Monday, 20 March 2017 00:00

የ‘እቅድና መቶኛ’ አዙሪት

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ከዚሀ በፊት ደጋግመን ያወራናት ነገር አለች… ‘ዜና’ ተብለው የሚነገሩ ነገሮች…አለ አይደል… ጎሽ ብለው ከማስጨብጨብ ይልቅ “እና ምን ይጠበስ!” የሚያሰኙ ናቸው፡፡ አንድ መሥሪያ ቤት የዕቅዱን ዘጠና በመቶ በማሳካቱ እኛ ምን እናድርገው! አይደለም ዘጠና፣ ለምን መቶ በመቶ አያሳካም! ደሞዝ የምንከፍለው መቶ በመቶ እንዲሠራ አይደለም እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… ባይሆን ካቀደው አልፎ ሁለት መቶ ፐርሰንት ካስመዘገበ ብንሰማ ላያስከፋን ይችላል፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ዘንድሮ ቁጥርን የመሰለ መደበቂያ የለም እኮ!
የምር ግን…‘ይሄ ለሰው ጆሮ የሚመጥን ዜና ነው’ የሚባለው በምን መለኪያ ነው! አሀ…የአየር ሰዓት ምናምን የሚባለው ነገር ውድ በሆነበት ዘመን ጊዜ ለምን መጫወቻ ይሆናል!
“ከዚህ ቀጥሎ ዜና እናሰማለን፡፡…. የወረዳ ሦስት መቶ ሠላሳ ሦስት የትምህርት ቢሮ ኃላፊ የተማረ ህብረተሰብ ለአገር ልማት ወሳኝ መሆኑን አስገነዘቡ።”
ብራቮ! ብራቮ! እኔ የእኚህ ሰው ጓደኛ ብሆን፣ ወይንም አብረን አንድ ዕቁብ የምንጠጣ ብሆን ኖሮ…አለ አይደል… “ድሮም እዚህ አገር እውቀትና አዋቂ አይወደድም…” እል ነበር፡ ልክ ነዋ… እንዲህ አይነት ከፍተኛ ‘ግኝት’ እየነገሩን (ያውም ‘ሀክ’ ተደርጎ ሳይወሰድብን!) ለምንድነው የቢሮ ኃላፊ ብቻ የሚሆኑት! ወፈር፣ ሰፋ፣ ተለቅ ያለ ወንበር ይሰጣቸዋ! መጀመሪያ ነገር ይህ ‘ዜና’ ሚዲያውን የሞላው ‘አሪፍ’ ስለሆነ አይደል!
(እነ ቢቢሲን ተዉአቸው፣ ይሄን የመሰለ ጮማ ወሬ እያለ ‘ፈሉጃ፣ ካንዳሀር’ ቅብጥርስዮ እያሉ ‘የአየር ሰዓት የሚያባክኑት’ አሁን ፍትሃዊ ነው! “ድሮም እነሱ ሰዎች አይወዱንም” የምንለው ከመሬት ተነስተን አይደለም፡፡)
ለምሳሌ እንበልና “ዶክተር እከሌ ጤናማ ህብረተሰብ ለአገር እድገት ወሳኝ ነው አሉ…” ከተባለ በኋላ እኝህ ሰውዬ የሆነ ህክምና ተቋም ሜዲካል ዳይሬክተር ብቻ አድርጎ ማስቀረት ‘በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸም ግፍ’ አይሆንም!  አሀ…አይደለም የእኛዋ አገር፣ ድፍን አፍሪካ እንደ እሳቸው አይነት የተደበቀ መረጃ ፈልፍሎ የሚያወጣ እውቀት የሞላቸው ሰዎች ያስፈልጓታላ! ለእኚህ ዶክተር የድፍን አፍሪካን የጤና ጉዳይ…አለ አይደል… “እንደምታደርገው አድርገው…” ብለን ልንሰጣቸው ይገባል፡፡  
“በአፍሪካ የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመቀነስ የህክምና ባለሙያዎች ጠንክረው ሊሠሩ ይገባል…” ብለው ዓለምን ጉድ የሚያሰኝ ‘መረጃ’ ተናግረው፣ ማታ በዜና መልክ ቤታችን ድረስ ከች ይሉልናላ!
እንኳንም ‘ዜና’ ሆነ፡፡ ዜና ሳይሆን ቀርቶ በየቤታችን ብናወራው…አለ አይደል…‘የመንደር ስለላ አይነት ነገር ሆኖ ይቀራላ!
የመንደር ስለላ ነገር ካነሳን… ይቺን ስሙኝማ…አንዳንዱ፣ አለ አይደል… ሲያወራችሁ ‘ቀሺም የመንደር ስለላ’ አይነት የሚመስል ነገር እንዳለ መጀመሪያ አትጠረጥሩም፡፡ እናማ… በየዋህነት ትለፈልፋላችሁ፡፡
“አሁንም እዛ እየሠራህ ነው፣ አይደል!”
“አዎ እዛው መሥሪያ ቤት ነኝ…”
“የእናንተ መሥሪያ ቤት እኮ ጥሩ ይከፈላል አሉ…”
“ምንም አይል…”
“እንደው አሁን አንድ ሰባት ሺህ ብር አያስቡልህም?”
“ወደዛው ገደማ ነው…”
እንዲህ ባላችሁ በሦስተኛ ቀን ያልታተመውን የህይወት ታሪካችሁን መስማት ትጀምራላችሁ፡፡
“ስማ ሰውየው እኮ ይዝቃል አሉ…የሚከፈለው ደሞዝ መሰለህ! አንድ የእግር ኳስ ቡድን ያስተዳድራል አሉ…”
“ቢያንስ ቢያንስ የተጣራ አንድ አሥራ አምስት ሺህ ብር ይከፍሉታል ሲባል ሰምቻለሁ…”
“ምን ቢሠራላቸው ነው ይሄን ያህል የሚከፍሉት…”
“ነገሩ ሌላ ነው እባክህ…ከቦርዱ ዳይሬክተር ጋር አበልጅ ሳይሆኑ አይቀሩም ይባላል…”
እንዲህ እንዲህ እያለ ምን የሚያክል ጥራዝ የሚወጣው ግለ ታሪክ ይቀናበርላችኋል፡፡
ስሙኝማ…ዘንድሮ አንድ በጣም የተለመደች ነገር አለች… በ‘መቶኛ’ ተሰልታ የምትነገር ‘እቅድ ማሳካት’ የሚሏት ነገር፡፡ ሁሉም የሚነገረን የእቅዱ ስንት ስንተኛ ‘እንደተሳካ’ ሆኗል፡፡ አለ አይደል… “ሳይሳካ የቀረውን መቀነስ በሚባለው የሂሳብ መደብ አስልታችሁ ራሳችሁ ድረሱበት…” ብለው ነው መሰለኝ… “ሀምሳ ሁለት በመቶ አልተሳካም…” ብሎ የሚነግረን የለም፡፡)
እናማ…ይቺ መቶኛ የሚሏት ነገር እንደ ቀበሮ ጉድጓድ አይነት አገልግሎት የምትሰጥ ትመስላለች፡፡
“የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን በተደረገው ርብርብ የእቅዱ ሰባ አንድ በመቶ ተሳክቷል፣” ምናምን ይባላል፡፡ ‘ሰባ አንድ በመቶ’ ማለት ምን ማለት ነው! ዋናውን እቅዳቸውን ለእኛ ማን ነገረን! ደግሞ ብናውቅ የምንፈልገው ሃያ ዘጠኝ በመቶው ለምን እንዳልተሳካ ነው።
ስሙኝማ… “ወርሃዊ ደሞዝ የሚከፈለው የእቅዱ ስንት ስንተኛ እንደተሳካ እየተሰላ ነው…” ቢባል… ከከተማዋ ሉካንዳዎች ሰማንያ አንድ ከመቶ ባይከረቸሙ ነው! (እኛም ‘መቶኛ’ ተጠቀምን…አሀ፣ ማን ተጨብጭቦለት ማን ‘ይጠቆራል!’)
“የእንትን ጫማ ፋብሪካ ሠራተኞች በንቃት በመሥራት የዚህ ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት እንደሚረባረቡ አሳወቁ፡፡”
የምር ግን፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ይሄንን ‘ዜና’ እንኳን ዶናልድ ትረምፕ አልሰሙ፡፡ ልክ ነዋ… ‘ተረባርበው’ ምድርን የሚያንቀጠቅጡ ሠራተኞች እያሉ ማን ዓይኑን ያሻል! “እንዲህ አይነት ሠራተኞች እያሉማ ቻይና ጥላን ለመሄድ ስትገሰግስ ዝም ብዬማ አላይም፣” ብለው ልዩ አይነት ቪዛ እንዲዘጋጅ ያዛሉ። በጉዞው እገዳ ምክንያት እንዳይገቡ በሚከለከሉ ሰዎች አሥር እጥፍ ከጦቢያ አገር እንዲገቡ የሚፈቅድ ‘ትዕዛዝ ይፈርሙ’ ነበር። ለሥራ የሚረባረብ ተገኝቶ ነው!  ያኔ እነ ሲ.ኤን.ኤን. እና ‘ሳተርዴይ ናይት ላይቭ’ አርፈው ይቀመጡላቸው ነበር፡፡  
እኔ የምለው… መሥሪያ ቤት ሁሉ የዕለት ሥራውን ሲሠራ ስለዋለ፣ የተለመደውን በመፈክር ተጀምሮ በኮክቴል የሚያልቀውን ዓመታዊ ምናምናዊ ስብሰባ ስላደረገ ለእኛ ሲነገረን የሚያመሸው….እኛ የድርጅቱ የዕለት ውሎ ማስታወሻ ነን እንዴ!...
በዚህ አይነት ዕድሉ ይድረሰና! ዜጋ አይደለንም እንዴ… የእኛም ዜና መዋዕል ለሰፊው አድማጭና ተመልካች ይድረስልና!
“እከሌ የተባለው ዜጋ በቀን ሦስት ሰዓት ከአርባ ደቂቃ የእግር ጉዞ ለማድረግ ያስቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካት እንደሚረባረብ አስታወቀ…” ምናምን ይባልልና!
ዘንድሮ… ‘መቼም እስኪያልፍ ያለፋል’ ምናምን አይነት እየተፈላሰፋችሁ ካላሳለፋችሁ መአት ነገሮች አሉላችሁ፡፡
በጣም ጥቂቱ “አጨብጭቡልኝ፣” “ዳስ ጣሉና ግብር አግቡልኝ” ምናምን ሳይል ሥራውን ይሠራል። ሌላው ደግሞ…“በዓመቱ ውስጥ የእቅዴን አርባ በመቶ አሳክቻለሁ” እያለ… ‘ሀያ አንድ መድፍ ተኩሱልኝ’ ሊል ምንም የማይቀረው አለ፡፡
ስሙኛማ…እግረ መንገዴን የሆነ አዲስ ተቋም ተከፍቶ ዜና ምናምን ሲተላለፍ ልብ ብላችሁልኛል!
የሆነ አዲስ ኮሌጅ ምናምን ነገር ይከፈትና ያው የተለመደው ሪባን ሲበጠስ ምናምን እናያለን፡፡ ከዚያም ባለቤቱ፣ ወይም ከባቤቶቹ አንዱ ‘ዲስኩር’ ያሰማሉ…
“ይህን ኮሌጅ ያቋቋምነው የተማረ የሰው ኃይል አስፈላጊነትን በመገንዘብ የአገሪቱን የትምህርት ስርአት ለማሳደግ በማሰብ ነው…” ምናምን ይላሉ፡፡
አንሸዋወዳ! አሀ… እንዲህ ፊት ለፊት አንሸዋወዳ! የትምህርት ስርዓት ማሳደጉ አሪፍ ነው…ግን ስንት ጊዜ የፈጀው የወጪና ገቢ ስሌትስ!
“ሆስፒታል ያቋቋምነው የህዝቡን ጤና ለመጠበቅ ብለን ነው…”
“ሆቴሉን የከፈትነው የቱሪዝሙን እድገት ለመደገፍ ነው…”
ሁሉም ‘ዲስኩር’ ለቲቪ ካሜራ ምናምን አሪፍ ነው፡፡ ግን ደግሞ አንዳንዴም…
“ይሄን ድርጅት የከፈትነው ከፍተኛ ትርፍ የማስገኘት እድሉ ጥሩ ስለሆነ ነው…” ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚናገር ከተገኘ፣ ቆመን ለማጨብጨብ ፈቃደኞች ነን፡፡ (የሆነ ጋዜጣ ከፍቼ… “ይህንን ባለ ብዙ ገጽ ጋዜጣ የከፈትኩት የህብረተሰቡን የስኳር መጠቅለያ ወረቀት ችግር በመገንዘብ ነው…” ብል… ‘ዜና’ ይሆንልኛል?)
እናማ… ይቺ የ‘እቅድና መቶኛ አዙሪት’ ጎንበስ ብሎ ቅዝምዝም እንደማሳለፍ’ ሆና ባትቀር አሪፍ ነው፡፡  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3820 times