Monday, 10 April 2017 10:59

የጦም ነገር

Written by  ነ.መ
Rate this item
(1 Vote)

እሱም አንተ ሂደው ሲለኝ፣ እኔም አንተ ሂደው ስለው
መንገዱን ጦም አሳደርነው!
እሱ ዕውቀት ተናገር ሲለኝ፣ እኔ አንተ ተናገር ስለው
ዕውነትን ጦም አሳደርነው!
እሱ አንተው ታገል ሲለኝ፣ እኔ ባንተ ያምራል ስለው
ትግልን ጦም አሳደርነው!
እሷ አንተ ተማር ስትል፣ እኔ ተይ ተማሪ ስላት
ይሄው ጦም አደረ ትምህርት!
እሷ አንተ አፍቅረኝ ስትል፣ እኔ ስል አፍቅሪኝ አንቺው
ፍቅርን ጦም አሳደርነው!
እኔ አንቺ ብይ ስላት፣ እሷ ስትል ‹‹ራስህ ብላው››
ምግቡንም ጦም አሳደርነው!
እኔ አንቺ ጡሚ ስላት፣ እሷ ስትል አንተው ጡመው
ጦምንም ጦም አሳደርነው!
የእኛ ነገር ሁሉመናው… ፍስክና ጦም ማህል ነው!...
ከጦሞቹ ሁሉ የከፋው ሰውና አገርን መጦም ነው!
እናም የማታ ማታ፣ የጦምን ነገር ሳስበው
ካልጦምነው ነገር ይልቅ፣ የጦምነው ነው የሚበዛው
ታዲያ ምን ይሻለን ብዬ፣ ዐይኔን ገልጩ ሳየው
የሱንና የሷን ሁሉ፣ የኔን ጨምሬ ሳስበው
እንደው የመጣው ቢመጣ
እሱም የራሱን ቢወጣ፣ እኔንም ሊያግዝ ቢመጣ
እሷም የሷን ብትወጣ፣ እኛን ልትረዳም ብትመጣ
እኔም ብችል የኔን ጣጣ፣ ደሞም የነሱን ብወጣ
አንድ እንቅልፍ እንዳንቀላፋን፣ አንድ ንቃት ብንነቃ
አንድ ዳገት እንድንወጣ፣ ቁልቁል ያደግነው ቢበቃ፤
ከቶ አንድ ህመም ብንታመም
አንድ-ወጥ ህልም ብናልም
አንድ መከራ ቢመክረን፣ አንድ መከር ብንመክር
ብዙ ዘፈን ብንዘፍንም፣ ባንድ ዜማ ብንዘምር
ብዙ ችቦ ብናበራም፣ አንድ ደመራ ብንደምር
ውነት ውነት (እ) ላችኋለሁ፣ ማንም ጦም አያድር ነበር!!!
መስከረም 15/2005
(ለጋራ ደመራችን)

Read 1062 times