Sunday, 02 April 2017 00:00

እንግሊዛዊው ድመት

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(11 votes)

ሶስተኛዬን ደብል ጂን አጋምሼዋለሁ፡፡ … በድሉ ከተቀመጠበት ተነስቶ ከጎኔ ተቀመጠ - የጎን ውጋት፡፡ ቸስ ብሏል፡፡ ሞቅ ሲለው ታሪክ ማውራት ይወዳል፡፡ የአያቱን ታሪክ፡፡ የአያቱን የሆዳምነት ታሪክ፡፡ በማንኛውም ድግስ ቦታ የአምስት ሰው  ኮታ ነበር የሚቀርብላቸው፡፡ የበሬ ታፋ፣ ሽንጥ፣ …….. ሲጥ! ያደርጉ ነበር… ነፍሳቸውን ይማረውና፡፡ ይህን ዕምብርት የለሽነታቸውን የዕድሜ ባለፀጎችም ይመሰክራሉ፡፡ በዚህም በድሉ በኩራት ይጀነናል፡፡ የአያቱ ሆዳምነት የኩራቱ ምንጭ መሆኑ ይደንቃል። “አያቴ በቃኝን የማያውቁ ከርሳም ነበሩ›› ብሎ ነገር ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው…….
“ሥራ እንዴት ነው?” አልኩት ……
“ሥራ ፈት ነኝ፤ የሚመጥነኝን ሥራ ማግኘት አልቻልኩም ….”
“የሚመጥነኝን ስትል ለየትኛው ደረጃህ ….. ዲግሪ አለህ …. ወይንም ማስተርስ …… ፒኤችዲህን የት ይሆን የሰራኸው?” በድሉ መልስ አልሰጠኝም፡፡ በጥላቻ አፈጠጠብኝ፡፡ ቡዳ ቢሆን መሬት ላይ ወድቄ በተንደፋደፍኩ …..
“….. ከትንሽ ሥራ ብትጀምር …. አንተ ግን የአንድ ትልቅ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የመሆን ህልም….” አላስጨረሰኝም ….” እየወቀስከኝ እኮ ነው፤ እንዲያው በደረቁ ቢራ ጋብዘኝ፡፡ ….”
‘እኔ በአልኮል እየተቃጠልኩ እሱን ቢራ ልጋብዝ ወገኛ!’
ሒሳብ ዘጋሁ - በጊዜ ወደ ሰፈሬ አቀናሁ፡፡
ወደ ቤቴ መግቢያ ቅያስ ላይ ባለቤቴን አየኋት - ከወንድ ጋር፡፡ እሷ ታወራለች፡፡ ሰውዬው አንገቱን እንደ ከዘራ ቆልምሞ ያደምጣል፡፡ ባለቤቴን በማንም አልጠረጥራትም፡፡ እኔን የሚያውቀኝ ሰው መንገድ ላይ ካገኘት አስቁማ የማታወራው ነገር የለም፡፡
“ … ትዳሬን ብዬ ከሰውነት ጎዳና ወጥቼ… ቤቴን ባልኩ ተንቄ ማቅቄ …. እሱ እንደሆነ ….” እያለች እንባዋን ስታፈስ ያየ፣ እኔን የማይረግም ፍጡር የለም። የእንባ ችግር የለባትም፡፡ በማንኛውም ጊዜ እንደ ዶፍ ዝናብ ታወርደዋለች፡፡ ወዳ አይደለም! ከውቃቤ ጋር የተያያዘ ችግር አለባት … የቤት ጣጣ የምንለው፡፡ በዚህ ላይ ጠንቋይ ስትወድ ለጉድ ነው፡፡ በሆነ ባልሆነው ወደ ጠንቋይ መመላለስ ታዘወትራለች፡፡ ከቤተ-ጥንቆላ የተዋወቀቻቸውን አስጠንቋይ ቢጤዎቿን ወደ ቤት ይዛ ስትመጣ አለማፈሯ ይገርመኛል፡፡ …..
ማለዳ ከእንቅልፌ ቀስቅሳኝ፤ “ቁርስ ደርሷል … ቡናም ወርዷል እንግዶች አሉብኝ”
“እንግዶች” የተባሉትን ሁለት ሴቶች እጅ ነስቼ ተቀመጥኩ፡፡ የቤተ ጥንቆላ ምዕመን ጓደኞቿ ናቸው። …..አንደኛዋ 69 ዓመት የሚገመቱ አሮጊት፣ ሌላኛዋ የ19 ዓመት ኮረዳ፡፡ ….
…. ዶኬ ሽሮው አልዋጥልህ ብሎኝ ተውኩት። ባለቤቴ ትሪውን እያነሳች… ‹‹አንተ መናጢ ድሃ ውቃቤህ የቱጃር” አሮጊቷ ከት! ብለው ሳቁ፡፡ ጥርሳቸው ከጥግ እስከ ጥግ የተሸራረፈ ነው፡፡ አሮጊቷ እንጀራ ተመጋቢ ሳይሆኑ ብርጭቆ ቆርጣሚ ይሆኑ እንዴ? ያስብላል፡፡ ልጅቷ አሮጊቷን ተከትላ ፈገግ ለማለት ሞከረች፡፡ ፊቷን ልብ ብዬ አየሁት፡፡ አምላክ ጥቁር ሬንጅ አድቦልቡሎ የፈጠራት ይመስል እንደ ከሰል የጠቆረች፡፡ …..
ቡና ተጠጥቶ ከተመ፡፡ አሮጊቷ ግን ሲኒ ውስጥ በቀረረው የቡና አተላ ላይ አፍጥጠዋል፡፡ ቀና ብለው እኔን እያዩ፤ “…. በቅርቡ ጥቁር እንግዳ ወደ ቤታችሁ ይገባል” ሲሉ ጠነቆሉ ወይንም አሟረቱ፡፡ ‘ጥቁር እንግዳ ምን ይሆን? …ሞት ይሆን እንዴ?’
….እኔን እያዩ ነው ያሟረቱት፡፡ መልዕክቱ ለኔ ነው። ናላዬ ዞረ፡፡ ማንም ሰብአዊ ፍጡር የህልፈቱን ዕለት  ማወቅ የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ ዕድሜ ለጣጠኛዋ ባለቤቴ! እነሆ የህልፈቴን ዕለት ቀን በቁሜ ሰማሁት .. በቅርብ ቀን! በቅርብ ቀን!....... በማግስቱ እንደ በረዶ የነጣ ባለ ወርቃማ ጭራ ድመት ወደ ቤታችን ሰተት ብሎ ገባ፡፡
ባለቤቴ፣ የአሮጊቷ ጥንቆላ ሳይውል ሳያድር በስኬት በመጠናቀቁ ተደሰተች፡፡ “መላዕክት የመሰለ ድመት” ወደ ቤታችን ስለመግባቱም ደውላ አበሰረቻቸው፤ ለአሮጊቷ፡፡
የድመቱ ወደ ቤታችን መግባት በህይወታች ላይ ምን ዓይነት ለውጥ እንደሚያመጣ ሊገባኝ አልቻለም። የተረፈኝ ነገር ቢኖር በሳምንት ሶስቴ ሳንባ እየገዛሁ ድመቱን መቀለብ ነው፡፡ አይጥ አድኖ መብላት የሚባል ነገር ያሰበውም አይመስልም፡፡ ምናልባትም በህይወት ዘመኑ ድመት አይጥን አድኖ ሲበላ አይቶ አያውቅ ይሆናል ….
ወራት እንደ ዘበት ነጎዱ፡፡ ለድመቱ በሣምንት አንዴ እንኳን ሣንባ የማልገዛበት ጊዜ ነበር፡፡ ሁኔታው ያላማረው ድመት ቤቱን ለቆ ወጣ፡፡ ወደ ጎረቤታችን አቶ ደምሴ ቤት ገባ፡፡ አቶ ደምሴ ሞልቶ የተረፋቸው ነጋዴ ናቸው፡፡ ቤታቸው ድግስ አይጠፋም፤ ዘወትር ጮማ የሚቆረጥበት ቤት፡፡ የድመቱ ብልጣብልጥ ምርጫ የሚደነቅ ነው፡፡ …..
አብይ ፆም ገባ፡፡ አቶ ደምሴ አጥባቂ ኦርቶዶክስ በመሆናቸው፣ አንዲትም ቅንጣቢ ሥጋ ቤታቸው ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡ እንኳን ለወራት ለአንዲትም ቀን ሆዱ እንዲጎድልበት የማይፈልገው ድመት መኮብለሉን… ከቤት እንደወጣ መቅረቱን አቶ ደምሴ ነገሩኝ፡፡
በቅርቡ ከውጭ ከመጣ ሰው መልዕክት ለመቀበል ወደ አንድ ስመ-ጥር ሆቴል ጎራ ብዬ ነበር። በምግብ አዳራሹ በኩል ሳልፍ፣ ያንን ጉደኛ ድመት አየሁት፡፡ ዓይኔን ማመን አልቻልኩም፡፡ እንደ ወተት የነጣው ፀጉሩ፣ ወርቃማ ጭራው አላሳሳተኝም፡፡ አንድ ተመጋቢ ከሚበላው የዶሮ አሮስቶ በቢላ ቆረጥ እያደረገ ይወረውርለታል፡፡ አጅሬም! በአየር ላይ ላፍ! እያደረገ ይሰለቅጣል፡፡ እንዴት እዚህ ባለ አራት ኮከብ ኢንተርናሽናል ሆቴል ሊገባ ቻለ?.... የሆቴሉ ማናጀር በአጠገቤ ሲያልፍ… ‹‹ያ! ድመት!…” የምለው ጠፍቶብኝ ዝም አልኩ… ማናጀሩ ከአፌ ቀበል አድርጎ ከወር በፊት አንድ እንግሊዛዊ እንግዳ ጥሎብን ሄዶ ነው….”
“ድመቱን እንግሊዛዊው ጥሎት ስለመሄዱ እንዴት እርግጠኛ ሆንክ?”
“የፅዳት ሰራተኛዋ ድመቱን በተጋጋሚ ከእንግሊዛዊው ጋር ስለማየቷ የአይን እማኝነቷን….”
“….የፈጠራ ታሪክ ነው፤ ድመቱ የኔ ንብረት ነው…” ማናጀሩ በፍጹም አላመነኝም… ‹‹ቶሚ! ቶሚ!” ብሎ ድመቱን ጠራው፡፡ ድመቱ ቀና ብሎ ወደ ተጠራበት ሲያማትር እኔን አየኝ፡፡ ከመቅፅበትም አውሬ እንዳየ በርግጎ ፈትለክ! አለ፡፡ ማናጀሩ በግርምት አንገቱን እየነቀነቀ “… አንተን ባየበት ቅፅበት ዱብዕዳ እንደወረደበት ….” ብሎ እያጉተመተመ በቆምኩበት ጥሎኝ ሄደ፡፡…….
ከሆቴሉ ወጥቼ ታክሲ ያዝኩ፡፡ ‘…. ድመቱ እንዴት እዚህ ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ሊገባ ቻለ? ከሰፈራችን እስከ ሆቴሉ ቢያንስ የአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት አለ። በዚህ ላይ መንገዱ በትራፊክ የተጨናነቀ ነው፡፡ …. እንኳን ባለ አራት እግሩ ድመት፣ በሁለት እግራቸው ቆመው የሚሄዱት የሰው ፍጡራን የትራፊክ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ይህ ጉደኛ ድመት ግን አደገኞቹን መንገዶች አቆራርጦ፣ ባለ አራት ኮከብ ኢንተርናሽናል ሆቴል ለመግባት በቅቷል፡፡ ቶሚ የሚል ስምና የእንግሊዛዊነት ዜግነት አግኝቷል፡፡’
….. ከሣምንት በኋላ የድመቱን መፃኤ ዕድል ለማወቅ ወደ ሆቴሉ ጎራ አልኩ፡፡ … ወደ ምግብ አዳራሹ  ገብቼ ተሰየምኩ፡፡ ዓይኖቼን በሰፊው አዳራሽ ላይ፣ ታች አማተርኩ፡፡ የድመቱ ደብዛ የለም። …. የፆም ምግብ ለማዘዝ ዋጋውን ሜኑ ላይ አየሁ፡፡ ወዳጄ! ዋጋው ቅስም ይሰብራል፡፡
የሆቴሉ ማናጀር ወደ ተቀመጥኩበት መጣ፡፡ “ድመቱ ..” ብዬ ሳልጨርስ ከአፌ ላይ “ዕድለኛ ድመት ነው!... ለጉብኝት የመጣ እንግሊዛዊ ቱሪስት የድመቱን ታሪክ ሰምቶ በጣም አዘነ…”
ግራ ገብቶኝ፤ “ምኑ ነው ያሳዘነው?....”
“…..እንዴት አንድ የተከበረ ጨዋ እንግሊዛዊ፤ ድመቱን በባዕድ ምድር ጥሎ ይሄዳል በሚል ነው ያዘነው፡፡ ድመቱንም ለሀገሩ እንግሊዝ ምድር ሊያበቃው ቃል-ገብቷል….”
“…. ለድመቱ የእንግሊዛዊነት የፈጠራ ታፔላ የለጠፍከውን አልቀበለውም… የኔ ንብረት ነው። እንዳየኝ ደንግጦ እንደተፈተለከ በዓይንህ ያየኸው ነው…”
“…አዎን አይቻለሁ!! ሊደርስበት የሚችለውን በደመነፍስ ገብቶት እግሬ አውጪኝ ብሏል…”
“ምንድን ነው የሚደርስበት …?” ግርም ብሎኝ ጠየቅሁት፡፡
“… ወደ ቀድሞ የመናጢ ድህነት ህይወቱ ልትመልሰው የመጣህ መስሎት ነዋ የሸሸህ….” ቀጠል አድርጎም “… ቢገባህ ደግሞ ድመቱ የሸሸው ከአንተ ሳይሆን ከድህነቱ ነው…›› እንጂ…..” በማለት ላይ ሳለ፣ አንድ ፈረንጅ ከዚያ ጉደኛ ድመት ጋር በአጠገባችን እልፍ! አለ፡፡
ድመቱ ዘለል! ዘለል! እያለ ከሰውዬው ጋር እየተላፋ በኋላ በር ወጡ፡፡ ድመት ከመቼ ወዲህ ነው እንደ ውሻ እየዘለለ ከጌታው ጋር የሚላፋው… ጉድ እኮ ነው ሰዎች…. ማናጀሩ ረጋ ብሎ “ድመቱን ወደ እንግሊዝ እወስደዋለሁ ያለው ሰውዬ ነው …”
“ሰውዬውን ማነጋገር አለብኝ፤ ሀቁን ማወቅ አለበት፡፡”
“የምን ሀቅ” ሲል አምባረቀብኝ…… የነገር መአቱን እንደ ዶፍ አወረደብኝ….
…‹‹የአንድ ምስኪን ድመት ወደ እንግሊዝ መግባት እንዲህ ያንገበግባል እንዴ!.. ቅናት እኮ ነው! የሀበሻ ምቀኝነት!… እንኳን ይሄን የመሰለ እንደ በረዶ የነጣ አውሮፓዊ ድመት ሊኖርህ ተራ የቀበሌ መታወቂያ …”
የሆቴሉ ጋርድ እንደ ሰው በምድር ተራምዶ ይምጣ እንደ ሸረሪት ከጣራ ይውረድ…. ፊት ለፊቴ ቆሟል፡፡ ወጠምሻ የሰማይ ስባሪ ጠረንገሎ! እንግሊዛዊ የተባለው ሰውዬ ወደ ባር ሲገባ አየሁት። ወደ ሰውየው ራመድ ስል ማናጀሩ “ተመለስ!” ሲል ጮኸብኝ … ጆሮ ዳባ ልበስ ብዬ ወደፊት ከመራመዴ ዱብዕዳ ወረደብኝ፡፡ ጋርዱ አንገቴን ቆልምሞ ጫማ ጥፊ አሳረፈብኝ፡፡ ከመቅፅበትም ከሥር በጠረባ ሲለኝ ወለሉ ላይ ተዘረጋሁ… ከአፍንጫዬ የወጣው ነሥር… ቀይ ደመና ተንጠልጥሎ ያየሁ መሰለኝ፡፡…..  




Read 4273 times