Monday, 13 March 2017 00:00

ኢትዮጵያዊው ታዳጊ የአህጉራዊ ሽልማት አሸናፊ ሆነ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(10 votes)

ከኢትዮጵያም ከአፍሪካም 1ኛ ወጥቷል
                          መንኮራኩር ሲመጥቅ ለማየት ወደ ፓሪስ ይጓዛል

     ዲኤስ ቲቪ አፍሪካ ስለ ሳተላይት ቴክኖሎጂና በዘርፉ ስላለው ሳይንስ ተተኪና የወደፊት መሪ ሳይንቲስቶችን ለማፍራት በየዓመቱ “የዩቴልሳት ስታር አዋርድስ”ን ያዘጋጃል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ከ14-19 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ታዳጊዎች የሚሳተፉ ሲሆን ዘንድሮም በኢትዮጵያ ደረጃ ከተለያዩ ት/ቤቶች ወደ 80 የሚጠጉ ተማሪዎች ተወዳድረው ነበር፡፡ የውድድሩን ርዕስ ራሱ ዲኤስ ቲቪ የሚያዘጋጅ ሲሆን ተወዳዳሪዎቹ ወደፊት ተመራምረው የራሳቸውን ሳተላይት እንደፈጠሩ አድርገው ካሰቡ በኋላ ያንን ሳተላይት ለምን ለምን ጥቅም እንደሚያውሉት በፅሁፍ (ኢሴይ) እና በፖስተር እንዲገልፁት ይደረጋል፡፡ ዘንድሮ በተካሄደው ውድድር የጊብሰን አካዳሚው የ11ኛ ክፍል የሳይንስ ተማሪው ልዑል መስፍን ከኢትዮጵያም ሆነ ከአፍሪካ አንደኛ በመውጣት ከፍተኛ አድናቆትና ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
ለመሆኑ ምን አይነት ሳተላይት ለመስራትና ለምን ጥቅም ሊያውለው አሰበ? እንዴት ወደ ውድድሩ ገባ? የወደፊት ህልሙስ ምን ይሆን? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ታዳጊ ልዑልን አነጋግራዋለች፡፡

       ልዑል፤ ወደዚህ ውድድር እንዴት ልትገባ ቻልክ?
ዲኤስ ቲቪ ያወጣውን ማስታወቂያ አይቶ ጓደኛዬ ነው የነገረኝ፡፡ ከዚያ በፊት ስለ ሳተላይት እውቀት አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን ስለ ማስታወቂያው ስሰማ ፍላጎት አደረብኝና ለመወዳደር ወሰንኩኝ፡፡ ከዚያም ስለ ሳተላይት ቴክኖሎጂ ጎግል ላይ ሰርች እያደረግሁኝ ብዙ ነገሮችን ለማወቅ ቻልኩኝና ከነዚህ መረጃዎች በመነሳት የውድድር ፅሁፉን (ኢሴይ) ለማዘጋጀት በቃሁ፡፡
በአገር ውስጥ ወደ 80 ከሚጠጉ ተማሪዎች ጋር ተወዳድረህ ነው ያሸነፍከው፡፡ ውድድሩ እንዴት ነበር?
እውነት ነው፤ ከተለያዩ ት/ቤቶች ተማሪዎች ጋር ነው የተወዳደርኩት፡፡ እኔ ደግሞ ጊብሰን ዩዝ አካዳሚን ነው የወከልኩት፡፡ እኔም ከነርሰሪ ጀምሮ በዚሁ ት/ቤት ነው ያደግኩትና ስለ ሳተላይት የፃፍኩት ፅሁፍ በዳኞች በኩል ሚዛን ደፍቶ ከአገር ውስጥ 1ኛ ወጣሁ፡፡ ከዚያ በአፍሪካ ደረጃ ለመወዳደር በቃሁ ማለት ነው፡፡  ከ20 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎች በውድድሩ ተካፍለው ነበር፡፡ በአፍሪካ ደረጃም የእኔ ፅሁፍ 1ኛ ወጣ፡፡ ይሄው ዛሬ የምታይው የሽልማት ስነ - ስርዓት የተዘጋጀው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ስለ ሳተላይት የፃፍከው ፅሁፍ ይዘት ምን ይመስላል?
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ ስለ ሳተላይት ብዙም አላውቅም ነበር፡፡ ከኢንተርኔት መጠነኛ ግንዛቤ ካገኘሁ በኋላ ሳተላይትን ተጠቅመን የአፍሪካን ችግሮች እንዴት መፍታት እንችላለን በሚለው ጉዳይ ላይ ትኩረቴን አደረኩኝ፡፡ በዚህም የኤሌክትሪክሲቲን ችግር፣ በግብርና ላይ ያሉብንን ኋላቀር አሰራሮች፣ የሽብርተኝነትን ጥቃት በሳተላይት ለማስወገድ ይቻላል በሚለው ላይ ነው የሰራሁት፡፡ የሳተላይቴን ስያሜም “Aptus 2063” የሚል ነው፡፡ አፕተስ ምህፃረ ቃል ነው፡፡ የአፍሪካን ብልፅግና በሳተላይት ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚገልፅ ነው፡፡ 2063 ደግሞ የአፍሪካ ህብረት “አጀንዳ 2063” በቅርቡ በተካሄደው ስብሰባ ትኩረት የተደረገበት ነው፤ ስለዚህ ርዕሱም ያነሳኋቸውም ሀሳቦች ቀልብ መሳብ የቻሉ ይመስለኛል፡፡
በአፍሪካ ደረጃ ውድድሩን የዳኙት ስፔስ ደርሰው የመጡ ትልልቅ ስም ያላቸው ሰዎች ናቸው። ለምሳሌ አንዷ ዳኛ ፈረንሳዊ ሲሆኑ በአውሮፓ ስፔስ ሳይንስ ኤጀንሲ (ESA) ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ናቸው፡፡ የእነዚህ 1 ሺህ ያህል የአፍሪካ ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ፅሁፍ አንብበው የእኔን መርጠውታል ማለት ነው፡፡
መሸለምህ ምን ስሜት ፈጠረብህ?
ምን ተሰማህ የሚለውን በቃላት ለመግለፅ እቸገራለሁ፤ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ የተወዳደርኩት እንደነ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባብዌና መሰል አገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ አገሮች በውድድሩ ልምድ ያላቸውና ሁሌ የሚያሸንፉ እንደሆኑ ሰምቻለሁ። ከእነሱ ጋር ተወዳድሬ ያውም ለመጀመሪያ ጊዜ … ከዚያ ደግሞ እነሱን ማሸነፍ መቻል ሊያመጣ የሚችለውን ስሜት አስቢው፡፡ ለቤተሰቤ፣ ለት/ቤቴ፣ ለአገሬ ይህን ውጤት ማምጣት፣ በዚህ የሚገኘው ምርቃትና ምስጋና ለሌላ ትልቅ ሀሳብ ያነሳሳል፡፡ ለአገሬ ልጆች ምሳሌና ብርታት መሆንም ሌላው ትልቅ ደስታ ነው፡፡ ሽልማትን በተመለከተ ገና ውድድሩ ሲካሄድ ተነግሮናል፡፡ ያው ፓሪስ ሄጂ መንኮራኩር ሲመጥቅ በአይኔ አያለሁ፡፡ እዚህ የተዘጋጀውን ሽልማት በተመለከተ አብረን እናየዋለን (ዲኤስ ቲቪ ባለ ሙሉ ፓኬጅ ዲኮደር ሸልሞታል)
ትምህርትህ ላይ እንዴት ነህ?
በአብዛኛው ተነበው የሚረዱ ትምህርቶች ላይ አተኩራለሁ፤ ቁጥሮች ላይ ብዙም ጥሩ አይደለሁም። በአብዛኛው ጠቅላላ እውቀቶች ላይ አተኩራለሁ፡፡ ብቻ ጥሩ ነኝ፤ ምንም አልልም፡፡
ወደፊት ምን ለመስራት ታስባለህ?
እንደነገርኩሽ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነኝ፤ ትምህርቴን በትጋት መከታተልና መጨረስ  እፈልጋለሁ፡፡ ከዚያም ስለ አጠቃላይ የስፔስ ሳይንስ በከፍተኛ ደረጃ ተምሬ ዛሬ በፅሁፌ ያስቀመጥኩትን ህልም እውን በማድረግ፣ አገሬንም አፍሪካንም ማገልገል እፈልጋለሁ፡፡
በዚህ አጋጣሚ ለዚህ ውጤት እንድበቃ የረዱኝን ዲኤስ ቲቪን፣ ት/ቤቴን፣ ጓደኞቼን፣ ቤተሰቦቼንና የደገፉኝን ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡

Read 5535 times