Monday, 03 April 2017 00:00

የቴአትር ባለሙያዎችን ያከራከሩ ጥናታዊ ፅሁፎች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

•    የቴአትር ት/ቤቶች የሚያስተምሩት በተለያየ ሥርዓተ ትምህርት ነው
•    ት/ቤቶቹ ከፍተኛ የመሰረተ-ልማትና የቁስ ችግር አለባቸው ተብሏል
•    ባንኮች ለኪነ ጥበብ ሥራዎች  ብድር እንዲሰጡ ተጠይቋል

ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የተቋቋመው የዛሬ ስድስት ዓመት ነው፡፡ ከወልቂጤ ከተማ በ13 ኪሜ ርቀት ላይ የተመሰረተው ዩኒቨርሲቲው፤ እጅግ በጣም ሰፊ በሆነና ለጥ ባለ ሜዳ ላይ የተቋቋመ ሲሆን ከአንዱ አጥር ጫፍ ተነስቶ ሌላው ጫፍ ለመድረስ አራት ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠይቃል፡፡ ዩኒቨርስቲው በመደበኛ፣ በማታና በርቀትና ተከታታይ መርሀ ግብሩ የቢኤ ዲግሪና የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቶችን እየሰጠ ሲሆን ከበርካታ ዲፓርትመንቶች ውስጥ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል አንዱ ነው፡፡
የዩኒቨርስቲው የቴአትር ትምህርት ክፍል ከሁለት ዓመት በፊት 53ኛው የአለም የቴአትር ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች ያከበረ ሲሆን ዘንድሮም 55ኛው የቴአትር ቀን ‹‹እንተዋወቅ›› በሚል መርህ ከመጋቢት 16-18 2009 ዓ.ም በድምቀት አክብሯል፡፡ በዚህ የቴአትር ቀን በዓል ላይ ከቀረቡ የተለያዩ ዝግጅቶች መካከል የቴአትር ት/ቤት ያላቸው ስምንት ዩኒቨርስቲዎች ያቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፎች ጉልህ ሥፍራ ይወስዳሉ፡፡
የመጀመሪያው ጥናታዊ ፅሁፍ አቅራቢ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትር ክበባት ት/ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ ሲሆኑ፤ ‹‹የመንግስት ድጋፍ ለባህልና ኢንዱስትሪ ልማት›› የተሰኘ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ ጥናታዊ ፅሁፉ ቴአትር ለአንድ አገር ያለውን ሁለንተናዊ ጥቅም የሚዳስስ ሲሆን ይህን ጥቅም የተረዱ እንደነ አሜሪካ፣ ካናዳና ቻይና ያሉ ሀገራት ለዘርፉ ምን አይነት ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ የሚያሳይ ነው፡፡ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ በምሳሌነት የጠቀሷት አሜሪካ ‹‹National Endowment for Arts›› የተሰኘ ቢሮ በማቋቋም፣ በዚህ ቢሮ ስር ባለው የገንዘብ ቋት፣ ለባህልና ለጥበብ ድጋፍ እንደምታደርግና በዓመት እስከ መቶ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምትሰጥ ገልፀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የጥበቡ ባለሙያዎችን አንድ የሚያደርግ፣ ስለ ሙያቸው ማደግና መከበር የሚወያዩበት የስነ-ጥበባት ብሄራዊ መማክርት ማቋቋሟንም ተባባሪ ፕሮፌሰሩ በጥናታቸው ጠቅሰዋል፡፡  
በተመሳሳይ ሁኔታ ካናዳም እንዲሁ በኢንዶውመንቷ በኩል ለስነ ጥበቡ 405 ሚሊዮን ዶላር በዓመት ድጋፍ እንደምትሰጥና የኪነ-ጥበብ ብሄራዊ መማክርት እንዳቋቋመች፣በተጨማሪም ‹‹ካናዳ ፊቸር ፊልም›› የሚል ተቋም ተመስርቶ፣በዓመት 10 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ የፊልምና የህትመት ኢንዱስትሪው እንዲጠናከር እንደምታደርግ ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል፡፡ በቻይናና በሌሎች አገራትም ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንዳሉ የገለጹት ጥናት አቅራቢው፤ በአገራችን ስነ - ጥበብ እንዲያድግ ከተፈለገ ብሄራዊ የስነ - ጥበባት ገንዘብ ድጋፍ ድርጅትና የስነ-ጥበባት መማክርት መቋቋም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ አትራፊ ያልሆኑ ለኪነ - ጥበብ ገንዘብ የሚለግሱ ተቋማት ላይ መንግስት ቀረጥ እንዲቀንስም ጠይቀዋል፡፡
ጥናት አቅራቢው አክለውም፤ባንኮች ለስነ ጥበብ ስራ ብድር እንዲሰጡ፣ በደርግ ጊዜ የነበረውና የፈረሰው ፊልም ኮርፖሬሽን ተመልሶ እንዲቋቋምና ከውጭ የሚገቡ የባህልና የስነ-ጥበብ እቃዎች ቀረጥ እንዲነሳ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ባህል ቢሮ የተደነገገው “ኪነ ጥበብ ለመሰረታዊ ለውጥ” የተሰኘው ማኑዋል በድጋሚ እንዲጤን፤ በአውሮፓ በአሜሪካና በእስያ ለኪነ - ጥበብ የተሰጠው እድል ለኢትዮጵያም እንዲሰጥ በመጠየቅ ጥናታቸውን አጠቃለዋል፡፡
በዚህ ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ በተደረገው ውይይት አርቲስት ኪሮስ ገ/ሥላሴ ባነሳው ሀሳብ፤ "የጋሽ አቦነህ ጥናት በጣም አማላይ ቢሆንም በእኔና በእርሱ እድሜ የምናየው አይደለም” ብሏል፡፡ አርቲስት ኪሮስ፤ባህልን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የትም የሚደርስ ልማትም ሆነ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳይ እንደሌለ ገልጾ፣ ባህልና ስነ - ጥበብ በአሜሪካ 4ኛ አጀንዳ ሆኖ መካተቱን ጠቁሟል፡፡ ‹‹በእኛ አገር ግን የባህልና የስነ - ጥበብ ዘርፍ  ድንገተኛ ደራሽ ጎርፍ እየሆነ በዘርፉ የተሾመው ሰው በደንብ ሲገባው እየተነሳ ወይ ግብርና አሊያም ንግድ ሚኒስቴር ተወስዶ እየተመደበ፣ እንደገና ያልሰማው እየመጣ እኛም ሰለቸን›› ሲል በምሬት ተናግሯል- አርቲስቱ፡፡ ስነ-ጥበቡ እንዲከበርና የሚገባውን ቦታ እንዲያገኝ ሙያተኛው እርስ በእርስ ጉልበት መፍጠር ካልቻለና ራሱም ሙያውን በማክበር ካልተባበረ በስተቀር እንደ በረሀው ዮሐንስ ጮሆ ጮሆ መቅረት ነው ያለው ኪሮስ፤ ከሶስት ሺህ በላይ ሞያተኞች ባሉበት አገር እንዴት ቴአትር አይከበርም በማለት ጠይቋል፡፡ ‹‹ጎበዝ ተደፍረናል፤ብታምኑም ባታምኑም በቁማችን ሞተናል›› ሲልም ታዳሚውን ፈገግ አሰኝቷል፡፡
በውይይቱ ላይ ተጋባዥ እንግዳ የነበረው አርቲስት ደበበ እሸቱ በበኩሉ፤‹‹ለገንዘብ ብሎ ሙያውን አሳልፎ የሰጠ ሰው ምን መብት አለውና ነው መንግስት ድጋፍ ያድርግ፣ የኪነጥበብ መማክርት ይቋቋም የሚለው›› ሲል ሞግቷል፡፡ ዛሬ ዛሬ ከሙያው ጋር የማይተዋወቅ ባለሃብት ገንዘብ ስላወጣ ብቻ ፕሮዲዩሰር እየተባለ፣ በፊልሙና ቴአትሩ እየገባ ይህን ቁረጥ፤ ይህን ቀጥል በሚልበት ወቅት ሙያተኛው ሙያውን ሳያስከበር፣ይሄ ይደረግልኝ፣ያ ይፈፀምልኝ ማለት አግባብ አለመሆኑን በአፅንኦት ተናግሯል፡፡
ገንዘብ ያመጣው ሰው ፕሮዱዩሰር ሳይሆን ፋይናንሰር መባል ነው ያለበት ያለው አርቲስት ደበበ፤"አንድ የቴአትር ባለሙያ ቤታቸው ውስጥ ያላቸው ሰዎች ያንን ባለሙያ መከታ በማድረግ ቴአትር አዘጋጅ ሆነው የሚታዩበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑ እየታወቀ፣አቦነህ ይህቺን ዘንግቶ ከመንግስት ብዙ ድጋፎችን እየጠየቀ ነው" ሲል ተችቷል፡፡ በሌላ በኩል በትክክል ትምህርቱን ተምረው ከዩኒቨርስቲ የወጡት ባለሙያዎች እድል አጥተው ምንም መስራት አለመቻላቸው እንደሚያሳዝነው አርቲስት  ደበበ ተናግሯል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል መምህር አንተነህ ሰይፉ በበኩላቸው፤ጋሽ አቦነህ መንግስት ለስነ-ጥበቡ በርካታ ነገሮች እንዲያደርግ መጠየቃቸውን አውስተው "ለየትኛው ቅድሚያ እንስጥ፣ የትኛው ቀድሞ ይተግበር" በሚለው ላይ ትኩረት  አለመደረጉን  ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በእርግጥ ይደረጉ የተባሉትን ነገሮች በሙሉ እንፈልጋቸዋን ወይ›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ተባባሪ ፕሮፌሰር አቦነህ በሰጡት ምላሽም፤‹‹የቅጅ መብት ስለተከበረ ለስነ-ጥበብ ስራ የሚገባ እቃ ላይ የተጣለው ከፍተኛ ቀረጥ ይቆይ የሚባል አይደለም፤ሁሉም ጉዳዮች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ናቸው›› ብለዋል፡፡  
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የቴአትር መምህር አስተዋይ መለሰ በበኩሉ፤ብዙዎቹ የቴአትር ት/ቤቶች ባልተሟላ መሰረተ-ልማትና ባልተመቻቸ ሁኔታ የሚያስተምሩ መሆኑን ጠቁሞ፤ይህ አግባብ ባለመሆኑ አንድ ሁለት ዩኒቨርስቲዎች በተሟላ ቁስና አደረጃጀት ቢያስተምሩና ሌሎቹ ቢዘጉ እንደሚሻል ሃሳቡን ሰንዝሯል፡፡ አርቲስት ደበበ እሸቱ ግን ይህን ሀሳብ አልተቀበለውም፡፡ ‹‹ባይሆን መንግስት ቀስ በቀስ በየዩኒቨርሲቲው ትምህርት ክፍሉን ቀስ በቀስ እንዳስፋፋ ሁሉ፣ የሚያስፈልገውን መሰረተ ልማትም ቀስ በቀስ እንዲያሟላ መጠየቅ እንጂ ይዘጋ ማለት ጥሩ ሀሳብ አይደለም›› ሲል አማራጭ ሀሳብ ሰንዝሯል፡፡  
ሁለተኛው የጥናት ፅሁፍ ‹‹የቴአትር ትምህርት በኢትዮጵያ›› የተሰኘና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር መምህር ተካልኝ ገብረ ሚካኤል የቀረበው ሲሆን  ጥናቱ ብዙ ክርክርና ብዙ ሀሳቦችን አስነስቷል፡፡ ወጣቱ የቴአትር መምህር ሌላው ቀርቶ ስምንቱ ቴአትር የሚያስተምሩ ዩኒቨርስቲዎች በአንድ አይነት ስርዓተ ትምህርት እንደማያስተምሩ ጠቁሞ ለምሳሌ ወሎ፣ ወልቂጤ፣ መቀሌና አዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች የተሻሻለውን፣ ጎንደርና አክሱም የድሮውን፣ ጅማና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የየራሳቸውን ስርዓተ ትምህርት ይዘው እንደሚያስተምሩ ጠቅሷል፡፡ አሻሽለው የሚያስተምሩት ዩኒቨርስቲዎች ያሻሻሉትን ለትምህርት ሚኒስቴር ቢያቀርቡም ሳያፀድቅላቸው መቆየቱንና ባልፀደቀ ስርዓተ ትምህርት እያስተማሩ እንደሚገኙም ጥናት አቅራቢው ተናግሯል፡፡  
በሌላ በኩል ተማሪዎች ቴአትር ለመማር ሲገቡ ‹‹what is theatre” ወይም “what is drama›› ከሚለው እንደሚጀምሩ የጠቀሰው መምህሩ፤ ቴአትር እንደ ስፖርትና እንደ ሙዚቃ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የሚሰጥበት ስርዓተ ትምህርት መዘርጋት አለበት ብሏል፡፡
የቴአትር ትምህርት ክፍሎች ከወሎ ዩኒቨርሲቲ በስተቀር ስለ ቴአትር የተፃፉ መፅሀፍትን የያዙ ትንሽ ቤተ-መፅሀፍት እንደሌላቸው የገለፀው ጥናት አቅራቢው፤ "አንድ ተማሪ መብራት (ላይት) በሌለበት ስለ ላይት፣ መጋረጃ ሳይኖር ስለ መጋረጃ፣ መድረክ ሳይኖር ስለ አክቲንግ ብናስተምረው፣የተማረውን በትክክል መስራት አለመስራቱን እንዴት እንገመግማለን?" ሲል ጠይቋል፡፡ ብዙ አልባሳት በየቴአትር ትምህርት ክፍሉ ቢኖሩ እንኳን ለሆነ ምክንያት የተገዙ እንጂ ለትምህርቱ ተብለው የተገዙ እንዳልሆኑም ጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል የሰው ሀብትን በተመለከተ በ8ቱ ዩኒቨርሲቲዎች 95 የቴአትር መምህራን እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 66 በመቶው ቢኤ ዲግሪ፣56 በመቶው ማስተርስ ያላቸው እንደሆኑና አብዛኞቹ ማስተርስ ሊኖራቸው ይገባ እንደነበር በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ በጥናቱ መጨረሻ ሀሳብ ያቀረበው አርቲስት ደበበ እሸቱ፤“እንዴት ባልፀደቀ ስርዓተ ትምህርት ታስተምራላችሁ? ትምህርት ሚኒስቴር አላውቅም ቢል ልጆቹ እውቅና የሌለው ዲግሪ ባለቤት ሆኑ ማለት አይደለም” ሲል ከጠየቀ በኋላ፣ "ከዚህ መዓት ፈጣሪ ይሰውራችሁ" ብሏል፡፡
ሶስተኛው ጥናታዊ ጽሁፍ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲው አስተዋይ መለሰ የቀረበ ሲሆን ጥናቱ የጉራጌ ሴቶች አገር በቀል ፐርፎርማንስን ማበልፀግ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ የጥናቱ ዋና ማጠንጠኛ የጉራጌንም ሆነ የሌሎች ክልሎችን አገር በቀል ፐርፎርማንሶች በመደገፍና በማበልፀግ፣ ቴአትር አገራዊ ቀለምና መልክ እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል የሚል ነው፡፡ አስተዋይ በጥናቱ “ጊቻምዌይ”፣ “ኑቁኧ” እና “ኩርፈ” በተሰኙ የጉራጌ ሴቶች አገር በቀል የሰርግና የባህል ጭፈራዎች ላይ ባደረገው ጥናት፤ በአሁን ሰዓት “ጊቻምዌ” ከተሰኘው የጉራጌ ሴቶች የሰርግ ጭፈራ በስተቀር ሌሎቹ ወደ መጥፋት መቃረባቸውን፣ ይህም ለአንድ ማህበረሰብም ሆነ ለአንድ አገር የስነ-ጥበብና የባህል እድገት ውድቀት መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በዚህ ጥናት ላይም ውይይት ተደርጎ ይበጃሉ የተባሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ከተሳታፊ ቀርበው ውይይቱ ተጠናቅቋል፡፡ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ የቴአትር ፌስቲቫል የተለያዩ ባህሎች ላይ ያተኮሩ ቴአትሮችን፣ ግጥሞችንና ሙዚቃዎችን ያቀረበ ሲሆን ከ70 በላይ ተዋንያን የተሳተፉበት የብሔራዊ ቴአትሩ “የቃቄ ወርዲዩት” ቴአትርም ቀርቦ ታዳሚውን አስደምሟል፡፡ በ53ኛው የዓለም ቴአትር ቀን፤ ለቴአትሩ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ አንድ ወንድና አንድ ሴት ጥበበኞች ተመስግነውና ተሸልመው ነበር፡፡ ተባባሪ ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬና አርቲስት አዜብ ወርቁ፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰና አርቲስት መዓዛ ወርቁ የምስጋናውና የሽልማቱ ተቋዳሽ ሆነዋል፡፡  




Read 2257 times