Monday, 27 March 2017 00:00

ተቃዋሚዎች “ያለገለልተኛ አደራዳሪ ድርድር አይካሄድም” አሉ

Written by 
Rate this item
(12 votes)

የድርድሩ ቀጣይ እጣ ፈንታ በኢህአዴግ እጅ ነው”

ከገዥው ፓርቲ ጋር የቅድመ ድርድር መመሪያ ላይ ውይይት እያደረጉ ያሉት 20 ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ያለ ገለልተኛ አካል ድርድር እንደማይኖር ያስታወቁ ሲሆን ኢህአዴግ ጉዳዩን ለማጤን ቀጠሮ ወስዷል፡፡
ፓርቲዎቹ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 9፣ ቀኑን ሙሉ ባደረጉት ውይይት ቀደም ሲል በዙር መድረክ እየመራን እንደራደር የሚል ሃሳብ ያቀረቡ ተቃዋሚዎች አቋማቸውን ለውጠው፣ ድርድር ያለ ገለልተኛ አደራዳሪ አይሆንም ሲሉ የተፈጠሙ ሲሆን ኢህአዴግና አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ በዙር መድረክ እየመራን መደራደር አለብን በሚል አቋም በመጽናታቸው መግባባት ላይ ሳይደረስ ቀርቷል። ይሄን ተከትሎም ኢህአዴግ ጉዳዩን በድጋሚ ለማጤን ጊዜ እንዲሰጠው የጠየቀ ሲሆን በመጪው ረቡዕ መጋቢት 20፣ አቋሙን እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል፡፡
የቅዳሜውን ውይይት አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ፤ በእለቱ ሁሉም ተቃዋሚዎች ገለልተኛ አካል ያደራድረን የሚል አቋም መያዛቸው ያልጠበቁት መሆኑን ገልፀው፤ “ፓርቲያችን በአደራዳሪዎች ገለልተኛነት ላይ የተሸራረፈ አቋም የለውም›› ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ አቋሙን ካልቀየረ የድርድሩ ቀጣይነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረውም አቶ ሙሉጌታ አስታውቀዋል፡፡
የኢዴፓ ዋና ፀሃፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ከአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ በስተቀር ሌሎቹ ገለልተኛ አካል ያደራድረን የሚለው አቋማቸው የፀና መሆኑን ጠቁመው፤ ኤዴፓም ይሄን አቋም እንደማይቀይር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ገለልተኛ አካል ካላደራደረ ኢዴፓ በድርድሩ ሊቀጥል አይችልም›› ብለዋል - አቶ ዋሲሁን፡፡
“ኢህአዴግ ወደ ብዙኃኑ አቋም ይመጣል የሚል ተስፋ አለኝ” ያሉት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ፤ የድርድሩ ቀጣይ እጣ ፈንታ በኢህአዴግ እጅ ነው ብለዋል፡፡  
21 ፓርቲዎች የሚያደርጉት ስብሰባ ውይይት እንጂ ድርድር ሊባል አይችልም የሚል አቋሙን ያፀናው መድረክ በበኩሉ፤ በዚህ ሁኔታ በድርድሩ እንደማይቀጥል የአመራር አባሉ አቶ ጥላሁን እንደሻው ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል። መድረክ ለገዥው ፓርቲ ሁለት አማራጮችን ማቅረቡን የጠቆሙት አቶ ጥላሁን፤አንደኛው ተቃዋሚዎች በመድረክ እንዲወከሉና ከኢህአዴግ ጋር እንዲደራደሩ አሊያም ኢህአዴግ ከሌሎቹ ጋር ከሚያደርገው ድርድር ጎን ለጎን ለብቻው ከመድረክ ጋር እንዲደራደር ሀሳብ አቅርቦ ምላሹን በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢህአዴግ ለዚህ ፍቃደኛ ካልሆነ መድረክ ከ21 ፓርቲዎች ጋር  ለድርድር እንደማይቀርብና ከድርድሩ እንደሚወጣ አቶ ጥላሁን አስታውቀዋል፡፡
‹‹ምንም ውጤት ያላመጣውን የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን የሚመስል ውይይት እንዲደረግ አንፈልግም” ያሉት የአመራር አባሉ፤ ‹‹የህዝቡን ችግር ነቅሰን አውጥተን ተጨባጭ መፍትሄ እንዲሰጥባቸው ነው የምንፈልገው” ብለዋል፡፡ ‹‹የታሰሩ ፖለቲከኞችም እንዲፈቱ ከተፈለገ ጠንካራ ድርድር ማድረግ አለብን›› ሲሉም አክለዋል፡፡   

Read 3769 times