Monday, 27 March 2017 00:00

መልአከ ሞትን ለሰባት ዓመታት ገዝቶ ያቆመው ባለቅኔ

Written by  ታደለ ገድሌ (ዶ/ር)
Rate this item
(11 votes)

  ደብረ ጥበብ ጎንጂ ቴዎድሮስ ገዳም ከአፈራቻቸው ታላላቅ ሊቃውንት ውስጥ በመጀመሪያው ረድፍ የሚሰለፈው የጎንጂ አገባብ ቀማሪው፤ የቅኔ ፈጣሪውና ዕፀ ሕይወት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተገለጸለት ፈላስፋው ተዋነይ ነው፡፡ ለሥራ ጉዳይ ወደ ቦታው ሔጄ በነበረበት ጊዜ  የጎንጂ ደብረ ጥበብ ቅዱስ ቴዎድሮስ  ገዳም ሰበካ ጉባዔ ሰብሳቢና አስተዳዳሪ ቄስ መልካም  በዜ በጽሑፍ በሰጡኝ ማስረጃ መሠረት፤ ተዋነይ የዚያው የጎንጂ ገዳም ተወላጅ ነው፡፡ ተዋነይ  አርከለዲስ  የተባለ ወንድምና ዐደይ የተባለች ታናሽ እህት ነበሩት፡፡ በገዳሙ እምነት ከላይ  ያለው  የእነ ተዋነይ ዝርያ ስለአልተመዘገበ ቢጠፋም ትውልዳቸው የቀጠለው  በታናሽ እህታቸው በወ/ሮ ዐደይ በኩል ነው፡፡
ለተዋነይና ለአርከለዲስ ግን ዘር የላቸውም ተብሎ ይታመናል፡፡  የዐደይ ዘሮች ግን እስከ አሁን ድረስ  ስለቀጠለ በዐፀደ ሥጋ የሚገኙ የተዋነይ ዘሮች ገዳሙ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ቄስ መልካም  በዜ ከተዋነይ ዘመዶች ጋር ሊያስተዋውቅኝ ቢያስቡም በጊዜ እጥረት ምክንያት ጉዳዩ ሳይሳካልኝ ቀርቷል፡፡
ተዋናይ ይኖርበትና ቅኔና ልዩ ልዩ ጥበባትን ያስተምርበት የነበረውም “በሀ ድንጋይ” ተብሎ ይጠራል፡፡ በሌላ በኩል ወዳጄ አቶ አያልነህ ሙላቱ በሰጡኝ አራት ገጽ ተኩል የሆነ የእጅ ጽሑፍ መሠረት፤ በአካባቢው ደሼት የሚባል ቦታ ያለ ሲሆን የተዋነይ የዘር ግንድ  የሆነው ዠረደሸት ከዚህ እንደተገኘ አባቶችን እማኝ አድርጎ ያቀርባል። ታላቂቱ የደብረ ጽላልሽ አማኑኤል ገዳም  የቅኔ  መምህርት የነበሩት እመት ገላነሽ ሐዲስም  ከዚህ ከዠረደሽት ዘር እንደተገኙና ከተዋነይ ጋር ዘመዳሞች እንደሆኑ ጽሑፉ ያትታል፡፡ የጽሑፉ ይዘት በዚህ መጣጥፍ  መጨረሻ ላይ ሰፍሯል፡፡
በቄስ መልካም በዜ ገለጻ መሠረት፤ ተዋነይ  የቅኔና የጥበብ ሰው የሆነው ተምሮ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው፡፡ ተዋነይ ቅኔውን የተማረው  ከሰው  ሳይሆን በመንፈስ ደርሶት ነው  ብለው አባቶች ያምናሉ፡፡ እዚህ ቦታ ሔዶ እገሌ ከተባለ መምህር ቅኔውን ተማረ የሚል ምንም ታሪክ አልተገኘም፡፡ እናም እዚያው ጎንጂ ውስጥ  በመንፈስ  ቅዱስ ተምሮትና በመንፈስ ቅዱስ ደርሶት  ቅኔን ሲያስተምረው ኖሯል፡፡
ለዚህም ተዋነይ ጎንጂ መወድስ ተቀኝቶ እንደገናም በደመና ተጠቅሶ በአንድ ጊዜ ጎንደር በመገኘት ዕጣነ ሞገር መቀኘቱ የመንፈስ ቅዱስ  ኃይል ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በገለጠለት ጥበብና እውቀት ተዋነይ በጣና ሐይቅ ላይ በእግሩ ይመላለስ ስለነበር ነው፡፡ ለዚህም ነው፡-  
“ተዋነይ በጣና፤
ይመስላል ደመና ፡፡” የተባለው፡፡
ተዋነይ በተለይ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን ያምናትና ያከብራትም ስለነበር ለራሱ ብጽዓት በመግባት በየቀኑ ሙሉ ቤት ቅኔ ያደርስላት ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ተዋነይ የደብረ ጥበብን ሊቃውንት ለመጋበዝ ፈለገና ድግስ አስደገሰ። ጥበቡንም አስቀድሞ ለፍየል አብልቶ በኋላ አሳረዳት። ታናሽ እህቱ  ዐደይ ወጥ ሠራች፡፡ ወጡንም እንዳትቀምሺው ብሎ አስጠነቀቃት፡፡ እህቱ ዐደይ ግን ወጡን እንዳትቀምሺው የተባለቺውን ማስጠንቀቂያ ወደ ጎን ትታ፣ ወጡን በወጥ እንጨት ጠንቆል አድርጋ ቀመሰቺው፡፡ ወዲያውም ምሥጢረ ጥበብ፤ ምሥጢረ ቅኔ ተገለጸላት፡፡ ቆይቶ ተዋነይ  ለተጋባዦች ቦታ ለማዘጋጀት ወደ ቤት ሲገባ፣ እህቱ ዐደይ በቅኔ ጥበብ ተሞልታ ቆየችው፡፡ የሚከተለውንም ቅኔ ዘርፋ  ሰደበቺው፡፡
“ጌጤር እንበለ ጌጤር፤
ለልብከ አልቦቱ ምሥጢር፤”  አለቺው፡፡
ተዋነይም ለታናሽ እህቱ ለዐደይ “ዐደይ” የተባለች ዐመዳም ላም ነበረቻትና
“ዐደይ እንበለ ዐደይ፣
ለገጽኪ አልበቱ ላህይ፡፡” ብሎ በመቀኘት ሰደባት፡፡
ይህ ቅኔ ሲፈታ ዐደይ አልባ የሆንሺው ዐደይ ለፊትሽ ደምግባት የለውም ማለት ነወ፡፡ ተዋነይ ይህንን ቅኔ ከተቀኘ በኋላ ወጡን አስደፍቶና ሌላ ወጥ አሠርቶ ካህናቱን በመጋበዝ ሸኝቷቸዋል፡፡
የዚያችኑ መተተኛና አስማተኛ ፍየል ጨጓራ ለማጠብ  አንድ የቤት ሠራተኛው (አሽከሩ) ታዘዘና ወደ ወንዝ ወርዶ ኖሮ፣ ሥጋው ሳስቶና ጎምዥ ኖሮ ከፍየሊቱ ጨጓራ ላይ ጎረድ አድርጎ አንድ ጉርሻ እንደ ጎረሰ፣ ያ ምንም የማያውቀው ጨዋ የቤት ሠራተኛ፣ ዋዜማ ቅኔ ዘርፎ ተቀኝቷል፡፡ ቅኔው የሚከተለው ነው፡፡
ጥሉል ጥሉለ ግርማ ሐራ መርመሬዎን ያርብህ ሐራ መርምርቄ  ጎርጉዋይ፡፡
 ግዮን ጋላዮን ጋለነ ኮራነ ሐቅለ  ኤቦር ማይ፡፡
ግበ ጊዱጋዳ ጋይድ ተርሴ ተርሌ ሉቃስ ሥቃይ፡፡
 አኮኑ ኤልያስ መስፍነ ፀሐይ ፡፡
 ዘነደሮ አድማስ ባሕርይ፡፡
ጨጓራ አጣቢው  ከላይ የተገለጠውን ዋዜማ ቅኔ የተቀኘውና ሲለፈልፍ የዋለው ጨጓራ ሲያጥብበት በነበረው  ወንዝ ዳር ነው፡፡
ከላይ እንደተገለጠው ተዋነይ ቅኔ ያስተማረበት ጎጥ በጎንጂ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ጎጡ አግዳሚ ልዩ ቦታው ቡሐ ድንጋይ  በመባል ይታወቃል፡፡ ተዋነይ በዚያው ቦታ በማስተማር ላይ እያለ ለዘለዓለም የሚኖረውንና ዕፀ ሕይወት የተባለውን መድኃኒት ከሚኖርበት ቤት ደጃፍ ላይ  ስለቀበረ ሊገድለው የተላከውን መልአከ ሞት ከበሩ ላይ ለ7 ዓመት አቆመው፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅም መልአከ ሞትን ለ10  ዓመት  ከበሩ ላይ እንዳቆመው ተዋነይ  አልሞትም ብሎ ለ7 ዓመት ከበሩ ላይ  ገትሮታል፡፡
በመጨረሻም እመቤታችን በገሐድ ተገለጠችለትና “ምነው ልጄ ወዳጄ ተዋነይ ልጄ ወዳጄ ፈጣሪህ ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተውን ሞት አልሞትም ብለህ እስከ መቼ መልአከ ሞትን አቁመህና አሥረህ ትኖራለህ” ብላ  ጠየቀቺው፡፡ ተዋነይም “ እመቤቴ ሆይ! እኔ ጌታየን በድየዋለሁ የት እገባ ይሆን?” ይላል፡፡ እመቤቴም “አይዞህ እኔ አለሁልህ” ስትለው ሞትን እየፈራና እየተንቀጠቀጠ የሚከተለውን  መውድስ ተቀኘ፡፡
መውድስ
እፈርህ አንሰ ወእርእድ በይነ ሀምስቱ ግብራት እለ ሀለሙ ምስሌየ፡፡
አሐዱ በሞት እንዘ ትትፈለጥ ነፍስየ፡፡
ወካልዕ በመቃብር በልማደ ሥጋ ትወርድ ነፍስየ፡፡
ወዘሣልስ በአምላኪየ ፤እንዘ በቅድሜሁ /እንዘ ቅድመ ገጹ/እቀውም
 ይርእዱ አባላትየ፡፡
ራብዕሂ ፍትሐ ኩነኔ እመ ትሰምእ ዕዝንየ፡፡
ወሐምስ መንገለ ደይን እንዘ ይወስዱኒ አፅራርየ።
ወዝኩሉ ነገር እምይኩን ብየ፡፡
ከዊኖተ ደም /ማይ/ እምትየሰኒ  በማሕፀነ ቅድስት ወላዲትየ፡፡
የቅኔው ትርጉም
ከእኔ ጋር ስለአሉ አምስት ነገሮች  እፈራለሁ እንቀጠቀጥማለሁ፡፡
፩ኛ ነፍሴ  ከሥጋዬ  ስትለይ ፤
፪ኛ  በሥጋዊ ባሕርይ ሥጋዬ ወደ መቃብር ስትወርድ፤
፫ኛ  አካላቶቼ እየተንቀጠቀጡ በአምላክ ፊት ስቆም፤
፬ኛ  የኩነኔን ፍርድ ጆሮየ ስትሰማ፤
፭ኛ ወደ ሥቃይ ቦታ ጠላቶቼ /አጋንንት/ ሲወስዱኝ፤ ይህ ሁሉ ነገር በእኔ ላይ ከሚፈጸም በተባረከቺው እናቴ ማሕፀን ውስጥ  ደም /ውሃ/ ሆኜ ብቀር /በቀረሁ/ የተሻለ ነበር ብሎ ፀፀቱን  ገልጧል፡፡
ይህንን ቅኔ ከተቃኘ በኋላ በደጃፉ ላይ  የቀበረውን  ዕፀ ሕይወት “ቆፍራችሁ አውጡ” አለና  ወገኖቹን  አዘዘ፡፡ ወገኖቹም  የተቀበረውን  ዕፀ ሕይወት አውጥተው ዞረው ቢመለከቱት ተዋነይ ለሰባት ዓመት የተኛበትን አልጋ እንደ መቃብር ቆጥሮት ሰውነቱ አፈር፤ አመድ  ሆኖ ተገኘ፡፡
በዚህ ጊዜ ዐደይ እህቱ በወንድሟ በተዋነይ ሞት በእጅጉ ስለአዘነች እንዲሁም ሌላው ወንድማቸው አርከለዲስ  አስቀድሞ ስለሞተባት ርጥብ ሬሳ ደርቅ ያስነሣ  ሆኖባት በሁለቱም ወንድሞቿ ሞት ምክንያት ደረቷን እየመታች
“ተዋነይ ጨረቃ አርከለድስ ፀሐይ፤
ደመና ሞት መጥቶ ሸሸጋችሁ ወይ? ጋረዳችሁ ወይ?
ተዋነይ ወይናችን አብቦ ሳያፍር፤
በረዶ ሞት መጥቶ ደባለቀው ከዐፈር፡፡” በማለት ሀገሩን አስለቅሳለች  ይባላል፡፡
ይህም ተዋነይ፤ ዐደይና አርከለዲስ የጎንጂ ደብረ ጥበብ ቴዎድሮስ ገዳም ተወላጆች መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ተፈልገው  የተገኙት የተዋነይ ቅኔዎች  በብላቴን ጌታ ኅሩይ መጽሐፈ ቅኔ /1918 )፤በመልከ ብርሃን አድማሱ  ጀምበሬ ዝቅረ ሊቃውንት  1963 እና በሌሎች መጻሕፍት ታትመዋል፡፡

Read 9369 times