Monday, 10 April 2017 10:59

የአባይ ግድብ የማን ነው?

Written by  ያለው አክሊሉ
Rate this item
(6 votes)

 ግብፆች ከምዕተ ዓመታት በፊት ወረራ አካሂደው ምፅዋን ይዘውብን ነበር፡፡ ቀጥሎም ባልተቋረጠ የጦርነት ዑደት ውስጥ ከትተውን በየማዕዘኑ ስንዋጋ ኖረናል፡፡ ደርቡሾችም በተቀፅላነት ጊዜ እየጠበቁ አጎሳቅለውናል፡፡
ከሻዕቢያ የሠላሳ ዓመታት ጦርነት ጀርባ ግብፆች በሎጂስቲክስ ድጋፍ፣ በፖለቲካ ስትራቴጂስትነትና በወታደራዊ አማካሪነት ዋና ተዋናይ ነበሩ፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ የበቀሉና የተለያየ ሥያሜ ይዘው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ቡድኖች ካካሄዱት ጦነት ጀርባ ግብፆች ነበሩ፡፡
ቀይ ባሕርን ተነጥቀን ወደብ አልባ እስረኞች እንድንሆን በተጠነሰሰው ዐረባዊ ዱለታም ግብፆች ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ጄኔራል ዚያድ ባሬ፣ እስከ አዋሽ ወንዝ ድረስ ዘልቆ ኢትዮጵያ የደም ዕንባ ባዘራችበት የ1969 ዓ.ም ወረራ ግብፆች ከጀርባ ነበሩ፡፡ ሌላው ቀርቶ ከኤርትራ ነፃነት በኋላ በተካሄደው የባድመ ጦርነት ጀርባ ግብፆች ረጅም እጅ ነበራቸው፡፡ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ከአልሸባብ ጋር በገጠምነው ትንቅንቅ፣ ግብፆች በኤርትራ በኩል እጃቸውን አሾልከው በእጅ አዙር ይፋለሙናል፡፡ በተጨማሪም “… እኛ ኢትዮጵያውያን አይደለንም፤ የራሳችንን ነፃነት እንፈልጋለን …” የሚሉ፤ ህልመኛ፣ ዘረኛ ድርጅቶች ባለቃቀሱ ቁጥር ግብፆች በእንባ አባሽነት ሲተውኑ እናያለን፡፡  በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ነፍጥ አንግበን እንዋጋለን የሚሉቱም ከግብፅ ጋር ወጣ - ገባ ያለ ግንኙነት መስርተዋል ሲባል እንሰማለን፡፡ (ወይ ተላላነት!) ከደርግ ዘመን አንስቶ ሀብት፣ ጉልበትና ህይወት የከፈልንበት የደቡብ ሱዳን ነፃነት ተሳክቶ፣ ነፃ ሀገር ሆና በተመሰረተች ማግስት መልካም ጎረቤት ፈጠርን ስንል፣ ሌላ የቶን ውጋት ወደ መሆን እያጋደለች ያለችበት፣ ሴራ ጠንሳሾች ግብፆች ናቸው፡፡
ግብፆች በኢትዮጵያ ውስጥ ቅርፅና ይዘቱ ምንም ይሁን ምን መንግሥት ተብሎ በሚቋቋም አካል ላይ በተቃዋሚነት ለሚነሳ ኃይል ሁሉ እርዳታ ለመለገስ ፈቃደኞች ናቸው፡፡ ካይሮ ውስጥ የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲ አቅምና የፀጥታ ሁኔታ ዕለት ከዕለት እየተከታተለ ለመንግሥት ሪፖርት የሚያቀርብ ልዩ ተቋም አላቸው፡፡ የዚህ ሁሉ ስጋት ምስጢር ከሃይማኖታዊ ትንኮሳው ግብ በተጨማሪ እነሱ የህይወታችን ምንጭ የሚሉት የአባይ ወንዝ እናት ኢትዮጵያ መሆኗ ነው፡፡ ይሄን ወንዝ መንካት የእያንዳንዱን ግብፃዊ ጉሮሮ አንቆ የመግደል ያህል ነው የሚል ጥላቻ አላቸው፡፡
እንዲህ ዓይነቷ ሙከራ ከግብፅ ጥቅም መጓደል ባሻገር የዐረብ ሊግ ሀገራትን ክብር እንደ መንካት ስለሚቆጠር ኢትዮጵያ ወዮላት ተብሎ በሳዑዲ ዐረቢያ የመከላከያ ሚኒስትር አንደበት ሳይቀር ሲዛትብን፣ ስንናቅና ስንዋረድ ሰምተናል፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን የአባይ ግድብን ጀምረን ለዚህ አድርሰነዋል። ከዚህ ሁሉ እሰጥ አገባ አኳያ ለእኔ የአባይ ግድብ፣ ከድንጋይ ካብነት ባለፈ ለአያት ቅድመ አያቶቼ ደምና አጥንት በካሳነት የቆመ የድል አድራጊነት ሐውልትነቱ ይጎላብኛል፡፡ ከኃይል ማመንጫነቱ ባለፈ በብርሐን ፋና የሚንቦገቦግ የኢትዮጵያውያን የቁጭትና የአንድነት ቀንዲልነቱ ይበልጥብኛል፡፡ ለኢኮኖሚያዊ ትንሳኤ ሞተር ሆኖ ከሚያበረክተው ግብዓት ባለፈ ሐበሻነት ከሸረሪት ድር የቀጠነ፣ ነገር ግን ከብረት የጠነከረ መንፈሳዊ ሰንሰለት ማለት እንደሆነ ለዓለም ሕዝብ ያረጋገጠ፣ የታላቁ ዐድዋ ድል ታናሽ ወንድምነቱ ድቅን ይልብኛል፡፡
ከግድቡ ግንባታ በተጓዳኝ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ ተከናውኖ፣ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ ያመኑ የተፋሰሱ ፈራሚ ሀገራትን ኅብረት ለመነጣጠል ግብፆች ምን ያህል እየተሯሯጡ እንደሚገኙ እያየን ነው፡፡ የአባይ ግድብን የመሰረት ድንጋይ ባኖርን ማግስት ተደናግጠው በወደቀው ፕሬዚዳንት በመሐመድ ሙርሲ ሰብሳቢነት፣ በአደባባይ ቅጥ አምባሩ የጠፋ የጦርነት አይሉት የማስፈራሪያ ናዳ ማዥጎድጎዳቸውን ልብ ይሏል፡፡ ጥቂት ከተረጋጉ በኋላ ደግሞ ከፈረንሳይ አገር እጅግ ዘመናዊ ሚራዥ የጦር አውሮፕላኖችን ከማዘዝ ጎን ለጎን ለድርድር ተዘጋጅተናል አሉ፡፡ ከዚህ ሰምና ወርቅ አቀራረብ አንፃር እኛም ከድንጋይ ካብ ባሻገር የህዝብን ልብና መከላከያንም አሻቅቦ የመካብ ግዴታ እንደሚጠበቅብን ትምህርት ወስደናል ብዬ አምናለሁ፡፡
ለአባይ ግድብ ግንባታ የምናዋጣው ገንዘብ፣ የምንገዛው ቦንድና የምናበረክተው አስተዋፅኦ የእዩልኝ ወይም የስሙልኝ አይደለም፡፡ ከህልውና፣ ከሉዓላዊነትና ከታሪክ ክብር አንፃር ልንከፍለው የሚገባን የዜግነት ግዴታ እንጂ፡፡ ተዋራጅነታችን ይብቃ! ማንነታችን ይታደስ! በራስ የመተማመን መንፈሳችን በትንሳኤ ይቃና! አመልህን በጉያ ሸክምህን በአህያ እንዲሉ ውስጣዊ እንከኖቻችንን አቻችለን፣ በአባይ ጉዳይ የጠላቶቻችንን ቅስም እንስበር! ያም ቢባል የድርሻችንን ከመጠቀም ባለፈ ሌሎችን በመጉዳት አባዜ፣ ለሰው ልጅና ለፈጣሪ የማይመች ክፉ ልቡና እንደሌለን ማሳያም እናድርገው፡፡
በግሌ ለአባይ ግድብ ከደመወዜ የከፈልሁት መዋጮ ወይም በአክሲዮን ማኅበራት በኩል የተፈፀመ የቦንድ ግዥ በደንቡ መሰረት ጊዜው ሲደርስ ይመለስልኝ ላለማለት ለራሴ ቃል ገብቻለሁ፡፡ እንዲህ ባደርግ በእኔ መዋጮ ተገዝታ ለግንባታ የዋለችዋን አንዲት ፍሬ ድንጋይ አፍሳችሁ አምጡልኝ የማለት ያህል ይሰቀጥጠኛል፡፡ አለዚያም ‹‹… ግድቡ ከተሰራ ከእኔ ገንዘብ ምን አላችሁ?...›› ብዬ ከዚህ የትውልድ ሐውልት የጋራ ባለቤትነት መዝገብ የተሰረዝኩ ያህል ያመኛል፡፡ እንዲህ ስል የሌሎችን መብት ለመጋፋት አይደለም፡፡ ለቅስቀሳ መነሳቴም እንዳልሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡ ለነገሩ ብቀሰቅስስ ለጋራ ጥቅምና ለጋራ ክብራችን እስከሆነ ድረስ ምን ያስነውራል? ይህ ግድብ የውርደትና የታናሽነት ሥማችንን ከቁጭትና ከፀፀት በመነጨ አርበኝነት ደምስስን፣ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን የምናሳፍርበት አቢይ ማሳያ ነው፡፡ ስለዚህ አቅሜ በፈቀደ መጠን ማዋጣቴን እቀጥላለሁ፣ የማዋጣው ለሦስተኛ ባዕድ ወገን ስላልሆነ ባለ ወለድ ተመላሽ ገንዘብ ብሎ ቋንቋ ለእኔ አይስማማኝም፡፡ ሰው ለጎረቤቱ እንጂ ለራሱ አያበድርም፡፡ የቦንድ ግዥ ሥርዐት በየትኛውም ዓለም የሚሰራበት ህግ አለው ከተባለም፣ ይሄ ደንብ ለእኛው አባይ አይሰራም ብዬ ራሴን ስላሳመንኩት በውሳኔዬ እፀናለሁ፡፡ (ከይቅርታ ጋር)
ቀደም ባሉት አመታት በውጭ ከሚኖሩ አንዳንድ ወገኖቻችን ግራ የሚያጋቡ አስተያየቶች ሲስተጋቡ እንሰማ ነበር፡፡ ‹‹… በዐረቡ ዓለም የተቀጣጠለው ፀረ ገዥ መደብ አብዮት እንዳይዛመትበት የሰጋው የኢትዮጵያ መንግስት፣ የሕዝቡን የተቃውሞ አቅጣጫ ለመቀልበስ የአባይ ግድብ…›› የሚል ነቀፋ ይሰነዘር ነበር፡፡ አሁንም የተዳከሙ ቢመስሉም አዘናጊ ሽሙጦች ሲሰነዘሩ ይሰማል፡፡
ስንት እልህ፣ በደል፣ ቁጭትና የተዋራጅነት ስሜት ጭኖብን በኖረው በአባይ ጉዳይ ‹‹ሀ››  ብለን ለዘመቻ ስንነሳ መደገፍ ባይቻል እንኳ ቆም ብሎ ከራስ ጋር መመካከር ሲገባ፣ በግብታዊነት ይህን መሰል ውግዘት ማዥጎድጎድ ከኢትዮጵያዊ ማንነት በዘለለ በገዛ ደጋፊዎች ዘንድም ጥያቄ ያስነሳልና ወንጋራው አተያይ መስተካከል እንደሚገባው አምናለሁ፡፡
ግድቡ የእኛ ነው፤ ግድቡ ያረፈባት ኢትዮጵያ ነዋሪ ስትሆን እኛ ግን አላፊዎች ነን፡፡ ይሄን ግድብ ከእኛ የዕድሜ ዘመን አንፃር እያስተያየን ከምንከተለው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ትይዩ ሌላ ትርጉም ለመስጠት መሞከር ተገቢ አይመስለኝም። መንግሥት ይመጣል ይሄዳል፤ ሕዝብ ይኖራል፤ ይተካል፡፡ የማያልፍ አሻራ ማኖር ቢያስመሰግን እንጂ አያስነቅፍም። እያንዳንዳችን መንግስትን የምንመለከትበት የየራሳችን መነፅር አለን፡፡ መንግሥት በድሎን ይሆናል፡፡ ይህ መንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የማይበጁ ሥራዎች ሰርቶ አበሳጭቶን፣ ለዚህም ከባድ ዋጋ ከፍለን ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም እንኳ ፖለቲካዊ ሥልጣንና ኢኮኖሚያዊ መዋቅር የገዥ መደብ መጨቆኛ መሳሪያዎች ስለሆኑ አይነጣጠሉም ቢባልም፣ የብሶቶቻችን መፍትሄ አማጭ አማራጮችን ከዚሁ ጋር ብቻ አቆራኝቶ ማጠቃለል መልካም ስላልሆነ እርማት ያሻዋል ባይ ነኝ፡፡ ይህ መንግስት ኖረም ቀረም በቁርጠኝነት የጀመረውን የአባይ ግድብ ወደ የትም ይዞት ስለማይሄድ ከጎኑ ልንቆም ይገባል፡፡ የሚታዩ ግዙፍ ተግባራትን ለማድነቅ ባንፈልግ እንኳ ዝም ለማለት ያለመቻል በታሪክ ስለሚያስወቅስ ስንቃወም “…ሀገር ወይስ መንግስትን…” ብሎ መለየት የግድ ይመስለኛል፡፡
 አሁን ላይ ለዚህ ድንቅ ፕሮጀክት ስኬት ጠጠር ያልወረወረ ዜጋ፣ ነገ ከትሩፋቱ ሲቋደስ በኅሊና ወቀሳ ራሱን እንዳይጎዳ ይጠንቀቅ፡፡ ላብ ሳያፈሱ አጥብቀው አይጎርሱ ነውና ሌሎች የደከሙበትን ለመብላት እጅን ማሾል በባህላችንም ነውር ስለሆነ አንዳንዶቻችን ከራሳችን ጋር እንታረቅ፡፡
በመቀጠል አንዲት ነጥብ ላነሳ ወደድሁ፡፡ የአባይ ግድብ ግንባታ ከ56% በላይ ተጠናቀቀ ለሚል ዜና ብዙም ፍቅር የለኝም፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታና ሌሎች ቀጣይ ሥራዎቻችን በፐርሰንት እየተለኩ አሀዝ የሚደረደርላቸው፣ ከዚያም ተጠናቀቁ ተብለው ዐዋጅ የሚነገርባቸው ናቸው ብዬ አልገምትም። ይህን ስል ሕዝባዊ የሞራል ግንባታ ለመፍጠር ሥርዐትን አማክሎ የሚቀርብ የክንዋኔ ሪፖርት አይኑር ለማለት ሳይሆን ቀጣይ ስራዎቻችን ግዙፍ፣ አካሄዳችን ትዕግስት የሚጠይቅ፣ ጉዟችን ፈተናዎች ያሉበት ስለሆነ ልባችን አይሰቀል ለማለት ፈልጌ ነው።
የአባይ ግድብ ግንባታ ሊጀመር ቀርቶ ገና ሳይታሰብ፣ ከ23 ዓመታት በፊት የፃፍኳት  ሚጢጢዬ ግጥም ባለፈው አመት በታተመው ‹‹ወሰብሳቤ›› በተሰኘው መጽሐፌ ገፅ 422 ላይ ስለምትገኝ መልዕክቷን ላጋራችሁ፡፡  
“አባይ የድኃ ዘር አባይ የንጉሥ ዘር
ሁሉም የእኔ ነው ባይ የት ይሆን ያንተ አገር?
ሲነኩህ አበሳ ቢተውህ መከራ
እሳተ ነበልባል እሳተ ጎመራ
እንጃ ያንተ ጉዳይ ነገር ያጓትታል ያማዝዛል ካራ።”
ከግብፆች ጋር የነበረው አተካራ ምዕተ ዓመታትን ይሻገራል፡፡ ዛሬ በጀግንነት የተያያዝነው የአባይ ግድብ ግንባታ ለምዕተ ዓመታት ልንጠቀምበት አቅደን የምንረባረብበት ብርቅ ፕሮጀክት ነው። ውጤቱን በማይናጋ መደላድል ላይ ለመትከል በታሳቢነት የሚያዙ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተዘንግተው ወይም ተለሳልሰው ታይታዋል የሚል ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ይሁን እንጂ ዘመኑ ከጦርነት ጋጋታ ይልቅ በዲፕሎማሲ ብቃት ድል የመቀዳጃት ጥበብ ያየለበት ጊዜ ነው ቢባልም፣ ቀጣዩ የአለም ጦርነት መነሻ የውኃ ጥያቄ ነው የሚሉ የታሪክና የፖለቲካ ሊቃውንት ስላሉ፣ምናልባት በዕብሪት ለጥፋት የሚያደቡ ቢነሱ፣ በብልጠትና በብርታት የምንመክትበትን ሰፊ ህዝባዊና ቁሳዊ አቅም ለመገንባት መልሕቅ የምንጥልበት ወቅት ዛሬ መሆኑን ደጋግመን እናስታውስ፡፡ ሁላችንም በምንፈለግበት ቦታ ሁሉ ለመድረስ በተጠንቀቅ እንቁም፡፡ በበኩሌ እድሜና ጤና ከሰጠኝ በግንባር ረድፍ እንደምገኝ በወላዲተ አምላክ ሥም ቃል ገባሁ! እንበርታ!

Read 3482 times