Monday, 27 March 2017 00:00

የ“ቆሼን” ቀጣይ እጣ ፈንታ ለመወሰን ጥናት እየተደረገ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

ለተጎጂዎች በነፍስ ወከፍ የ1 ሚ. ብር ካሳና ቦታ ሊሰጥ ነው
መስተዳደሩና ቴሌ በSMS የማቋቋሚያ ገንዘብ እያሰባሰቡ ነው

   የአዲስ አበባ አስተዳደር በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሞት ምክንያት የሆነውን የ“ቆሼ” እጣ ፈንታ ለመወሰን ጥናት እያደረገ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን ለተጎጂዎች የ1 ሚሊዮን ብር ካሳና ምትክ ቦታ በመስጠት ለማቋቋም መወሰኑ ታውቋል፡፡
ተጎጂዎች ከአስተዳደሩ ጋር በቀጣይ እጣ ፈንታቸው ላይ ሰሞኑን የመከሩ ሲሆን ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ጀሞ አካባቢ ለመኖሪያ ቤት ተስማሚና የለማ ቦታ እንዲሁም ለእያንዳንዱ አባወራ የ1 ሚሊዮን ብር የቤት ግምት ካሳ እንደሚከፈል ፋና ብሮድካስቲንግ ዘግቧል፡፡
ጉዳት በደረሰባቸው ቤቶች ተከራይ የነበሩ ተጎጂዎች የ10/90 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በኪራይ እንዲያገኙ ለማድረግ መታቀዱም ታውቋል። ተጎጂዎቹ ወደ ግል ቤታቸው እስኪገቡ ድረስ አስተዳደሩ የቤት ኪራይ እንደሚከፍልላቸው ተገልጿል፡፡
በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የአስተዳደሩ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዳግማዊት፤ በጉዳዩ ላይ ገና ውይይት እየተደረገ መሆኑንና ተጎጂዎች በጊዜያዊነት እርዳታ የሚያገኙበትና በዘላቂነት የመኖሪያ ቤትን ጨምሮ መቋቋም በሚችሉበት ጉዳይ ላይ እየተመከረበት ነው ብለዋል፡፡
ለግማሽ ክፍለ ዘመን ቆሻሻ መጣያ ሆኖ የሰው ህይወት የቀጠፈው “ቆሼ” ቀጣይ እጣ ፈንታን ለመወሰን ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት መጀመሩን የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ ጥናቱ የሚያመጣቸውን ውጤቶች በመንተራስ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል “ቆሼ”ን ለመዝጋት የረጅም ጊዜ እቅድ መያዙንና አሁን የሚደረገው ጥናት በአጭር ጊዜ እጣ ፈንታው ምን ይሁን የሚለውን የሚወስን ነው ብለዋል- ኃላፊዋ፡፡ አስተዳደሩ አሁንም “ቆሼ”ን በቆሻሻ መድፊያነት እየተጠቀመ መሆኑ ታውቋል፡፡
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በቅርቡ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ለደረሰው ጉዳት መንግስት እስከ አሁን ማንንም ተጠያቂ ማድረግ እንዳልቻለና የአደጋውን የምርምራ ውጤት በመጠባበቅ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ለተጎጂዎች ከተለያዩ ወገኖች ከ76 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ የተሰበሰበ ሲሆን ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ በአይነት መሰብሰቡ ታውቋል። መስተዳደሩ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር በአጭር የሞባይል መልዕክት ለተጎጂዎቹ ማቋቋሚያ የሚሆን ገቢ-ሰሞኑን ማሰባሰብ መጀመሩም ታውቋል፡፡  


Read 2994 times