Monday, 20 March 2017 00:00

የዓለም አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዓይኖች ወደ ኢትዮጵያ ያማትራሉ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(5 votes)

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (አይሲኤኦ) ጋር በመተባበር፣ በአፍሪካ አኅጉር ለመጀመሪያ ጊዜ አራተኛውን ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም እንደሚያዘጋጅ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ከማኔጅመንት ቡድን አባላት ጋር በመሆን ሰሞኑን በአቪዬሽን አካዳሚ በሰጡት መግለጫ፤ ‹‹የአቅም ግንባታ ሥልጠናን በጋራ ማሳደግ›› (ቱጌዘር፣ ኢንሃንሲንግ ትሬይንግ ቱ ቢዩልድ ካፓሲቲ) በሚል መሪ ቃል፣ ከሚያዝያ 3 እስከ 5 2009 በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም፣ በዓለም አቀፍ  አቪዬሽን ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ አካላት እንደሚሳተፉ፣ ምርጥ የሰው ኃይል ልማትና የአቪዬሽን ሥልጠና ልምድ ልውውጥ እንደሚካሄድ በይበልጥ ደግሞ ትሬን ኤየር ፕላስ ፕሮግራም ላይ በሰፊው ውይይት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
በሲምፖዚየሙ ላይ በተለይ የአይሲኤኦ ቆንሲል ፕሬዚዳንትና ዋና ጸሐፊው እንደሚገኙ የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ የትራንስፖርት ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ የሲቪል አቪዬሽንና የኤርፖርት ባለሥልጣናት፣ የሲቪል አቪዬሽን ኃላፊዎች፣ የአውሮፕላን አምራች ድርጅቶች፣ የአየር መንገድና የኤርፖርት ድርጅት ሠራተኞች፣ የኢንዱስትሪው ፖሊሲ አውጪዎችና የቱሪዝም ባለሙያዎች፤ በአጠቃላይ 500 ያህል ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ሥልጠናና ትሬይን ኤር ፕላስ ሲምፖዚየም በሲንጋፖር፣ ሁለተኛው በደብሊን - ሰሜን አየርላንድ፣ ሦስተኛው በሰዑል- ደቡብ ኮሪያ፣ አራተኛው በአዲስ አበባ - ኢትዮጵያ እንደሚካሄድ የገለጹት አቶ ተወልደ፤ ይህ አጋጣሚ በአፍሪካ እጅግ ዘመናዊ የሆነውን፣ አይሲኤኦ አውሮፕላን ላይ የሚሰሩ ሰዎችን እንዲያሰለጥንና  በአህጉር ደረጃ የልቀት (ኤክሰለንስ) ማሠልጠኛ ማዕከል በማለት እውቅና የሰጠውን፣ ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ባለሥልጣን (አይኤቲኤ) ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ሥልጠና እንዲሰጥ የፈቀደለትን፣ በዓመት 4 ሺህ ተማሪዎችን የማሰልጠን አቅም ያለውን አዲሱን የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚን የማስጎብኘትና የማስተዋወቅ ዕድል ይሰጠናል ብለዋል፡፡
ሲምፖዚየሙ ለቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ጠቅሰው፣ ተሳታፊዎቹን ‹‹3.2 ሚሊዮን ዕድሜ ወዳላት ቅድመ-አያታችሁ ወደ ሉሲ አገር ወይም “ላንድ ኦፍ ኦሪጅን” እንኳን ደህና መጣችሁ›› በማለት በዓለም የታወቁትን የላሊበላ የአለት ፍልፍል ቤተ ክርስቲያናት፣ ከአንድ አለት የተሰራውን የአክሱም ሀውልትና ሌሎች ድንቅ የቱሪስት መስህቦች እንዲጎበኙ ለመቀስቀስ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ‹‹ቪዥን 2025›› የ15 ዓመት ስትራቴጂክ ፕላኑ፣ በአፍሪካ ቀዳሚው የአየር ግሩፕ ለመሆን በሰባት የቢዝነስ ማዕከላት እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ እነሱም የአገር ውስጥና የአኅጉር በረራ፣ የዓለም አቀፍ ተሳፋሪዎች በረራ፣ የጥገና አገልግሎት (ኤምአርኦ) የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ፣ የበረራ ላይ ምግብ ዝግጅትና የምድር ላይ (ግራውንድ) አገልግሎት በመስጠት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በመፍጠር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አየር መንገዱ ካለፈው ሁለት ዓመት አንስቶ ማስፋፊያዎችን እየሰራ ነው፡፡ ከተሰሩት ማስፋፊያዎች አንዱ በዓመት 4 ሺህ ሙያተኞችን ተቀብሎ የማሰልጠን አቅም ያለው እጅግ ዘመናዊና በአፍሪካ ትልቁ የስልጠና አካዳሚ ነው፡፡ በአፍሪካ ትልቁ፣ ከዓለም 10 መጋዘኖች አንዱ የሆነውና 600 ሺህ ቶን ዕቃ የመያዝ አቅም ያለው የዘመናዊ ዕቃ ተርሚናል ግንባታው እያለቀ ሲሆን በመጪው ሰኔ ወር የአይሲኤኦ የካርጎ ሲፓዚየም ሲካሄድ ታውቋል። እንደሚመረቅ፣ ሁለተኛው ተርሚናል ሲያልቅ 1.2 ሚሊዮን ቶን ዕቃ የመያዝ አቅም እንደሚኖራቸው ታውቋል፡፡ 15 ሚሊየን ዶላር ኢንቨስት የተደረገበትና አምና በጥቅምት ወር (2016) የተመረቀው ዘመናዊ የምግብ ማዘጋጀ (Catering) አሁን በቀን የሚመረተውን 36 ሺህ ወደ 100 ሺህ ምግቦች ከፍ፡፡
በቦሌ አየር መንገድ ፊት ለፊት እየተገነባ ያለው በላይ ኮከብ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሆቴል ግንባታው 40 በመቶ ያህል ተጠናቋል፡፡ ይህ ሆቴል 371 ክፍሎች ይኖሩታል፣ በአዲስ አበባም ሆነ በኢትዮጵያ ትልቁ ሆቴል ሲሆን በአንድ ጊዜ 2,500 ሰዎችን መያዝ የሚችል አዳራሽ እንዲሁም በአፍሪካ ትልቁ የቻይና ሬስቶራንት ይኖረዋል ተብሏል፡፡
የቻይናውያን አገር ጎብኚዎች ቁጥር በዓለም ትልቁ ሲሆን በዓመት 120 ሚሊዮን ቻይናውያን ዓለምን ይጎበኛሉ፡፡ አንዱ የአየር መንገዱ ዓላማ ኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻ ማዕከል ማድረግ ስለሆነ ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ብዙ ቻይናውያን ለመዝናናት አፍሪካን እየጎበኙ ናቸው ያሉት አቶ  ተወልደ፤ በተቀናጀ ጥረትና ማርኬቲንግ ብዙ የቻይና ቱሪስቶችን ወደ ኢትዮጵያና አፍሪካ ለማምጣት እንዳቀዱ ተናግረዋል፡፡ ከቻይና ኤምባሲ ጋር በመተባበርም ሰዎችን በቻይንኛ ቋንቋ ማሰልጠን ተጀምሯል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየሳምንቱ በሚያደርጋቸው 28 በረራዎች በየቀኑ ከ4 ሺህ በላይ ቻይናውያን ከአፍሪካ ወደ ቻይና ወይም ከቻይና ወደ አፍሪካ በአዲስ አበባ ስለሚተላለፉ አየር መንገዱ፤ ከሌሎች አየር መንገዶች የበለጠ የገበያ ድርሻ እንዳለውና ይህን ብልጫውን አስጠብቆ መቆየት እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡
በሲፖዚየሙ ወቅት የሚመረቀው ማስፋፊያ ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው፣ 100 ሚሊዮን ዶላር የፈጀውና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እጅግ ዘመናዊ የአውሮፕላን ጥገና (ሃንጋር) ነው፡፡ ይኼኛው ለመሥራት ከታቀዱት ሦስት የአውሮፕላን ጥገና ሃንጋሮች የመጀመሪያው ሲሆን ሁለት ክፍሎች አሉት- የትላልቅ አውሮፕላኖች መጠገኛና የቀለም መቀቢያ ክፍሎች፡፡ በአሁኑ ወቅት የሃንጋሩ ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት ጀምሯል፡፡
በ1949 ዓ.ም የተመሰረተው ይህ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል፣ በአሁኑ ወቅት በትልቅነቱ ከአፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዝ፣ ለአኅጉሩና ለመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የጥገና አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡
ድርጅቱ ሦስተኛውን ዘመናዊ A350 አውሮፕላን የተቀበለ ሲሆን 4ኛውን በሚቀጥለው ወር፣ አምስተኛና ስድስተኛውን በግንቦትና በሰኔ ወር እንደሚቀበል፣ እነዚህ የአካባቢ አየር የማይበክሉና የድምፅ ብክለታቸው አነስተኛ የሆኑ ዘመናዊና የመጪው ዘመን አውሮፕላኖች A350 እና ቦይንግ 787፤ አየር መንገዱ 2025 እቅዶች ለማሳት እንደሚረዷቸው አቶ ተወልደ ገልጸዋል፡፡

Read 1918 times