Monday, 27 March 2017 00:00

‹‹የዚህች አገር ዲሞክራሲ ቁልቁል እየሄደ ነው››

Written by  ቢኒያም ከበደ (ቤን)
Rate this item
(8 votes)

  ከአዘጋጁ፡- ከዚህ በታች የቀረበው አስተያየት ጋዜጠኛ ቤኒያም ከበደ (ቤን) “Ethiopian First” በተባለው የራሱ ድረ ገፅ ከለቀቀው ቪዲዮ የተወሰደ ሲሆን ሃሳቡ የተናጋሪውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ነው፡፡
                 
       ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፓርላማ ቀርበው አንድ የተናገሩት ንግግር ነበር፡፡ እጅግ በጣም ነው ያሳዘነኝ፡፡ እውነቴን ነው… በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ያፈርኩበት፤ አንገት የሚያስደፋ ሂደት ያየሁበት ነው፡፡ እኔን ወክለህ ተናገርልኝ ብሎ ህዝብ የላካቸው የህዝብ እንደራሴዎች ተሰብስበው ያነሱት ጥያቄ ነበር። “አርሶ አደሩ ከመሬቱ እየተነሳ ነው፣ አርብቶ አደሩ ከመሬቱ እየተነሳ ነው፤ በተገቢው ግን ካሳ እየተከፈለው አይደለም፡፡ አንደኛ በድሮው ስሌት ነው የሚታሰብለት፤ እሱም ቢሆን ገንዘቡ እየተሰጠው አይደለም፤ ህዝባችን ተማሯል፡፡ ህዝቡ ልማት ጠልቶ አይደለም፤ ነገር ግን በተገቢው እየደረሰው አይደለም፤ የእናንተ ሹመኞች እየሰጡት አይደለም…” በሚል ሁኔታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዴት አድርገው ይመልሱለታል ብዬ ሳስብ … በጣም በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹አንድ ክልል አለ ስሙን የማልነግራችሁ… እዚያ ደግሞ ይገርማችኋል …100 ሚሊዮን ብር ለካሳ ብለን ሰጥተን ተበልቷል፤ ክልሉን ግን አልነግራችሁም›› አሉ፡፡ አስቡት ----- እዛ ያሉት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባልኮ ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብን ወክለው የተገኙ ከፍተኛው የሀገሪቱ ወኪል ናቸው፡፡ የህዝብ እንደራሴ ናቸው። እዚያ አዳራሽ ውስጥ የተቀመጠው የኢትዮጵያ 90 እና ከዚያ በላይ ሚሊዮን ህዝብ ወኪል ነው። ህዝቡ በሙሉ እዚያ አለ ማለት ነው፡፡ ‹‹ክልሉ ማን እንደሆነ አልነግራችሁም፤ ግን 100 ሚሊዮን ብር ተበልቷል …›› እንዴት አይነት ድፍረት ነው! እኔ የገረመኝ ደግሞ… የህዝብ ተወካዮቹም አመስግነው መውጣት ነው፡፡ እንዴ! ዲሞክራሲያችን እንዴት የሞተ ቢሆን ነው!? ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኮ የመናገር ግዴታ አለባቸው…፡፡ እዚያ የተቀመጠው’ኮ የህዝብ እንደራሴ ነው፡፡ መቶ ሚሊዮኑ ከየት ነው የመጣው? ከኢትዮጵያ ግብር ከፋይ ህዝብ ላይ እኮ ነው በጀት የተሰጠው፡፡ ‹‹ከበጀቱ ላይ መቶ ሚሊዮን ተወስዷል ግን አልናገርም›› ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ፡፡ ፓርላማው እንዲህ ሲባል እንዴት አይቆጣም! የህዝብ ተወካይ’ኮ ነው፡፡ ‹‹ያ ገንዘብ እኮ እኔ ተመርጬ የመጣሁበት፣ እንደራሴ ሁነኝ ያለኝ ህዝብ፣ የግብር ከፋዩ ገንዘብ ነው፤ ስለዚህ ያገባኛል፡፡ እኛ እኮ ነን በጀቱን የፈቀድንለት፤ ስለዚህ ያ በጀት ከተበላና ከተዘረፈ የማወቅ መብት አለን። የማወቅ መብት ብቻ አይደለም፤ እንዲያውም ዘራፊዎቹና ሌቦቹ ፍርድ ማግኘታቸውን ተከታትለን የማወቅ መብት አለን›› ማለት ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን የፓርላማ አባላቱ አጨብጭበው ብቻ ወጡ፡፡
እውነቴን ነው የምለው… የኛ ዲሞክራሲ ሙት መሆኑን ያየሁት እዚያ ላይ ነው፡፡ በጣም ያሳፍራል፡፡ 95 ሚሊዮን ህዝብ አደራ ብሎ የላካቸው ሰዎች ጠ/ሚኒስትሩ ‹‹100 ሚ. ብር ተበልቷል፤ ግን የት ክልል እንደሆነ አልነግርም›› ሲሏቸው አመስግነው ወጡ፡፡ አንድ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል እንኳ ከዚያ በኋላ በደብዳቤም ሆነ በሚዲያ ያወገዘ የለም። ለእኔ የዚህች ሀገር ዲሞክራሲ ቁልቁል እየሄደ ለመሆኑ ከዚህ በላይ ማሳያ የለም፡፡ ፓርላማችን ሙት ነው። ምክንያቱም አደራ የተባለውን እየሰራ አይደለም። መጠየቅ አልቻለም፡፡ እሳቸው ራሳቸው እንዴት ሊሳሳቱ እንደቻሉ ገርሞኝ ነበር፡፡ ምናልባት አንድ እሳቸው ሊሳሳቱ ይችላሉ ብዬ ተውኩት፡፡ 547 የምክር ቤት አባላት ግን እንዴት አጨብጭበው ይወጣሉ?! ይሄ መቀየር አለበት፡፡
እውነቴን ነው የምለው… የኢትዮጵያ ሁኔታ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ በጣም ቁልቁል ሄደናል፤ መንግስትም አለቀለት፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርአት አለን የምንል ከሆነ ግን ፓርላማው መብት አለው የምንል ከሆነ፣ “100 ሚሊዮን ብር ካንተ ላይ ተወስዶ ጠፍቷል፤ እኔ አውቃለሁ፤ ግን አልነግርህም፤ ይሄን ሚስጢር ለማወቅ አንተ ተገቢ አይደለህም›› የሚል ጠቅላይ ሚኒስትር … ይሄንን እሺ ብሎ አጨብጭቦ የሚወጣ የህዝብ ተወካይ… እንደ አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በጣም ነው ያፈርኩት ----- በጣም፡፡
የእነዚህ ነገሮች ሁሉ ---- የእነ ቆሼ አካባቢ፣ የእነ ጋምቤላም አለ … ለምሳሌ ቆሼ አካባቢ ህፃናትን ጨምሮ 100 ምናምን ህዝብ አልቆ፣ መንግስት የሀዘን ቀን ለማወጅ 4 ቀን ፈጅቶበታል፡፡ መአት ህዝብ ሞቶ አራት ቀን መፍጀት ነበረበት!? እሱ ብቻ አይደለም፤ ፕሬዚዳንቱ ጭምር እዚያ ሄደው ለማየት 5 ቀን ፈጀባቸው፡፡ አስቡት እንግዲህ ---- ከ4 ኪሎ ቤተ-መንግስት ቆሼ ለመሄድ 20 ደቂቃ የሚፈጅ አይመስለኝም፤ ያውም እነሱ መንገድ ተዘግቶላቸው ስለሆነ፣ 4 እና 5 ደቂቃ ቢፈጅባቸው ነው፤ ግን 4 ቀን ነው የፈጀባቸው፡፡ ይሄ ተገቢ ነው!? አካውንተቢሊቲ (ተጠያቂነት) አለ? የለም! ለምንድነው የሌለው? የቆሼውንም የጋምቤላውንም ከኤርትራ ጋር ያለውንም ደመርኩትና ለምንድን ነው እንደዚህ የሆነው? መፍትሄውስ ምንድነው? በሚል ማሠብ ጀመርኩኝ፡፡
በእኔ እይታ የዚህ ሁሉ ምክንያቱ የዲሞክራሲያችን መሞት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ ቆሼ ወይም ኮልፌ ክፍለ ከተማ አካባቢ በሚቀጥለው ምርጫ እንደሚያሸንፍ አውቋል… ስለዚህ ያንን ህዝብ ሄዶ ማስተዛዘን፤አለሁልህ አይዞህ ማለት አይጠበቅበትም፣ በቃ ምክንያቱም እንደሚያሸንፍ አውቆታል… አሁን ባለው ሲስተም ከተሄደ፣ በሚቀጥለው ምርጫ 99.6 ፐርሰንትም 99 ፐርሰንትም ኢህአዴግና አጋሮቹ ማሸነፋቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ ኢንሴንቲቭም የለም‘ኮ ለመሄድ።
 ሠሞኑን ተመልክታችሁ ከሆነ ኦሮሚያና ሶማሌ አካባቢ ህዝብ እየተላለቀ ነው፡፡ እንዴት ነው ሲባሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንድን ነው ያሉት… “ህዝባችን ጋ ምንም ችግር የለም፤ ሚሊሻ ከሚሊሻ፣  የፖሊስ ሃይሉ ከፖሊስ ሃይል እና የአመራሩ ችግር ነው›› አሉ። ህዝቡ ጋ ችግር የለም፤ እኛ የምንመራው አመራር ነው ህዝብን እያመሠ ያለው ማለታቸው ነው፡፡ ምን አይነት ድፍረት ነው?! ወልቃይት ጋ ስንሄድ ‹‹ህዝቡ ጋ ምንም ችግር የለም፤ ችግሩ ያለው በሁለቱ ክልል ያሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋ ነው›› አሉ… ህዝብ “እባካችሁ አመራሮቻችሁን አደብ አስገዙ፤ህዝብ ለህዝብ እያስተላለቁ ነው” እያለ ነው፡፡ መንግስት ‹‹እናውቃለን ችግሩ ያለው ከፍተኛ አመራሩ ጋ ነው›› ይላል… ሌላው ደግሞ ይቀጥላል፡፡

Read 3771 times