Monday, 27 March 2017 00:00

የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን እንድትፈርስ ፍ/ቤት ወሰነ

Written by 
Rate this item
(25 votes)

የደብሩ አስተዳደር ይግባኝ ጠይቋል

       በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 12 ውስጥ የምትገኘው፣ የየካ አባዶ ደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን፣ በሕገ ወጥ ይዞታ ላይ፣ ያለግንባታ ፈቃድ መሠራቷን የገለጸው ፍ/ቤት፣ እንድትፈርስ ወሰነ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት፣ የካ ምድብ ችሎት፣ ባለፈው ረቡዕ በሰጠው ውሳኔ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዳትፈርስ በደብሩ ለቀረበው የ“ሁከት ይወገድልኝ” ክሥ፣ ኅዳር 28 ቀን 2009 ዓ.ም አስተላልፎት የነበረውን የእግድ ትእዛዝ ማንሣቱን አስታውቋል፡፡
በከሣሽ የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያንና በተከሣሽ የወረዳው ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት መካከል የቀረቡትን አቤቱታዎችና ሲካሔድ የቆየውን የቃል ክርክር መመርመሩን የገለጸው ፍ/ቤቱ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ የተሠራችበትን ቤትና ቦታ፣ ከሰኔ 24 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በስጦታ ያስተላለፉት ግለሰቦች፤ ይዞታውን በሕጋዊ አግባብ እንዳገኙት የሚያስረዳ ማስረጃ በከሣሽ በኩል አለመቅረቡን ጠቅሷል፡፡
ቤቱም፣ የሚመለከተው የከተማው አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽ/ቤት ፈቃድ ሰጥቶ ስለመሠራቱ ማስረጃ አለመቅረቡንና በመሥመር ካርታ ወይም በ1997 ዓ.ም የአየር ካርታ ላይ እንደማይታይ፣ የክፍለ ከተማው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽ/ቤት ማረጋገጡን አስረድቷል፡፡
ለክሡ መነሻ የሆነው ቤት፣ የቤተ ክርስቲያን ቅርጽ እንዲኖረው ተደርጎ የተሠራውም፣ በሕግ ሥልጣን ከተሰጠው የከተማው አስተዳደር አካል፣ የግንባታ ፈቃድ ሳይገኝ መሆኑን በውሳኔው ጠቅሷል፡፡
የወረዳው ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትፈርስ፣ ለደብሩ የሰጠው ማስጠንቀቂያ፣ በሕግ የተሰጠውን ሓላፊነት መወጣቱ እንጂ የሁከት ተግባር አይደለም፤ በደብሩ የቀረበውም ክሥ ተቀባይነት የለውም፤” ሲል ወስኗል፡፡ ለክሡ መነሻ በሆነው ግንባታ ላይ ቀደም ሲል ተላልፎ የነበረው የእግድ ትእዛዝ መነሣቱንም አስታውቋል፡፡  
በሌላ በኩል፣ የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ የፍ/ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ መጠየቁ ታውቋል፡፡  

Read 7680 times