Wednesday, 04 April 2012 08:33

ደብረዘይትን በአፄ ዋሻ ማርያም ገዳም

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች በየዓመቱ ከሚሳተፉባቸው ሰባት አጿማት አንዱና ታላቁ የሆነው የአቢይ ፆም አጋማሽ ወይም አራተኛ ሳምንት መጠናቀቅን ምክንያት በማድረግ የደብረ ዘይት በዓል ባለፈው እሁድ ሲከበር፣ ምዕመናን ሳማ ሰንበትን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ገዳማት ተጉዘዋል፡፡ በበዓሉ ዋዜማ በባንዲራ አጊጠውና በተለያዩ ጥቅሶች አሸብርቀው የየነበሩ አውቶብሶችና ሚኒባሶች፤ የጉዞው ዕለት በየመናኸሪያው፣ በየቤተክርስቲያናት ደጅና በየመንደሩ ተደርድረው ነበር፡፡ እሁድ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም ማለዳ መርካቶ የሚገኘው የራጉኤል ቤተ ክርስቲያን በእነዚህ አውቶቢሶችና ሚኒባሶች ተከብቦ ነበር፡፡

ጠዋት 1 ሰዓት ላይ ከመርካቶ ተነስቶ፣ በፒያሳ በኩል አራት ኪሎን አቋርጦ፣ የኮተቤ መስመርን በመያዝ ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ በሚጓዘው አውቶቢስ ውስጥ፤ እኔና ለጉዞው የጋበዙኝን ባልና ሚስት ጨምሮ 50 ያህል ሰዎች ተሳፍረን ነበር፡፡

መድረሻችን በሰሜን ሸዋ ከደብረ ብርሃን ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ በሚገኘው ወግዳ ወረዳ ሲሆን፤ የአፄ ዋሻ ማርያም ገዳም በአካባቢው ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አንዱ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ገዳሙ በመኪና ያደረግነው ጉዞ የ3 ሰዓት ጊዜ ፈጅቶብናል፡፡ በዚህ ፅሁፌ በጉዞው ወቅትና በክብረ በዓሉ ላይ ያስገረሙኝንና ያስደመሙኝን አንዳንድ ጉዳዮች ለአንባቢያን ላስቃኝ እወዳለሁ፡፡

“ፆም ያለ ፀሎት የረሀብ አድማ ነው”

በሕብረት የሚደረጉ መንፈሳዊ ጉዞዎችን የሚያዘጋጁና የሚያስተባብሩ መንፈሳዊ ማህበራት፤ በጉዞው ወቅት ከሚያቀርቧቸው አገልግሎቶች አንዱ፣ ክብረ በዓሉን አስመልክቶ ትምህርት የሚሰጡ መምህራንን ማዘጋጀት ነው፡፡ በመዝሙር ደምቆ ሲጓዝ በነበረው አውቶብስ ውስጥ ትምህርት ያቀረቡት መምህር፤ ፆምና ፀሎትን አቀናጅቶ የመተግበርን ጠቀሜታ አመልክተው፤ ፆም በፀሎት ካልታገዘ ፋይዳው ዝቅ እንደሚል ሲገልፁ፤ “ፆም ያለ ፀሎት የረሃብ አድማ ነው” በማለት አስደምመውኛል፡፡

በፐርሺያ (ኢራን) የተጀመረው ቅጣት

የኩዳዴ ወይም የአቢይ ፆም የሚፆመው ኢየሱስ ክርስቶስ በምድረ በዳ ለ40 ቀናት በፆምና ፀሎት የቆየባቸውን ቀናት ለማስታወስና ስቅለቱንና ትንሳኤውን ለመዘከር መሆኑን ያመለከቱት መምህሩ፤ ለታሪካዊ ጉዳዮችም ትርጉምና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ኢየሱስ ለፀሎት አዘውትሮ ይጠቀምበት የነበረው “ደብረዘይት” የቦታ ሥም ሲሆን ትርጉሙም የወይራ ዛፍ የሚበዛበት ተራራማ ስፍራ እንደሆነ ተናግረዋል - መምህሩ፡፡ አይሁዳዊያን ኢየሱስን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት ያደረጉት ከሮማውያን በወረሱት ባህል መሠረት ነው ያሉት ትምህርት አቅራቢው፤ ሮማውያንም ሰውን በእንጨት ላይ ሰቅሎ እንዲሞት የማድረግን ባህል ከፐርሺያ ወይም አሁን ኢራን ተብላ ከምትጠራው አገር መውሰዳቸውን፤ ኢራናዊያንም ያንን ባህል ይከተሉ የነበረው ከጣኦት አምልኮ ጋር በተያያዘ እንደነበር አብራርተዋል፡፡

50 ሎሚ ለ50 ሰው ጌጡ

ደብረ ብርሃን ከተማ እንደደረስን 07 ጠለስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የነዳጅ ማደያ ወደ ግራ በመታጠፍ፣ ፒስታ መንገዱን ይዘን ለግማሽ ሰዓት ያህል ከተጓዝን በኋላ ቀድመውን ከተገኙ በርካታ አውቶብሶች ጋ ተገናኝተን ለእግር ጉዞ ተዘጋጀን፡፡ መኪኖቹ ከቆሙበት ስፍራ የአፄ ዋሻ ማርያም ገዳም እስካለበት ለመድረስ በእግር ከመጓዝ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም፡፡

በእግር ጉዞ መጀመሪያው ስፍራ ላይ በትናንሽ ከረጢቶች የተሞላ አሸዋ ተቀምጧል፡፡ ቋጠሮው በትንሹ 5 ኪሎ ይመዝናል፡፡ ተጓዡ አንዳንድ እስር እንዲይዝ የሚያስተባብሩ አሉ፡፡ የቻለ በግሉ ያልቻለ አንዱን ከረጢት በጋራ እየያዘ ጉዞው ተጀመረ፡፡ አሸዋው በገዳሙ ለሚሰራ ሕንፃ ግንባታ የሚውል ነው፡፡ የግንባታውን ቁሳቁስ ወደ ቦታው ለማድረስ የተዘየደው ብልሀት “50 ሎሚ ለ50 ሰው ጌጡ” የሚለውን ሀገራዊ ይትብሃል የሚያስታውስ ነበር፡፡

አወዳዳሪ ያጡ የተራራ ስፖርተኞች

ከአውቶብሶቹ መቆሚያ ወደ ገዳሙ በእግር የተጀመረው የጥቂት መቶ ሜትሮች ርቀት ጉዞ አልጋ ባልጋ አይነት ነበር ሊባል ይችላል፡፡ እንዲያውም “ይህ ጐዳና በግሬደር ታርሶ አሸዋ ቢበተንበት መኪኖቹን ወዲህ ማቅረብ ይቻላል” ያሉም ነበሩ፡፡ “ጉድና ጅራት …” እንዲሉ የሜዳውን ጉዞ ስናጠናቅቅ፣ ረጅም ቁልቁለት ያለው ተራራ ጫፍ ላይ መሆናችንን አጤንን፡፡

ወደ አፄ ዋሻ ማርያም ገዳም ቁልቁለቱን ስንወርድ ከቦታው ገደላማነትና አስፈሪነት የተነሳ በእንፉቅቅ ያልሄደ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ የሽማግሌዎቹንና የአሮጊቶቹን ብርታትና ጽናት ግን እንዴት መግለጽ እንደሚቻል አላውቅም፡፡ በከተሞች አጭር ርቀት እንኳን ያለ መኪና መጓዝ የማይሆንላቸው ወጣት ሴቶች፣ ፕሮፌሽናል የተራራ ስፖርተኞች መስለው ነበር፡፡ ምን ውስጥ የደበቁትን አቅምና ብቃት እንዳወጡት ፈጣሪ ይወቀው!!

ይህንን መገረሜን ያዩ “አባይን ያላየ…” ብለው ተርተውብኛል፡፡ የሚኬደው ጉዞ ርቀት፣ የሚወረደው ቁልቁለት፣ የሚወጣው ዳገት መርዘምና ማጠር የቱንም ያህል ቢሆን በትንሽ ገጠመኜ ያየሁት እውነታ ግን በውስጤ ጥያቄ ፈጥሮብኛል፡፡ ሌላው ቢቀር ቁልቁለቱ ከብዷቸው በእንፉቅቅ የሚጓዙ ሰዎች፣ ያለ ማንም አስገዳጅነት በፍላጐታቸው የያዙትን የከረጢት አሸዋ ግማሽ መንገድ ላይ ትተው ላለመሄድ ሲጥሩ ሲታይ ምን ስሜት እንደሚፈጥር አስቡት፡፡ ተራራ በመውጣትና በመውረድ ስፖርት የሚታወቁ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች ይህንን ቢያዩ እንደሚደነቁ እገምታለሁ፡፡ በንግሥ በዓሉ ዕለት እንደተገለፀው ለአፄ ዋሻ ማርያም ቤተክርስቲያን አዲስ ሕንፃ ለመሥራት፣ የመሠረት ድንጋዩ የተጣለው ጥር 21 ቀን 2002 ዓ.ም ነበር፡፡ ጣራ የማልበስና ጥቃቅን ሥራዎች ተጠናቀውለት አዲሱ የቤተክርስቲያን ሕንፃ የፊታችን ግንቦት ወር 2004 ዓ.ም ይመረቃል ተብሏል፡፡ በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ የደረሰውን አዲስ ሕንፃ፤ በከተሞችና በገጠር የሚኖረው ሕዝብ በትብብር ለውጤት በማብቃቱም ተመስግኖበታል፡፡

የገበሬው እንግዳ ተቀባይነት

አፄ ዋሻ ማርያም ገዳም በሚገኝበት አካባቢ፣ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ውጤት የሆነ የተቃጠለ የድንጋይ ክምችት በየመንገዱ ይታያል፡፡ በአካባቢው ተመሳሳይ ትናንሽ መንደሮች ተራርቀው ይታያሉ፡፡ በየቤቱ ደጃፍ ደርቆ የተከማቸ ኩበት በብዛት ተከምሮ ይታያል፡፡

በአፄ ዋሻ ማርያም ገዳም የንግሥ በዓል ላይ ታድመው የሚመለሱ ምእመናን፣ በገበሬዎች ደጅና ቤት ውስጥ እያረፉ ውሃ፣ ጠላ፣ ቆሎና ዳቦ ይስተናገዳሉ፡፡ በእንጨት ችግር ይሁን በሌላ ባላውቅም የአካባቢው ቤቶች በሙሉ በድንጋይ የተገነቡ ናቸው፡፡ እኛ እረፍት ባደረግንበት የገበሬ ቤት የከተማ ሰዎች፣ የገጠር ነዋሪዎች፣ ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የመጡ ተማሪዎች በጋራ ተቀምጠን በገበሬው እንግዳ ተቀባይ ተስተናግደናል፡፡

ለአንድ ፎቶ ጨረታ 10ሺህ ብር

የእኛን ጉዞ ያስተባበረው ማህበር ከተመሠረተ አምስት ዓመት ሆኖታል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ሕዝብን አስተባብረው በግሸን ማርያም አካባቢ የሚገኘውን የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሕንፃ በማሰራት እንዳስመረቁ ተነግሮናል፡፡

በመልስ ጉዞአችን ላይ ማህበሩ ያስመረቀውን የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የሚያሳይ ፎቶግራፍ ለጨረታ አቅርቦ ነበር - አውቶብስ ውስጥ፡፡ጨረታው “የመክፈቻ” እና “የመውሰጃ” በሚል ተከፍሎ የተካሄደ ሲሆን ለአንድ ሰዓት ያህል ጨረታው በተሟሟቀ ሁኔታ ከተከናወነ በኋላ ማህበሩ 10ሺህ ብር እንደሰበሰበ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

 

Read 11740 times Last modified on Friday, 06 April 2012 11:08