Print this page
Sunday, 26 March 2017 00:00

...ጎረቤቴ

Written by  አሌክስ - ከድሬዳዋ
Rate this item
(31 votes)

 “ሄሎ!....”    አለኝ   ለስለስ ያለ፣ ለአቅመ ትዳር ከደረሰች ሴት የሚወጣ የሚመስል ድምጽ፡፡
“ሄሎ.... እንዴት ነሽ”
“አለሁ... ማን ልበል”
“እ.. ስልኬን አላየሽውም እንዴ?”
“ይቅርታ ቀፎ ስለቀየርኩ ይሆናል፤ ቁጥር ብቻ ነው ያወጣልኝ....”   ትህትናዋ ደስ ሲል!
“ጎረቤቴን  ሀይ!.......ልበል ብዬ ነው..... የቅርብ እውቂያ የለንም.....”
“ምነው ቅር አለሽ?”
“አይ!... ምን ማለት እንዳለብኝ ጠፍቶብኝ ነው”
“ያው.. ሰላም ነው!... አንተስ.... ምናምን ነዋ!”
“OK!.. እኔ ደህና ነኝ..... አንተ እንዴት ነህ!”  ....ትሁት ድምጽዋ  ...ትህትናውን ሳይለቅ እንደ መሞላቀቅ.....የምታውቀውን ሰው እንደማናገር አደረገው፡፡
“am good..  ምነው አንቺ ግን በፍጥነት ያወቅሽኝ አስመሰልሽው”
“Of course ... i mean... i know you physically”   የእንግሊዘኛውን ቃል የምትጠራበት መንገድ ሲያምር!
“physically...?”  እንደመደናገር አደረገኝ፡፡
“yapp!.... እንደ አብሮ አደግ ስሜን ትፊያት ብለህ ልታኮርፍ ባልሆነ!”
“ኧረ! ..የኔን ትፋት ብትይኝ ምን ይውጠኝ ብየ `የምቀብጥ......ባይሆን ለወደፊቱ እንድተፋት አቀብይኝና ልዋጣት......”
“ስሜን?”
“ለምን!..... ልብሽን!”  ወፍራም ሳቅዋ ሙዚቃ ይመስላል....የሆነ ከአዚም እስራት ያላቅቃል፤ታማሚ መንፈስ ያክማል! የተባለለትን አይነት......
እየሳቀች፡- “ሜላት” አለችኝ
“ok!.. ሜሊ ...ያምራል”
“እና......”
“እና ምን?”
“ለውጤን ትፋታ......በነጻ’ኮ እርግማንም ቀርቷል”
“ወልደ ነጎድጎድ!”
ከረዥም ሳቅ በኋላ “ው..ሸ..ታ..ም..!!”  እያንዳንዱን ሆሄ  ነጠል ነጠል   አድርጋ፡፡ ..ጥብቅ እያደረገች ስትቃወመኝ፣ በከንፈሮችና በምላሷ ቃሉ ለመውጣት መታሸቱ ይታወቃል! .....በማሸት ምሩቅ ሳትሆን አትቀርም......ቃሉን በሆንኩ!
“ከምሬ ነው..... አትሳቂ”
“ሃይ!.... አንተን የመሰለ ሰውማ እንዲህ የሚንጎዳጎድ ስም አይኖረውም...”
“አንቺን የመሰልሽ ውብ----ጉሮሮሽ ውስጥ የሚንጎዳጎድ ሳቅ አለሽ አይደል.... እንዴ..?”
“አ...አ ስንቶች የሚሞቱለትን ሳቅ ብትተች ቅናት ይመስልብሃል..... ይቅርብህ......”
“ጉረኛ!... ጉረኛ ነገር ነሽ፤ ለማንኛውም የሆነ ስሜት ቀሰቃሽ ነገር እንዳለው አልካድኩም....”
“ስትል---?”
“.....በተለይ በዚህ ነፋሻማ ምሽት በስልክ ሲሰሙት መኝታ ክፍል መብራት ጠፍቶ፤ ልብስ ወልቆ.... አንሶላና ብርድልብሱ የትም ተዝረክርኮ  ......በኮበሌው መለክለክ ጉብሏ ስትስቅ፤ በውሸት ቁጣ አፏን ሲያፍናት.... በጣቶቹ መሃልና  ባፍንጫዋ እየሾለከ የሚወጣ ሳቅ ይመስላል.....ስላልተገራ --- ቆይ sorry.....ሄሎ”
“እ.... እየሰማሁህ ነኝ”
“ታዲያ ምነው ድምጽሽ ጠፋ”
“መቸም.. እንዲህ ተጫዋች ትሆናለህ ብዬ አስቤም አላውቅ...”
“ኧረ ባክሽ .....እኔ’ኮ...”
“ተው ተው!!.....እኔ’ኮ ብሎ እንደሚጀምር የወንድ ዲስኩር ያንገሸገሸኝ ነገር የለም......አንተማ እንዲያውም እንዲያው ነህ”
ወፍራሙ ሳቅዋ ስልኩን ስለሞላው ለመናገር መጠበቅ ግድ ሆነብኝ....ግን    “.....አንተማ እንዲያውም እንዲያው ነህ”  ስትል ምን ማለቷ ነው?
“ደግሞ እኔን ምንድነህ ልትይኝ ነው?”
“ጉረኛ!”
“እሰይ!..... በምን መስፈርት፤እንዲያው በሞቴ ከምን ተነሳሽ?”
“አረማመድህ.... ለሰው ያለህ ንቀት....”
“ኧረ በናትሽ....  ምንድነው እምታወሪው? እኔ ሰው ንቄ አላውቅም......”
“ሰው ባትንቅ ነው.... የኮንደሚንየሙ ሶሳይቲ በሙሉ የሚሰበሰብበት ሠረሞኒ ላይ የማትገኘው!”
ያልተካፈልኩበት ዝግጅት ትዝ ስለማይለኝ ግራ ተጋባሁ፡፡
“በትክክል........እኔ’ኮ...”  እንደገና አቋረጠችኝ
“በናትህ እንጭጭዋን ጓደኝነታችንን እንዳትጨፈልቃት፤.....እኔ’ኮ ብለህ ነገር አትጀምር..... ምን መሰለህ ይሄ ቃል የወንዶችን ትምክህት ለመዘርገፍ መንደርደሪያ በመሆን የሚያገለግል የቃል አቃጣሪ ስለሚመስለኝ አይመቸኝም....”
“እሺ! ይሁንልሽ.... ለቃሉም ለኔም ግን ያለ ስማችን ስም እንደተሰጠን በተከበረው የቃሉና የወንድ ትምክህት ትስስር ስም እንዲታወቅልን እንጠይቃለን”
ምን አከራከረኝ!
“እሺ... እዚህ ኮንዶሚንየም ከጥበቃዎች ውጭ ሰላም የምትለው አለ?    .....እነሱንም አስገድዶ ከመድፈር ባልተናነሰ ሁኔታ አስገድደው ሰላም ስለሚሉህ መሆኑ ሰው መናቅህን አያሳይም?”
ይች ልጅ ስለምንድነው የምታወራው? ኮሚኒቲው በሙሉ እገሌ ታመመ  ለሱ ንገሩት.....  መብራት ጠፋ ..... እሱን ጥሩት....  ጥበቃ ላይ ችግር እያንዣበበ ነው........ ለምን እሱን አታሳውቁትም ..... እከሊት እኮ ምጥ እያጣደፋት ነው...... በጥቅሉ እሱ የማያውቀው የላዳ ሹፌር፤ ዶክተር፤ ፖሊስ፤ ደላላ፤ ጠጋኝ ወ.ዘ.ተ የለም፤ እንዲሰማ አድርጉ የምባለውን ልጅ!.......
ለነገሩ ምን አገባኝ፤ እንደ መሰላት ትፈርጀኝ.......
“የኔ ሙጢ ሌላስ...?”
“በተለይ በኛ በሴቶች የምትጀነነው!”
 አሁንም አማላዩ ሳቋ፣ በጆሮዬ መንቆርቆሩን ቀጠለ ....
ግልጽነትዋ ደስ ይላል ...
ሴት አኩሪ እንጂ ጅንን ተብዬ ስለማላውቅ ድርቅናዋ ብል ይቀላል....
“ቆይ ቆይ ክፍል ሁለትን በኋላ ትስቂዋለሽ”  .... ሌላ ሳቅ-....
“አንቺ!.. በዚህ ከቀጠልሽ ፍርስርስሽ ወጥቶ፣ አንቺን ለመስራት ተገትሬ ማደሬ ነው........ ነገ ደግሞ ስራ አለብኝ”
“ኧረ ባክህ! ...ከኔ መፍረስ ያንተ ሲሰሩ ማደር ነው እሚቆጭህ?”   
ማኩረፏ ከድምጽዋ ይታወቃል፤ የሆነ የላይኛውን ከንፈሯን ሞጥሞጥ፤ የታችኛውን ጣል አድርጋ ያወጣችው አይነት........ድምጽ ሲያምር!
ከንፈሯን ጣል ስታደርገው ማሰብ ራሱ፣ በልጅነት ምጽዋት ሰጥቶ ለአምላክ እንዳበደሩ እርግጠኛ በመሆን የሚሰማን አይነት የመዝናናት ስሜት ይፈጥራል፡፡
“ስትፈርሽ ለመጠራቴ እርግጠኛ ብሆን እኮ፣ ሁሌ እንድትፈርሽ እመኝ ነበር...”
“አንተ!.. ስፈርስ አያማትም አሉህ?!”
“አንቺ!..  ካንቺ ህመም አብሬሽ የመሆኔ ደስታ አይበልጥብኝም አሉሽ?!”
“ውሸታም!!”
“በይ’ኮ  ሰብሰብ... ሸከፍ አርጊው”
“ምኑን?”
“ያን መከረኛ ከንፈርሽን ነዋ! ዛሬ ደግሞ ብሶበታል፤ እንቅፋት ሊመታው እኮ ነው!”  የወደድኩት ሳቋ መጣልኝ .... ተመስገን!
“ስትገርም!”
“በምን?”
“እንኳን እኔን እነ ሌንሲን’ኮ አይተሃቸው የምታውቅ አይመስለኝም ነበር..... ጭራሽ ከእነ ኩርፊያ!!”
“እነማናቸው ደግሞ እነ ሌንሲ?”
“እነዚያ ናቸዋ ስትወጣና ስትወርድ ደረጃ ላይ እየጠበቁህ ትኩረትህን ለመሳብ የሚያስካኩት......  እነዛ .. የሆነ ከሴት የማይጠበቅ ነገር ሁሉ የሚያደርጉት......”
ትዝ ሊሉኝ አልቻሉም፤ሲጀመር የኔ ትኩረት መች ከሴት ይነሳና ነው ትኩረቴን ለማግኘት መደከሙ!
“sorry... የምትያቸውን ልጆች የማውቃቸው አይመስለኝም......ምን አልባት.... የተሳሳተ..... ማለቴ....”
“ ......ታድያ!!”
“ምነው ምን ተገኘ?”
“አይ ... ተወው በቃ ........ሳላስበው ነው”
“አሃ!.. ሚስጥር መደባበቅ ጀመርን ማለት ነው.....”
“ሚስጥር አይደለም ....ያው የሴት ጉዳይ ስለሆነ ስላሳፈረኝ ነው”  
የምትገርም ልጅ ናት፤መሽኮርመሟን ሳይቀር ድምጽዋ .... /የጣቷን ጥፍር እየቀረጠፈች ብዙ ጊዜ መሬቱን......ሰረቅ አድርጋ እኔን የምትመለከት/ የአስራ አምስት ዓመት ኮረዳ አስመስሎ አመጣልኝ፡፡
“እሺ...  ሚጡ መሽኮርመሙን ስትጨርሽ  ብትወጅ በውድ፣ ባትወጅ ጆሮሽን ተቆንጥጠሸ እንደምታወጫት እወቂ...”
“.....እነግርሀለሁ ግን እንዳትስቅ፣ ሙድ ለመያዝ እንዳትሞክር.....”
 “ምን መሰለህ ---- እኔና ጎደኞቼ ባንነጋገርም ያንተን ኩራት ጥሶ ያንተ ጓደኛ ...ሌላው ቢቀር ካንተ ጋር ሲያወሩ ለመታየት እንወዳደራለን”
“እንዴ! ...እንዴት ነው እሱ ሳትነጋገሩ የምትፎካከሩት?”
“ይሄ የሴቶች ጉዳይ ነው.... ሊገባህ  አይችልም.......እኛ እንደናንተ ሙግት መግጠም፣ እርባናቢስ ቃላትን መደርደር ....ገንዘብ ማስያዝ ምስክር መቁጠር አይገባንም፤ በቃ እንግባባለን...”
አሃ.. የወንድን ትምክህት የምትፈራው፣ የሴት ትምክህት ባልተለመደ ሁኔታ ከፍ ያለ በመሆኑ እንዳይናድባት ነው፤ ድምጽዋ ግን ግሩም ነው፡፡
“በጣም አካበድሽ፤ ወንድን አብሮት የኖረ ሳይሆን ድንገት የበቀለ ዩፎ አስመሰልሽው”
“ይቅርታ አድርግልኝና ሴትን በመረዳት፣ ዩፎዎች እንደሚበልጡዋችሁ አልጠራጠርም”
“ኧረ ባክሽ!”
“ለምሳሌ ይሄን ዲያሎግ ከዩፎ ጋር አድርጌው ቢሆን፣ ቅድም በጣም ያሳቀኝን እንዳትፈርሽ ምናምን ብሎ ከማላገጥ ይልቅ ምክንያቱን እንደ ሴት ባይፈጥንም ሳይጠይቀኝ አያልፍም ነበር”
“ልክ ነሽ ልጄ!.... ምን ሆኜ ነው... ያልጠየኩሽ”
“ወንድ ሆነህ ነዋ!”
እርግጠኛ ነኝ ይሄ ሳቋ ጉሮሮዋን እንደ መከርከር እየቃጣው ስለሚወጣ ደስ የሚል ስሜት ይፈጥርላታል፡፡
“እሺ እንዳልሽ..... ለምን ነበር የሳቅሽ!?.....”
“የመስቀል ቀን የሰራኸኝ ማለቴ...... ያፈርኩት ትዝ ብሎኝ ነው”
“እኔ?”
“አዋ!!... ያውም ጥበቃውን እሺ ካለ ጥሩት ሲባሉ፣ እነ ሌንሲ ሳይቀድሙኝ እኔ እሄዳለሁ ብዬ ስመጣ....”
ሳቅ አቋረጣት...... እኔን ግን ፈጽሞ ግራ አጋባችኝ፤ እንደ ምንም በሳቅዋ መሃል ጣልቃ ገብቼ፤
“እኔ ሰው ተሰብስቦ ሳልወርድ አንቺ ልትጠሪኝ መጣሽ....”
“ወደህ!... ባክህ አታጥፋፋ ...ያውም የሚያምር ቢጃማ ለብሰህ በሩን ስትከፍትልኝ፣ በቤትህ ውበት ፈዝዤ... የምልህ ጠፍቶብኝ...ያፈጠጥክብኝ......”
“ምን!! የኔ ቤት ውበት ነው የሚያፈዝ!?”
አሁን እኔም አልቻልኩ፤ ከጣራ በላይ ሳቅሁ.....
“ያውም ሰው እየጠበቀህ መሆኑን ስነግርህ፣ በቀጥታ አልመጣም ያልከኝ ቀን!!”
“እኔ ምልሽ እየቀለድሽብኝ አይደለም አይደል?”
“ሂድ ጉረኛ” ኩርፊያዋ እየመጣ፤“ለዚያውም ስመለስ ጠርተህ፣ በቃ መጣሁ ሊለኝ ነው ብዬ በጉጉት ስዞር፣ እኔም ሆንኩ ሌላ ሰው ተመልሶ እንዳያስቸግርህ አላስጠነቀከኝም”
“እኔ አላስጠነቀኩሽም!..... ግን መጥፎ ነገር ብዬ ቢሆን ....ማለቴ  የሰራኸኝ የተባልኩት አልገባኝም”
“አንተ ውሸታም አትዋሽ..... ለነገሩ አንተ አይደለህም ጥፋተኛ፤ በጣም ከፍቶኝ ስለተመለስኩ እንባ እየተናነቀኝ  አልመጣም አንቺም ተመልሰሽ እንዳትመጭ  አለኝ ብዬ ተናገርኩ...... /ረዥም ሳቅ/ ያዝኑልኛል ብዬ ነው መሰል እንዲያጽናኑኝ ምናምን........  ሰው በሙሉ በሳቅ ሞተ፤ በተለይ እነ ሌንሲ ሲያስካኩ ድፍን የገርጂ ኮንደምኒየም እየሳቀብኝ ያለ......”
ቶሎ አቋርጬ፤
“የት?..የት ኮንደምኒየም?”
“ገርጂ ነዋ!”
“እንዴ... ገርጂ ነሽ እንዴ?”
“ታዲያ!.. አንተስ?”
“እኔማ ጎፋ ነኝ”
“እንዴ! ....ጎረቤት ነን አላልክም?”
“ታዲያ የስልክ ነዋ”
“ማለት?”
“ያንቺ 0912101536፣ የኔ 0912101537”
“እንዴ! ከኔ ቤት ፊት ለፊት የምትኖረው ቀብራራው አይደለህማ!”
“ኧረ! ... አያድርግብኝ! ቀብራራ ልሆን ቀርቶ ቀብራራ ሲያስጠላኝ!”
“እኔ ደግሞ ቀብራራ ያልሆነ ወንድ ሲደብረኝ!!”
ስልኩን ጆሮዬ ላይ ጠረቀመችው..........

Read 6251 times