Saturday, 25 March 2017 13:09

ዞን 4.2 የአፍሪካ ቼስ ሻምፒዮና በጅማ ከተማ ይካሄዳል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 ዞን 4.2  የአፍሪካ ቼስ ሻምፒዮና በጅማ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን፤ ከ10 በላይ የአፍሪካ አገራትን የወከሉ እስከ 100 ወንድና ሴት የቼስ ተወዳዳሪዎችን ያሳትፋል፡፡  አህጉራዊ ሻምፒዮናው ከኢትዮጵያ ቼስ ፌደሬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የጅማ ቼስ ፌደሬሽን ሲሆን ውድድሩ ለ1 ሳምንት በጅማ ዩኒቨርስቲ ስፖርት ስቱድዮ የሚስተናገድ ነው፡፡ በሻምፒዮናው ለመሳተፍ ማረጋገጫ የሰጡት አገራት ግብፅ፤ ሱዳን፤ ደቡብ ሱዳን፤ ኬንያ፤ ኡጋንዳ፤ ታንዛኒያ ጅቡቲ፤ ሶማሊያ ፤ ሩዋንዳና ሲሸልስ ናቸው፡፡
በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የኢትዮጵያ ቼስ ፌደሬሽን እና የጅማ ቼስ ፌደሬሽን ከፍተኛ አመራሮች የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እና አትሌቶች በተገኙበት በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ  መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በየዓመቱ በሰሜን እና በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አገራት ሲካሄድ የቆየው ውድድሩ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ መስተናገዱ እንዳስደሰታቸው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ሲያመለክቱ፤ አህጉራዊ ሻምፒዮናው ስፖርቱን ለማስፋፋት የሚያግዝና ከፍተኛ መነቃቃት የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ በ2017 ዞን 4.2  የአፍሪካ ቼስ ሻምፒዮናው የሚካሄደው በ9 ዙር የግል የበላነይት ግጥሚያዎች ሲሆን በሁለቱም ፆታዎች የሚያሸንፉት  ተወዳዳሪዎች በቼስ  ዓለም አቀፍ የማስተርስ ማእረግ ከመጎናፀፋቸውም በላይ፤ በባቱም ፤ ጆርጂያ በሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮና አፍሪካን በመወከል የሚሳተፉበት እድል ይፈጥርላቸዋል።
በሻምፒዮናው  ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታዎች በድምሩ 22 ተወዳዳሪዎችን የምታሳትፍ ሲሆን፤ በወንዶች ምድብ 14 በሴቶች ምድብ 8 ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ የተሳታፊዎች ብዛት የጨመረው ውድድሩን ለማስተናገድ ከፍተኛ ጥረት ላደረገው የጅማ ቼስ ፌደሬሽን ተጨማሪ ስድስት ተወዳዳሪዎችን እንዲያሳትፍ የአፍሪካ ቼስ ፌደሬሽን ፈቃድ በመሰጠቱ ነው፡፡ በጅማ ከተማ የቼስ ስፖርት የተዋወቀው ከ30 ዓመታት በፊት ሲሆን፤ ከተማዋ አገርን ወክለው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተወዳደደሩ ምርጥ ተወዳዳሪዎችን እንዳፈራች እና ስፖርቱን በማስፋፋት ልዩ ትኩረት አድርጎ በመስራት ጥሩ ደረጃ ላይ እንደምትገኝም  አቶ ተሾመ በቀለ የጅማ ቼስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
 በቼስ ሻምፒዮናው የግብፅ ተወዳዳሪዎች ባለፉት አመታት ከነበራቸው የበላይነት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ግምት ሲሰጣቸው ለምስራቅ አፍሪካዎቹ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ እንዲሁም ለአዘጋጇ ኢትዮጵያም ልዩ ትኩረት ተፈጥሯል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቼስ ተወዳዳሪዎች የተመረጡት በግል የበላይነት  በተዘጋጀ አገር አቀፍ ውድድር ሲሆን በየፆታ መደባቸው  ከ1-8 ደረጃ ያገኙት በቀጥታ በአፍሪካ ዞን ሻምፒዮናው እንዲሳተፉ ተደርጓል። ዋና አሰልጣኙ በዓለም የቼስ ፌደሬሽን የኢንስትራክተር ማዕረግ ያላቸው አቶ አበባው ከበደ ናቸው፡፡ አህጉራዊ ሻምፒዮናው በስፖርቱ ዙሪያ ያለውን እንቅስቃሴ በማነቃቃት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የገለፁት፤ የቼስ ኢንስትራክተሩ  በአንድ አገር ስፖርት ፌዴሬሽን እድገት አስመዘገበ የሚባለው በርካታ ክለቦችና ውድድሮች ሲኖሩ ነው ይላሉ፡፡ በአዲስ አበባ በቼስ ስፖርት የሚንቀሳቀሱ ክለቦች ጥቂት መሆናቸውና የብሄራዊ ፌዴሬሽኑ የበጀት አቅም ደካማነት ከዋና ችግሮች የሚጠቀሱ ናቸውም ብለዋል፡፡ ስፖርቱን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት በሚዲያው በኩል  ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ኢንስትራክተሩ በአዲስ ዘመን፣ በሰንደቅ እና ሌሎች ጋዜጦች ስለ ቼስ ስፖርት በመፃፍ ያላቸውን ልምድ በማካፈል ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን  በመግለፅ ለተመሳሳይ ድጋፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በቼስ ስፖርት ያሉት ባለድርሻ አካላት በጨዋታ ማኑዋሎች፣ ወቅቱን በጠበቁ መረጃዎች ከአፍሪካ አገራት በሰፊ ልዩነት የራቁ አይደሉም የሚሉት ኢንስትራክተሩ ተወዳዳሪዎች በግላቸው የሚያደርጉት ጥረት ለስፖርቱ ህልውና ማገዙን በአድናቆት አንስተዋል፡፡  
በአህጉራዊው የቼስ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች  ጠንካራ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ እጠብቃለሁ ያሉት ኢንስትራክር አበባው፣ በሻምፒዮናው በወንዶች ምድብ ሁለት የፌ.ዲ.ኤ ማስተሮች እና አንድ የዓለም አቀፍ ማስተር በሴቶችም አዳዲስ ካንዲዴት ሴት ማስተሮች እንደሚገኙ ተስፋ ማድረጋቸውን ለስፖርት አድማስ ተናግረዋል፡፡

Read 1730 times