Saturday, 25 March 2017 12:42

“የቡና ቤት ሥዕሎችና …”

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 አንድ ቡና ቤት ውስጥ ግድግዳው ላይ የተሣለ ነው፡፡ ሰውዬው በአንበሳው ላይ ይነጣጥራል። በሰውዬውና በአንበሳው መካከል ጅረት አለ። አዳኙን እግሩ ቀጥ እንዳለ ስታዩት ሣሩ ላይ ተኝቷል ብላችሁ ታስባላችሁ፡፡ ነገር ግን መሆን አለበት ብላችሁ ስለምትገምቱ ነው እንጂ ሥዕሉ ላይ የሚታየው በሣሩ ላይ ሲንሳፈፍ ነው፡፡
እሺ ብሎ አይዞርላችሁም እንጂ ግድግዳውን ዞር ብታደርጉት ደግሞ ቆሞ እሚተኩስ ይመስላችኋል። አንበሳው በተዝናና ሁኔታ ሰውዬውን ትኩር ብሎ ያየዋል። አስተያየቱን ለመግለጽ ያስቸግራል፡፡ ብቻ፣ ‹‹እውነት አሁን ልትተኩስ ነው እስቲ ወንድ!›› የሚል ይመስላል፡፡
የሥዕሉ ምጣኔ ነገር አይወራም፡፡ የፊት እግሮቹ እኩል አይደሉም፡፡ አንዱ ወፍራም አንዱ ቀጭን ነው፡፡ የጅራቱን ማጠር ስታዩ፣ ሥዕሉ ሲሣል ግድግድጋው ጠባብ ነበር እንዴ ማለታችሁ አይቀርም፡፡ የወገቡም ቅጥነት፣ ‹‹ሽንጧ ስምንት ቁጥር›› የሚለውን ዘፈን ያስታውሳችኋል፡፡ የቅርበት-ርቀቱ ሚዛን እንዳልተጠበቀ በግልጽ ይታያል። ለምሳሌ ጠመንጃው ከሰውዬው በልጦ ጅረቱን አቋርጦ አንበሳው አፍንጫ ሊደርስ ትንሽ ቀርቶታል። ከወዲያ ማዶ ያለው ጋራ ደግሞ አንበሳው ጀርባ ላይ ያረፈ ይመስላል፡፡ ከሁሉም ይልቅ የሚገርመው አውሬው ጥቂት እንኳ እንደ መዝለል ወይም እንደ መሸሽ ሳይል በኩራት ዝም ብሎ አዳኙን ማስተዋሉ ነው፡፡ ይኸን ሥዕል ሳይ የአንዳንድ አርበኞች ሥዕል ትዝ አለኝ፡፡
ወረቀቱ ስለማይበቃ ነው እንዳይሉን እንጂ የአርበኛው ጠመንጃ የጣልያኑን ዓይን እየወጋ፣ ‹‹ደጃች እገሌ ጠላት ላይ ሲያነጣጥሩ›› የሚል ከሥሩ እየተለጠፈበት፣ እንደ እንቁጣጣሽ አበባ እየዞረ ሲሸጥ፣ የእነ አብየ ገብረ መንፈንስ ቅዱስ፣ የቅዱሳን፣ የሰማዕታት፣ ያ ያ ሁሉ ታየኝ፡፡›› ታዲያ አሁን እዚህ ለምናነሣቸው መሰረቱ እነሱ ይመስሉኛል፡፡ ጥንት ከምዕተ ዓመታት በፊት የተሣሉትን ግን ለጥናት ሊጠቅሙ ስለሚችሉ ለታሪክና ቅርስ ተመራማሪዎች ቢተው ጥሩ ነው፡፡
ሌላው ያየሁት የፋሲል ግንብ ነው፡፡ ይኸ ሥዕል በብዛት በየቦታው ይታያል፡፡ አሣሣሉ አንድ ይምሰል እንጂ አጠቃላይ መልኩ የተለያየ ነው። አጥር ያለው፣ አጥር የሌለው፣ ዛፍ ያለው ዛፍ የሌለው፣ በጽጌረዳና በሀረግ ያጌጠ፣ በለምለም ሣር ያሸበረቀ፡፡ የአንዳንዱ ጥላ አጣጣል ፍጹም ቅጥ ያጣ ከመሆኑ የተነሣ ፀሐይዋ ሁለት የሆነች ሊመስላችሁ ይችላል፡፡ አንዳንዱ ከበረንዳው በታች ዘንባባ፣ ባሕር ዛፍ፣ ጥድ፣ በያይነቱ በሰልፍ ይተከልበታል፡፡ ምን ያህል እውነት እንደሆነ አላውቅም እንጂ ፓፓያ የተሣለበትም አለ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡
የግንቡ የአካባቢ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ ቀለሙም ብዙ ዓይነት ነው፡፡ ቢጫ፣ ሰማያዊ፣ ሮዝ፡፡ የአራት መቶ ዓመት ህንፃ በፒያሳ ቀለም መታደሱ እንኳን አይከፋም፡፡ እኔን በጣም ያስገረመኝ ግን፣ ከግንቡ ፊት ለፊት፣ ከቤተ መንግሥቱ ፊት ለፊት አንዲት ሹርባ የተሠራች የሀገር ልብስ የለበሰች ውብ ወይዘሮ፤ ጃንጥላዋን ከፍ አርጋ ይዛ ገበያ አዳራሽ እምትሄድ ይመስል በቄንጥ ስትራመድ የሚያሳየው ሥዕል ነው፡፡ እስቲ ሴትየዋ እዚያ ምን ታደርጋለች? ላልጠፋ ግድግዳ … ለብቻዋ መሳልስ ይቻል የለም!
በተለይ የፋሲል ግንብን፣ የአክሱም ሐውልትን፣ ጢስ ዐባይን፣ ላሊበላን የሚሥሉ ሰዎች፣ ባዶ ቦታ ለምን ባዶውን ይቅር እያሉ ነው መሰለኝ፤ ደስ ያላቸውን ነገር ይጨምራሉ፡፡ ባዶ ቦታ ማስፈለግ አለማስፈለጉን ሳያስተውሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ወፎችፐ ከሩቅ እየበረሩ ሲመጡ እንዲያውም ሰማይ ካለ ወፎች በግድ ይኖራሉ፡፡ ወንዝ ወይም ኩሬ ከተነሳ ዳክዬዎች ሲዋኙ መታየት አለባቸው፡፡ ዛፍ ደግሞ ጦጣ ከሌለችበት ዛፍ ሊሆን አይችልም። ሣሩም ሁልጊዜ አረንጓዴ ነው፡፡ ምናልባት ለዚህ የሚገፋፋቸው የኢትዮጵያ ልምላሜ ይሆን? በአጠቃላይ የቡና ቤት ሠዓሊያዎች ትልቅ ድክመት ዝምድና ወይም ግንኙነት የሌላቸውን ነገሮች ጎን ለጎን ማስቀመጣቸው ነው፡፡ ማን ያውቃል፣. ከፍ ብሎ የተጠቀሰችዋ ሴትዮ ሲገርመን፣ ላሊበላ ቤተክርስቲያን ላይ ጂንስና ቢትልስ ለብሶ ኳስ የሚያነጥር ልጅ እንድ ቀን እናይ ይሆናል፡፡
(ከደራሲ መስፍን ሀብተማርያም
“የቡና ቤት ሥዕሎች እና ሌሎችም ወጎች”
መፅሃፍ ላይ የተቀነጨበ)

Read 8133 times