Monday, 03 April 2017 00:00

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ 42ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤና ያለፉት 4 ዓመታት

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ 42ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በአዳማ ከተማ  ሪፍት ቫሊ ሆቴል ይካሄዳል። የጉባኤው አባላት  በስምንት ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፉ የሚጠበቅ ሲሆን የኦሎምፒክ  ኮሚቴውን ለቀጣይ 4 ዓመታት  የሚመሩትን አዲስ ፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ ቦርድ አባላት ምርጫ ይደረጋል፡፡ የኦሎምፒክ ኮሚቴው የኮምኒኬሽን ክፍል ለስፖርት አድማስ በላከው መግለጫ የ41ኛው ጠቅላላ ጉባኤ  ቃለ ጉባኤ፤ የ2016 እቅድ አፈፃፀም፣የፋይናንስና የኦዲት ሪፖርቶች፤ የ2017 -2020 ረቂቅ የስትራቴጂ እቅድ፤ የ2017 ዓመታዊ እቅድ እንዲሁም የስራ አስፈፃሚ ቦርድ ምርጫ ማስፈፀሚያ ረቂቅ መመርያ መርምሮ ማፅደቅ ሌሎች የጉባኤው አጀንዳዎች መሆናቸውን በዝርዝር አመልክቷል፡፡
ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ  አዲስ ፕሬዝዳንት ምርጫ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በብቸኛ ዕጩነት እንደቀረቡ ታውቋል፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታት የፕሬዚዳንትነቱን ኃላፊነትን ይዞ የቆየው የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ሲሆን፣ አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን የሚወክል ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን ለ4 ዓመታት ለመምራት የሚወዳደሩ የስፖርት ማህበራት  እጩ ተወዳዳሪዎቻቸውን  ከ2 ሳምንት በፊት ታውቀዋል። ከአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ እጅ ኳስ፣  ቅርጫት ኳስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ጅምናስቲክ፣ ውኃ ዋና፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቦውሊንግ፣ ካራቴ፣ ውሹ፣ ክብደት ማንሳት፣ ባድሜንተንና መረብ ኳስ ፌዴሬሽኖች  የተወከሉ ናቸው። በጉባኤው አብላጫ ድምፅ የሚያገኙት ሰባቱ የስፖርት ፌደሬሽኖች  አመራሮች  ለመጪዎቹ አራት ዓመታት በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴነት ይካተታሉ፡፡ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል የሆኑት ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማይ፣ በቀጥታ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ሲሆኑ፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካይና የኦሊምፒያኖች ተወካይ ያለ ድምፅ እንደሚካተቱም ለማወቅ ተችሏል፡፡  
ከ2005-2009 ዓ.ም ባለፈው የስትራቴጂክ ዘመን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ በጠቅላላ ጉባኤው በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በመንቀሳቀስ  በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ የኦሎምፒክ ፍልስፍናና እንቅስቃሴን በተለያዩ መድረኮች በመላ አገሪቱ በማስፋፋት፤ የተቋሙን አሠራር በማሻሻል እና መዋቅራዊ አደረጃጀቱን በማጠናከር ፤ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላትን በአቅም ግንባታ እና ተያያዥ ስልጠናዎች በማሳተፍ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ነባር የአሠራር ሥርዓት ጋር የተያያዙ ሁኔታዎችን በመገምገም ለውጦችንም አድርጓል፡፡
በሌላ በኩል የኦሎምፒክ ኮሚቴው ባለፉት አራት አመታት የገቢ ምንጮቹን በማሳደግ በትኩረት ተንቀሳቅሶ ከ141 ሚሊዮን ብር በላይ አግኝቷል፡፡ ከአጋርና ለጋሽ ድርጅቶች የፋይናንስ እና የማቴሪያል ድጋፍ በማፈላለግ፣ በተለያዩ ዘዴዎች ከስፖንሰርሺፕ፤ ከህብረተሰቡ የፋይናንስ እና የማቴሪያል ድጋፎችን በማሰባሰብ ነው። ለተለያዩ የስፖርት ማህበራት  የገንዘብና የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፎችን ያደረገ ሲሆን ፤ ለማጣሪያ ውድድሮች ዝግጅትና ተሳትፎ፣ በክልል ደረጃ ለተካሄዱ ክልል አቀፍ ውደድሮች ለመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች፣ ለኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኀበራት ኮንፌዴሬሽን፣ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስፖርት ፌስቲቫሎች፣ ለፖሊስ ሰራዊት ስፖርት ፌስቲቫሎች፣ ለማዘውተሪያ ስፍራ ግንባታዎችና ክልሎች ላቋቋማቸው የአትሌቲክስ ክለቦች መቋቋሚያ ፣ለኢትዮጵያ ፀረ-ዶፒንግ ማደራጃ  ፣ ለቀድሞ የአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች የህክምና ወጪዎችን ለመሸፈን በድምሩ  ከ11.7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ አድርጓል፡፡ በተያያዘ ኮሚቴው ባለፉት አራት ዓመታት ከ272 ሺ ብር በላይ ወጭ በማድረግ    የስፖርት ቁሳቁስ ግዥ የፈፀመ ሲሆን፤  ለአገር አቀፍ የስፖርት ማኀበራት፣ ለክልሎች፣ ለከተማ አስተዳደሮች እና ለስፖርት ተቋማት ከ14.7 ሚሊዮን ብር በላይ  በድጋፍ ማበርከቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡  ይህ የስፖርት አድማስ ልዩ ሪፖርት በ42ኛው የኦሎምፒክ ኮሚቴ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤና የስልጣን ዘመኑ የሚያበቃውን የስራ አስፈፃሚ ቦርድ ያለፉት አራት አመታት እንቅስቃሴዎች ይዳስሳል፡፡
በኦሎምፒክ እንቅስቃሴ 1 ሚሊዮን ህዝብ ተሳትፏል
የኦሊምፒክ  ፍልስፍና እና እንቅስቃሴ በአገር አቀፍ ደረጃ በተፈለገው ለማስፋፋት በኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮሩ መጽሔቶች፣ ዶክመንተሪ ፊልሞች እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ብሮሹሮችን ተዘጋጅተው በመላው አገሪቱ ተሰራጭተዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ምስረታ ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ የሚከበረውን ‹‹የኦሊምፒክ ቀን›› በዓላት በኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞች ሲካሄድ ከ500ሺ በላይ የህብረሰተብ ክፍል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡  በሌላ በኩል ‹‹ስፖርት ለሁሉም›› በሚል መርህ ሕብረተሰቡ በሚሰራበት፣ በሚኖርበትና በሚማርበት አካባቢ የስፖርት ፌስቲቫል እና ሲምፖዚየሞችንም የተካሄዱ ሲሆን፤ ባህርዳር፤ ድሬዳዋ፤ ሐረር፤ መቀሌ፤ ደብረብርሃን፤ አምቦ ሚኤሶ፤ አዳማ እና ቢሸፍቱ አስተናጋጆቹ ከተሞች ነበሩ፡፡  ከክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ጋር በመነጋገር ደግሞ ‹‹የስፖርት ለሰላም›› ሳምንት በአራት የክልል ከተሞች ማለትም በአምቦ፣ በደብረ-ብርሃን፣ በመቀሌና በሀዋሳ ማረሚያ ቤቶች ተዘጋጅተዋል፡፡ የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች፣ የመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ጨዋታዎች፣ የታዳጊ ወጣቶች ውድድሮችም የኦሎምፒክ እንቅስቃሴውን ለማስፋፋት የተሰራባቸው መድረኮች ሲሆኑ፤ በኦሊምፕአፍሪካ ቢሾፍቱ ማዕከል፣በትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድሮች እና በስፖርት ጋዜጠኞች ስልጠና እና የፓናል ውይይቶች በተያያዘም ሌሎች ስድስት መድረኮችም ተካሂደዋል፡፡ በኦሊምፒክ፣ ኦሊምፒዝም ፍልሰፍና፣ በኦሊምፒክ ሎጎ ጥበቃ፣ በስፖርትና አካባቢ ጥበቃ እንዲሁም  በኤች.አይ.ቪ ላይ ያተኮሩ ርዕሰ ጉዳዮች የተነሱባቸው  ሲሆን ለ235  ሺህ የህብረተሰብ ክፍል ግንዛቤ ተፈጥሮባቸዋል። በአጠቃላይ ባለፉት አራት ዓመታት የኦሎምፒክ እንቅስቃሴን በ10 የተለያዩ ከተሞች በተለያዩ መርሆች በማካሄድ ከ1 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን ለማሳተፍ ተችሏል፡፡
የቤተመፅሃፍት እና የኦሎምፒክ ሙዚዬሙ አገልግሎት ተጠናክሯል
የኦሎምፒክ ኮሚቴው የሙዚየም አደረጃጀት እና የቤተመጻህፍት አገልግሎት አሠጣጥም ተሻሽለዋል። በጽ/ቤቱ የሚገኘው ቤተመጻህፍት አዳዲስ መፃሃፍት እና ኢ-ቡክስ በማካተት በአዲስ መልክ እየተደራጀ ነው። ስለሆነም 3500 መፅሃፍት ፤ ልዩ ልዩ ፅሁፎችና  ሰነዶች የሚገኙበት  ቤተመፅሃፍቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን እና ተማሪዎች ለሚያደርጓቸው የተለያዩ ጥናቶች እና ምርምሮች የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ጨምሯል፡፡ በሌላ በኩል የኦሊምፒክ ሙዚየሙን ክፍት አድርጎ በመንቀሳቀስ ኮሚቴው እየሰራ ነበር፡፡ በተለይ የተለያዩ ኩነቶች በሚካሄዱባቸው አጋጣሚዎች ተዘዋዋሪ ኤግዢቢሽኖች በማቅረብ መስራቱ የሚጠቀስ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ሙዚዬም ውስጥ ከ96 በላይ መጎብኘት ያለባቸው የተለያዩ ታሪካዊ ስብስቦች የሚገኙ ሲሆን፤ የበለጠ ለማደራጀትና ታሪካዊ መረጃዎችን አሰባስቦ ወደ የላቀ አገልግሎት እንዲሸጋገርም በየአቅጣጫው ጥረቶች ተጀምረዋል፡፡
ስልጠናዎች በብዛት ተዘጋጅተዋል
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የባለድርሻ አካላቱን አቅም ለመገንባት ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን ባለፉት አራት አመታት ለባለድርሻ አካላቱ በማመቻቸት ሰርቷል፡፡ አትሌቶች፣ የሚዲያ ተቋማት ባለሙያዎች እና ኦሊምፒዝምን ወደ ህብረተሰቡ ለማስረፅ ቀዳሚ ሚና ያላቸው የስፖርት ባለሙያዎች፣ የስፖርት አመራሮች፣ ስፖርተኞች፣ ሀኪሞች የተሳተፉባቸው ናቸው፡፡   በስፖርት ህክምና ማዕቀፍ 65 የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች እንዲሁም ከ5 የተለያዩ ስፖርቶች ለተውጣጡ 144 አሰልጣኞች የቴክኒክ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡315 የስፖርት አመራሮች እና 28 አገር አቀፍ ማህበራት የስፖርት አስተዳደር ስልጠናዎችን የወሰዱ ሲሆን ለ135 የሚዲያ ባለሙያዎች የሁለት ዙር ስልጠናዎችም ተዘጋጅተው ነበር፡፡ በተጨማሪም የኦሎምፒክ ዝግጅት ነፃ እድል ለ10 አትሌቶች በመስጠት የተሰራ ሲሆን እጩ ኦሎምፒያኖቹ  ስልጠናቸውን ያለምንም የገንዘብ፣ የትራንስፖርት እና የህክምና ወጪ ለ2 ዓመታት ዝግጅት አድርገው ከመካከላቸው 5 አትሌቶች ሚኒማ በማሟላት የኦሎምፒክ ተሳትፏቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በአራት አገር አቀፍ ጨዋታዎች 6.1 ሚሊዮን ስፖርተኞችና ህዝብ ተሳትፈዋል፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከፌዴራል ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከአገር አቀፍ የስፖርት ማኀበራት ጋር በመተባበር አራት ሀገር አቀፍ ጨዋታዎችን አካሂዷል፡፡ የመላ ኢትዮጵያ እና የመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ጨዋታዎች ናቸው፡፡ አራቱን የመላ ኢትዮጵያ እና የመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ጨዋታዎች ለማዘጋጀት በድምሩ ከ3.6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ያደረገው ኮሚቴው ከ6.1 ሚሊዮን በላይ ስፖርተኞች እና ኢትዮጵያውያን ሊያሳትፍ ችሏል፡፡ በ4ኛውና 5ኛው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች በኦሎምፒክ እና የፓራሊምፒክ ስፖርቶች በውጤት የአማራ ክልል የበላይነት የታየ ሲሆን በፈርቀዳጅነት የተጀመሩት 1ኛው እና 2ኛው የመላው የኢትዮጵያ ሴቶች ጨዋታዎች የሴቶች ሁለንተናዊ የስፖርት ተሳትፎ የተነቃቃባቸው ነበሩ፡፡
በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባለፉት አራት አመታት በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የውድድር መድረኮች ንቁ ተሳትፎዎችን አድርጓል፡፡ በዚህ መሰረት ባለፉት አራት አመታት ኢትዮጵያ በቦትስዋና፤ ጋብሮኒ 2ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሊምፒክ፣ በኮንጎ ብራዛቪል 11ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ፣ በቻይና ናይንጂንግ  2ኛው የዓለም ወጣቶች ኦሊምፒክ ጌምስ እና የሪዮ 2016 ኦሊምፒክ ጌምስ ላይ ተሳትፋለች፡፡ በቦትስዋና ጋብሮኒ በተዘጋጀው 2ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጌምስ ኢትዮጵያ በ6 የስፖርት አይነቶች በነበራት ተሳትፎ 14 የወርቅ፣ 6 የብር፣ 7 የነሐስ በድምሩ 27 ሜዳሊያዎች ተሰብስበዋል፡፡ ይህም ከአፍሪካ በአትሌቲክስ እና በወርልድ ቴኳንዶ አንደኛ ደረጃን በአጠቃላይ ደግሞ 5ኛ ደረጃ የተመዘገበበት ሲሆን 14 ሜዳሊያዎችን ለማግኘት ታስቦ ከዕቅድ በላይ 27 ሜዳሊያዎች ማስመዝገብ መቻሉም እንደልዩ ስኬት የሚጠቀስ ነው፡፡ በተለይ በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት 5 ወርቅ ሜዳሊያዎችን በ2ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጌምስ ማስመዝገብ መቻሉ ኢትዮጵያ በተለያዩ የስፖርት አይነቶችም በትኩረት ከሰራች ውጤታማ እንደምትሆን ተስፋ የሚፈጥር ሆኗል፡፡  በኮንጎ ብራዛቪል ከተማ በተካሄደውም 11ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በ11 የስፖርት አይነቶች በነበራት ተሳትፎ በአትሌቲክስ ስፖርት 6 የወርቅ፣ 5 የብር፣ 6 የነሐስ፣ በወርልድ ቴኳንዶ 1 የወርቅ፣ በፓራሊምፒክ 2 የነሐስ፣ በብስክሌት 1 የነሐስ፣ በቦክስ 3 የነሐስ በአጠቃላይ 24 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች ፡፡በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ በወርልድ ቴኮንዶ እና በብስክሌት ስፖርቶች ሜዳሊያዎች በዚሁ አህጉራዊ የውድድር መድረክ መገኘቱ ፈርቀዳጅ ታሪክ ነው ፡፡ በ2014 በቻይና ሀገር ናይንጂንግ ከተማ በተካሄደው 2ኛው የዓለም ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ኢትዮጵያ በነበራት ተሳትፎ በአትሌቲክስ ስፖርት 3 የወርቅ፣ 3 የብር እና 2 የነሐስ ሜዳሊያዎች በድምሩ 8 ሜዳሊያዎች በማግኘት ከአለም 16ኛ ከአፍሪካ 1ኛ ደረጃን በማግኘትም ተሳክቶላታል፡፡
በ31ኛው ኦሎምፒያድ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በ3 የስፖርት አይነቶች 35 ኦሎምፒያኖችን ተሳትፈዋል። 1 የወርቅ፤ 2 የብር እንዲሁም 5 የነሐስ ሜዳልያዎች ተገኝተዋል፡፡ የሜዳልያ ስብስቡ  ከ207 አገራት 44ኛ ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን ከአፍሪካ በ3ኛ ደረጃ  ነው፡፡  የሜዳልያ ውጤቶቹም በአልማዝ አያና በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ፤    በፈይሳ ሌሊሳ በማራቶን የብር ሜዳልያ፤  በገንዘቤ ዲባባ በ1500 ሜትር የብር ሜዳልያ፤ በጥሩነሽ ዲባባ    በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ፤    በአልማዝ አያና በ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ፤  በማሬ ዲባባበማራቶን የነሐስ ሜዳልያ፤  በሃጎስ ገብረህይወት በ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ፤  እንዲሁም በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ ፤ በታምራት ቶላ የተመዘገቡት ናቸው።  ከሜዳልያ ውጭ ከ4 እስከ 8ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች በሚሰጠው የኦሎምፒክ ዲፕሎማ 6 ኦሎምፒያኖች ተሸላሚ ናቸው፡፡ በወንዶች 10ሺ ሜትር በ4ኛ ደረጃ ይገረም ደመላሽ፤ በሴቶች 1500 ሜትር  በ8ኛ ደረጃ ዳዊት ስዩም፤ በሴቶች 5000 ሜትር በ5ኛ ደረጃ ሰንበሬ ተፈሪ፤ በሴቶች10ሺ ሜትር  በ8ኛ ደረጃ ገለቴ ቡርቃ፤ በሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል  በ5ኛ ደረጃ ሶፍያ አሰፋ እንዲሁም በሴቶች ማራቶን  በ4ኛ ደረጃ ትርፌ ፀጋዬ ናቸው፡፡
በልማት ሥራዎች አበረታች ጅምሮች ቢኖሩም መጠናከር አለባቸው
ባለፉት አራት አመታት ጠቅላላ ጉባኤውና የስራ አስፈፃሚ ቦርዱ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ልዩ ትኩረት በመስጠት ስፖርቱን ሊለውጡና የተቋሙን ሁለንተናዊ አቅም ሊያጐለብቱ የሚችሉ የልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ አበረታች ጅምሮችን ማድረግ ችሏል፡፡ በተለይ በጅምር ላይ ያሉትንና እና የመንግስትን እና የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ከፍተኛ ዕገዛ የሚጠይቁት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የልማት ሥራዎች መካከል ዋናዎቹ የኦሊምፕአፍሪካ ቢሾፍቱ ማዕከል፣ የእምቧይ መስክ መዝናኛ ማዕከል እና የኦሊምፒክ አካዳሚ ናቸው፡፡
በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው የኦሊምፕአፍረካ ቢሾፍቱ ማዕከል ባለበት አንደኛ የግንባታ ደረጃ ለከተማው ማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ወጣቶች በትርፍ ጊዜያቸው ከአልባሌ ቦታ እራሳቸውን ጠብቀው ብሎም እአምሯቸውን እና አካላቸውን በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጎለብቱ የተቋቋመውን ማእከል የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያስተዳድረዋል፡፡  ከ12 የመጀመሪያ ት/ቤቶች ከተውጣጡ ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች በሆኑ ታዳጊ ወጣቶች መካከል በተካሄደ የፉት ቦል ኔት ማጣሪያ ጨዋታዎች በማዕከሉ የተወዳደሩ ሲሆን አስር ተማሪዎች በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ሱዳን-ካርቱም ላይ በተዘጋጀው የምስራቅ አፍረካ የፎት ቦል ኔት ውድድር በመሳተፍ ከምድቡ አንደኛ በመውጣት ለሀገራቸው ዋንጫ ይዘው ተመልሰዋል፡፡
የእምቧይ መስክ ስፖርት መዝናኛ ማዕከል ለመገንባት ጨረታ ወጥቶ  ግንባታ ለመጀመር የሚያስችል የዲዛይን ክለሳ ስራ ተጠናቅቆም ነበር፡፡ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ቦታውን ለተቋሜ ግንባታ ያስፈልግኛል በሚል ባነሳው ጥያቄ ችግር በመፈጠሩ የማዕከሉን ግንባታ ሊገፋበት አልተቻለም እንጅ፡፡ የእምቧይ መስክ ደረጃውን የጠበቀ ጅምናዚየም፣ ቦውሊንግ፣ ሬስቶራንት እና ሌሎች አገልግሎቶች የሚሰጥ ነው፡፡
የኦሊምፒክ አካዳሚ ግንባታ ለማካሄድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ 120 ሺ ካሬ ሜትር እንደሰጠው የሚታወቅ ሲሆን፤ በአካባቢው ለነበሩ የቦታው ተነሺዎች የካሳ ክፍያ ተፈፅሟል፡፡ የካሳ ክፍያውን ተከትሎ የኦሊምፒክ አካዳሚው በከፊል የአጥር ስራው ተጀምሯል፡፡  የኦሊምፒክ አካዳሚው ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሚፈጅ ውጪ በአስራ ሁለት ሺህ ካሬ ሜትር ላይ በአዲስ አበባ ከተማ (አቃቂ ለቡ) የሚገነባው እጅግ ዘመናዊ የስፖርት መሰረተ ልማት ነው። የአካዳሚው የዲዛይን እና ተያያዥ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመጪው ዓመት እንደሚጀመሩ ይጠበቃል፡፡ አካዳሚው እጅግ ዘመናዊ የእግር ኳስ፣ የሩጫ፣ የመረብ ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ፣ የቴኒስ እና የዋና መጫወቻ ሜዳዎች፣ ደረጃውን የጠበቀ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ላይብረሪ፣ ሬስቶራንት እና ሎሎች አገልግሎቶች ይኖሩታል፡፡


Read 1996 times