Monday, 20 March 2017 00:00

ካርሎስ ቀበሮው ብዙ ሰው ባለመግደሉ እንደሚጸጸት ገለጸ

Written by 
Rate this item
(16 votes)

  - ከ43 አመታት በፊት በፈጸመው ግድያ ተከስሶ ፍ/ ቤት ቀርቧል
                    - የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ያለፉትን 23 አመታት በእስር አሳልፏል

      ካርሎስ ቀበሮው በሚል ስሙ የሚታወቀውና ከአለማችን ቀንደኛ ገዳዮች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ኢሊች ራሚሬዝ ሳንቼዝ፣ እስር ቤት ከመግባቱ በፊት ብዙ ሰዎችን ባለመግደሉ እንደሚጸጸት፣ ከ43 አመታት በፊት በፓሪስ በሚገኝ የገበያ ማዕከል በተፈጸመ ወንጀል ተከስሶ ባለፈው ሰኞ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት መናገሩ ተዘገበ፡፡
እ.ኤ.አ በ1974 የተከሰተውንና 2 ሰዎች ለሞት፣ 34 ሰዎች ደግሞ ለመቁሰል አደጋ የተዳረጉበትን የቦምብ ጥቃት ፈጽሟል በሚል ፍርድ ቤት የቀረበው ካርሎስ፤ ከመታሰርህ በፊት በነበረህ የገዳይነት ህይወት ዘመንህ የምትጸጸትበት ነገር አለ? በሚል ከዳኛው የቀረበለትን ጥያቄ ሲመልስ፣ “አዎ… ልገድላቸው ሲገባኝ ያልገደልኳቸውን ሰዎች ሳስብ ይጸጽተኛል” ማለቱን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የ67 አመቱ ካርሎስ፣ ባለፈው ሰኞ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት የሙያ መስክህ ምንድን ነው በሚል ከችሎቱ ለቀረበለት ጥያቄ፣ ብቁ አብዮተኛ ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ዕድሜውን ሲጠየቅም፡- 17 ነው፤ ደስ ካላችሁ 50 አመት ጨምሩበት ሲል ያላገጠ ሲሆን  የተከሰሰበትን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን አስረድቷል፡፡
ካርሎስ ከ43 አመታት በኋላ የተከሰሰበትን የግድያ ወንጀል መፈጸሙን የሚያስረዱ 17 ያህል ምስክሮች በቀጣይ የምስክርነት ቃላቸውን እንደሚሰጡ የጠቆመው ዘገባው፤ የምስክሮችን ቃል የመስማቱ ሂደት በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጧል፡፡
ከ23 አመታት በፊት በፈረንሳይ ልዩ ሃይል ክትትል በካርቱም በቁጥጥር ስር የዋለው ቬንዙዋላዊው አደገኛ ገዳይ ካርሎስ፤ በ1970 ዎቹ እና 80 ዎቹ በፈጸማቸውና ባስፈጸማቸው በርካታ የግድያ ወንጀሎች የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ከዚያ ጊዜ አንስቶ በፈረንሳይ በእስር ላይ ይገኛል፡፡

Read 6488 times