Monday, 20 March 2017 00:00

አምላክን የምለምነው ሦስት ነገሮች

Written by 
Rate this item
(30 votes)

   1ኛ. ፍፁም የማላሸንፈውን ነገር እንድተው እንዲያደርገኝ
                 2ኛ. የማሸንፈውን ነገር ዳር እንዳደርስ ድፍረት እንዲሰጠኝ
                 3ኛ. በአንደኛውና በሁለተኛው መካከል ያለውን ልዩነት እንዳውቅ እንዲረዳኝ

     በጥንት ዘመን በህንድ አገር የሚነገር አንድ ዝነኛ አፈ - ታሪክ እንዲህ ይላል፡፡
ከሂማሊያ ተራራ ግርጌ በሚፈሰው በታወቀው የጋንጀስ ወንዝ ዙሪያ የሚኖሩ የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ነበሩ ይባላል፡፡ ከልዩነታቸው ሁሉ በተለየ የሚያጨቃጭቃቸው የውሃ ሀብታቸው ነበር፡፡ ሁሉም ስለ ውሃቸው ጉዳይ ከመንደሩ ብልህ አዛውንት ፊት እየቀረቡ በየጊዜው ይከራከራሉ፡፡
“የእኛ ውሃ ከተራራ አለት መካከል የሚፈልቅ በመሆኑ ጥራት አለው፡፡ ከዚያ ሌላ በመጠጥም ቢሆን በማናቸውም አቅጣጫ ከሚፈሰው ውሃ ብዛት አለው፡፡ ስለዚህ ለጋንጀስ ወንዝ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለን እኛ ነን፡፡” ይላሉ፡፡
ከሂማሊያ ተራራ በተቃራኒው አቅጣጫ የሚኖሩት ሰዎች ደግሞ፤
“የለም፤ የተሻለ ውሃ ያለን እኛ ነን፡፡ የእኛ ውሃ ብዙ ማዕድን ያለው፣ በጥንታዊነቱም የታወቀ፣ የበለፀገ ሀብት ያለው፣ ዙሪያ ገባውን እያራሰ፣ የሜዳውን መስክ እያረሰረሰና መስኩን እያለመለመ፣ ለከብት ግጦሽ ጭምር የሚያገለግል ነው፡፡ ዋና ተጠቃሚ መሆን ያለብን እኛ ነን” ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
ከሁለቱ ወገኖች የሚለዩት ከሂማሊያ ጀርባ የሚኖሩት ሶስተኛዎቹ ሰዎች፤
“የእኛን ውሃ የሚያክል በፍፁም የለም! ምክንያቱም የኛ ውሃ ፀበልነት አለው፡፡ ቅዱስ ነው፡፡ ስንቱ ቢስ - ገላ፣ ስንቱ ሽባ፣ ስንቱ በሽተኛ የሚፈወስበት ነው፡፡ አገር የሚድነው በእኛ ውሃ ነው፡፡ ስለዚህም የተሻለ አስተዋፅኦ ስላለን የተሻለ ጥቅም ይገባናል” ይላሉ፡፡
በአራተኛ ወገን ቆመው የሚከራከሩትና ከሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ የሚፈሰው ወንዝ ዙሪያ የሚኖሩት ሰዎች በበኩላቸው፤
“ከማናችሁም የተሻለ ገባር፣ ወንዝ ያለን እኛ ነን፡፡ ለምን ብትሉ የእኛ ውሃ ገስጋሽ ነው፡፡ ኃይል አለው፡፡ ትልቁን የጋንጀስ ወንዝ እየገፋ፣ አቅም እየሰጠ፣ የሚያንቀሳቅሰቀው የእኛ ውሃ ነው!” አሉ፡፡
እንግዲህ የአራቱም ወገኖች ክርክር ዳኝነት እንዲያገኝ የሚጠበቀው ከመንደሮቹ አባት ከብልሁ አዛውንት ነው፡፡ አንዳቸው በጥራት አንዳቸው በማዕድን ይዞታ፣ አንዳቸው በፈዋሽነት፣ አንዳቸው በፍጥነትና በኃይል የተሻልን ነን በሚል የተሻለ ጥቅም ጠየቁ፡፡
የመንደሩ ብልህ አዛውንት ሁሉንም ካዳመጡ በኋላ፣ ሰፈራቸው ላይ ወጥተው፤
“ኑ ተከተሉኝ” አሉና ከመንደሩ ርቀው የጋንጀስ ወንዝን ተከትለው ጋለቡ፡፡ አራቱም ወገኖች እየጋለቡ ተከተሉ፡፡ መንደሮቹን ወደ ኋላ እየተዉ ፍፁም ከማይታዩበት ሌላ አካባቢ ሲደርሱ አዛውንቱ ወረዱና፤
“ይሄ ማን የሚባለው ወንዝ ነው?” ሲሉ አራቱንም ወገኖች ጠየቁ፡፡
“የጋጀስ ወንዝ ነዋ!” ሲሉ መለሱ፤ ሁሉም በአንድ ድምፅ፡፡
አዛውንቱም፤ “መልካም፡፡ በሉ አሁን እያንዳንዳችሁ የየራሳችሁን መንደር ውሃ ከዚህ ወንዝ ውስጥ አውጡና አሳዩኝ!” ሲሉ ጠየቁ፡፡ አንዳቸውም የኔ ነው የሚሉትን ውሃ ሊያሳዩ አልቻሉም፡፡ የሁሉም መንደር ውሃ አንድ ጋንጀስ ሆኗል፡፡
*         *       *
ሁሉም ገባር ወንዞች ተቀላቅለው ወደ አንድ ትልቅ ወንዝ ይፈስሳሉ፡፡ ማናቸውንም ከሌላው መለየት የማይቻልበት ደረጃም ይደርሳሉ፡፡ የእኔ መንደር ውሃ ከሌላው መንደር ውሃ ይበልጣል የሚለውን አስተሳሰብ የጋንጀስ ወንዝ ይዞት ሄዷል፡፡ ሁላችንም ስለ ትልቅ ስዕል ማሰብ ስንችል አገር እናድናለን፡፡ ትልቁ የጋንጀስ ወንዝ ትናንሾችን ገባር ወንዞች ሁሉ ጠቅልሎ፣ አንድ ወንዝ ሆኖ መፍሰስ፣ የአንድን ትልቅ አገር ህልውና ምስል ይሰራልናል፡፡
ፍትሕም፣ ዲሞክራሲም፣ መልካም አስተዳደርም፣ የፖለቲካ ጥራትም፣ ንፁህ እጅም አንድ ላይ በአግባቡ ሲፈስሱ፣ አገር የመንቀሳቀስ ኃይልና አቅም ታገኛለች፡፡ የእኔ አስተዋፅኦ ይበልጣል ብሎ ተገዳድቦ መለያየት የአንድነት ፀር ነው፡፡ አገርን ይሸረሽራል፡፡ አቅምን ያኮስሳል፡፡
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤
“የአበሻ መኪና አነዳድ በሌላው መንገድ
መገድገድ፣ የአበሻ ንግድ የሌላውን ንግድ ማሽመድመድ›› የሚለን፤ ይሄንኑ ሀቅ ለማፀህየት ነው!
ተነጣጥለን ልዩነትን በማስፋት የትም አንደርስም፡፡ ኅብር ልንፈጥር የምንችለው ዜማችን አንድ ሲሆን ነው፡፡ ፍቅራችን ከልብ ሲሆን ነው፡፡ ከልብ መደማመጥ ስንችል ነው፡፡ ልዩነት ቢኖረን እንኳን በሠለጠነ ጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት አሊያም ተከባብሮ መቀመጥ ስንችል ነው፡፡ ለዚህ ቁልፉ በመቻቻል ማመንና በተግባር ማሳየት መቻል ነው፡፡ ትዕግሥት ፍርሃት አለመሆኑን የምናውቀውን ያህል፤ አጉል ድፍረትና አጉራ-ዘለል ፖለቲከኝነት ወንዝ እንደማያሻግር ማወቅ ያስፈልጋል…
ዛሬ ‹‹በቆሼ ሠፈር›› የደረሰውን አሰቃቂ አደጋ በሐዘንና በቁጭት እናስበዋለን፡፡ አደጋን አስቀድመን ለማሰብ እንችል ዘንድ የህዝብን ፍርሃትና ሥጋት አለመናቅ ዋና ነገር ነው፡፡ ቅን ልቦና ቢኖረን መልካም ነው፡፡ የሕዝብን ደግ ማሰብ፣ የልብ ትርታውን ለማዳመጥ፣ ኑሮውን መመርመር ተገቢ ነገር ነው። ለቅድመ ጥንቃቄ ይጠቅመናል፡፡ አደጋ ከደረሰም በኋላ በኅብረት መረባረብን ህዝብን ለመታደግ አቅምና ልብን መስጠትን፤ ህዝብን ማስተባበርን ሆነኝ ብሎ ማሰብ፣ ከዚያም የሚገኘውን ትምህርት ማጤን፣ አፋጣኝ መፍትሔ ለማግኘትም ሳይነጣጠሉ መጣር ያሻል፡፡ የአገር ጉዳይ ነውና አገር አደጋውን መቋቋሚያ ማሽኖችን ማቅረብ አለባት፡፡ የክሬኖችንና የመቆፈሪያዎችን እጦት መቋቋም ካቃተን የአደጋ አደጋ አለብን፡፡ ወይ ህዝብን ለመርዳት ፈቃደኝነት ማጣት አለ፡፡ አሊያም የችግራችን ጥልቀት አሰቃቂነት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል ማለት ነው፡፡ ለወገን መድረስ ይጠበቅብናል፡፡ ጊዜ እየመረጥን ሳይሆን ሁልጊዜ!! ተከታዩ ጉዳይ የተጎዳውን ህዝብ ማቋቋምና ሌላ ቦታ ለማስፈር ምን አርምጃ እንውሰድ የሚለው ነው፡፡ የሚመለከተው ክፍል ይህን ያስብበታል ብለን እንገምታለን፡፡ አደጋው ድንገተኛና በችግር ላይ ችግር የፈጠረ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ አገራችን አንዴ በጎርፍ አንዴ በድርቅ፣ አሁን ደግሞ በናዳ፣ መጠቃቷን እናያለን፤ ችግር ፈቺ ዘዴንና ቅድመ ዕቅድን  የማዘጋጀትን ሥራ አቅም በፈቀደ መሥራት አለብን፡፡ አገራችን የችግር ቋት መሆኗን ደጋግመን አውስተናል፡፡ የፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውንና የማኅበራዊውን ድርብርብ ችግር በቅደም ተከተል የምንፈታበትን ዘዴ ካላዘጋጀን ወደ ባሰ ማጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ አቅምን አግዝፎ ማየትም፣ ከልኩ በታች አቀጭጮ ማየትም አደጋ ነው፡፡ ስለዚህ ፀሎተኛው እንዳለው፤ አምላክን የምለምነው ሶስት ነገሮች፡-
1ኛ/ ፍፁም የማላሸንፈውን ነገር እንድተው እንዲያደርገኝ
2ኛ/ የማሸንፈውን ነገር ዳር እንዳደርስ ድፍረት እንዲሰጠኝ
3ኛ/ በአንደኛውና በሁለተኛው መካከል ያለውን ልዩነት እንዳውቅ እንዲረዳኝ ነው ማለት ብልህነት ነው፡፡
አደጋ ለደረሰባቸው ሁሉ ፅናቱን እንዲሰጣቸው እንመኛለን!!

Read 5929 times