Monday, 13 March 2017 00:00

ካዛቶፒያ - የዲጂታል ሙዚቃ ትምህርት ቤት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

 ከፍተኛ የሙዚቃ ስሜት አለው - በተለይ ሙዚቃን የማቀናበር፡፡ ወደ እንግሊዝ ከመሄዱ በፊት እዚሁ አገር ቤት እያለ የተለያዩ ሶፍትዌሮች በመጠቀም “ቢት ሜኪንግ” ይሰራ ነበር፡፡ እንግሊዝ ሙያውን ለማሻሻልና ፕሮፌሽናል ለመሆን ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረለት፡፡ ስለዚህ ላይንዳ (Lynda) ኢንስቱትዩት ተመዝግቦ በኢንተርኔት (ኦንላይን) በዋነኛነት ሙዚቃ የማቀናበር (ሚክሲንግ)፣ ማስተሪንግና ዲጄ ፕሮዱዩሰር እንዲሁም ቪዲዮ ፕሮዳክሽን፣ ሶሻል (ማህበራዊ) ሚዲያ ማርኬቲንግ ሲማር አንድ ዓመት ተኩል ፈጀበት፡፡
የምዕራብ አፍሪካ ሙዚቃ ዓለም አቀፍ ደረጃ ስላለው፤ በእኛም አገር ሆነ በሌሎች የዓለም አገሮች ይደመጣል፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ግን በብዙ አገሮች  አይሰማም፤ አይደመጥም፡፡ የአገራችን ሙዚቃ በሌሎች አገሮች የማይደመጠው ዓለም አቀፍ ደረጃ ስለሌለው አይደል? ንዴትና ቁጭት አደረበት፡፡ ስለዚህ  የኢትዮጵያን ሙዚቃ ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲኖረው ማድረግና የቀሰመውን እውቀት ለሌሎች ሙዚቃ አፍቃሪ ዜጎቹ ለማስተላለፍ “ካዛቶፒያ የዲጂታል ሙዚቃ ማሠልጠኛ ተቋም” አቋቁሞ፤ ዲጂታል (በኮምፒዩተር) ሙዚቃ ማስተማር እንደጀመረ ይናገራል - እንዳልክ ድሉ፡፡
እንዳልክ ፈቃድ አውጥቶ በኮምፒዩተር ሙዚቃ ማስተማር ከጀመረ ዘጠኝ ወራት ሆነው፡፡ ተቋሙ፤ የሙዚቃ ቅንብር፣ ዲጄ ፕሮዱሰር፣ ሚክሲንግ ኤንድ ማስተሪንግ፣ የፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ ቅንብር ኮርሶችን ይሰጣል፡፡ ወደፊት በክረምቱ ደግሞ ግራፊክስና ቪዲዮ ኤዲቲንግ ለመጀመር እየተዘጋጁ እንደሆነ የሙዚቃ ት/ቤቱ መሥራች ተናግሯል፡፡
ዲጂታል ሙዚቃዎች ምን እንደሆኑ ሲገልጽ፡- ‹‹ሙዚቃ ማስተማሪያ ሁለት ዓይነት ዘዴዎች አሉ። አናሎግና ዲጂታል፡፡ አናሎግ የሙዚቃ መሳሪያዎች በመጠቀም ማስተማሪያ ነው፡፡ ዲጂታል ወይም ኮምፒዩተራይዝድ ሙዚቃ ሲባል ኮምፒዩተርን በመጠቀም የሚሰሩ ሙዚቃዎችን፣ ቅንብሮችን ማለት ነው” ብሏል፡፡
የሙዚቃ ቅንብር ከመሠረታዊ አንስቶ መማር ለሚፈልጉ የ4 ወር ኮርስ ይሰጣል፡፡ ‹‹ሙዚቃ የሚያውቁትን ደግሞ እንፈትንና እንደየእውቀታቸው 3 ወር 2 ወር ወይም ከዚያ በላይ ሊሆን ይችላል›› ብሏል - እንዳልክ፡፡
አንድ ሰው ሙዚቃ ለመማር ወደ ተቋሙ ሲሄድ መጀመሪያ የሚደረገው፤ ያ ሰው ስለ ሙዚቃ ምን ያውቃል? ስለ ሙዚቃ ያለው እውቀት ምን ያህል ነው?..... በማለት በተማሪውና በተቋሙ መካከል  የኢንፎርሜሽን ልውውጥ ይደረጋል፡፡ ምክንያቱም ‹‹ስለ ኮምፒዩተር (ዲጂታል) ሙዚቃ ቀርቶ ስለ ኮምፒዩተር አጠቃቀም የማያውቅ ሰው አለ፡፡ ስለ ኮምፒዩተር የማያውቅ ከሆነ ከዚህ እንጀምራለን። ይኼ በነፃ የሚሰጥ ትምህርት ነው፡፡ ከዚያም ትምህርቱ ስለሙዚቃ ቅንብር ስለሆነ ስለ ሙዚቃ መሰረታዊ እውቀት እንዲኖራቸው እናደርጋለን። ይህን ከተማሩ በኋላ ቀጣዩ ደረጃ ቅንብሩ ነው። ቅብሩን ለመሥራት ደግሞ የተለያዩ ሶፍትዌሮችን ይጠቀማሉ፡፡ እነዚያን ሶፍትዌሮች በመጠቀም አንድ ሙዚቃ ማቀናበር እንዲችሉ እናስተምራቸዋለን›› ብሏል መስራቹ፡፡
‹‹ኮምፒዩተራይዝድ ሙዚቃ ሲባል፣ ብዙ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ድምፅ መቅዳት፣ በአናሎግ ዘዴ የተቀዳውን ወደ ኮምፒዩተር (ዲጂታል) መለወጥ፣ ሚክስና ማስተር፣… ይኖራሉ፡፡ ዲጄ ፕሮድዩሰርም እናስተምራለን፡፡፡ በእኛ አገር ዲጄ የተለመደው የተለያዩ ዘፋኞችን ሙዚቃ ማጫወት ነው፡፡ በውጪው ዓለም ግን የተለየ ነው፡፡ ዲጄ ፕሮዱሰሩ ራሱን የቻለ የሙዚቃ አቀናባሪ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የራሱን ሙዚቃ ሙያዊ በሆነ መንገድ አቀናብሮ ለተመልካቹ ያቀርባል፡፡  እኛ የምናስተምረው የሌላውን ብቻ ሳይሆን የራሱንም ሙዚቃ እንዴት አቀናብሮ ማቅረብ እንዳለበት ነው›› በማለት ገልጿል።
እንዳልክ እስከሚያውቀው ድረስ ዲጂታል ሙዚቃ ትምህርት ያለው በደቡብ አፍሪካና በኬንያ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የወደፊቱ ሕልው የኢትዮጵያን ሙዚቃ ዲጅታል አድርጎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነትን እንዲያፈራ መሥራት ነው፡፡ ለምሳሌ ይላል፤ ‹‹የምዕራብ አፍሪካ ሙዚቃዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ናቸው፡፡ ሙዚቀኞቹም ጥሩ ገንዘብ ስለሚያገኙ ኑሮአቸውም የምቾት ነው። የእኛ አገር ሙዚቀኞች በዓለም አቀፍ  ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኙ እንሠራለን፡፡
‹‹የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ባህላዊ ዘፈኖቻቸውን ነው ዘመናዊ አድርገው በዓለም ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደረጉት፡፡ የእኛ አገር ሙዚቀኞች ብዙዎቹ የሚበረታታና የሚደነቅ ችሎታ አላቸው። ክፍተት የሚታይባቸው በቴክኖሎጂ ላይ ነው። ጥሩ ድምፅ ያላቸው ሙዚቀኞችም ሞልተዋል፡፡ ይህ ችሎታ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ቢታገዝ ከዚህ በላይ መሆን ይችላሉ፡፡ እኛ የድምፅ ሥልጠናም ለመስጠት አቅደናል፡፡ አንድ ሰው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚሆነው በተፈጥሮ ባለው ላይ እሴት ጨምሮ ሲገኝ ነው፡፡
‹‹እውነቱን ለመናገር የኢትዮጵያ ሙዚቃ ብዙ ጊዜ ስናየው ከድንበር አላለፈም፡፡ የምዕራብ አፍሪካኖቹ በአገራችን እንኳ ተደማጭ ናቸው፡፡ ይህም ወደ ዓለም አቀፍ ገበያው ምን ያህል እንደገቡ የሚያሳይ ነው፡፡ በዓለም ደረጃ 4 x 4 የሚባል የሚያስደንስ ሙዚቃ አለ፡፡ ምዕራብ አፍሪካኖች ባህላዊ ዘፈኖቻቸውን በቅንብር ለዳንስ እንዲመች ስላደረጉ ነው ተቀባይነት ያገኙት፡፡ እኛም ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ማደግ የሚችሉ ብዙ ባህላዊ ዘፈኖች አሉን፡፡ ለምሳሌ ወላይትኛውን ሙዚቃ በቅንብር ወደዚያ ማሳደግ እንችላለን፡፡ ይህ የሚሆነው ግን እውቀቱ ሲኖር ነው፡፡ አንድ ሙዚቃ ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ማደግ የሚችለው በቅንብር ብቻ ሳይሆን በሚክሲንግና በማስተሪንግ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ሙዚቀኞቻችንን ስናይ ቅንብር ላይ ጥሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሚክሲንግና ማስተሪንግ ይጎድላቸዋል፡፡ አንድ ሰው መጀመሪያ ሙዚቃ ቅንብር ይማራል፡፡ ከዚያም የተማረውን ከተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች (ከበሮ፣ ሳክስፎን፣ ጊታር…) ጋር ለጆሮ እንዲጥም አድርጎ ሚክስ ያደርጋል፡፡ ማስተሪንግ ማለት ደግሞ ሚክስ ያደረገውን ሙዚቃ ለገበያ እንዲውል ማድረግ ነው፡፡
ድሬደዋ ተወልዶ አዲስ አበባ ያደገው እንዳልክ ድሉ፣ ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በማርኬቲንግ ተመርቋል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ተምሮ ነው፤ ወደ ለንደን (እንግሊዝ) ሄዶ 7 ዓመት የቆየው፡፡ ከካዛቶፒያ መምህራን አንዱ እንዳልክ ሲሆን ቀሪዎቹ የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት መምህራን ናቸው፡፡       

Read 3959 times