Saturday, 11 March 2017 11:47

አስገድዶ መድፈር ... የኃይል መግለጫ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

 አስገድዶ መድፈር ወይንም ጾታዊ ጥቃት ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ከዘር፣ ከድህነት፣ ማህበራዊ እና ሃይማኖታዊ ችግሮች በላይ እጅግ አስከፊ ችግር ነው። ጥቃቱ በተደጋጋሚም የሚፈጸመው በሴቶች እና ወጣቶች ላይ በተለይም በድህነት ችግር ባሉና ሊከላከሉት ወይንም እንዳይፈጸም ሊያስወግዱት በማይችሉት ላይ ነው። በእርግጥ ትዳር በያዙ እና ለአቅመ አዳም በደረሱ ሴቶች ላይ ሲፈጸም ምናልባትም በቤት ውስጥ ጥቃት፣ ወሲባው ትንኮሳ ወይንም ሳይፈልጉ ለወሲብ መጋለጥ በሚል ሊተካ ይችላል። በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ምን ያህል አስገድዶ መድፈር ይከሰታል የሚለውን ለማወቅ ከአቅም ውስንነት የተነሳ ተከታታይ ጥናት ማድረግ የማይቻል ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ከዚህም በላይ በባህልና ማህበራዊ ትስስር የተነሳ ድርጊቱን በቀጥታ ወደፍትህ ከማቅረብ ይልቅ መሸመጋገልና ጥፋቱ እንዳይጋለጥ ማድረግ በብዙዎች ዘንድ የተለመደ በመሆኑ በእርግጠኝነት ይህን ያህል ብሎ ለመናገር ያስቸግራል። በአለም አቀፍ ደረጃ ከ40-47% የሚሆነው በሴት ልጆች ላይ የሚፈጸመው ወሲባዊ ጥቃት በእድሜያቸው 15 አመትና ከዚያ በታች በሚሆኑት ላይ ነው።
የአለም የጤና ድርጅት በ2012 ባወጣው ዘገባ አንዳስነበበው ተገዶ መደፈር ከድህነትና ከስራ አጥነት ጋር በተያያዘ ይበልጥ የሚያጋጥም ጉዳት ሲሆን ይህም በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ 30% ማለትም ወደ 30,000 የሚሆኑ ሴቶች በወሲብ ንግድ ስራ ላይ እንዲተዳደሩ የሆኑበት ምክንያት በመሆን ተጠቃሽ ሲሆን እድሜያቸውም ከ12-26 አመት የሚደርስ ነው። ከዚህ ጥናት በሁዋላ ባሉት አመታት ሁኔታዎች በምን ደረጃ ተለውጠው እንደሆን ለማመሳከር የሚረዱ መረጃዎች ለጊዜው ከእጃችን አልገባም። ወጣት ሴቶች በገንዘብ እጦት ምክንያት መበሸሮቈሮሳሽሹገር ዳዲ የሚል ቅጸል ስም ለተሰ ጣቸው እና በእድሜያቸው ጠና ላሉ ወንዶች ወሲብ መዝናኛነት እራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡ ሲሆን በተጨማ ሪም ተገደው ሊደፈሩ የሚችሉበትን አጋጣሚ መሸሽ ወይንም እራሳቸውን ከአደጋው ለመከላከል የማይችሉበት ሁኔታ ያይላል።
ሴቶች ተገደው ሲደፈሩ እራሳቸው ጥቃቱ የደረሰባቸውም ይሁኑ ቤተሰብ ለምን ድርጊቱን ይፋ አያደርገውም ሲባል ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉትን የአለም የጤና ድርጅት እንደሚከተለው አስቀምጦታል።
ድርጊቱን ይፋ አውጥቶ ተገቢውን ምላሽ ለማግኘት በቂ ድጋፍ አለመኖር፣
በተፈጸመው ነገር ሀፍረት መሰማትና ራስን ለመደበቅ መሞከር፣
ወደፍትሕ ለማቅረብ ሲሞከር በምላሹ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መፍራት፣
ሊደርስ የሚችለውን ወቀሳ ወይንም በሰዎች ዘንድ መጠላትን በመፍራት፣
ታማኝነትን ሊያሳጣ ይችላል የሚል ስጋት፣
በህብረተሰቡ ወይም በቤተሰብ ዘንድ ሊደርስ የሚችለውን መገለል ወይም መናቅ በመፍራት የመሳሰሉት ናቸው።
የአለም የጤና ድርጅት ዘገባ እንደሚያስረዳው በሕይወት ዘመን የተፈጸመ እና ሪፖርት የተደረገ ወሲባዊ ጥቃት በእድሜያቸው ከ15-49 አመት በሚሆናቸው ላይ በጃፓን 6% እስከ 59% በኢትዮጵያ ነው። ተገዶ መደፈር በማህጸን ላይ ሕመም የሚያደርስ ከመሆኑም በተጨማሪ ከሚያስከትላቸው ችግሮች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
የስነተዋልዶ ጤና ችግር፡-
ያልተፈለገ እርግዝና
ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስን ማቋረጥ
በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፍ በሽታ የመሳሰሉት ይገኙበታል።
የአእምሮ ሕመም፡-
ድብርት
ጭንቀት
የእንቅልፍ መዛባት
ፍርሀት
ሕይወትን ለማጥፋት መሻት
የባህርይ ችግር፡-
ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ መፈጸም
ከብዙ ሰዎች ጋር ወሲብ መፈጸም
ሰዎችን ለወሲብ ድርጊት ማነሳሳት እና መገፋፋት ፈቃደኛ መሆን
አልኮሆል፣ ሱስ አስያዝ እጾችን መጠቀም...ወዘተ
ወደ ሕልፈት ማምራት፡-
እራስን ማጥፋት
ባልተፈለገ እርግዝና ምክንያት በሚፈጠር ችግር ሕይወትን ማጣት
ደህንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ጽንሱን በማቋረጥ ምክንያት
በኤችአይቪ ኤይድስ መያዝና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት
ተገዶ በመደፈር ወቅት የሚደርስ ሞት
ተገዶ በመደፈር የተወለደውን ልጅ መግደል የመሳሰሉት ናቸው።
 ጾታዊ ጥቃት ለማድረስ ምክንያት ናቸው ተብለው ከሚገመቱ መካከል የሚከተሉት ይገኙበ ታል።
መጥፎ አስተዳደግ ፡-
ይህ ወላጆች የልጆቻቸው የወደፊት ማንነት ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን ድርሻ ግዙፍነት የሚያሳይ ነው። እናት ልጅዋን በጣም ጨቁና ወይንም ምንም ሳትረዳው የምታሳድግ ከሆነ ወይንም ደግሞ አባት በሌለበት ቤት ውስጥ ልጆች የሚያድጉ ከሆነ አለዚያም አባት ቢኖርም ከሚስቱ ወይንም ከልጆቹ ጋር ጥሩ የሆነ ሰላማዊ ሕይወትን የማይመራ ከሆነ እንዲሁም በተሳሳተ ግንዛቤ ሴቶች እኛን አይቀርቡንም ወይንም አይፈልጉንም የሚል ስሜት ይዘው የሚያድጉ ከሆነ ጾታዊ ጥቃት አድራሽ የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ይሆናል የሚል ግምት አለ።
ክብርንና ዝናን ምክንያት በማድረግ ፡-
ወንዶች በተለያየ አጋጣሚ ቀድሞ ከነበራቸው ስልጣን ወይንም ክብራቸው ወይንም ታዋቂነታቸው ወርደው ፍጹም የማይታወቁና ለማህበረሰባቸው እንደማይጠቅሙ ተደርጎ መቆጠር ደርሶብኛል ብለው የሚያምኑ ከሆነ ሽንፈታቸውን ያስወገዱ እንዲመስላቸው ሴቶችን መድፈርን ይፈጽሙታል።
የተሳሳተ ግንዛቤ፡-
አንዳንድ ወንዶች ሴቶችን በጥቅሉ በሁለት ከፍለው ይመለከቱዋቸዋል። ይኼውም አንዳንዶቹ ወሲብ መፈጸምን በክብር እና ትልቅ ግምት ሰጥተው ለፍቅር ሲሉ የሚያደርጉት ሲሆን አንዳንድ ሴቶች ግን ለገንዘብ ወይንም ጥቅም ማግኛነት ሲሉ ይፈጽሙታል ብለው ያምናሉ። ስለዚህ እነዚህን የግብረስጋ ግንኙነትን ለገንዘብ ወይንም ለጥቅም ሲሉ የሚያደርጉትን ሴቶች መድፈር ምንም ጥፋት አይደለም ብለው የሚያምኑ ወንዶች ሲፈጽሙት ይስተዋላል።
“ወንድ ሴትን የሚደፍረው ብዙ ጊዜ የስርአተ ጾታ ክፍፍል ልዩነቱ ወይንም ጀንደር ከሚለው ሁኔታ ጋር ይያያዛል። ሴት እንዲህ ነች ወንድ ደግሞ እንዲህ ነው የሚለውን ህብረተሰቡ የሚያምንበትና ተግባራዊ እያደረገው ለው ጋር በተያያዘ አስገድዶ መድፈሩ ብዙ ጊዜ ይፈጸማል። ምክንያቱም ህብረተሰቡ ለወንድ ልጅ ኃይል ወይንም አቅም እንዳለው እየነገረ ስለሚያሳድገው ወንዱ በተፈጥሮው ገኘው ጥንሬ ባሻገር በአስተሳሰብም ኃይል እንዲኖረው ያደርገዋል። ከዚህ በተለየም በልጅነታቸው የመደፈር ወይንም የመገለል እንዲሁም የተለያዩ ጥቃቶች የደረሰባቸው ከሆነ አስገድዶ መድፈርን እንደ እልህ መወጫ ይጠቀሙበታል። አንድ ወንድ እንደዚህ ያለ ጉዳት እየደረሰበት ያደገ ከሆነና እሱም ጥቃቱን መፈጸሙ በሳይንሳዊው መንገድ ሲተረጎም አእምሮው በሚያድግበት ሰአት የተለያዩ ኢንዛይሞች ማለትም ነርቭ ከነርቭ የሚገናኝበት መልእክት የማስተላለፊያ ኬሚሎች በደም ውስጥ እየቀነሰ ይመጣል። አእምሮው እያደገ ሲመጣ ደሙ ግን እየቀነሰ መምጣቱ በሚያድጉበት ሰአት ላይ ይህንን ወሲባዊ ጥቃትም ሆነ ማንኛውንም ወንጀል እንደሰው መግደል የመሳሰሉትን ጨምሮ የመፈጸም እድላቸው የሰፋ ይሆናል። ብዙ ጊዜ አስገድዶ መድፈር የሚፈጽሙ ሰዎች ከአንድ ሰው ጋር ወይንም ከተለያዩ ሰዎች ጋር ጥሩ አይነት ግንኙነት መመስረት የማይችሉ ናቸው። ይህ እንግዲህ ከአስተዳደግ ወይንም ከተለያዩ የህይወት አጋጣሚዎች ሊሆን ይችላል። በተረጋጋ ሁኔታ ከሰዎች ጋር መኖር ልተቻለ ወይንም ህብረተሰቡ የሚጠብቀውን ደረጃ ማሟላት ልተቻለ እንደመሸሻ የሚቆጠረው የአስገድዶ መድፈር ወንጀልን የመሳሰሉ ሊሆኑ ይችላሉ።
አስገድዶ መድፈርን በሚመለከት የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይኖር ያሰጋል። አስገድዶ መድፈርን የሚፈጽም ወንድ የግብረስጋ ግንኙነት ፍላጎት ኖሮት ስሜትን ለማርት ሲባል አይደለም። አንድ ወንድ አስገድዶ መድፈርን በሚፈጽምበት ወቅት በግብረስጋ ግንኙነት ወቅት የሚያገኘውን እርታ ያገኛል ማለትም አይደለም። እንዲያውም የወንድ የዘር ፍሬያቸውን ሳይለቁ አስገድዶ መድፈሩ ሊያበቃም ይችላላ። ስለዚህ ዋናው የአስገድዶ መድፈር ምክንያት ሐይልን መግለጽ መሆኑ ነው በተለያዩ ጥናቶች የተደረሰበት። አንድ ወንድ በህብረተሰቡ የተሰጠው ኃይል ከሴት የተሻለ እንደሆነ እንዲያስብ አድርጎታል። በጾታ ክፍፍሉ ወንድ ከሴት ይበልጣል የሚል ነገር በአእምሮው ውስጥ ስላለ አስገድዶ መድፈር በጥቅሉ ሲታይ የኃይል መግለጫ ነው። ስለሆነም አስገድዶ መድፈር እኔ እበልጣለሁ የሚለውን ስሜት መግለጫ እንጂ ወሲብን ማርኪያ አይደለም።”
 ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት

Read 3959 times