Monday, 20 March 2017 00:00

ከቆሻሻ ናዳ አደጋው የተረፉት ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

“የቆሻሻው ክምር አደጋ ሊፈጥርብን እንደሚችል አመልክተን ነበር”
                   
        በተለምዶ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ባለፈው ቅዳሜ ከደረሰው አደጋ የተረፉና ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ተጎጂዎች “ሰሚ አጥተን እንጂ የቆሻሻው ክምር አደጋ ሊፈጥርብን እንደሚችል በተደጋጋሚ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመልክተን ነበር” ብለዋል፡፡ አስተዳደሩ ግን እስካሁን የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን ከመግለጽ ውጭ ያለው ነገር የለም፡፡  
ባለፈው ማክሰኞና ረቡዕ አደጋው በተከሰተበት ስፍራ ተገኝተን የተጎጂዎችን ቤተሰቦች አነጋግረን ነበር፡፡ አብዛኞቹ በመንግስት መገናኛ ብዙኃን የሚወራውን ያህል ከአደጋው በኋላ ከመንግስትና ከማህበረሰቡ ድጋፍ እያገኘን አይደለም ብለዋል፡፡
በመጀመሪያ ያነጋገርናቸው በአካባቢው በሚገኝ መስጊድ ጊቢ ውስጥ ሁለት ድንኳኖችን ጥለው በጋራ ለቅሶ የተቀመጡ የእስልምና እምነት ተከታይ ወገኖችን ሲሆን “አደጋው ከደረሰብን በኋላ የት ወደቃችሁ ያለን አካል የለም” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡  
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉና በአደጋው ባለቤታቸውንና ህፃን ልጃቸውን ያጡ አንድ ጎልማሳ፤  “ይሄው 3ኛ ቀናችን ነው፤ ውሃና ስንቅ እንኳ የሚያቀብለን አጥተናል፡፡ ምን ቸግሯችኋል ብሎ ያነጋገረን አንድም የመንግስት አካል የለም፤ ከህዝቡ እየለመንን ነው እርስ በእርስ እየተረዳዳን ያለነው፤ አሁን እናንተ ጋዜጠኞች ብትመጡ ለኛ ምንም ትርጉም የለውም” በማለት ከዚህ በላይ ሊያነጋግሩን እንደማይፈቅዱ ነግረውናል፡፡  
ሌላዋ 9 ቤተሰባቸውን በአደጋው እንዳጡ የገለፁልን አንዲት እናት በበኩላቸው ከእንባቸው ጋር እየታገሉ፤ ”አደጋው በተፈጠረ ወቅት ከፍርስራሽ ውስጥ ድምፅ እየሰማን ነው፤ እባካችሁ አድኑልን ስንል ፈጥኖ እርዳታ የሚያደርግ አካል አላገኘንም” ሲሉ በጥልቅ ሃዘን ተናግረዋል፡፡ “እኔ መንግስትን ብቻ አልወቅስም፤ ለወገን ደራሽ ነው በሚባለው የኢትዮጵያ ህዝብ አዝኛለሁ፤ ለሶስት ቀናት ያህል ከጎናችን ሆኖ የሚደግፈን አልነበረም” ያሉት እኚሁ እናት፤ “አሁንም እኛ ከመንግስት ብዙ አንጠብቅም፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከወደቅንበት ይታደገን” በማለት ተማጽነዋል፡፡
መንግስት በሚዲያ እየገለፀ ያለው የሟቾች ቁጥርም ትክክል አይደለም ይላሉ - እኚህ እናት። “ይህ መንግስት ያመጣው አደጋ ነው አላልንም፤ ለምን በትክክል የሞቱት ሰዎች ቁጥር አይገለፅም” ሲሉ በምሬት የጠየቁት እኚሁ እናት፤ ከእህታቸው ቤት ብቻ የዘጠኝ ቤተሰቦቻቸው አስከሬን መውጣቱንና በግቢው ውስጥም 7 ተከራዮች ከልጆቻቸውና ሌሎች ቤተሰቦቻቸው ጋር ይኖሩ እንደነበር ገልጸዋል። ሌሎች ተጎጂዎችም 18 ተከራዮች ያሉባቸው ግቢዎችም እንደነበሩ በመጠቆም፣ የሟቾች ቁጥር መንግስት እንደሚለው 70 እና 80 ሳይሆን በመቶዎች የሚቆጠር እንደሚሆን ግምታቸውን ይናገራሉ፡፡  
ሌላዋ እናት ይቀጥላሉ፡- “ቤተሰብ ከሚያመጣልን ሻይና ዳቦ በስተቀር መንግስት ምንም እየረዳን አይደለም፣ ቤተሰቦቻችንን የሌሊት ልብስና ብርድልብስ እንዲያመጡልን ስንነግራቸው፣ መንግስት እየረዳችሁ ነው እየተባለ አይደለም እንዴ? ይሉናል፣ ግን ማንም የረዳን የለም”  
በተለይ ህጋዊ  የይዞታ ማረጋገጫና ካርታ ያላቸው የአደጋው ሰለባዎችን መንግስት መዘንጋቱንና ድጋፍ እያደረገ ያለው በቆሻሻው ላይ ላስቲክ ወጥረው ይኖሩ ለነበሩት ብቻ ነው ሲሉ አማረዋል፡፡ “አሁንም ቢሆን ተስፋችን አላህ ብቻ ነው” ብለዋል፤ እኚህ እናት፡፡
 አደጋው ከደረሰ በኋላ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በአካባቢው ፈጥነው በመድረስ በሚፈለገው መጠን የነፍስ አድን ስራ ለመስራት አልቻሉም ሲሉ ያማረሩት የተጎጂ ቤተሰቦች፤ “በራሳችን ወጪ ኤክስካቫተሮችን በመከራየት ቤተሰቦቻችንን በህይወት፣ ካልሆነም አስከሬናቸውን ለማግኘት ጥረት ስናደርግ ነበር” ብለዋል፡፡  
በአብዛኛው በአደጋው ህይወታቸውን ያጡት አቅመ ደካሞችና አዛውንቶች፣ እናቶችና ህፃናት መሆናቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች ያስረዳሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ አደጋው የደረሰበት ሰዓት አስተዋፅኦ  አድርጓል፡፡ ከምሽቱ 2 ሰዓት ገደማ በመሆኑ አብዛኛው ወጣት ከስራ ወደ ቤቱ የሚገባበት እንዲሁም እለቱ ቅዳሜ እንደመሆኑ በአካባቢው ባሉ መዝናኛ ቤቶች የማመሻሸት ነገር ስለሚኖር አብዛኞቹ ተጎጂዎች በቤት የሚውሉ እናቶችና ህፃናት ሊሆኑ እንደቻሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡
“ወገኖቼ! ልጆቼ ሁሉም አፈር በልቷቸዋል፤ የልጆቼን አስክሬን አውጥተውልኝ አፈር እንዳለብሳቸው እድሉን ስላገኘሁ አላህ ይመስገን” ሲሉ በእንባ እየታጠቡ መሪር ሃዘናቸውን የገለፁት ሰባት ልጆቻቸውን በአደጋው ያጡ የ55 ዓመት ባልቴት ናቸው፡፡
“የልጆቼ ሬሳ ስለተሰጠኝ አመሰግናለሁ፤ ለፍቼ ደክሜ፣ ፍርፋሪ ለቅሜ ያስተማርኳቸው ተማሪ ልጆቼን አጣኋቸው፣ ተራራ ውስጥ ገቡብኝ … ይሄ ከመንግስት አቅም በላይ የሆነ አደጋ ነው፤ አሁን ልጆቼን አጥቻለሁ፣ ቤት ንብረቴን አጥቻለሁ፣ ቤቴ ካርታ ያለው ቤት ነበር አሁን መውደቂያ የለኝም፣ከዚህ በላይ የምናገረውም የለኝም” ብለዋል እኚሁ ሃዘን የጸናባቸው እናት ከእንባቸው ጋር እየታገሉ፡፡  
ተጎጂዎች ስለ መኖሪያ አካባቢያቸው
አብዛኞቹ ተጎጂዎች በአካባቢው መኖር ከጀመሩ ከ20 እስከ 40 አመትና ከዚያ በላይ እንደሚሆናቸው ይገልጻሉ፡፡ አቶ ኑረዲን አምስት የቤተሰብ አባላቸውን በአደጋው ካጡትና በመስጊድ ተጠልለው ካገኘናቸው ተጎጂዎች አንዱ ናቸው፡፡ በአካባቢው በምሪት ቦታ ላይ ህጋዊ የቤት ካርታ አግኝተው መኖር ከጀመሩ ከ40 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ በደርግ ጊዜ በቁጠባ ተደራጅተው ቦታውን ተመርተው፣ በወቅቱ ደረጃውን የጠበቀ ቤት ሰርተው መኖር እንደጀመሩ ያስረዳሉ - አቶ ኑረዲን፡፡
“ቆሼ የሚባለው ቦታ ከኛ የመኖሪያ አካባቢ ከ200 ሜትር የሚበልጥ ርቀት ነበረው” የሚሉት ነዋሪዎቹ፤በቆሻሻውና በመኖሪያ መንደሩ መካከል ወንዝና ልጆች ኳስ የሚጫወቱበት ሰፊ ሜዳ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ “ቀስ በቀስ ቆሻሻው እየገፋ … እየገፋ ወደ ቀዬአችን መጣ፣ ቆሻሻው በአካባቢው ለነበረው ወንዝ መተላለፊያ እየከለከለው በመምጣቱ በክረምት ወቅት ከሁለት ጊዜ በላይ በጎርፍ አደጋ ተጎድተናል” የሚሉት አቶ ኑረዲን፤ በወቅቱ መንግስት ጎርፉን ለማስወገድ እንኳ የረባ ድጋፍ ሳያደርግ በራሳቸው መዋጮ እያንዳንዱ አባወራ 3 ሺህ ብር አዋጥቶ ማሽን በመከራየት ለጎርፉ መተንፈሻ አበጅተው መኖር እንደቀጠሉ ያስረዳሉ፡፡
በወቅቱ የቆሻሻው ክምር እየፈጠረ ያለውን አደጋ በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው የአስተዳደር አካላት ሲያመለክቱ “ቆሻሻውን ምንም ማድረግ አይቻልም፤ እናንተ ተለዋጭ ቦታ ተሰጥቷችሁ ትነሳላችሁ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውና አብዛኛው አባወራ በዚህ ሳይስማማ ከንቲባው ድረስ በመሄድ “ይሄን ቆሻሻ አስቁሙሉን፤ እኛ ከ40 ዓመት በላይ የኖርንበትን አካባቢ ለቀን ወዴትም መሄድ አንችልም” የሚል አቤቱታ ማቅረባቸውን ይናገራሉ፡፡ ከከንቲባው ፅ/ቤትም “ችግራችሁን እንረዳለን፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ እልባት እንሰጣችኋለን፤አካባቢውን አበባ ነው የምናስመስለው” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው አስታውሰው፣ በወቅቱ ቃል የተገባላቸው ጉዳይ ተግባራዊ ይሆናል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው ነገር ግን የከንቲባው ፅ/ቤት አደጋው እስከተከሰተበት እለት ድረስ የውሃ ሽታ ሆኖ እንደቀረባቸው ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
 “ቆሻሻውን አስወግዱልን የሚለው ተደጋጋሚ አቤቱታችን ተሰምቶ ወደ ኦሮሚያ ሰንዳፋ ተቀይሯል ብለን ነበር፤ነገር ግን መልሰው አምጥተውት በቆሻሻው ክምር ተራራ ላይ ጨምረው መድፋት ጀመሩ” የሚሉት ተጎጂዎቹ፤ ቦታው ተመልሶ ቆሻሻ መድፊያ ከሆነ በኋላ በመኖሪያ ቤቶቹና በቆሻሻው ክምር መካከል የነበረው ቦታ እየጠበበ መምጣቱንና ድንበር የነበረው ወንዝም መደፈኑን ያስረዳሉ፡፡  
አደጋው በደረሰ እለት በቦታው እንደነበሩ የገለጹልንና ልጃቸውን ጨምሮ ሁለት የልጅ ልጆቻቸውን እንዳጡ የነገሩን የ70 ዓመቱ አዛውንት፤ቆሻሻው እየገፋ በመምጣቱና የግቢያቸውን አጥር እስከመታከክ በመድረሱ በዕለቱ ይህ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል ገምተው እንደነበር ጠቁመው፣ የዚያኑ እለት ማታ አደጋው ማጋጠሙን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሁሉንም ነገር መንግስት ያውቀዋል›› ብለዋል፤አዛውንቱ፡፡
ለችግሩ መፍትሄ እንዲሰጠው መጠየቅ ከጀመርን 3 ዓመት አልፎናል የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፤‹‹ሠላማዊ ሰልፍ ሁሉ ወጥተናል፣ መኪና ገብቶ እንዳያራግፍ መንገድ ሁሉ ለመዝጋት ሙከራ አደርገናል” ይላሉ፡፡ በወቅቱ የነበሩ አንድ የስራ ሃላፊም፤ ‹‹እናንተ ወደ ቆሻሻው መጣችሁበት እንጂ እሱ አልመጣባችሁም›› የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ከንቲባው ግን ቆሻሻ የሚጣልበት ቦታ ተቀይሯል፤ ከዚህ በኋላ ንጹህ አካባቢ ይኖራችኋል የሚል ተስፋ ሰጥተውን ነበር፤ግን መልሶ ቆሻሻው መጣብን” ሲሉ ነዋሪዎቹ በምሬት ተናግረዋል፡፡
አደጋውና የነፍስ አድን ስራው
የቆሻሻ ናዳው ያጋጠመው ቅዳሜ ምሽት 2 ሰዓት ገደማ መሆኑን የሚናገሩት ተጎጂዎቹ፤ ሌሊቱን በሚገባ ፍለጋ ሳይካሄድ አስክሬን እንኳ ማውጣት የተጀመረው እሁድ ከረፋዱ 4 ሰዓት ገደማ ነው ይላሉ፡፡ የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል በበኩሉ በተለያዩ ሚዲያዎች በሰጠው መግለጫ፤ ጥሪ በደረሰለት በ5 ደቂቃ ውስጥ በቦታው ተገኝቶ ከፍተኛ የነፍስ አድን ስራ መስራቱን አስታውቋል፡፡ ተጎጂዎቹ ይህ  እገዛ እንደተደረገ ነገር ግን በሚፈልጉት መጠን እንዳልሆነና ርብርብ ቢደረግ የበርካቶችን ህይወት ማዳን ይቻል እንደነበር ገልጸዋል፡፡ አብዛኛው የሟች ቤተሰብም ኤክስካቨተሮችን በሰዓት እስከ 9 ሺህ ብር በግል በመከራየት የቤተሰቦቻቸውን አስክሬን አስወጥተው መቅበራቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ነፍስ ለማዳን የተደረገው ርብርብ እጅግ አናሣ ነው ሲሉ የሚያማርሩት ተጎጂዎቹ፤ በራሳችን መዋጮ ከግለሰቦች ኤክስካቫተር ልንከራይ የቻልነው ተገቢውን እርዳታ ባለማግኘታችን ነው፣ በዚህም በጣም አዝነናል ብለዋል፡፡
በዚህ አደጋ የ8 ወር ነፍሰ ጡር ከሁለት ልጆቿ ጋር፣ ከወለደች ሳምንት የሆናት አራስና ልጇ፣ ሁለት እህታማማቾች ከእነ ልጆቻቸው፣ አካል ጉዳተኞች፣ አዛውንት እናቶች በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ሙሉ የቤተሰብ አባላትም ህይወታቸውን እንዳጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ህፃን ልጇን በጀርባዋ ያዘለች እናትም አስክሬናቸው ተገኝቷል፡፡ ባለቤቱንና 4 ህፃናት ልጆቹን አጥቶ ብቻውን የቀረ አባወራ፣ወላጅ እናቷንና ሁለት እህቶቿን አጥታ ብቻዋን የቀረች ወጣት----ሃዘናቸው በቃላት የሚገለጽ አይደለም። አዲስ አበባ አይታ የማታውቀው አስከፊ አደጋ  መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
እስካሁን ድረስ የአደጋው መንስኤ በውል አልታወቀም፡፡ ለመሆኑ ለጠፋው የወገን ህይወት ተጠያቂው ማን ነው? ቅድመ ጥንቃቄ ቢደረግ ኖሮ አደጋውን ማስቀረት አይቻልም ነበር?  የሟች ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆኑ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምላሽ የሚፈልጉላቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡  

Read 2961 times