Monday, 27 March 2017 00:00

ኖርዌይ የ2017 የአለማችን “ደስተኛዋ” አገር ተብላለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ከሰሞኑ ይፋ የተደረገው የ2017 የአለማችን አገራት የደስተኛነት ደረጃ ሪፖርት፣ ኖርዌይን ከ155 የአለማችን አገራት በቀዳሚነት ሲያስቀምጥ፣ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ደግሞ በመጨረሻ ደረጃ ላይ ትገኛለች ማለቱን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡ ስድስት ያህል የአገራትን ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መመዘኛ መስፈርቶችን በመጠቀም በየአመቱ የአገራትን የደስተኛነት ደረጃ ይፋ የሚያደርገው ሰስቴኔብል ዲቨሎፕመንት ሶሊዩሽንስ ኔትወርክ የተባለው አለማቀፍ ተቋም፣ በ2017 ሪፖርቱ ዴንማርክን በሁለተኛ፣ አይስላንድን በሶስተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧቸዋል፡፡
ስዊዘርላንድ፣ ፊላንድ፣ ኒዘርላንድስ፣ ካናዳ፣ ኒውዚላንድ፣ አውስትራሊያ እና ስዊድን ተከታዮቹን ደረጃዎች መያዛቸው የተነገረ ሲሆን፣ ዴንማርክ ለአራት አመታት የአለማችን ቁጥር አንድ ደስተኛ አገር ሆና መመዝገቧንም አስታውሷል፡፡
የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ዜጎች ጥናቱ ከተሰራባቸው 155 የአለማችን አገራት ህዝቦች ሁሉ በኑሯቸው የማይደሰቱ ህዝቦች ናቸው፤ አገሪቱም በአመቱ የአለማችን አገራት የደስተኛነት ዝርዝር ውስጥ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች ያለው ሪፖርቱ፤ ብሩንዲና ታንዛኒያ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከመጨረሻ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን አመልክቷል፡፡
የአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርትና የነፍስ ወከፍ ገቢ፣ አማካይ በህይወት የመኖር ጣራ፣ የህይወት ምርጫን የማድረግ ነጻነትና የመሳሰሉት ጉዳዮች የአገራቱን የደስተኛነት ደረጃ ለመገምገም በጥቅም ላይ ከዋሉ መስፈርቶች መካከል ይጠቀሳሉ ያለው ሪፖርቱ፤ ደስተኛነት ገንዘብ የመያዝና ያለመያዝ ጉዳይ አይደለም፤ ለዚህም አንዳንድ ሀብታም አገራት ዝቅ ያለ የደስተኝነት ደረጃ ይዘው መገኘታቸው ማረጋገጫ ነው ብሏል፡፡

Read 2909 times