Monday, 03 April 2017 00:00

ተሸክመዋል እንዳይባል በብብታቸው፣ ፈጭተዋል እንዳይባል ግማሽ ቁና

Written by 
Rate this item
(14 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን፤ አመሻሹ ላይ አንድ የተራበ ተኩላ የሚበላ ነገር ባገኝ ብሎ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር፣ ድንገት አንድ ግቢ ውስጥ የህፃን ልጅ ድምፅ ይሰማል፡፡ ግራ ቀኝ ቃኝቶ ማንም በአካባቢው እንደሌለና እንደማይታይ አረጋግጦ፤ ቀስ ብሎ ኮሽታ ሳያሰማ ወደ ግቢው ይገባል፡፡ ወደ መስኮቱ ተጠጋና ከቤት ውስጥ የሚሰማውን ድምፅ በጥሞና ማዳመጥ ይጀምራል፡፡
ህፃኑ አሁንም እያለቀሰ ነው፡፡ እናትየው ልታባብለው ትሞክራለች፡፡
‹‹ማሙሽዬ ዝም በል፤ ነገ የማረግልህን አታውቅም፡፡ ከረሜላ፣ ብስኩት፣ እገዛልሀለሁ፡፡ ግን ማልቀስህን ካቆምክ ነው፡፡ እሺ?›› ማሙሽ አልተበገረም፡፡ ብስኩቱም ከረሜላውም ሊያማልለው አልቻለም፡፡
እናት ትዕግሥቷን ጨረሰችና፤
‹‹እንግዲህ ዋ! ውጪ ላለው ተኩላ ነው የምወረውርህ!›› አለችው፡፡
ተኩላ ይሄን ሲሰማ ልቡ ጮቤ ረገጠች፡፡
‹‹አሃ ልጁን ሊወረውሩልኝ ነው፡፡ እራቴን የምበላው ላገኝ ነው ማለት ነው!›› አለ፡፡ በፀጥታ መጠበቁን ቀጠለ፡፡
መስኮቱ ሥር ሆኖ ኮሽ ባለ ቁጥር እየቋመጠ ቀና ይላል፡፡ ምንም የለም፡፡ በጊዜ ለማይለካ ጊዜ በረሀብና በጉምዥት እያዛጋ ጠበቀ፡፡ ልጁ አልተወረወረለትም፡፡
እየመሸ ሲሄድ ልጁ እየተረጋጋላት ሲመጣ፤ እናትየዋ፤
‹‹ጎበዝ የኔ ልጅ!! ያ ተኩላ ቢመጣ በጭራሽ ልጄን አልሰጠውም፡፡ አንተ ፀባይ ያለህ ቆንጅዬ ልጅ ነህ፡፡ በል እንዲሞቅህ ቢጃማህን ድርብርብ አድርገህ አልጋህ ውስጥ ግባና ለጥ በል፡፡ እሺ የእኔ ቆንጆ?››
ልጁም፤
‹‹እሺ እማዬ ለጥ እላለሁ!›› አለና ተኛ፡፡ ተኩላው በጣም ተናደደ፡፡
‹‹በጣም የሚያሳዝነው እነዚህ ሰዎች ቃላቸውን ይጠብቃሉ ብዬ ልቤን ማውለቄ! ከእንግዲህ የዚያ ቤት ሰዎች የሚናገሩትን አንድም ቃል አላምንም!›› ብሎ ግቢውን ለቅቆ ወጣ!
*   *   *
ተጨባጭና ላም አለኝ በሰማይ ተስፋን መለየት፣ ካሮትና ዱላን ማወቅ፣ ዋናና አቋራጭ መንገድን ልብ ማለት ዋና ነገር ነው፡፡ አገኛለሁ ተብለው የሚጠበቁና የማይጠበቁ ነገሮችን ለይቶ ማወቅ ብልህነት ነው፡፡ ሰጪዎች በዋዛ የማይለቋቸው፣ ተቀባዮች ሲመኙዋቸው የሚኖሩ አያሌ ጉዳዮች እንዳሉ አለመርሳት ነው፡፡ ልጅ ራበኝ ብሎ ማልቀሱ፣ የፈለገውን ካልሰጣችሁኝ ብሎ ማልቀሱ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ እናት ማባበሏና እንዲተኛ ማድረጓ ግን የእናትነት ኃላፊነትና ፍቅር ነው፡፡ ህዝብ የሚጠይቃቸው ነገሮች አያሌ ናቸው፡፡ አንዳንዴ አልቅሶ ይጠይቃል፡፡ አንዳንዴ ጮኾ ይጠይቃል። አንዳንዴ በምሬት ይጠይቃል፡፡ ሁሉንም ጥያቄዎች እንደየጠባያቸው መልስ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ የራሱና ራሱ ነጥቆ የሚወስዳቸው እንደ ሰብዓዊ መብቶችና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያሉ ቁልፍ ነገሮች መኖራቸውን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ህዝቡ ራሱም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ የእኔ ነው የሚለውንና ጎደለብኝ የሚለውን ለይቶ ማወቁ ነው ጥያቄዎችን እንዲያነሳ የሚያደርገው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሲቪክ ተቋማት፣ የሙያ ተቋማት፣ ፓርቲዎች፤ አጋዥ ኃይላት ናቸው፡፡ እነሱም ቢሆኑ በወግ በወግ ሆነው፣ “ጋን በጠጠር ይደገፋል” የሚሉና በጥበባዊ ስልት የህዝብ ጥያቄ እንዲመለስ ተግተው የሚረዱ መሆን አለባቸው፡፡
መግባባትን፣ መቻቻልን፣ ዕርቅን፣ ትዕግሥትን፣ የጊዜ አጠቃቀምን ማወቅ አለባቸው፡፡ በመንግሥት በኩል ህዝብ ምሬት ደረጃ እስኪደርስ፣ የኑሮ ውድነቱ አንገፈገፈኝ እስኪል፣ ቸል ብሎ ማየት ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎችን አለመገንዘብ ነው፡፡ ሁኔታዎችን አለመገንዘብ ኋላ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትልና ዋጋም እንደሚያስከፍል ልብ ማለት የልባሞች ክህሎት ነው፡፡
በሀገራችን ውስጥ የምናካሂዳቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ አብዮቶች የተሣሠሩ ካልሆኑ ዋጋ አይኖራቸውም፡፡ እንደገና ይበተናሉና፡፡ የሁሉም ግብ አገርን ማዘመን ነው፡፡ ይህም የህዝብ ህይወት የተሻለ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡
ዳንኤል ለርነር የተባለ ፀሐፊ፤ ስለ ዝመና ሲናገር፤ “ዝመና እጅግ መልከ - ብዙ ሂደት ሲሆን በሁሉም የሰው ልጅ ሀሳብና እንቅስቃሴ ውስጥ ያለና ተጠቃሽ ነው፡፡ ዋና ዋናዎቹ ፍሬ ጉዳዮቹ፡- ከተማዊነትን ማበልፀግ (urbanization) ኢንዱስትሪያዊነት፣ ዓለማዊ ይዞታን ማሳደግ፣ ዲሞክራሲን ማስፋፋት፣ ትምህርትን ማራባትና የሚዲያ ተሳትፎን ማጎልበት ሲሆኑ፤ ቁም ነገሩ ግን ሁሉም የሚያድጉት ከተጣመሩና ከተሳሰሩ መሆኑ ላይ ነው” ይለናል፡፡ ዝምድናቸውና ሰምሮ - ተጓዥነታቸውን በትጋት መከታተል ያሻል፡፡
የእነዚህን ፍሬ ጉዳዮች ዕድገት ማረጋገጥ የሚቻለው ደግሞ ህዝብን አምኖ የህዝብን ተሳትፎ በእያንዳንዳቸው ውስጥ በአስተማማኝ መንገድ ማሳየት ሲቻል ነው፡፡ እንደ ድሮው ዘመን ፖለቲካዊ ንትርክ፤ “ሥርዝ ያንተ፣ ድልዝ የእኔ፣ እመጫት የእሷ፤ ሆያ - ሆዬ የሰፊው ህዝብ!” ብለን የምናልፈው ነገር አይደለም፡፡ ህዝብን ሳይዙ ጉዞ “እንሥራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች” እንደሚባለው ዓይነት ነው። በየዘመኑ በተደጋጋሚ “ህዝብን ማገልገል” ፣ “ህዝባዊነት”፣ “ህዝባዊ ተሳትፎ”፣ “ዲሞክራሲያዊ አሳታፊነት”፣ “አረንጓዴ ዘመቻ”፣ “የኢኮኖሚ አብዮት”፣ “የባህል አብዮት” ወዘተ … ሲባል እንሰማለን። የዚህ ሁሉ መቋጫ ግን አንድ ጥያቄ ነው፡፡ “በተግባር አለ ወይ? አፍአዊ ነው ልባዊ?” የሚለው ነው። የሀገራችን ዕውነታ አብዛኛውን ጊዜ አሉታዊ መልስ እንዳለው ነው የሚያመላክተን፡፡ ወረቀት ላይ እንጂ መሬት ላይ የለም፡፡ ለምን ተብሎ ሲጠየቅ፤ በርካታ ምክኖችን መደርደር ቢቻልም አንዱ ዐቢይ ምክን ሐቀኛ ተግባሪ መጥፋቱ ነው! የወሬ ሰው መብዛቱ ነው፡፡ ለታይታና ለአደባባይ እይታ አለሁ አለሁ ባዩ መበርከቱ ነው! ደስኳሪው ከአንድ ቦይ እንደሚፈስ ውሃ የሚለፈለፍ ንግግር ሚዲያውን መሙላቱ ነው! ሁሉን መነካካት፣ ስለ ሁሉም ማውራት፤ በተጨባጭ  ምንም ፍሬ አለመያዝ… እየተለመደ መጥቷል፡፡ የለብ - ለብ ፖለቲካ፣ የለብ ለብ ኢኮኖሚ፣ የለብ ለብ ቢሮክራሲያዊ ዘመቻ ተጠናውቶናል፡፡ “ተሸክመዋል እንዳይባል በብብታቸው፣ ፈጭተዋል እንዳይባል ግማሽ ቁና” የሚለው ተረት የሚያስረዳን ይሄንኑ ነው!  

Read 4994 times