Monday, 13 March 2017 00:00

44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ይኖርበታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   42ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከሳምንት በኋላ በኡጋንዳዋ ከተማ ካምፓላ አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን፤ 66 አገራትን የወከሉ ከ600 በላይ አትሌቶች በአምስት አይነት የአገር አቋራጭ ውድድሮች ይሳተፉበታል፡፡ በሻምፒዮና ከፍተኛውን የውጤት ግምት ያገኙት የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች ናቸው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ለሻምፒዮናው ከ1 ወር በላይ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሙሉ የቡድን ዝርዝር ባይታወቅም፤ በ34ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ በሁሉም የውድድር መደቦች ከ1 እስከ 4 ደረጃ ያገኙት እንዲሁም በወቅታዊ ብቃታቸው እና የጤንነት ደረጃ አስተማማኝ ሆነው የተገኙትን በ5ኛ እና በ6ኛ ደረጃ ለማካተት 40 አትሌቶች በዓለም አገር አቋራጭ ቡድኑ ጊዜያዊ ዝርዝር ተካትተዋል፡፡ በወንዶች ምድብ እነ ሙክታር ኢድሪስ፤  ኢብራሂም ጄይላን እንዲሁም ዮሚፍ ቀጀልቻ በሴቶች ደግሞ ገንዘቤ ዲባባ ልምድ ካላቸው ምርጥ አትሌቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በ9 አሰልጣኞች እና ረዳቶቻቸው እየተዘጋጀ የሚገኘው  ቡድኑ በአራራት ሆቴል ተቀምጦ ከሚያደርጋቸው ስልጠናዎች ባሻገር በአዲስ አበባ ዙርያ በሚገኙ ትንንሽ ከተሞች የጎዳና ላይ እና የጫካ ልምምዶች እያደረገም ነው፡፡ ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት በተለይ በረጅም ርቀት ውድድሮች በወንዶች ከ1981 እኤአ ጀምሮ እንዲሁም በሴቶች ከ1991 እኤአ ጀምሮ ሌሎች አገራትን ጣልቃ ሳያስገቡ በአሸናፊነቱ ላይ ተፈራርቀዋል፡፡ ከኢትዮጵያ እና ኬንያ ባሻገር በተለይ በአዋቂዎች ምድብ ምናልባትም በግል ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ አትሌቶችን እንደሚያሰልፉ የተወሳላቸው ከአፍሪካ አዘጋጇ ኡጋንዳ እና ኤርትራ እንዲሁም የቱርክ፤ የባህሬን፤ የአሜሪካ፤ የእንግሊዝ፤ የአየርላንድ እና የጃፓን አትሌቶች ናቸው፡፡ ውድድሩን የምታስተናግደው የካምፓላ ከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስፈልገውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቋን አረጋግጧል፡፡ ሻምፒዮናውን የሚያስተናግደው በ2014 እኤአ ላይ የአፍሪካ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ያስተናገደው የስፖርት ማእከል እንደሆነ ሲታወቅ፤ በከፍተኛ እድሳት ለውድድሩ መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል  አይኤኤኤፍ እውቁን የኬንያ አትሌት ፖል ቴርጋ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና አምባሳደር አድርጎ ሾሞታል፡፡ በአይኤኤኤፍ እና በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባልነት የሚያገለግለው ፖል ቴርጋት በዓለም አገር አቋራጭ ከፍተኛ ውጤት ካመዘገቡ አትሌቶች አንዱ ሲሆን ለአምስት ጊዜያት በረጀም ርቀት 12 ኪሎ ሜትር በማሸነፍ የወርቅ ሜዳልያዎቹን ሰብስቧል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው  ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለቱም ጾታዎች ድብልቅ የዱላ ቅብብል ውድድር እንደሚኖርም ታውቋል፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር በሻምፒዮናው በግልና በቡድን  ከ1ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች እና አገራትም የገንዘብ ሽልማት ያበረክታል።  በአዋቂ አትሌቶች የሁለቱም ፆታዎች የውድድር መደቦች በግል  ውጤት ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ለ1ኛ 30ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 15ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 10ሺ ዶላር፣ ለ4ኛ 7ሺ ዶላር፣ ለ5ኛ 5ሺ ዶላር እንዲሁም ለ6ኛ ደረጃ 3ሺ ዶላር ይበረከታል፡፡ በቡድን ውጤት ለሚያሸንፉ አገራት ደግሞ ለ1ኛ 20ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 16ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 12ሺ ዶላር፣ ለ4ኛ 10ሺ ዶላር፣ ለ5ኛ 8ሺ ዶላር እንዲሁም ለ6ኛ ደረጃ 4ሺ ዶላር የሚታሰብ ሲሆንበሁለቱም ፆታዎች ድብልቅ የዱላ ቅብብል ውድድር ለ1ኛ 12ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 8ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 6ሺ ዶላር፣ እንዲሁም ለ4ኛ 4ሺ ዶላር እንደሚሸለም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በ2021 እ.ኤ.አ የ44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ አዘጋጅነት ለኢትዮጵያ?
የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ስር ከሚካሄዱ ውድድሮች በአንጋፋነቱ እና በፈታኝነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡  ከ1973 እኤአ ጀምሮ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ለ38 ጊዜያት በየዓመቱ ሲካሄድ የነበረ ሲሆን፤ ከ2011 እ.ኤ.አ ወዲህ ግን በየሁለት ዓመቱ የሚደረግ ሆኗል፡፡ በተለይ ባለፉት 25 አመታት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በየውድድር መደቡ እስከ 10 ያለውን ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ በመቆጣጠር ያሳዩት የበላይነት  ባስከተለው ጫና ነው፡፡ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው በየሁለት ዓመቱ መካሄድ ከጀመረ ዘንድሮ 5ኛው  ነው ማለት ነው፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በተሳትፎ ታሪኳ  ታላላቅ ውጤቶችን አስመዝግባለች፡፡ በኦሎምፒኮችና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ታላላቅ ስኬት ያገኙ አትሌቶች የተገኙት ከፈታኙ የአገር አቋራጭ ሩጫ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዘንድሮ የሻምፒዮናውን መስተንግዶ በጐረቤቷ የምስራቅ አፍሪካ አገር ኡጋንዳ መቀደሟ የሚያስቆጭ ይመስላል፡፡    ሻምፒዮናውን በአፍሪካ አገር ሲካሄድ የዘንድሮው የኡጋንዳ፤ ካምፓላን መስተንግዶ ጨምሮ ለ5ኛ ጊዜ ሲሆን ሞሮኮ ለሁለት ጊዜያት በ1975 እና በ1998 እኤአ፤ ደቡብ አፍሪካ በ1996 እኤአ እንዲሁም ኬንያ በ2007 እኤአ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን አዘጋጅተዋል። ከአውሮፓ እንግሊዝ፤ ፖላንድ፤ ፈረንሳይ፤ ስፔን፤ ፖርቱጋልና ጣልያን ከአንድ ጊዜ በላይ ውድድሩን ያስተናገዱ ከተሞች ሲሆኑ፤ አሜሪካም ከአንድ ግዜ በላይ አዘጋጅ ነበረች፡፡ ከኤስያ ጃፓን፤ ከመካከለኛው ምስራቅ ጆርዳን ሁሉ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን አስተናግደዋል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ ውድድሩን የማዘጋጀት እድሏ ሰፊ በመሆኑ በዚህ አቅጣጫ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ከኡጋንዳዋ ካምፓላ ከተማ በኋላ በ2019 እኤአ ላይ 43ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና እንድታዘጋጅ የዴንማርኳ አሩውስ ከተማ የተመረጠች ሲሆን፤  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ቢያንስ   በ2021 እ.ኤ.አ ላይ 44ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ለማስተናገድ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ውጤት ታሪክ ባለፉት 41 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች
ባለፉት 41 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ላይ በሁለቱም ፆታዎች በአዋቂዎች እና በወጣቶች የውድድር መደቦች የቡድን ውጤት ከቀረቡ 168 ሽልማቶች ኢትዮጵያ  123ቱን ማግኘት የቻለች ሲሆን፤ በአዋቂዎች ምድብ በሁለቱም ፆታዎች በተለይ በረጅም ርቀት ውድድሮች    19  የወርቅ ሜዳልያዎችን አስመዝግባለች።  በሻምፒዮናው የኢትዮጵያ የተሳትፎ ታሪክ በአዋቂዎች ምድብ የአጭርና ረጅም ርቀት ውድድሮች ድርብ የወርቅ ሜዳልያዎች በማግኘት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አትሌት  ቀነኒሣ በቀለ ነው። ቀነኒሣ በአጭር ርቀት 4 ኪ.ሜ እና በረጅም ርቀት 12 ኪ.ሜ ውድድሮች በ5 ሻምፒዮናዎች በተከታታይ በማሸነፍ ብቸኛው አትሌት ሲሆን በ2008 እ.ኤ.አ ላይ በረጅም ርቀት 6ኛውን የወርቅ ሜዳልያ በማግኘቱ ደግሞ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ታሪክ ከፍተኛውን የውጤት ክብረወሰን ያስመዘገበ አትሌት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው በአዋቂዎች ምድብ ውጤታማ ከሆኑ የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች መጠቀስ ያለባቸው ደራርቱ ቱሉ፤ ጌጤ ዋሚ፤ ጥሩነሽ ዲባባ፤ ወርቅነሽ ኪዳኔ ዋናዎቹ ናቸው፡፡  አትሌት ደራርቱ ቱሉ በረጅም ርቀት ለ3 ጊዜያት ያሸነፈች ሲሆን፣ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ በአዋቂዎች ምድብ በረጅም ርቀት ለ3 ጊዜያት እንዲሁም በአጭር ርቀት 1 ጊዜ ማሸነፍ ከኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ትልቁን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በኢትዮጵያዊ አትሌት የመጀመሪያው የሜዳልያ ድል የተመዘገበው በ1981 እ.ኤ.አ ላይ በአዋቂዎች ምድብ በወንዶች የ12 ኪ.ሜ ውድድር ሲሆን መሃመድ ከድር ባገኘው የብር ሜዳልያ ነው፡፡ አትሌት መሐመድ ከድር ከዓመት በኋላ በ1982 እኤአ በተመሳሳይ ረጅም ርቀት አሸንፎ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ አስገኝቷል፡፡ በአዋቂ ወንዶች የ12 ኪሎሜትር ውድድር ኢትዮጵያ ከሰበሰበቻቸው 10 የወርቅ ሜዳልያዎች ስድስቱን ያስመዘገበው አትሌት ቀነኒሣ በቀለ ከ2002-2008 እ.ኤ.አ በተካሄዱት የዓለም ሻምፒዮናዎች ነው። ሌሎቹን 4 የወርቅ ሜዳልያዎች ደግሞ መሃመድ ከድር (በ1982 እ.ኤ.አ)፣ በቀለ ደበሌ (በ1983 እ.ኤ.አ)፣ ገብረእግዚአብሔር ገ/ማርያም (በ2009 እ.ኤ.አ) እንዲሁም ኢማና መርጋ በ2011 እ.ኤ.አ ላይ አስመዝግበዋል፡፡
በአዋቂ ሴቶች የ8 ኪ.ሜ የረጅም ርቀት ውድድር ደግሞ በኢትዮጵያዊ አትሌት የመጀመሪያ የሜዳልያ የተገኘው በ1991 እ.ኤ.አ ደራርቱ ቱሉ በወሰደችው የብር ሜዳልያ ነው፡፡ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ደግሞ በ1995 እ.ኤ.አ ላይ አሁንም ደራርቱ ቱሉ የተጐናፀፈች ሲሆን ሌሎች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ደግሞ በ1975 እና በ2000 እ.ኤ.አ አግኝታለች፡፡ በአዋቂ ሴቶች ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው 9 የወርቅ ሜዳልያዎች 3 ከጥሩነሽ ዲባባ (በ2005፣በ2006፣ በ2008 እ.ኤ.አ) 2 በጌጤ ዋሚ (በ1996፣ በ1999 እ.ኤ.አ) እንዲሁም በወርቅነሽ ኪዳኔ (2003 እ.ኤ.አ) ተገኝተዋል፡፡
በርካታ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሜዳሊያዎችን በግል እና ከቡድን ጋር በማግኘት በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ በአጠቃላይ 27 ሜዳሊያዎችን በመውሰድ ከዓለም አንደኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፣ በሴቶች ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ ወርቅነሽ ኪዳኔ በ21 ሜዳሊያዎች መሪነቱ ላይ ተቀምጣለች። በግልና በቡድን የወርቅ ሜዳሊያዎች ድምር የአለም አገር አቋራጭን የተቆጣጠሩትም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ናቸው። በወንዶች በግል ያገኛቸውን 12 ወርቅ ሜዳሊያዎች እና በቡድን ያገኛቸውን አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች ጨምሮ በ16 ወርቅ ሜዳሊያዎች ቀነኒሳ በቀለ መሪነቱን ሲይዝ፣ በሴቶችም በግሏ አምስት፣ በቡድን ዘጠኝ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያገኘችው ጥሩነሽ ዲባባ በ14 ወርቅ ሜዳሊያዎች በሴቶቹ ምድብ  አንደኛነቱን ይዛለች። በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪካቸው ቢያንስ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሰባት የኢትዮጵያ አትሌቶች ክብረወሰኑ አላቸው። እነሱም ሀይሉ መኮንን፣ ጌጤ ዋሚ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ ገብረእግዚአብሄር ገብረማሪያም፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰለች መልካሙ ናቸው።

Read 1511 times