Monday, 20 March 2017 00:00

የጉይዲ እና አባዲየ ሥራዎችን በጥቂቱ

Written by  ታደለ ገድሌ (ዶ/ር)
Rate this item
(1 Vote)

       “-- አንቶን የአሰባሰባቸውን 86 ቅኔዎች በራሱ ቋንቋ አልተረጎማቸውም፡፡ጉይዲም እንዲሁ አንዳንድ ቃላትን በጣሊያንኛ ከማብራራቱና ከራሱ ሥራ ጋር ከመጠረዙ በስተቀር ለአንቶን የቅኔ ስብስቦች ትርጉም አልሰጠም፡፡--”    
                   
        ኢኛሲዮ ጉይዲ እና አንቶን ዲ አባዲየ በተለያየ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ምርምር ከአደረጉና ታላላቅ ሥራዎችን ከሠሩ የአውሮፓ ተመራማሪዎች ተርታ የሚመደቡ ባለሙያዎች ናቸው፡፡
ጉይዲ እ.ኤ.እ በ1844 ኢጣሊያ ውስጥ ተወለደ። ያረፈውም እ.ኤ.አ ሚያዚያ 18 ቀን 1935 ዓ.ም ነው። ኢጣሊያዊው ኢኛሲዮ ጉይዲ የምሥራቅ ሀገሮች ተመራማሪና በሮም ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ነበር። በሒብሩ ቋንቋ ተመራማሪነቱና ተርጓሚነቱም ይታወቃል፡፡ ከፒየስ ዚንገርል ከአባ ቬንኤቲ የሴማዊ ቋንቋዎችን አጥንቶ በራሱ ጥረት ግእዝ ተምሯል። የኩዚስታንን ዜና-መዋዕል ከማጥናቱም ባሻገር የኦዴሳን ዜና መዋዕል አስተካክሏል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም ስለ ናይራን ሰማዕትነት የሚያትተውንና ለታሪካዊ ክንውን ትክክለኛ ማስረጃ የሆነውን የቤዝ አርሓሻሙን የስምዖንን ደብዳቤ አቃንቷል፡፡
ስለ ቀዳማዊ ኢያሱ (አድያም ቀዳማዊ በካፋ (መሲሕ ሰገድ)፤ ስለ ዳግማዊ ኢያሱ (ብርሃን ሰገድ ወይም ቋረኛውኢያሱ) የተጻፉትን የንግሥና ታሪኮች፤ ስለ ገድለ አረጋዊ፤ ስለ ፍትሐ ነገሥት፤ በአጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ሥነ ጽሑፍ፤ ባህል፤ ቋንቋ፤ ቅኔ፤ ተመራምሮ በጣልያንኛ ትንታኔና አርትዖት ሠርቷል፡፡
ኢኛሲዮ ጉይዲ፤ ‹‹ኦ ቅኔ አቢሲኒ›› ብሎ በሰጠው ርእስ ሥር ዐርባ ዐራት የዘመነ ጎንደር ቅኔዎችን አሰባስቦ ወደ ጣልያንኛ ተርጉሟቸዋል፡፡
አንቶን ዲ አባዲየ ለዘገባቸው ሰባ ቅኔዎች ግን፣ እንበለትርጉም ጥቃቅን ማስተካከያ አድርጎ ከራሱ ጥራዝ ጋር አያይዟቸዋል፡፡ ጉይዲ ለራሱ የቅኔ ስብስቦች በዐራት ገጽ ተኩል መግቢያ ጽፏል፡፡ ስለ ቅኔ ምንነትና ስለ የቅኔ ዓይነቶች፣ በጣልያንኛ ፍች ለመስጠት ሞክሯል፡፡
ነገር ግን ቅኔያቱን ያስቀመጠው በደረጃቸውና በቅደም ተከተላቸው መሠረት ከጉባኤ ቃና ጀምሮ ሳይሆን በዘፈቀደ ከመወድስ በመነሣት ነው። ቅኔያቱን ሲጽፍ ስሕተት የመሰሉትን ቃላት በግርጌ ማስታወሻው አብራርቷል፡፡ ግን ሥራው እንደተጠበቀው ከስሕተት የጸዳ አይደለም፡፡
በሥራው መጨረሻ በሁለት ገጽ ከነስሕተታቸው አምስት የአማርኛ ግጥሞችንና ዘጠኝ ብሂሎችን ሰንዶ በጣልያንኛ ተርጎሟቸዋል። ለባለቅኔዎች ከቤተ ክህነትና ከቤተ መንግሥት የተሰጡትና የሚጠሩባቸው የሹመት ደረጃዎችም ተብራርተዋል። አንቶን ዲ አባዲየ በበኩሉ፤ ለኢትዮጵያ ጥናት ጠቀሜታ ያለው ሥራ ያከናወነና ሰፊ ምርምር ያደረገ ፈረንሳዊ ምሁር ነው፡፡ አንቶን ዲ አባዲየ በቅኔ ረገድ ለሠራው ሥራ የሰጠው ርእስ “MS 145 La Raccolta Di Qne1908,Nota Ignazio Guidi,Roma” የሚል ነው፡፡
አንቶን የአሰባሰባቸውን 86 ቅኔዎች በራሱ ቋንቋ አልተረጎማቸውም፡፡ ጉይዲም እንዲሁ አንዳንድ ቃላትን በጣሊያንኛ ከማብራራቱና ከራሱ ሥራ ጋር ከመጠረዙ በስተቀር ለአንቶን የቅኔ ስብስቦች ትርጉም  አልሰጠም፡፡
አንቶን ዲ አባዲየ የተወለደው በሶውሌ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ይኖሩ ከነበሩ ከመሳፍንት ቤተሰብ ሲሆን አባቱ ሚኻኤል የተወለደው አራስት ላሬቢዩ ውስጥ ነው፡፡ እናቱ አይሪሽ ናት፡፡ አያቱ ጂው ፔሪየ በሳውሌ ውስጥ ውል እና ሰነድ አርቃቂና የወንድ መነኮሳት አለቃ ነበር፡፡ እ.ኤ.እ በ1848 ዓ.ም በቤተሰቦቹ ውሳኔ መሠረት ወንድሞቹ ጥንቃቄ የተመላበት ሳይንሳዊ ትምህርት ሊማሩ  ወደሚችሉበት ወደ ፈረንሳይ ተዛወሩ፡፡
አንቶን ዲ አባዲየ በምፅዋ በኩል አገር ለማሰስ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው እ.ኤ.አ የካቲት 18 ቀን 1838 ዓ.ም ላይ ነው፡፡አንቶን በቆይታው ሰማኒያ ዐራት ያህል የግእዝ ቅኔያትን ከማሰባሰቡ ባሻገር ሌሎች ሥራዎችንም ያጠና ተመራማሪ ነው፡፡ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ እ.ኤ.አ በ1848 ዓ.ም ቨርጂን ቪንሴንት ዶ ሴንት ቦኔት የተባለች ሴት አግብቶ ሔንዳይ ውስጥ ከፍተኛ ወጭ የወጣበትን የመኖሪያ ሕንጻ ገንብቶ መኖር ጀመረ፡፡
አንቶን ዲ አባዲየ እ.ኤ.አ ከ1871 እስከ 1875 የሔንዳይ ከተማ ከንቲባ ሆነ፡፡
ሕዝባዊ የክብር ማዕረግ የነበረው አንቶን ዲ አባዲየ የፈረንሳይ ሳይንስ አካዴሚ አባል ነበር፡፡ አባዲየ እ.ኤ.አ በ1897 ዓ.ም ሲሞት ሔንዳይ ከተማ እንደ ቤተ መንግሥት አድርጎ አንጾት የነበረውና በዓመት 40 ሺህ ፍራንክ ሊያስገኝ የሚችለው መኖሪያ  ቤቱ ለፈረንሳይ የሳይንስ አካዴሚ ተሰጠ፡፡ የፈረንሳይ ሳይንስ አካዴሚ አባዲየን እ.ኤ.አ በ1835 ዓ.ም ሳይንሳዊ ጥናት እንዲያደርግ ወደ ብራዚል ልኮት ነበር፡፡
የጥናቱ ውጤትም እ.ኤ.አ በ1873 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ታትሞለታል፡፡ ወጣቱ አባዲየ ከ1837 ዓ.ም በፊት ለጥቂት ጊዜያት ያህል አልጀሪያ ውስጥ ኖሯል፡፡ አባዲየና ወንድሙ በምፅዋ በኩል እ.ኤ.አ የካቲት 18 ቀን 1838 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ በወቅቱ በትንሹ ይታወቁ  የነበሩትን የእናርያንና የከፋን ወረዳዎች ጨምሮ የኢትዮጵያን ቦታዎች በተናጥልና በጋራ እየሆኑ ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸው ወቅት ብዙ አስቸጋሪና አስደናቂ ነገሮች ገጥመዋቸው እንደነበር ጽፈዋል፡፡
ወንድማማቾቹ በፈረንሳይ የፖለቲካ ሤራ በተጠነሰሰበት ወቅት ቀንደኛ ተሳታፊዎች ነበሩ። በዋነኛነት አንቶን በፈረንሳይ መንግሥት
መልእክተኛነቱና በሮማ ካቶሊክ ሚሽነሪነቱ ተጽዕኖ ለማድረግ ይሞክር ነበር፡፡ ሁለቱ ወንድማማቾች በጂኦግራፊ፤ በጂዎሎጂ፤ በአርኪዎሎጂና በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የተመሠረቱ ጠቃሚ መረጃዎችን ይዘው ወደ ሀገራቸው ፈረንሳይ እ.ኤ.አ.በ1848 ዓ.ም ከተመለሱ በኋላ ለኅትመት አዘጋጁዋቸው፡፡
 በተለይ አንቶን በጂኦግራፊ የምርምር ውጤቱና በፖለቲካ ሤራ ተሳታፊነቱ አከራካሪና አወዛጋቢ ጉዳዮች ውስጥ ገባ፡፡ ከዚህም የተነሣ በተለይ ወደ ካና በተደረገው ጉዞ “ዓባይ ዋነኛ ወንዝ ነው፤ የእኔ የጥናት ማስረጃ በዚህ ትክክለኛ ነው” እያለ ተጽዕኖ ሲያደርግበት በነበረው በቻርለስ ቲልስቶን ቤኬ ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶበታል፡፡
ነገር ግን የእርሱ ተከታይ ተመራማሪዎች አንቶን ያቀረበው ጥናት ትክክለኛና ሳይንሳዊ መሆኑን እየጠቀሱ ተከራክረውለታል፡፡ በአሰሳው ስለ ኢትዮጵያ ሥነ ምድር ያጠናው ጥናትና የሠራው ዐሥር ካርታ የአሰሳው አስተማማኝ ውጤትና ጠቃሚ ማስረጃ ተደርጎ ፈረንሳይ ውስጥ ስለታየ እ.ኤ.አ በ1860 እና በ1873 ታትሞለታል፡፡ ስለ ሀገራችን የብራና መጻሕፍት ሁኔታ የሚያትት ዝርዝር ካታሎግ ከማዘጋጀቱ ባሻገር 224 የኢትዮጵያን የብራና መጻሕፍት አሰባስቦ ስለ ይዘታቸው መግለጫ አውጥቷል፡፡ ሁለቱ ወንድማማቾች ስለአከናወኑት ጥናት ከፈረንሳይ የጂኦግራፊ ማኅበረሰብ እ.ኤ.አ በ1850 የፈረንሳይ መንግሥት ሜዳሊያ ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡

Read 1602 times