ፣ ብዙ ጊዜ አስበውና አሰላስለው የነበረ ነው፡፡ … ምናልባት እነዚህ ባጭሩ የተዳሰሱ ገጣሚያን ጉዳይ ጥቂት ይምሰል እንጂ እጅግ ጠለቅ ወዳለው ምርመራ የተገባበት ነው፡፡… ከዚህ ቀደም ሁላችንም (ዳሰሳና ሂስ የሠራን ሰዎች) የምናተኩረው ጭብጥ ላይ ብቻ ነበር፡፡
ይህ ደግሞ ለመዝረክረክ ዳርጎናል፡፡ መዝረክረኩ ታዲያ፤ የቀደሙትም ሆነ የዚህን ዘመን ገጣሚያን ስራዎች በቀድሞ የግጥም ዳሰሳ አይን ብናያቸው ልዕቀታቸው የትናየት ነው!.... የፈጠራ ሃይላቸውና ፍጥነታቸው ጉድ የሚያሰኝ ነው፡፡… መንግሥቱ ዘገየን ከእነ ወንድዬ ዓሊ ዘመን ወዲህ ካመጣነው፤ ቦታውን ባላውቅም በፌስቡክ ላይ የሚፅፋቸው ግጥሞች ብቻ ‹‹እገሌ›› የምንላቸውን ይተልቃል፡፡ አቅሙ በጣም እየጨመረም ነው፡፡
በላይ በቀለ ወያ እንደዚሁ ፈጣንና አስገራሚ አተያይ ያለው፣ ባለ ድንቅ ምናብ ነው፡፡ ግጥምን እንደ ወሬ በማድረግ በፌስቡክ እንዳያረክሰው እፈራለሁ፤ ምክንያቱም ለሁሉም ነገር አይገጠምም፡፡ ግጥም የተመረጠ ሀሳብ፣ በተመረጡ ቃላት ነውና!
አሁን በዘመኑ የሚታየኝ ክፍተት የሁለገብ ዕውቀት ማነስ ነው፡፡… ገጣሚዎች ምናብም ዕውቀትም ያስፈልጋቸዋል፡፡ በተረፈ ሌላ ጊዜ ደግሞ በስፋት እመለስበታለሁ፡፡

Read 6397 times