Saturday, 11 March 2017 12:55

ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች “ማን ያደራድር” በሚለው ላይ አልተስማሙም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

   በቀጣይ ቀጠሮ ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል
                               
        ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በ4ኛ ቀን ቀጠሮአቸው በድርድር ስነ ምግባር ደንቡ ላይ ባደረጉት ውይይት ማን ያደራድር በሚለውና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ክርክር አድርገው ባለመስማማታቸው በይደር ለቀጣይ ቀጠሮ አስተላልፈውታል፡፡
ከትናንት በስቲያ በነበረው ቀጠሮ በቅድሚያ ውይይት የተደረገበት በድርድሩ እነማን ይሳተፉ በሚለው ጉዳይ ላይ ሲሆን ኢህአዴግ፤ “የሶማሌ፣ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የሐረርና የጋምቤላ ክልልን የሚመሩ 5 ፓርቲዎች መሳተፍ አለባቸው” የሚል ሀሳብ ያቀረበ ቢሆንም አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች “ፓርቲዎቹ የክልል ፓርቲዎች እንደመሆናቸው ሊደራደሩ የሚገባው ከክልል ፓርቲዎች ጋር ነው” በማለት ተከራክረዋል፡፡
ኢህአዴግ በበኩሉ፤ በድርድሩ የሚወሰነው ውሳኔ አምስቱን ፓርቲዎችንም የሚነካ በመሆኑና በፓርላማው 46 መቀመጫ ያላቸው በመሆኑ እንዲሳተፉ እፈልጋለሁ የሚል ሀሳብ ቢያቀርብም በአብዛኞቹ ፓርቲዎች ባለመደገፉ  ሀሳቤን ትቼዋለሁ ብሏል፡፡
በመድረክ በኩል ሁለት አማራጮች የቀረቡ ሲሆን ከኢህአዴግ ጋር በዋናነት መደራደር ያለበት ‹መድረክ› ነው የሚልና በተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍለን እንደራደር የሚል ነበር፡፡ ሆኖም ሁለቱም ሀሳቦቹ በአብዛኞቹ ፓርቲዎች ተቀባይነት አላገኙም፡፡
ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ የተደራዳሪዎች ቁጥር ቢመጠን እንደሚስማማ ያስታወቀው ኢዴፓ፤ ነገር ግን የሚመጠንበት መስፈርት በግልፅ የሚታወቅና ሁሉም ሊቀበለው የሚገባ መሆን እንዳለበት ሀሳብ አቅርቧል፡፡
የመድረክ ተወካይ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፤ “ድርድር በሸንጎ አይቻልም፡፡” በማለት የተሳታፊ ፓርቲዎች ቁጥር መወሰን እንዳለበት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ኢህአዴግ በበኩሉ ሶስት አማራጮችን አቅርቧል። ሁሉም 21 ተቃዋሚ ፓርቲዎች በድርድሩ መሳተፍ አለባቸው፤ ተቃዋሚዎች እርስ በእርስ ተመካክረው በቡድን በቡድን ሆነው በተወካዮች መቅረብ ይችላሉ እንዲሁም ለብቻዬ ልዩ አጀንዳ አለኝ የሚል ወገን  ከሌሎች ጋር የተጀመረው ድርድር ሲያልቅ ለብቻው ከኢህአዴግ ጋር መደራደር ይችላል የሚሉ ናቸው፡፡
እነዚህን ሶስት አማራጮች ተቃዋሚዎች ተነጋግረውበት የሚስማማቸውን መርጠው ካሳወቁኝ እነሱ የተመቻቸውን እቀበላለሁ ብሏል - ኢህአዴግ፡፡ በቀጣይ ቀጠሮም ተቃዋሚዎች ውሳኔያቸውን እንዲያሳውቁት ጠይቋል፡፡
ከተሳታፊዎች ምን ያህሎች ሲገኙ ነው ድርድሩ መካሄድ የሚችለው የሚለውም ፓርቲዎቹን በርከት ላሉ ደቂቃዎች ያከራከረ ጉዳይ ሲሆን በመጨረሻም ከተደራዳሪ የፓርቲ ተወካዮች 2/3ኛ የሚሆኑት ሲገኙ ብቻ ድርድር እንደሚካሄድ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ሰፊ ጊዜ የወሰደውና ሳይቋጭ በይደር የቆየው ጉዳይ ‹‹አደራዳሪ ማን ይሁን?›› የሚለው ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ‹‹ገለልተኛ አካል ይምራ›› እና ‹‹ራሳችን በዙር መድረኩን እንምራ›› የሚሉ ሀሳቦች ቀርበው ፓርቲዎቹ ተከራክረውበታል፡፡
የገዳ ስርአት አራማጅ ፓርቲ በበኩሉ፤ ቀላል ጉዳዮች ላይ በሚደረግ ድርድር ሌላ አደራዳሪ ሳያስፈልግ ራሳችን እንደራደር፣ ከባድ አጀንዳዎች ላይ ደግሞ በገለልተኛ አደራዳሪ መደራደር ይገባናል የሚል ሶስተኛ አማራጭ አቅርቧል፡፡
ኢህአዴግና በርከት ያሉ ፓርቲዎች ‹‹ድርድሩን ራሳችን በዙር እንምራው›› የሚል ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን መድረክ፣ መኢብን፣ መአህድ፣ ኢዴፓ እና 6ቱ ፓርቲዎች፤ ‹‹ድርድር በአደራዳሪና በተደራዳሪ አይመራም፤ ስለዚህ በገለልተኛ ወገን እንደራደር›› የሚል አቋም አንፀባርቀዋል፡፡
ገለልተኛ አካል ለመምረጥ አስቸጋሪ መሆኑንና ገለልተኛ የሚባል አካል ለማግኘት አዳጋች እንደሆነ በመግለፅም የተወሰኑ ፓርቲዎች ‹‹ድርድሩን በዙር መምራት አለብን›› ሲሉም ሞግተዋል፡፡
ኢህአዴግ በመጨረሻ ባቀረበው ሃሳብ፤ ሌላ ገለልተኛ አካል እንደማያስፈልግ በመግለፅ፣ በዙር ይመራ የሚለውን ሀሳብ እንደሚደግፍ ጠቁሞ ኢህአዴግ መድረክ እንዳይመራ ከተፈለገም ላለመምራት ፍቃደኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በነዚህ ሀሳቦች ላይ ሰፊ ክርክር ከተደረገም በኋላ ጉዳዩ መቋጫ ባለማግኘቱ የመድረኩ መሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ “ጉዳዩን በይደር አቆይተን በሚገባ አስበንበት በቀጣይ ቀጠሮ እንወስን” በሚል ያቀረቡት ሀሳብ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን ቅዳሜ መጋቢት 9 ቀን 2009 ዓ.ም በድጋሚ ለመገናኘትና በእለቱ በሁሉም የስነ ምግባር ደንቡ ሀሳቦች ላይ ተወያይቶ ለማጠናቀቅ በማቀድ በቀጠሮ ተለያይተዋል፡፡

Read 2739 times