Monday, 27 March 2017 00:00

ስለ ማሪና ኦቫኖቫ ስቬታየቫ ሥራዎች በጥቂቱ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሩሲያ ካፈራቻቸው ታላላቅ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች ውስጥ ገጣሚና ተርጓሚ የሆነችው ማሪና ኢቫኖቫ ስቬታየቫ አንደኛዋ ናት፡፡ ማሪና ኢቫኖቫ ሳይንስና የኪነ ጥበብ ዕውቀት ከአላቸው ቤተሰቦች ሞስኮ ውስጥ የተወለደቺው እ.ኤ.አ መስከረም 26 ቀን 1892 ዓ.ም ነው፡፡
ያረፈችው ደግሞ እ.ኤ.አ በ1941 ዓ.ም ላይ ነው። አባቷ ኢቫን ብላዲሚሮቪች ስቬታየብ የሞስኮ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር፣ የታወቀ ፈላስፋ፣ ዲሬክተርና የኪነ ጥበብ ሙዚየም መሥራች (በአሁኑ ሰዓት በፑሽኪን ስም በሚጠራው ከተማ የሚገኘው ሙዚየም) ነበር፡፡
ወላጅ እናቷ እመት ማሪያ ኔ ሜንም የተለየ ዕውቀት የነበራትና የኮንሰርት ፒያኖ ተጫዋች ነበረች፡፡
ማሪና ሞስኮ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተማረቺው በግል ት/ቤት ነው። በልጅነቷ ቤተሰቧ የተለያየ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድነሰ ወደ ሶርቦን ፓሪስ በሚሄድበት ወቅት አብራ በመሄድ ትምህርቷን ትከታተልና ቋንቋም ታጠና ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1908 ደግሞ በራስዋ ፍላጎት ወደ ፈረንሳይ (ፓሪስ) ሄዳ ሶርቦን ውስጥ የጥንት ፈረንሳይኛ ሥነ ጽሑፍ ኮርስ መከታተል ጀመረች፡፡ በ16 ዓመቷ ግጥም መግጠም የጀመረቺው ስቤታየቫ፤ 18 ዓመት ሲሞላት ወደ ሩሲያ ተመልሳ የመጀመሪያዋ የሆነ የሥነ ግጥም ስብስብ መጽሐፍ ‹‹ የምሽት አልበም›› (EVENING ALBUM) በሚል ርዕስ አሳተመች። በኋላም ማለት እ.ኤ.አ በ1912፣በ1913፣በ1916 ዓ.ም የተጋጋለ ውስጣዊ ስሜቷንና የሩሲያን ነባራዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቁ ሌሎች ሥራዎቿን ለህትት አበቃች፡፡ በተለይም “ከፍታ” የተሰኘው ግጥሟ ለሩሲያና ለሩሲያ ገጣሚዎች የተበረከተ ሲሆን ኩራትን፣ ጀግንነትን፣ የበለፀገ እውቀትንና ፍፃሜ የሌለው ስሜትን ያመለክታል፡፡
‹‹የምሽት አልበም›› የሚለው ግጥም ስለ ልጅነቷና ስለ ወጣትነቷ ዘመን ያትታል፡፡ ማስታወሻ አድርጋ ያበረከተችውም ለዚሁ ዘመኗ ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ1912 ዓ.ም ማሪና ሰርጌይ ኢፎርን የተባለና የዛሩ መንግሥት ወታደር የነበረ ሰው አግብታ ሁለት ሴቶችንና አንድ ወንድ ልጅ ወልዳለች፡፡ የማሪና ሰቬተየቫ ሕይወት ከሩሲያ አብዮት ጋር የያያዘ ነበር፡፡ ባለቤቷ ኢፎርን ነጩ ጦር (the white guard) እየተባለ ከሚታወቀው የዛሩ መንግሥት ጦር ሰራዊት ጋር ተሰልፎ አብዮተኞችን/ ሶቭየቶችን ወይም ቦልሸቪኮችን/ ሲወጋ ነበር፡፡
ማሪና ‹‹ገርልፍሬንድ›› በሚለው ግጥሟ ተደንቃና ተመስጣ ገጣሚና የኦፔራ ቲአትር ባለሙያ ከሆነችው ከሶፍያ ፓሞክ ጋር ተዋወቀች። ምክንያቱም ሶፍያ ፓሞክ በወቅቱ በዚህ ግጥሟ ዝናን አትርፋ ነበር፡፡ ቀጥላም በዛሩ ዘመነ መንግሥት የቀይ ጦር ሽምቅ ታዋጊ ወታደር ከነበረና ኮንስታንቲን ፎዜቪች ከተባለ ገጣሚ ጋር ትውውቅ አደረገች፡፡ ኮንስታንቲን ‹‹የተራራ ግጥሞች›› እና ‹‹ የመጨረሻ ግጥሞች›› የተሰኙ ሥራዎች ስለነበሩት እነዚህን አንብባ አድናቆቷን ገለጸለችለት፡፡
እ.ኤ.አ በ1917 የኦክቶቨር ሪቮሉሽን ወቅት ተይዛ ለ5 ዓመት ታሥራለች፡፡ ከአብዮቱ ጋር በተያያዘ በተከታታዮቹ ዓመታት ድርቅና ረሀብ በሩሲያ በተከሰተበት ወቅት አንደኛዋ ሴት ልጇ በረሀብ ምክንያት ሞታበታለች፡፡
እ.ኤ.አ በ1922 ዓ.ም ማሪና ባለቤቷንና ቤተሰቧን ይዛ ወደ በርሊን፣ ከዚያም ወደ ፕራግ፣ ቀጥላ በ1925 ወደ ፓሪስ ተሰደደች፡፡ በፓሪስ የሩሲያ ማኅበረሰብ አባላት ጋርም መኖር ጀመረች። ነገር ግን አብዛኞቹ ስደተኞች የቀድሞው የዛር መንግሥት ወታደሮች ስለነበሩ የማሪና ባለቤት ሰርጌይ ኢፎርን የቦልሸቪኮች ሰላይ ሳይሆን አይቀርም ብለው ስለገመቱ እርሱን መፍራት ጀመሩ፡፡ በኋላም ነገሩ እውነት ሆኖ ተገኘ፡፡ ከጊዜ በኋላ ሰርጌይ ኢፎርን ወደ ሩሲያ ተመለሰ፡፡ ሞስኮ እንደደረሰም ታሥሮ ከቆየ በኋላ ተገደለ፡፡ ማሪና በስደት ዘመኗ ወጎችንና የትረካ ሥራዎችን ደርሳ ለማሳተም ችላለች፡፡ የአብዛኞቹ ግጥሞቿ ጭብጥ የሚነሳው ከአፈ-ታሪክና ከኅብረ ዝማሬ ሲሆን የአገጣጠም ስልቱ ደግሞ በታላቁ ሩሲያዊ ገጣሚ በአሌክሳንደር ብሎክና በታላቂቱ የኪነ ጥበብ ሰው በአና አህማቶቫ የአጻጻፍ ቴክኒክ የተቃኘ ነው፡፡ በሥራዎቿ ውስጥ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖትና ጸሎተኞች፣ የእምነት ዕሴቶች ከዘመናዊ አስተሳሰብ ጋር ተቃኝተው ይታያሉ፡፡
ማሪና ከብዙ ነገር ተገልላና ብቸኛ ሆኖ በስደት ብትቀመጥም የነፍስ ጥሪዋን ግን አልረሳችም። በከፍተኛ ስሜት ተነሳስታ ብዙ የጻፈችው በስደት ጊዜዋ ነው፡፡ ‹‹መለያየት››፣ ‹‹ንግድ››፣ ‹‹ሥነ ልቡና››፣ ‹‹ከሩሲያ በኋላ››፣ ‹‹ይድረስ ለልጄ››፣ ‹‹የአገር ናፍቆት››፣ ‹‹ቼቺያ›› /በወቅቱ ፖለቲካ ላይ የሚያተኩር ሥራ / የተባሉትን ሥራዎች ደርሳ ያሳተመቻቸው በስደት ዘመኗ ነው፡፡ ከማሪና ታላላቅ የግጥምና የልቦለድ ሥራዎች ውስጥ
በፖሪስ ውስጥ፣ ጸሎተኛው፣ ለእናቴ፣ ስብሰባ፣ ኒና ይቅርታ አድርጊልኝ … የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ማሪና እ.ኤ.አ ከ1939 ዓ.ም ጀምራ ወደ ሀገሯ በመመለስ ሞስኮ ውስጥ ለመኖር ብትፈልግም በፖለቲካ አመለካከቷ ምክንያት የሥነ ጽሑፍ አፍቃርያንና በማኅበረሰቡ ዘንድ የተገለለች ሆነች። ከዚህም የተነሣ እ.ኤ.አ በ1941 ዓ.ም ራስዋን አጥፍታለች፡፡
ታላቁ ገጣሚ ቦሪስ ፖስተርናህ አሟሟቷን አስመልክቶ ሲናገር፡-
‹‹ማሪናን ቀደም ብሎ የሥነ ጽሑፍ ቢሮክራቶች ልበቢስ በሆነ መንገድ ባይቀርቧት ኖር ራስዋን አታጠፋም ነበር›› ብሏል፡፡
የጽሑፍ ሥራዎቿ የሰላ አእምሮ፣ በጥልቀት የሚያይ ዐይንና አስተዋይ ልቡና የነበራት ታላቅ ሴት የነበረች መሆኗን አስመስክረዋል፡፡
በ20ኛው ክፍለ ዘመን በወጥነት ከቀረቡት የግጥም ሥራዎች ውስጥ የማሪና ስቤታየቫ በዋነኛነት ይጠቀሳል፡፡ የእርስዋ የሥነ ግጥም ምንጭ የፈለቀው ተቃርኖ ከበዛበት የግል ሕይወቷ ነው፡፡ የቋንቋ አጠቃቀሟ የተመጠነ፣ በጥቂት ቃላት ብዙ የምትናገርነ ገጣሚ ናት፡፡ በጭብጥ ረገድ ካነሳቻቸው በርካታ ርእሰ ጉዳዮች ውስጥ የሚበዛው ሴታዊነት፣ ወሲብ፣ የሴቶች ግላዊ ሕይወትና በማኅበራዊ ኑሮ ስለአላቸው ሚና ነው፡፡
ለማሪና ስቬታየቫ በአሁኑ ሰዓት የሩሲያ መንግሥት በመኖሪያዋ አካባቢ በሚገኘውና ቦሪስግሌቭስኪ ተብሎ በሚጠራው ሠፈር ሐውልት አቁሞላታል፡፡

Read 1886 times