Monday, 10 April 2017 10:50

ሹሩባ ልትሰራ ሄዳ ጸጉሯን ተነጭታ መጣች

Written by 
Rate this item
(23 votes)

   ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ትልቅ አውቶቡስ በርካታ መንገደኞች ይጓዛሉ፡፡ ከተጓዦቹ መካከል አንዲት ህፃን ልጅ የያዘች እናት አለች፡፡ ልጇን እሹሩሩ ትላለች፤ ታባብላለች፡፡
በመካከል እዚያው ተጓዦች ዘንድ ያለ አንድ ዠርዣራ ሰካራም ከተቀመጠበት ይነሳል። እየተንገዳገደ፤ ፊት ለፊቷ ይቆምና ቁልቁል እያያት፤
“ስሚ ሴትዮ፤ እኔ በህይወቴ እንደዚህ ያለ አስቀያሚ ልጅ አይቼ አላውቅም” አላት እየተኮለታተፈ፡፡
ሴትዬዋ በመከፋትና በቁጣ መካከል ባለ ድምፅ፤
“ምን አገባህ! አርፈህ አትቀመጥም?” አለችው፡፡
“እኔ ቢያገባኝም ባያገባኝም ልጁ አስቀያሚ መሆኑን አይለውጠውም!” አላት ደግሞ።
ሴትዮይቱ በጣም ሆድ ባሳትና ስቅስቅ ብላ አለቀሰች፡፡
ተጓዡ ህዝብ በጣም ከማዘኑ የተነሳ አንዱ ተነሳና ያን ሰካራም ገፈተረው፡፡ ሌላው በቦቅስ ተቀበለው፡፡ ግርግር ተፈጠረ፡፡
ይሄ ሁሉ ሲሆን ሴትዮይቱ መንሰቅሰቋን ቀጠለች፡፡ እዬዬዋን አስተጋባች፡፡ ጩኸቷ በጣም ከመሰማቱ የተነሳ በመጨረሻ ሹፌሩ አውቶቡሱን ከመንገዱ ወደ ጥግ አደረገውና፣ ልቅሶዋን ወዳላቆመችው ሴት ዞሮ፤
“እሄውልሽ የእኔ እህት፤ ያ ጭንጫ ራስ ሰካራም ምን ክፉ ነገር እንደተናገረሽ አላውቅም፡፡ ሆኖም እንድትረጋጊ አሁን ሄጄ ሻይ ይዤልሽ እመጣለሁ፡፡ አንቺ ግን አይዞሽ፤ ረጋ በይ!”
አላትና ከዓይን ተሰወረ፡፡
በአቅራቢያው ወዳለ አንድ ሬስቶራንት ገብቶ፣
“ለአንድ ለከፋትና ሆድ ለባሳት ሴት የሚሆን ቆንጆ ሻይ ስጠኝ” አለው አስተናጋጁን፡፡
“ቅመም ይኑረው ጌታዬ?” አለና ጠየቀው ቦዩ፡፡
“አዎ፡፡ ያጣፍጠዋል ያልከውን ማናቸውንም ቅመም ጨምርበት፡፡ ብቻ ሴትዮዋን ሰላም ይስጣት”
“ሁሉንም አረጋለሁ፤ ጥቂት አረፍ ይበሉ”
ቆይቶ ሹፌሩ ወደ ሴትዮዋ ተመለሰና እንዲህ አላት፡-
“ተረጋጊ የእኔ እመቤት፡፡ ሁሉም ነገር ይረጋጋል፡፡ ታገሺ፡፡ ይሄውልሽ በጣም ምርጥ የሆነ፣ በቅመም ያበደ ሻይ አምጥቼልሻለሁ፡፡ ላንቺ ቀርቶ ለዚህ ዝንጀሮ ለመሰለ ልጅሽም ሙዝ ገዝቼለታለሁ!”
*          *       *
የችግሩን መንስኤ ሳናውቅ መፍትሄ እንፈልግ ማለት ተጨማሪ ችግር ወደ መሆን እንድናመራ ሊያደርገን ይችላል፡፡ ልጇ ተሰድቦባት ለምታነባ እናት፤ ምንም ዓይነት ማባበያ እንስጣት፣ መልሰን ልጇን እምንሰድብባት ከሆነ በቁስል ላይ ቁስል ጨመርንባት ማለት ነው፡፡ የህዝብን ችግር መንስኤ ሳናውቅ ጊዜያዊ መፍትሔ ብቻ በመፍጠር ጉዳዩን ገለነዋል ብለን ማሰብ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” መሆኑን አለመዘንጋት ነው፡፡ ህዝብ፤ ቀን ጠብቆ፤ ይብስም ምሬቱን አመርቅዞ፣ እንደሚመጣ በጭራሽ አለመርሳት ነው፡፡
ሰዎችን ከሥልጣን ሥልጣን  ቦታ በመቀያየር መሰረታዊ ለውጥና መፍትሄ አናመጣም፡፡ ተሐድሶም ሆነ ጥልቅ - ተሐድሶ የኃላፊዎችን ውስጠ ሕሊናዊ መለወጥ በቅድሚያ ይጠይቃል፡፡ “ዕውነተኛ ንቃት የሚኖረው አንቂው አስቀድሞ ሲነቃ ነው” ይላሉ አበው፡፡ የአንቂዎች ከሙስና ፅዱ መሆን ወሳኝ ነው፡፡ የአንቂዎች ፍትሐዊ መሆን እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ የጎሸ ይጠራ ዘንድ፣ የታመመው ይፈወስ ዘንድ፣ የደከመው ይጠነክር ዘንድ፣ የማይድን ጋንግሪን ቁስል ደረጃ የደረሰው፤ በመላ ተቆርጦ ይጣል ዘንድ፣ አይነኬ አይሞከሬ ነው የተባላ ሹም፣ ቡድን፣ ተቋም የግድ የሚፈተሽበት ዘዴ ይፈጠር ዘንድ፤ ወቅቱ ይጠይቃል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ቡድነኝነት (groupism)፤ የማይመለስ መዓት (irreversible catastrophe) ላይ ሊጥደን እንደሚችል ሳይመሽ መገንዘብ ጥበበኝነት ነው፡፡ የሚመለከተው አካል የተረጋጋ ቦታ ቆሞ ሊያጤነው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በመፈራራት አገር ወደ አዘቅት ስትወርድ እያዩ እርምጃ ሳይወስዱ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ የሴራ መረቦችን መበጣጠስ ያሻል፡፡ ቀልባሽ (subversive) አካሄድን በንሥር ዓይን ማየት ለእርምጃ መውሰድ ዝግጁነትን ያመላክታል፡፡ ተናጋሪ ምላሶች የዕውነት ምስክር ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ “ነገር አሳማሪ አድሮ፣ ሾተል ሰንዛሪ” እንዲሉ፣ ተጠንቅቆ መከታተል የአባት ነው፡፡ “እባብ ለእባብ፣ ይተያያል ካብ ለካብ” የዋዛ ተረት እንዳልሆነ ልብ ማለት የሚገባን ዛሬ ነው፡፡
ጎራና ወገን ለይቶ የእኔ ድምፅ የተለየ ቃና አለው ማለት፤ ትላንት ካሰመርኩት መስመር ውጪ ንቅንቅ አልልም ማለት፤ ቃል መግባትና አድሮ መሻር፣ ስብሰባን ረግጦ ለመውጣት ሁሉ ማኮብኮብ፣ ብቆጣም እመታሻለሁ፣ ብትቆጪም እመታሻለሁ ማለት፤ አሳሳቢ ነው፡፡ ዋናው ነገር በማናቸውም ተደራዳሪና ዕርቅ-ፈላጊ ወገን ላይ ኢ-ፍትሃዊ አካሄድ መከሰት የለበትም፡፡ ሆደ ሰፊነትና ብልህነት መቼም ቢሆን መሳሪያዎቻችን መሆናቸውን በብስለት ማየት፤ ለአገርና ለህዝብ ለቆመ ሁሉ ተስፋ ሰጪ ማረጋገጫው ነው፡፡ አለበለዚያ ግን “ሹሩባ ልትሰራ ሄዳ ፀጉሯን ተነጭታ መጣች”  የሚለው ብጤ ይሆናል! 

Read 5027 times