Monday, 13 March 2017 00:00

ንጉሥ የቆረጠው እጅ እንዳለ ይቆጠራል!

Written by 
Rate this item
(19 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ - ዓይነ - ሥውር እናት የነበረችው አንድ ልጅ ነበረ፡፡ ይሄ ልጅ እናቱን አደባባይ ማውጣት አይፈልግም፡፡ ያፍርባታል፡፡ በሄደበት ቦታ ሁሉ ሌሎች ልጆች ስለ እናታቸው ሲያወሩ፣ እሱ አያወራም፡፡ ሌላው ቀርቶ ሌሎቹ ስለ እናታቸው ደግነት ሲያወሩ እሱ እናቱን አያነሳም። እናቱ በእናትነቷ እስክትሸማቀቅና እስክትሸሸግ ድረስ በሰፈር ልጆች መሳቂያ መሳለቂያ እንድትሆን አደረጋት፡፡
በትምህርቱ እየገፋ ታዋቂ ልጅ እየሆነ ሲሄድ፣ ስለ እናቱ መናገሩን ጨርሶ ተወ - ያለ እናት የተወለደ እስኪመስል ድረስ፡፡ ውጪ አገር ሄዶ አድጎ ተመንድጎ፣ አንቱ ተብሎ ትልቅ ስራ ያዘ፡፡ እናቱን ረሳት፡፡ እናቱን የከዳና የናቀ መሆኑን ግን የሚያውቅ ማንም የለም፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ትውልድ አገሩ ውስጥ ለሚደረግ ትልቅ ኮንፈረንስ ተጋበዘና ወደ ሀገሩ መጣ፡፡
ስብሰባው ሲያበቃ እስከ ዛሬ ረስቷት የነበረችውን እናቱን እስቲ ከመጣሁ አይቀር ልያት ብሎ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ቤት ግን የጠበቀችው እናቱ ሳትሆን፣ የእናቱ ታናሽ እህት፣ አክስቱ ናት፡፡
“እናቴስ ወዴት አለች?” አለና ጠየቀ እንደደረሰ፡፡
አክስቱም፤ “እናትህ የለችም?”
ልጅ፤ “ወዴት ሄደች?”
አክስት፣ “ወደማይቀረው አለም”
ልጁ ያልጠበቀው ነበረና ድንጋጤ ላይ ወደቀ፡፡ አለቀሰ፡፡
ሲረጋጋ፤ “እናትህ ከመሞቷ በፊት ‹ድንገት ልጄ ከመጣ ይሄን ደብዳቤ ስጪልኝ› ብላለች፡፡ እንካ ውሰደው” ብላ አክስቱ ትሰጠዋለች፡፡
ሲፈራ ሲቸር እጁ እየተንቀጠቀጠ ይቀበላትና ደብዳቤውን ከፍቶ ያነበዋል፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“ልጄ! አንድ ልጄ ሆይ!
ብትገፋኝም፣ ብትርቀኝም፣ ብትንቀኝም ብታስንቀኝም፣ ብትጠላኝም፣ ብታስጠላኝም፣ ብታኮርፈኝም፣ ሰዎች እንዲያፍሩብኝ ብታደርግም፣ አሁንም ያው አንድ ልጄ ነህ! ህይወቴ ከማለፉ በፊት አንድ ነገር ልነግርህ እፈልጋለሁ፡-
ወጣት ሆነህ አንድ ዐይንህን ክፉኛ ያምህ ነበር፡፡ ሐኪም ቤት ወስጄህ ዶክተሩ ዐይንህ ሊጠፋ እንደሚችልና በቀዶ - ጥገና ሌላ ዐይን ካልተተከለልህ ተስፋ እንደማይኖርህ፣ ጨርሶም እንደሚጠፋ፣ ነገረኝ፡፡ የአንተ፣ የነገ ተስፋዬ፣ ገና ብዙ ማየት ያለብህ አንድ ልጄ፤ ዐይንህ - ብርሃንህ ከሚጠፋ የእኔ ዐይን ይጥፋ፤ ብዬ፣ የእኔ ዐይን ይጥፋና አንተ ብርሃን ይኑርህ ብዬ፣ ዐይኖቼን አስወልቄ ላንተ አስተከልኩልህ!! ዛሬ አንተ ሁለት ዐይን የኖረህና እኔ ዐይነ - ስውር የሆንኩት ለዚህ ነው! እይበት! ሰው ሁንበት ብዬ ነው!”
ልጅ በእጁ ይዞ የቀረው ፀፀትን ብቻ ነው!
*   *   *
እናትየውን ኢትዮጵያን አድርገን ብናይ ብዙ ነገር እንማራለን! የዛሬው ትውልድ ከላይ እንደተጠቀሰው ወጣት እንዳይሆን እንመኛለን፡፡
ዛሬም ወጣቱ የማያፍርበት አገር እንዳለው ልናሳውቀው ይገባል፡፡ ከራስ ወዳድነት የፀዳች አገር እንዳለችው በኩራት ማሰብ ይገባዋል፡፡ ጽጌረዳ ያለ እሾክ እንደማትኖር ልብ ይል ዘንድ ልንመክረው ይገባል!
ድርቅ እና የኑሮ ውድነት ዛሬም ከጫንቃችን ላይ አልወረዱም! “የደመናው ሎሌ” የሚለውን ግጥም ያስታውሰናል፡-
ለወትሮው ደመና ፊቱ እየጠቆረ
ዐይኖቹን አሻሽቶ ያነባ ነበረ
    ይዘንብ ነበረ
የዘንድሮ ሰማይ ፈጋግ ሰማያዊ
መልኩን አሳምሮ
ስንቱን ፈጀ በላ ከራብ ተመሳጥሮ
የምድር ከርስ አረረ
አገር ጦም አደረ
ሰው ምጡ ጠናና
ዐይኖቹን አቀና
እንዲሁ ከርተት ከርተት ሰማይ ለሰማይ
ውሃ የለሽ ህዋ ጠብታ-አልባ ጠፈር
ሰማይ አይታረስ በዐይን ብሌን ሞፈር
የዳመናው ሎሌ የዳመናው አሽከር
የዕለት ግብሩ ሆነ ጦም ውሎ ጦም ማደር
ዕንባውን እረጫት ሽቅብ ወደ ላይ ድንገት
ዝናብ ሆና ትወርድ ይሆን ወይ?!
ታህሣሥ 1977 ዓ.ም
(ለ1977 ድርቅ)
የመንግስት ሠራተኞች የተጨመረውን ደሞዝ መሰረት ያደረገ የነጋዴዎች የሸቀጥ ዕቃ ዋጋ መጨመር፤ ሌባና-ፖሊስ ጨዋታ አስገራሚ ነው! ህዝብና ነጋዴ አይጥና ድመት ሆነው መኖር የለባቸውም! ውስጠ-ነገሩ የሀገራችንን ነገር፣ የሀገራችንን የፖለቲካ ሂደት፣ የየትውልዱን ማንነትና የፖለቲካ ተዋንያን ከእናት አገራቸው ጋር ያላቸውን ትሥሥር ሊያመላክተን የሚችል ነው፡፡ መልካም-ትውልድ የመሠረቱን አይረሳም፡፡ ሰፊውን የሀገሩን ሥዕል በሆደ ሰፊነት ያስተውላል፡፡ ከሀገር በፊት የሚመጣን ራስ ተኮርና ራስ ጠቀም አካሄድ ያስወግዳል፡፡ ከእርስ በእርስ መናቆርና መወጋገዝ፤ ከእኩይ ሙግት፣ ከእኔ ልግዘፍ ፖለቲካ፣ ከቀረርቶና ከሜዳሊያ ፍለጋ ሩጫ ራሱን ያገልላል ‹‹ከወጡ ሳይወጠወጥ ወስከንባዩ ፍጥጥ›› ጨዋታ ራሱን በጊዜ ይገላግላል!
መጪው ትውልድ አርአያ ይሻል! አርአያ ልንሆነው ልባችን ይሙላ፣ ሁሉን ነገር ለመንግስት ጥለን አንችለውም! መንግሥት ያለውን ቢል ህዝብ እንደምን ተቀበለው ብሎ ጥናት ማካሄድ የነገራችን ሁሉ አልፋ- ኦሜጋ ነው፡፡ መንግሥት ሊሣሣት ይችላል፡፡ ማረሚያ ነጥቦቹ (Check-points) እኛ ነን!
ተሳስተሃል አቅጣጫህን ቀይር ማለት ኃላፊነታችን ነው (We are the watch-dogs) ይላሉ ፈረንጆቹ እንጂ ተረቱ እንደሚለው፤ ‹‹ንጉሥ የቆረጠው እጅ እንዳለ ይቆጠራል›› እያልን ብዙ አንራመድም! በቀናነት ዕድሜውን ይስጠን!!

Read 4876 times