Monday, 20 March 2017 00:00

“ወሰብሳቤ”

Written by  መክብብ እንግዳወርቅ - ከአዲስ አበባ
Rate this item
(5 votes)

 ቁጭት፣ ፀፀት፣ ስጋትና መላ የሚርመሰመስበት ውብ መፅሐፍ!
                    
      በሙያዬ ከቋንቋና ስነ ጽሑፍ መምህርነት ባልርቅም ከተማሪዎቼ ጋር ካለኝ መስተጋብር ውጭ የመጽሐፍ ሐያሲ፣ መነሻ አስተያየት አቅራቢ ወይም ገምጋሚ መስዬ የመገናኛ ብዙኃን አማራጮችን ተጠቅሜ ብዕር ያነሳሁበት ወይም መድረክ ላይ የወጣሁበት ወቅት ስለመኖሩ አላስታውስም። የምለው አጥቼ ሳይሆን ለማለት የሚነሽጠኝ አጋጣሚ ሳጣብር ቆይቼ ወይም ለራሴ ያልተገለጸልኝ ሌላ ምክንያት ኖሮ እንደሆነ አላውቅም፡፡
በየዓመታቱ ጥሩና አይዘነጌ የስነ ጽሁፍ ውጤቶችን አድንቄ ያለፍሁባቸው ጊዜያት ድርብርብ ናቸው፡፡ ነገር ግን በነገረ መቅድሜ እንደጠቆምሁት ስለ ማንም ምንም ያላልሁበትን ምክንያትና ግንብ ንጄ፣ ዛሬ የጠለቀ ሂስና የተሟላ ግምገማ ለማቅረብ ሳይሆን የወፍ በረር ምልከታ ብቻ እንድሰነዝር ወደ ኮረኮረኝ “ወሰብሳቤ” ስለተባለ መጽሐፍ ጥቂት ለማለት ወደድሁ፡፡
በያለው አክሊሉ ተደርሶ በቅርቡ ለንባብ የበቃውን ባለ 429 ገጽ “ወሰብሳቤ” መጽሐፍ ከሽፋን ስዕሉ አመራማሪ ጥንቅር (ካራክተር ኮምቢኔሽን) ጀምሮ ውስጣ ውስጡን በአንክሮ በርብሬዋለሁ። ሥነ-ፅሁፋዊ አላባውያን ተብለው ከሚሰፈሩት መቃኛዎች አንጻር እያነጣጠርሁ እንዲህ እንዲያ ወደሚል ጥልቅ ትንተና እንደማልሰማራ አበክሬ ማሳሰቤን ያዙልኝ፡፡ ሆኖም የመሰረታዊ መልሕቁን ማደሪያ እንደማልለቅ ልብ ይባልልኝና መጽሐፉ የተከለብኝን ኮርኳሪ ስሜት (ኢምፕሬሽን) እናገር ዘንድ ፈቅጃለሁ፡፡
የ“ወሰብሳቤ” ደራሲ መግቢያ ብሎ ያሰፈረው መተዋወቂያ በራሱ ሊፈነዱ በሚታመሱ መልእክቶችና በድርጊት አመላካች ቅጽሎች የታመቀ አጠር ያለ ጽሁፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ልቦለድ ይሁን ታሪካዊ ልቦለድ ወይም እውነተኛ ታሪክ ሳያሻማ ሊገልጽልን አልፈለገም፡፡ ደንብ ጥሷል አልጣሰም የሚለውን ለጊዜው ልተው፡፡ ምክንያቱን የተረዳሁት ታሪኩን አንብቤ ከጨረስሁ በኋላ እንደሆነ ግን ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡ የመጽሐፉ አስኳል እውነት፣ ግቡም እውነት ሆኖ ሳለ ለምን አፍርጦ ሊጠቁመን እንዳልወደደ ሳሰላስል ያቃጨለብኝ መላምት በምርጫ ረገድ የሚወላውሉ አንባቢያንን ላለማጣት ጓጉቶ የተጠቀመበት ስልት ይሆናል ብዬ አመንሁ፡፡ እናም ወደ ውስጡ ዘለቅሁ፡፡
ከታሪኩ መዋቅራዊ ቅንብር አንጻር የምክንያቶችና የውጤቶች መነሻ አካል ተደርጎ በመንደርደሪያነት የቀረበው ክፍል አንድ ዋዘኛ ወግ መስሎ አንባቢን ከምንጭ ወደ ሐይቅ እያባበለ የሚወስድ መሸጋገሪያ ስለመሆኑ ገመትሁ፡፡ ጠጣር ርእሰ ጉዳይና የፖለቲካ ትግል ትረካ የማይጥማቸው አንባቢያንን በብልሐት ወደ ውቅያኖሱ የታሪክ ምእራፍ እንዲሳቡ የተጠቀመበት ዘዴ ጥሩ ነው፡፡ በክፍል አንድ የተጸነሱ አቢይ፣ ንዑስና ወካይ ገጸ ባህርያትን እንደየፍላጎቱ የወደደ አንባቢ እነሱን ሲፈልግ ራሱም ምርኮኛ ሆኖ ከእስር የሚፈታው በመጽሐፉ መቋጫ ገጽ ላይ እንደሚሆን ሳስብ የሄደበትን ቴክኒክ ወደድሁለት፡፡
የመጽሐፉ ታሪክ ፍቅር ነው፣ ማህበራዊ ጉዳዮች ናቸው፣ የጠለቀ ፖለቲካ ነው፡፡ እነዚህ በየፊናቸው ሲታዩ በቀላሉ የሚዋሃዱ የማይመስሉ ሞጋች እውነቶች ሳይጎሻሸሙ አዋድዶ፣ የጭብጡን ተዐማኒነት ጠብቆ እያጓጓ፣ ተጀምሮ የሚያልቅ ሥራ ማከናወን ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር “ወሰብሳቤ” ለአንዳንዶቻችን እንግዳ የሚሆንብንን የኤርትራና የኦጋዴን ጦርነት አውደ ውሎም ሆነ የደርግ ዘመንን የሰቆቃ ጊዜያት ያላለፍንበት፣ ያልሰማነውና ያላየነው እስኪመስለን ድረስ በልብ - አውልቅ የፍቅር ታሪክ አጅቦ ያቀረበበት መንገድ ማራኪ እንደሆነ ለመመስከር እደፍራለሁ፡፡
መቼቱን በተመለከተ አቢያ ምሰሶው የተተከለው ኤርትራና አዲስ አበባ ላይ ነው ቢባልም በየምእራፉ በርካታ የሀገሪቱን ክፍሎች እያስጎበኘ፣ በተጠናከረ ምልስት የሚያዥጎደጉደው መልዕክት ሜዳው ኢትዮጵያ እንደሆነች ያሳያል፡፡ የታሪኩ የጊዜ መነሻና መድረሻ እውን በደርግ ዘመነ መንግስት ማክተሚያ ዓመታት ላይ የተንጠለጠለ ነወይ? የሚል ጥያቄ ቢሰነዘር፣ ደራሲው የሚሰጠውን ምላሽ መጠበቅ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ መጽሐፉ ከአብዮቱ ፍንዳታ አንስቶ እስከ ደርግ የውድቀት ዋዜማ ባመላከተን ታሪክ ተወስኖ እንዳልቀረ ክፍል አራትና አምስትን መመርመር ይጠይቃል፡፡ “ወሰብሳቤ” ዛሬንም ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፣ ነገንም በነገነቱ ስሎ “ወዮልን!” ይለናል፡፡ የዚህ አስተያየት አቅራቢ ከተመሰጠበት ፍሬ ነገሮች አንዱ ይህ አቀራረብ ነው። የመጽሐፉ ጭብጥ የሚጓዝበትን ሃዲድ ሳይለቅ እንዲህ መሰል ሰንሰለት አበጅቶ በትናንትና ውስጥ ዛሬንና ነገን የማሳየት ጥበብ፣ ትምህርት የሚወስድበት መላ ነው እላለሁ፡፡
ስለ ቋንቋው ሳነሳ የተሻለ ስሜት የሚሰጠው በተለይ መጽሐፉን ላነበቡ ሰዎች ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ የአንድ መጽሐፍ ነፍሱ መጎናጸፊያው ሳይሆን ቋንቋው ነው፡፡ በዚህ አባባሌ “Language is the dress of thought” የሚለው ጥቅስ የቋንቋን ኃያል ዋጋ አሳምሮ አልጠቀሰውም ከሚል እሳቤ ተነስቼ ትርጓሜውን አላልቼ ጎንትያው ከሆነ ራሴን ደግ አደረግሁ ብለው እንጅ አልጸጸትም። ድንቅ ቁም ነገር የያዙ መጽሐፍት በቋንቋ ረገድ ሲያነክሱ የተነሱበት አላማም አብሮ እየተልወሰወሰ የጭብጡን ዋጋ እያሳነሰ ፍሬ ከርስኪ ሲያደርጋቸው እናውቃለን፡፡ “ወሰብሳቤ” በዚህ ረገድ የተዋጣ ብቃት ይታይበታል። ቋንቋ ሲጻፍና ሲነገር ብቻ ሳይሆን እየጣፈጠ ሲበላና ሲጠጣ የሚሰማንን ያህል በሚያመረቃ ክህሎት ታጅቦ እስከ ፍጻሜው ሲዘልቅ ተመልክቻለሁ፡፡
መጽሐፉ በግጭቶችና ልብ በሚሰቅሉ ድርጊቶች የተሞላ ነው፡፡ አንድን ወጥ ስራ ወይም እውነታ ከተመሰረተበት መዋቅር ሴራ ጋር አቆላልፎ የሚጓዝበትን ጎዳና ማበጀት ዋዛ ፈጠራ አይደለም። አንዱ ከተወላከፈ ሌላውንም ይጎትተዋል፡፡ ሁሉም አላባዊያን ያለ እከን ነፍስና ስጋ የሚሆኑበት አጋጣሚ ስንትም ነው ተብሎ ከሚታመነው አንጻር “ወሰብሳቤ” የግጭት፣ የመዋቅር ሴራ፣ የገጸ ባህሪያት አሳሳል፣ ታሪኩ የተያዘበትን ገመድና እንዲሁም የምክንያትና ውጤቶች ግንኙነትን ያስተሳሰረበት ሰንሰለት ጠንካራ ነው፡፡
በመቀጠል ልጠቅስ የምወደው ስለ መጽሐፉ ጭብጥ ይሆናል፡፡ ጭብጥ አብይና ተቀጽላ ክንፎች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ “ወሰብሳቤ” ሲፈጥረው ልክ እንደ ርእሱ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ማህበራዊና ከገጸ ባህሪያቱ ማንነት ከሚመነጭ ተፈጥሯዊም ሆነ አካባቢያዊ እምነቶችና አመለካከቶች ጋር በጽኑ ተሳስሮ የተዋቀረ ውስብስብ ስራ ነው፡፡ ድፍን ኤርትራን ተዟዙረን አይተንበታል፡፡ የዛሬን አያርገውና ምጽዋ ወስዶ ቀይ ባህር አስዋኝቶናል፡፡ አስመራ ከተማን የኖርንባት እስኪመስለን ተመልክተናታል። በየውጊያው ግንባር እያሳለፈ አዋግቶናል፡፡ ኦጋዴን ወስዶ አብሽቆ በምላሹ አፍነክንኮናል፡፡ ጎጃም በቸና ይዞን ሄዶ ህዝብ እንደ ቆሎ በመትረየስ ሲቆላና ዘማች ተማሪዎች ፍዳ ሲያዩ እያሳየ አሰቃይቶናል፡፡ መተከል ወስዶ ያሳየን ትዕይንት ምን ፍለጋ እንደሆነ ሰነባብቶ ገብቶናል፡፡ የዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ምስጢር እውን ታደለ የተባለ ዋና ገጸ ባህሪን እንክርት ብቻ ለመዘከር ይሆን? ለኔ እንደገባኝ ታደለ ተምሳሌት ነው፡፡ የማን?
ደርግ በጣም ግዙፍ ሠራዊት ገንብቶ እጅግ በጣም ግዙፍ ሽንፈት አጋጥሞት (አጋጥሞን እንድል ይፈቀድልኛል?) ድል ተነሳ፡፡ ማን አሸነፈው? ለውጥ ወይም እድገት የክስተቶች ውጤት ነው፡፡ ሁለት የውጤት ምንጮች ውስጣዊና ውጫዊ ግጭቶች ናቸው፡፡ የዚያ ሰራዊት ትንቅንቅ ከውስጥና ከውጭም እንደነበር እናስታውስ፡፡ ተዘውትሮ ይተረክልን የነበረው ሠራዊቱ ከሻዕቢያና ከሕወሀት (በኋላ ኢህአዴግ) ጋር አሰቃቂ ጦርነት ያካሂድ እንደነበር ነው፡፡ ‹‹ወሰብሳቤ›› ደግሞ ገና የ1981 ዓ.ም የግንቦት ወር መፈንቅለ መንግስት ሠራዊቱን ሳያሟሽሸው ከዚያ በፊትም ለሰራዊቱ ሽንፈት መንስኤ የነበሩ ብዙ ያልተዘመሩ መዝሙሮች ስላሉ እነሱንም እናዳምጣቸው ይለናል፡፡ በሠራዊቱ ውስጥ የተካሄደው መልከ ብዙ ንቁሪያ እንኳን እራሱን ሀገር የሚንድ ምክንያት ፈጥሮ አልፏል ነው የሚለው። የአንድ ትውልድ ሕይወት የተሰለቀጠበትን ያንን መራራ የጦርነት ዘመን ከንቱነት ነው በቁጭት አንርሳው የሚለው፡፡ ያንን እውነታ በሚያምርና በሚያጓጓ የፈጠራ ሥራ አጊያጊጦ አሳየን፡፡
ደራሲው የታሪኩን ዕድሜ በራሱ ምክንያት ያሳጥረው እንጂ እውነታው ከዚያም ዘልሎ እንደሚሄድ ስብሐት ገ/እግዜአብሔር ስለ በአሉ ግርማ አሟሟት ተጠይቆ ሲመልስ ‹‹እሱን ኮ/ል መንግሥቱ እንዳልገደለው ነፍሴ ትነግረኛለች›› እንዳለው ሁሉ እኔም የ‹‹ወሰብሳቤ›› ዋና ገፀባህሪ ተምሳሌታዊ ፍፃሜ እውን ስለ ታደለ ዕጣ ብቻ የሚደሰኩር እንዳልሆነ ነፍሴ ሹክ ትለኛለች፡፡ ደራሲው ያንን ልብ ያልተባለ የታሪክ ዘርፍ የመፅሀፉ አቢይ ጭብጥ አደርጎ ለትውልድ ሊያቀብል የፈለገ ይመስለኛል፡፡ (ይሄ እንግዲህ A reader is not a mind reader የሚባለውን ችላ በማለቴ፣ አንተ ያነበብከውን ትተህ ለምን ያልተፃፈ ታነባለህ ካልተባልሁ ነው፡፡)
ሌላው የጭብጥ ዘርፍ የዚህችን ሀገር መፃኢ እድል እየነካካ በተለይ በክፍል 5 እየተብከነከነ የገለፀልን እውነታ ነው፡፡ የኬይርያና የታደለ ከምንጭ ውኃ የጠራ የፍቅር ግንኙነት፤ የድንቁና የታደለ ከቃላት በላይ የተከወነ ጓደኝነት፤ የእነ በሻህ ለእውነት ኖሮ ለእውነት የማለፍ ጽናት፤ የእነ ሺበሺ ደመ-ጠጭ ሰብዕና፤ የእነ ሣባ ወካይ ገፀባህሪ መልዕክት፤ የዋናው ገፀባህሪ የሥጋ ዘመዶች ክህደትና ሌሎችም ድርጊቶች በ‹‹ወሰብሳቤ›› ውስጥ የያዙት ጥልቅ መልዕክት ጭብጡን ፈርጅ ብዙና አንፀባራቂ አድርጎታል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ስለመጽሀፉ የተሰማኝን በዚህ ቋጭቼ፣ ‹‹ቢሆን ኖሮ›› ወዳልኋቸው ጥቂት ነጥቦች ልለፍ። ‹‹ወሰብሳቤ›› ትልቅ መጽሐፍ ሲሆን የተማከለው በአምሥት ክፍሎች ብቻ ነው፡፡ ደራሲው ለእያንዳንዱ ክፍል መከለያ ያበጀው ታሪኩ የሚንደረደርባቸውን አዳዲስ ቦታዎች መነሻ እያደረገ እንደሆነ ተመልክቻለሁ። ይህ ምርጫ የሚደገፍ አይደለም፡፡ መጽሐፉን በበርካታ ምዕራፎች ማቅረብ የሚያስችሉ መሰረቶች ፍንትው ብለው እየታዩ፣ ያንን አለመጠቀም መልካም አይመስለኝም፡፡
ሌላው ፍሰቱን የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ጥሩ ሥራ ተከናውኗል ብንልም ከአንድ ድርጊት ወደ ሌላ ድርጊት በማሸጋገሩ ሂደት አያያዥ ሳይሰነዳላቸው እየዘለሉ የሚቀላቀሉ ተደጋጋሚ አጋጣሚዎች ስለሚታዩ ይህ አካሄድ መስተካከል ያስፈልገዋል እላለሁ፡፡
‹‹ወሰብሳቤ›› በአንድ ክፍል የሚቋጭ መጽሐፍ አልነበረም፡፡ ከላይ እንደጠቆምሁት ዋናው ገፀባህሪ ተምሳሌታዊ አካል ነው ቢባልም የፈጠራ ክህሎት ታክሎበት ተከታይ መጸሐፍ ሊወጣው ሲችል እንዲያ ባለ መልክ መደምደሙ አሞኛል፡፡ አጨራረሱ ተዐማኒ አይደለም ማለቴ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። ሆኖም እንደ ሰው ልጅነቴ ውስጤ አለቅጥ አዘነ። ደራሲው ጨክኖ ሀገሬ-ሀገሬ እያለ ሲማስን የኖረ አንድ የኮሰመነ ኢትዮጵያዊ ሲያሳጣን ተቀየምኩት። 420 ገፆች አንብቤ ወደ መጨረሻው በተጠጋሁ ቁጥር ገፆቹ ሲሳሱብኝ ተጨነቅሁ፡፡ የሆነው ሁሉ ሆነ፤ ባይሆን እወድ ነበር፡፡
ለማጠቃለል ያህል፣ ያለው አክሊሉ በሚል ስም ከዚህ ቀደም የተፃፈ መጽሐፍ አላነበብሁም፡፡ ‹‹ወሰብሳቤ›› የበኩር ሥራው ከሆነ የሚደነቅ ነው። ስለ ፍቅር ሲነግረን ያምርለታል፡፡ ስለ ማህበራዊ ጉዳዮች ሲያነሳ ያስደምማል፡፡ ስለ ሀገር የሚነካካቸው የፖለቲካ፣ ወታደራዊና የታሪክ ቁም ነገሮች ኮርኳሪ ናቸው፡፡
የሥነልቦና እና የፍልስፍና ዝንባሌው ከሥነ ጹሁፍ አቅሙ ጋር ጉልበት ሆኖ እንዳገዘው አይተናል፡፡ መጽሐፉ ከሀገር ውጭም ተቀባይነት አግኝቶ ጀርመን ሀገር የሚኖሩ አንባቢያን በዩቲዩብ መተረክ መጀመራቸውን በስልክ ለጥቂት ደቂቃዎች ያነጋገርሁት የመጽሐፉ ደራሲ ገልፆልኛል፡፡
ደስ ይላል- ደህና እንሁን!

Read 2356 times