Monday, 13 March 2017 00:00

በመስዋእትነት አምልኮ፣ ዓይናቸውን እየጋረዱ፣ በቃላት ቁማር ይሸዋወዳሉ!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(6 votes)

 እስቲ፣ በየእለቱ የሚነበነቡ አባባሎች ምን እንደሚመስሉ ከነትርጉማቸው፣ ለአፍታ ተመልከቱ።  
የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን ለማድረግ፣ የሚሌኔየም ግቦችን ለማሟላት፣ ሕፃናትን እናስከትብ! (ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስከተብ የሚነሳሱት፣ ለኢትዮጵያ ህዳሴና ለUN ግቦች በመቆርቆር?)
የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድን ለማሳካት፣ የትራፊክ አደጋን በጋራ እንከላከል! (ያ እቅድ ባይኖር፣ በትራፊክ አደጋ መሞት አያሳስበኝም? በግሌም አልጠነጠቀቅም!)
የትምህርት አላማ፣ የአገር ልማትንና የሕዝብ ጥቅም ግብአት የሚሆን የሰው ሃይል ማፍራት ነው! (የምትማሪው፣ ኑሮሽን ለማሻሻል አይደለም። አገርን ለማልማት፣ ህዝብን ለማገልገል ነው?)
1200 ሰራተኞች ተሰማርተው ከተማዋን ያፀዳሉ። እግረመንገዳቸውም የኑሮ ገቢ ያገኛሉ። (በ‘እግረመንገድ’ እንጂ፣ የሰራተኞቹ አላማ ገቢ ማግኘት አይደለም። ከተማ ለማሳመር?)
መንግስት፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ተማሪ ህፃናት፣ በየቀኑ ዳቦ በወተት ሊያበላ ነው። በዚህም፣ ለ120ሺ ሰዎች የስራ እድል ይፈጠራል። (ይህንን ‘ድንቅ የቃላት ቁማር’፣ በዝርዝር እናየዋለን)።
እውቁ ተመራማሪ፣ በአገሪቱ አዝማሚያ አዝኖ፣ በምሬት እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-
“የአእምሮ ስራ፣ በትክክል እውነታን አስተውሎ ግንዛቤ መጨበጥ ነው” (... ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመውን ለማየት ከፈለጋችሁ ይሄውና - “the task of every mind is to comprehend reality accurately.”)
የቃላት ጠቀሜታም፣... ለዚህ የአእምሮ ስራ የሚያገለግሉ መሆናቸው ነው። ታዲያ፣... ቃላት፣ እውነታን ለማገናዘብ ሊገልግሉን የሚችሉት፣ በእውነታ ላይ የተመሰረቱ ከሆኑ ብቻ ነው። በአገራችን ግን... በማለት ተመራማሪው ንፅፅር ያቀርባል...
“እኛ፣ በጣሙን ትኩረታችን የሚማረከው፣ ወደ ቃላት ነው። ለእውነታ፣ ቅንጣት ያህል ደንታ የለንም” በማለት የአገሬው ዋና ችግር ምን እንደሆነ ያስረዳል - ተመራማሪው። (We are mostly interested in words and have little concern for reality)።
የአገሬው ኋላቀርነት፣ ጭፍን ተቃውሞ፣ ፕሮፓጋንዳና የመንግስት አፈና፣...
የአገሬው ድህነት፣ አመፅ፣ የድጎማ የራሽን ሽሚያና የመንግስት ገናናነት፣...
የአገሬው ሚስኪንነት፣ የስልጣን ሽኩቻ፣ ትርምስና የመንግስት ጌትነት...
እነዚህ ሁሉ መዘዞች፣ በአጋጣሚ የተፈጠሩ ወይም በእርግማን የመጡ ‘መዓቶች’ አይደሉም። አእምሮና ቃላት፣... ከእውነታ ተነጥለው እንዲርቁ ስናደርግ ነው፣... መዘዞቹ እየተግተለተሉ የሚመጡት።
መንግስትን አፍርሰን ሌላ ብናቋቁም፣ አንዱን ፓርቲ ጥለን በሌላ ፓርቲ ብንተካው፣ አንዱን ባለስልጣን ሽረን ሌላ ፖለቲከኛ ብንሾም፣... ብዙም ውጤት አያስገኝም። አእምሮንና ቃላትን፣... ከእውነታ ጋር ካላስታረቅን በስተቀር፣ የመጠንና የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፣ በመዘዞቹ መደፍጠጣችን አይቀሬ ነው። ከቀውስ መላቀቅና ወደ ብሩህ አቅጣጫ መዞር፣ ከውድቀት መዳንና ወደ ስኬት መጓዝም አንችልም። ተመራማሪው እንዳለው፣ የአእምሮ ስራ እና የቃላት አገልግሎት፣... በትክክል እውነታን አስተውሎ ግንዛቤ መጨበጥ ነው። ይህንን መሸወድ አይቻልም።
ተመራማሪው፣ ኢቫን ፓቭሎቭ ነው። ፓቭሎቭ፣ በአገሩ በራሺያ የተስፋፋውን የተሳሳተ አስተሳሰብና ጠማማ ባህል ምን እንደሚመስሉ በመግለፅ፣ ለአገሬው ቀውስና ውድቀት ዋነኛ መንስኤ መሆናቸውን ለማስረዳት ሞክሯል - የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ። ለዚያውም፣ በዚህ አነጋገሩ የተነሳ፣ እስርና ግድያ ሊደርስበት እንደሚችል አልጠፋውም። ግን፣ ከመናገር አልተቆጠበም። በቃ፣... “በትክክል፣ እውነታን አስተውሎ፣ ግንዛቤ መጨበጥ ነው” - የአእምሮ ስራ፣ የቃላት አገልግሎት። ነገር ግን፣ በተገላቢጦሽ፣ የብዙዎቹ ሰዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ፓርቲዎችና ባለስልጣናት የዘወትር ቅኝት፣ የዚህ ተቃራኒ ነው። የአእምሮ ስራ እና የቃላት አገልግሎት፣... እውነታን ለመደበቅ፣ በእውነታ ምትክም፣ ምናባዊ ተለዋጭ “እውነታ” መፍጠር እንዲሆንላቸው ይፍጨረጨራሉ።
እንዴት?... ለምን? ብለን እንጠይቅ።     

ከእውነታ ጋር በአደባባይ መጣላት! ለምን?
“በየትምህርት ቤቱ፣ ሚሊዮን ሕፃናትን ዳቦና ወተት አበላለሁ። በዚህም ለመቶ ሺ ሰዎች የስራ እድል ይፈጠራል” ወደሚለው የምናባዊ ዓለም ቁማር ከመዝለቃችን በፊል ሌሎቹን ገለጥ ገለጥ አድርገን እንያቸው።
“የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድን ለማሳካት፣ የትራፊክ አደጋን በጋራ እንከላከል!”...
ዋና የመቀስቀሻ መሳሪያ እንደሚሆን ታስቦ፣... በትልቅ ባነር ተዘጋጅቶ፣ በሰፊው ተዘርግቶ የተሰቀለ፣ አውራ መፈክር እንደሆነ ልብ በሉ።
ለትራንስፎርሜሽ እቅድ ተቆርቁረን... የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ስንነሳሳ ይታያችሁ። ያስገርማል። ግን፣... ያን ያህልም አግራሞት ሲፈጥር አታዩም። አለምክንያት አይደለም።
ላለመሞት፣ አካልን ላለማጣት አስበህ፣... ንብረት እንዳይወድምብህ ተቆርቁረህ፣... ከትራፊክ አደጋ ተጠንቀቅ! ከጉዳትና ከስቃይ ለመዳን አስበሽ፣ የትራፊክ አደጋን ተከላከይ! እንዲህ አይነት መልእክቶች ወደ ጎን ገሸሽ የሚደረጉትም አለምክንያት አይደለም።
ምክንያቱም፣ እያንዳንዱ ሰው፣ ለራሱ ሕይወትና ጥቅም ተቆርቁሮ፣ የትራፊክ አደጋን ቢከላከል፣ ትርጉም የለውም። ራስ ወዳድነት ነው! ነውር ነው... ወይም ቢያንስ ቢያንስ እርባና የሌለው ነገር ነው። ለራሱ ሕይወትና ንብረት በመቆርቆር ሳይሆን፣ በግል ምንም ጥቅም ሳያገኝ፣ ለለአገር ልማት፣ ለህዝብ ጥቅም፣ ለትራንስፎርሜሽን እቅድ በመቆርቆር፣... የትራፊክ አደጋን መከላከል ግን፣ “መስዋእትነት” ስለሆነ፣... ቅዱስ ተግባር ነው። ይሄ ነው የሚፈለገው።
በእርግጥ፣ ለራሱ ሕይወት ሳይቆረቆር፣ ለአገር ልማት እየሳሳ፣ የትራፊክ አደጋን የሚከላከል ብዙ ሰው ይኖራል ማለት አይደለም። ቅስቀሳውም፣ ለውጥ እንደማይመጣ ይታወቃል። ግን፣ ቅስቀሳው ውጤታማ ባይሆንም እንኳ፣ ችግር የለውም። “መስዋእትነት”ን የሚያስቀድምና የሚያወድስ ቅስቀሳ ስለሆነ፣ ተመራጭ ይሆናል።
አዎ፤ ሺ ጊዜ ቢደጋገም ውጤት አያመጣም። ነገር ግን፣ ቅስቀሳው የሚካሄደው፣ ውጤት እንደሚያመጣ በማስመሰል ነው (ራስን በማታለል፣ ራስን በመዋሸት፣ ከእውነታ ጋር በመራራቅ)። ሌሎች ተመልካች ሰዎችም፣ በቅስቀሳው ውጤት የሚመጣ እንዲመስላቸው ይፈለጋል (ውሸት፣ ፕሮፖጋንዳ፣ ከእውነት ጋር የተጣላ ቁማር... በየመስኩ የሚስፋፋው እንዲህ እንዲህ እያለ ነው)።

ለህዳሴና ለUN ብላችሁ አስከትቡ!...
የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን ለማድረግ፣ የሚሌኔየም ግቦችን ለማሟላት፣ ሕፃናትን እናስከትብ!... ራሳችንን መሸወድ፣ እርስበርስ መሸዋወድ፣ የዚህን ያህል በዝቷል።
“ልጆቻችሁ እንዳይታመሙና እንዳይሞቱ በማሰብ፣ አስከትቡ” ብሎ የሚናገር ሰው ቢመጣ፣ ወላጆች አይሰሙትም? ይሰሙታል እንጂ። ልጆቻቸውን የሚያስከትቡትም፣ ለህዳሴና ለUN በማሰብ እንዳልሆነ ይታወቃል። ግን፣ ይሄ አይበረታታም። ራስ ወዳድነት ነዋ። ለኢትዮጵያ ህዳሴ ወይም ለUN በመቆርቆር ልጆችን ማስከተብ ግን፣ “በጎ ተግባር” ነው። ለራስ ጥቅም በማሰብ ሳይሆን፣ የሌሎችን ጥቅም በማስቀደም፣ አገርን በማስቀደም የተሰራ ነገር፣ መስዋእትነት ስለሆነ ቅዱስ ተግባር ይሆናል። አዎ፣ “ለኢትዮጵያ ህዳሴና ለUN  ስትሉ፣ ልጆችን አስከትቡ” የሚለው ቅስቀሳ፣ ብዙ ሰሚ አይኖረውም። ውጤትም አያስገኝም። ችግር የለውም። መስዋእትን የሚያመልክ ስለሆነ፣ ውጤት ባያመጣም፣ ተገቢ ነው። ውጤት እንደሚያመጣ ማስመሰል... መዋሸት )   

የምትማረው ግብአት ለመሆን ነው!
የትምህርት አላማ፣ ለአገር ልማትና ለሕዝብ ጥቅም ግብአት የሚሆን የሰው ሃይል ማፍራት ነው! ይሄ በአዋጅ የሰፈረ ሃሳብ ነው። እና፣ ለመማር የምንነሳሳው፣ ኑሯችንን ለማሻሻል ሳይሆን፣ እንደ ማዳበሪያ “ግብአት” ለመሆን ነው። ለአገር ልማት፣ ለህዝብ ጥቅም በመቆርቆር!
ለነገሩ፣ በየአመቱ፣ የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች፣ “ለአገር ልማት፣ የሚጠበቅብኝን ሁሉ፣ ለመስራት ዝግጁ ነኝ” እያሉ ሲናገሩ እንሰማ የለ!
የብዙ ተመራቂዎች ሃሳብና ጭንቀት፣ ስራ አግኝተው በጥሩ ደሞዝ ኑሯቸውን ለማሻሻል ቢሆን እንኳ፣ ይህንን እንደ ውሸት፣ እንደ ነውር፣ እንደ ተራ ነገር እንቆጥረዋለን። “የተማርኩት፣ ለአገር ልማትና ለህዝብ ጥቅም ነው” የሚል ሃሳብ ግን፣ እየተደጋገመ ይስተጋባል። ራሳችንና ሌሎችን እያታለልን እንደሆነ ብናውቅም።  
ሰሞኑን በኢቢሲ የሰማነውንም ዜና መጥቀስ ይቻላል። ለአዳማ ከተማ ፅዳት፣ 1200 ሰራተኞች ተሰማርተው ከተማዋን ያሳምራሉ። እግረመንገዳቸውን፣ የኑሮ ገቢ ያገኛሉ ብሏል ዜናው። እግረመንገዳቸውን?... በ‘እግረመንገድ’ እንጂ፣ የሰራተኞቹ አላማ ገቢ ማግኘት አይደለም። ደሞዝ ባይከፈላቸውም፣ ከተማዋን እያፀዱ ማሳመራቸውን ይቀጥላሉ - እንዲህ አይነት መስዋእትነት ይደነቃል፤ ይወደሳል። ውሸት እንደሆነ ብናውቅም፤ እንዳላወቅን ሆነን እንቀበለዋለን። የመስዋእትነት አምልኮ፣ እንዲህ በየእለቱ ከእውነታ ጋር ያጣላናል። ያለደሞዝ፣ በመስዋእትነት ከተማ ይፀዳል እያልን በምናብ የውሸት አለም እየፈጠርን በአድናቆት ብንጥለቀለቅ ምንም ውጤት እንደማያመጣ ጠፍቶን ነው? እንደማያዋጣና እንደማይሰራ ሳናውቅ ቀርተን ነው? እናውቃለን። ግን፣ ለመስዋእትነት ካለን አምልኮ የተነሳ፣ እውነታን ወዲያ አሽቀንጥረን፣ የውሸት ዓለምን እንክባለን።
የመስዋእትነት አምልኮ፣ ከእውነታ እና ከእውነት ጋር የማይታረቅ ፀብ እንዳለው፣ ደራሲዋና ፈላስፋዋ አየን ራንድ እንዲህ ትገልፃለች። ያው ሶሻሊዝም፣ በመስዋእትነት አምልኮ ላይ ከተመሰረቱ አስተሳሰቦች አንዱ አይደል? አዎ፣ የትም አገር፣ ከጥፋት በስተቀር፣ ጠቃሚ ውጤት አስገኝቶ አያውቅም። ነገር ግን፣ ብዙዎቹ የሶሻሊዝም አጨብጫቢዎች፣ “ውጤት አላስገኘም” ብለው አስተሳሰባቸውን አልቀየሩም።
“The arguments that socialism would not and could not work, did not stop them: neither has altruism ever worked, but this has not caused men to stop and question it.”...
“...What blinded them? The morality of altruism.”

ተማሪዎችን በመቀለብ የስራ እድል መፍጠር?
ኢቢሲ ሰሞኑን፣ ከባህርዳር ያስተላለፈው ዜና እንዲህ ይላል። መንግስት፣ ተማሪ ህፃናትን፣ ዳቦ በወተት ሊያበላ ነው። በዚያው ክልል ብቻ፣ 1.7 ሚሊዮን ተማሪ ህፃናት፣ በየእለቱ ዳቦ በወተት እንዲበሉ ነው የታቀደው። የሌሎቹ ክልሎች ሲጨመርበት፣ የተማሪዎቹ ቁጥር፣ 7 ሚሊዮን ገደማ ይሆናል።
ግን፣ ወደ ዝርዝር ጉዳይ ሳንገባ፣ አንድ ጥያቄ ላንሳ? ሚሊዮን ተማሪዎች መቀለብ ለምን አስፈለገ? አገሬው ይበልጥ እየደኸየ ነው እንዴ? ልጆቹን መመገብ የማይችል ድሃ በዝቷል ማለት ነው?
አንድ ጥያቄ አነሳለሁ ብዬ፣ በእሩምታ ለቀቅኩት!
ለመሆኑ፣ በየቀኑ ለሚሊዮን ህፃናት ዳቦና ወተት ለማቅረብ፣ ገንዘቡ ከየት ይመጣል? ያው፣ ከዜጎች ኪስ ተቀንሶ፣ የስራ እድል ከሚፈጥሩ ኢንቨስተሮች ተወስዶ ነዋ!
“ከኪሳችሁ ወስጄ፣ ልጆቻችሁን እመግባለሁ” እንደማለት ነው።
እንዲያው ስታስቡት፣ ኢንቨስተሮች በገንዘባቸው ቢዝነስን ሲያስፋፉ፣ ብዙ ዜጎች የስራ እድል እያገኙ፣ በራሳቸው ጥረት ህይወታቸውን ማሻሻል፣ ልጆቻቸውን መመገብና ማሳደግ ቢችሉ፣... ከተመፅዋችነት የፀዳ ክቡር ሕይወት ቢጎናፀፉ አይሻልም? ወላጆች፣ የራሳቸውን ልጆች ቢመግቡ፣ ምን ትርጉም አለው? የራሳቸውን ልጆችን መመገብ ይፈልጋሉ። ይመግባሉ። ይሄ እንደ ቅዱስ ተግባር መቆጠር የለበትም። ከመስዋእትነት የራቀ ነዋ። ይልቅስ... ለልጃቸው ያሰቡትን ገንዘብ፣ ቢዝነስ ለማስፋፋትና ስራ ለመፍጠር ያሰቡትን ገንዘብ፣... ለራሳቸው ጥቅምና ለቤተሰባቸው ሳያስቡ፣... በታክስ መልክ ለመንግስት ቢሰጡ፣... ለአገርና ለህዝብ ጥቅም የተከፈለ መስዋእትነት ስለሆነ ይደነቃል።
ከዚህ ምክንያት፣ ቢዝነስ ባይስፋፋ፣ ዜጎች የስራ እድል ባያገኙ፣ መተዳደሪያ ገቢ ባይኖራቸው... ችግር የለውም። አትጨነቁ፤ ጨርሶ አታስቡ። ለቢዝነስ የታሰበውን ገንዘብ መንግስት እየወሰደ፣ ህፃናትን ለመርዳትና ለመቀለብ ያውለዋል። ይሄ “በጎ ተግባር” ነው። ዜጎች፣... ልጆቻቸውን መመገብና ማሳደግ አይችሉም። ግን፤ ምፅዋት ይኖራል። እለት በእለት፣ ልጆችን የሚያበላ፣ “ደግ መንግስት” አለላችሁ። ይህም ብቻ አይደለም።
የምፅዋት ኢንዱስትሪው ሲስፋፋ፣ ከምፅዋት ዋና መስሪያ ቤት ጀምሮ፣ እስከ ወረዳና እስከ ትምህርት ቤት ድረስ፣ ስራ አስኪያጅ፣ ረዳት፣ ፀሐፊ፣ ተላላኪ፣ የፋይናንስና የግዢ ክፍል፣ የመዝገብ ቤት ሰራተኛ፣ የመጋዘን ሃላፊ፣... ያው እንደማንኛውም የመንግስት አገልግሎት... እየተዝረከረከና እየተንዛዛ... የምፅዋት ቢሮክራሲው እየሰፋ እንደሚሄድ አትጠራጠሩ። ብዙም ሳይቆይ፣... ብልሽትና እጥረት፣ ብክነትና ስርቆት... መስፋፋቱ ስለማይቀር፣...... የጥራት ተቆጣጣሪ፣ የአቅርቦት ተቆጣጣሪ፣ የሙስና ተቆጣጣሪ፣...  እየተለጠጠና እየተደራረበ፣ በእልፍ አእላፍ “አገልጋዮች” የተጠላለፈ የቢሮክራሲ መረብ ይዘረጋል - አላስፈላጊ የድለላ መረብ በሉት። ህፃናትን ለመመገብ፣ አላስፈላጊ የደላላ መዓት ማሰለፍ!
ግን፣ አትርሱ፤ ይሄ ሁሉ የሚሆነው፣ “ለበጎ አላማ” ነው። አላስፈላጊ አዲስ የድለላ (የቢሮክራሲ) መረብ የሚፈጠረው፣ ሕፃናትን ለመመገብ ስለሆነ፣ ቅር ሊላችሁ አይገባም። ሕፃናት እንዳይመገቡ ትቃወማላችሁ እንዴ? በዚያ ላይ፣ የፈቃደኝነት ጉዳይ ነው እንጂ፣... የምፅዋት ቢሮክራሲን እንደ ጥፋት አለመቁጠር ይቻላል። እንዲያውም፣ መልካም ገፅታ ልናላብሰው እንችላለን። “አዲስ የስራ ፈጠራ ነው” ብለን፣ በጥቂት ቃላት፣ ነገሩን ማሳመር አያቅተንም። ልናሳምረው እንችላለን። በየትምህርት ቤቱ፣ ህፃናትን ዳቦ በወተት ለማብላት በሚፈጠረው አዲስ የምፅዋት ቢሮክራሲ አማካኝነት፣... በአንድ ክልል ብቻ፣ 120ሺ የስራ እድል እንደሚፈጠርኮ ሰሞኑን ተነግሮናል። በሁሉም ክልሎች ተስፋፍቶ ሲደማመር፣ የምፅዋት ኢንዱስትሪው፣ 500ሺ የስራ እድሎችን ሲፈጥር ይታያችሁ።
ዜጎች ልጆቻቸውን ለመመመገብ፣... ይሄ ሁሉ ደላላ እንደሚያስፈልግ መች አወቁ? በእርግጥ፣ ይሄ አባባል ስህተት ነው። የድለላን ሙያ የሚያንቋሽሽ አባባል ነው። አንዱ ደላላ መጥቶ፣ እንዲህ ቢላችሁ አስቡት።...
“ከመንደሩ ነዋሪዎች በሙሉ ገንዘብ እወስዳለሁ። እምቢ ማለት አትችሉም። በዚሁ ገንዘብ፣... ልጆቻችሁን የሚመግቡ ብዙ ‘አገልጋዮችን’ እቀጥራለሁ። ወጪው ቀላል አይደለም። ግን፣ ለበጎ አላማ ነው። ደግሞም፣ ስንትና ስንት ሰው፣ አዲስ የስራ እድል እያገኘ እንደሆኑ ተመልከቱ። ልጆቻችሁን ለመመገብ የቀበልነው ሃላፊነት ከባድ ቢሆንም፣ ይህንን የተቀደሰ ህዝባዊ ሃላፊነታችንን በአግባቡ ለመምራት፣ እንደአስፈላጊነቱ በየወረዳው፣ ቢሮዎችን እንከፍታለን፣ በቁሳቁስ እናሟላለን። ቢሮዎችን ስንከፍትና በቁሳቁስ ስናደራጅ፣ ስንትና ስንት ቤት አከራዮች፣... ጠረጴዛና ወንበር ሰሪዎች፣... ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አትዘንጉ። የገበያ ትስስር ተፈጠረ ማለት ነው። ዳቦ የሚያመርቱ፣ ዳቦ ገዝተው የሚያቀርቡ፣... ዳቦ የሚያጓጉዙ፣ ዳቦ የሚጭኑና የሚያወርዱ፣ ዳቦ ለተማሪዎች የሚያከፋፍሉ... ለእልፍ አእላፍ ሰዎች ደሞዝና ክፍያ ለመስጠትም ገንዘብ ያስፈልጋል። እልፍ አእላፍ፣ የስራ እድል ተፈጠረ ማለት ነው።... ዘርዝሮ መጨረስ ይከብዳል። ወጪው ብዙ ነው። ከእናንተ በወሰድኩት ገንዘብ፣ ይሄን ሁሉ ወጪ እሸፍንና፣... በቀረው ገንዘብ፣ ልጆቻችሁ የሚበሉትን ምግብ እገዛላቸዋለሁ። እመግባቸዋለሁ።” ... ቁምነገር ብሎ እንዲህ የሚናገርና፣... ሰምተን እንድናጨበጭብለት የሚጠብቅ ደላላ ሊኖር ይችላል?
የሰከረ ደላላ ካልሆነ በቀር። ራሴ ሁለት ዳቦ ገዝቼ ልጄን ማብላት እየቻልኩ፣... ለምን ገንዘቤን ላንተ እሰጣለሁ? ግማሹን ገንዘብ ለቢሮክራሲ አባክነህ፣ በቀሪው ገንዘብ አንድ ዳቦ ብቻ ገዝተህ ልጄን ለማብላትና ያንተ ተመፅዋች እንድንሆን ነው የፈለግከው? ብክነቱን... “የስራ እድል ፈጠራ ነው” ብለን እንድንደግፍ፣... ተመፅዋች እንድሆን ማድረግህን ደግሞ፣ “በጎ ተግባር ነው” ብለን እንድናደንቅ፣ “ቅዱስ” ብለን እንድናወድህም ትጠብቃለህ? ንግግርህ፣ ከስካር ስሜት የመጣ ንግግር መሆን አለበት... ብንለው አይገርምም።      
በደላላው ምትክ፣... ያንኑን ተመሳሳይ ገለፃ የሚነገረን፣... መንግስት ከሆነስ? የእርዳታ ድርጅት ወይም ዩኤን ከሆነስ? ያኔ፣ የስካር ንግግር መሆኑ ይቀራል። ያኔ፣ ቅዱስ ንግግር ይሆናል።

Read 3259 times