Monday, 06 March 2017 00:00

“እዚሁ ጋብዙኝ… ባይሆን እኔ የማሩን እከፍላለሁ”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይቺን ስሙኝማ…ሰውየውን ጓደኞቹ “ና ጠጅ እንጋብዝህ…” ይሉታል፡፡ እሱም “እሺ፣ ግብዣ ተገኝቶ ማን እምቢ ይላል…” ይላቸዋል፡፡ ግን የግብዣው ቦታ ሩቅ መሆኑን ሲያውቅ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“እዚሁ ጋብዙኝ…ባይሆን እኔ የማሩን እከፍላለሁ፣” አለና አረፈው፡፡
ምን ያድርግ…ገና ለገና ለሦስት ብርሌ ጠጅ ‘ከወንዝ ወዲያ ማዶ’ የሚያስኬደው ምን አለና ነው፤ ከራሱ ቤት ዝቅ ብሎ እኮ ምን የመሰለ ጠጅ ቤት አለ።
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ዘንድሮ እኮ ስንጋብዝም ብልጥ እየሆንን… አለ አይደል… ‘እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው’ የሚሏትን ስትራቴጂ እየተካንንባት ነዋ!
“ቅዳሜ ምሳ የምጋብዘው እኔ ነኝ፣ እምቢ ብትል የመጨረሻችን ነው የሚሆነው…” ምናምን ብሎ ለአምስት ወዳጆቹ ይነግራል፡፡ ቅዳሜም ይደርስና አምስቱም ይመጣሉ፡፡
እናላችሁ… ለአምስቱም በጋራ ምን ቢታዘዝ ጥሩ ነው… ሁለት በያይነቱ! ከዛ ጋባዥ ሆዬ ምን ይላል…
“ብሉ እንጂ! በቃኝ ብሎ ነገር የለም፣ ይሄ ምግብ ካላለቀ እንጣላለን…” ይልላችሁዋል፡፡ እሱ ተናግሮ እስኪጨርስ ምግቡ አልቋል!
የሆነ ወዳጄ የነገረኝ ነው፡፡ የሆነ ቡና በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጅበት ቤት ይገባሉ፡፡ የቡናው ስነ ስርአት አሁን፣ አሁን በየአቧራው ላይ ‘እንደሚነጠፈው’ አይነት ሳይሆን አሪፍ አይነት ነበር።
እናላችሁ… ወዳጄ አብሮት ላለው ሰው ምን ይለዋል…
“ባህላዊ የቡና ስነ ስርአት ደስ አይልም…” ይለዋል፡፡ ያኛው ምን ቢለው ጥሩ ነው…
“ምኑ ነው ደስ የሚለው… ይሄ እኮ ፕሪሚቲቭ ነው፣” ብሎላችሁ አረፈው፡፡
እናላችሁ… እንደ ከዚህ በፊት እንዳወራነው…አለ አይደል…አገሯ የምትጮህ እየጠፋች ተቸግረናል፡፡
“ስማ ‘ሰው ማመን ቀብሮ ነው’ የሚለውን ፊልም ሳታየው እንዳያመልጥህ…”
‘ያኛው’ ደንገጥ ይልና…አለ አይደል…አንድ፣ ሁለቴ ከፍ ዝቅ አድርጎ ያያችኋል፡፡
“ሶሪ…ምን የሚል ፊልም አልከኝ!”
በነገራችን ላይ እሱዬው ሲናገር… አለ አይደል…ለሰው መልስ የሚሰጥ ሳይሆን የሆነ የሚጠየፈው ነገር ፊት ለፊቱ የተደነቀረበት ነው የሚመስለው፡፡ (ለነገሩ እኛም እኮ ’እንደሚጠየፉን‘ እናውቃለን፡፡)  
እናላችሁ ጠያቂ…
“‘ሰው ማመን ቀብሮ ነው’ የሚለውን ፊልም፣ ከፊልም ቤት ሳይነሳ ቶሎ እየው…”
ታዲያላችሁ… ‘ያኛው’… ‘ሾክድ’ ምናምን ሆኖ  “ኦ ማይ ጋድ!” ይላል፡፡ ልክ እንደ ጆርጅ ክሉኒ ማለት ነው፡ መቼም ክሉኒ ይህን ያህል ፊልም ሲሠራ አንድ፣ ወይም ሁለት ጊዜ “ኦ ማይ ጋድ!” ሳይል አይቀርም፡፡
“አር ዩ ክሬዚ! የአማርኛ ፊልም እይ እያልከኝ ነው!”
“አዎ የአማርኛ ፊልም፡፡ ምነው የአማርኛ ፊልም ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ምናምን ነው አሉህ!…”
“አይ ካንት ቢሊቭ ኢት! እዚህ አገር ምን ፊልም አለና ነው!”
ይሄ እንግዲህ…ፌስቡክ አድራሻ ስላለው፣ ወይንም ዩቲዩብ ላይ ጋንጋም ስታይል ነው ምናምን የሚሉትን ዘፈን ስላየ… አለ አይደል… ‘ዓለምን የጨበጠ’ የሚመስለው ነው፡፡ እዚህ አገር ደግሞ የእውቀት መጀመሪያ… አለ አይደለም… ‘እውቀትን መፍራት’ የሆነ ይመስላል! ቂ…ቂ…ቂ…
“አይተሀቸው የጠላሀቸውን፣ ወይም ፊልም እንድትጠላ ያደረጉህን የአማርኛ ፊልሞች ንገረኝ፡፡”
“እንኳን ገብቼ ላይ ፖስተራቸውን እንኳን እንዳላይ በፊልም ቤት በራፍ ማለፍ ትቻለሁ…”
አንድም ፊልም ሳያይ እንዴት የአማርኛ ፊልሞች ‘ደመኛ ጠላት’ እንደሆነ ብትጠይቁት… አለ አይደል… ትንፋሽ መጨረስ ነው የሚሆነው፡፡
“ስማ… የሆሊዉድን ፊልም አይተህ እንዴት ነው የአማርኛ ፊልም የምታየው! በእነ ብራድ ፒት ላይ መቀለድ እኮ ነው!” ቂ…ቂ…ቂ….
እናላችሁ… ለእንደዚህ አይነት ሰዎች… ‘ነጭ ፊት’ የሠራው ነገር ሁሉ አሪፍ፣ የ‘እኛ ፊት’ የሠራው ሁሉ ቀሺም ነው፡፡ ልክ የሆነ ሰነድ በተጻፈ ቁጥር…
“ከጀርመን ጋር ተመሳሳይ…”
“ከእንግሊዝ ተሞክሮ የወሰድነው…” ምናምን ይባል እንደነበረው ማለት ነው፡፡
ሰውየው ‘ከወንዝ ማዶ አሻግረን እንውሰድህ’ ቢሉት… “እዚሁ ጋብዙኝ…ባይሆን እኔ የማሩን እከፍላለሁ፣” ያለው ቢቸግረው ነው፡፡
እናላችሁ…ይሄ ነገር ብናወራው፣ ምን ብንለው እንኳን ሊለቀን እየባሰብን የመጣ ነገር ነው፡፡ አንዳንዴ ፊት ለፊት ለማለት በሚችል አገላለጽ፣ አንዳንዴ ደግሞ በውስጠ ታዋቂ የእነኛን አሪፍነት፣ የእኛን ቀሺምነት የሚነግሩን ብዙ ነገሮች አሉላችሁ፡፡ አንዳንድ ማስታወቂያዎች ላይ እዚህ አገር ክህሎቱና ችሎታው ሳይጠፋ… “ከእንትን አገር በመጡ…” ምናምን የሚባለው ነገር ሁሉ…አለ አይደል… ‘አሪፍ ነጭ ፊቶች’ እንደማለት ነው፡፡
“ስማ ‘የቆጡን አወርድ ብላ’ የሚለውን በቀደም የወጣ የአማርኛ መጽሐፍ አነበብከው?”
ድንግጥ ይላል…መጽሐፍ ስለማንበቡ የጠየቃችሁት ሳይሆን የሆነ መርዶ የነገራችሁት ነገር ይመስላል፡፡ እናላችሁ…
“ማነው የጻፈው?” ሲል ይጠይቃል፡፡
“እንትና የሚባለው ደራሲ…”
በከፍተኛ ሀዘን ራሱን ይነቀንቃል…አለ አይደል… “እናንተ አስኮናኝ ሀበሾች…” የሚል ይመስል፡፡ (በሆዱ ቃል በቃል እንደዛ ባይል እንኳን ተመሳሳይ ትርጉም ያለው የሆነ ነገር ሳይል አይቀርም፡፡)
ሰውየው ‘ከወንዝ ማዶ አሻግረን እንውሰድህ’ ቢሉት… “እዚሁ ጋብዙኝ…ባይሆን እኔ የማሩን እከፍላለሁ፣” ያለው ቢቸግረው ነው፡፡
ታዲያላችሁ…
“እዚህ አገር ሰው ጠፋና እሱም ደራሲ ተባለ!” ይልላችኋል፡፡
“እሺ፣ ከእሱ መጽሐፎች ያነበብካቸውን ንገረኝ እስቲ…” ስትሉት ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ምን ቁም ነገር ጻፈና ነው የማነበው?”
እሱ ‘ቁም ነገር’ የሚለውና እናንተ ‘ቁም ነገር’ የምትሏቸው ነገሮች እኮ…በፈለገ የሳይንስ ግኝት እንኳን ሊቀራረቡ አይችሉም፡፡
“አንድ ምሳሌ ስጠኛ…”
“ስማ እንኳን መጽሐፉን ላነብለት ገና ርእሱን ሳየው ነው ብሽቅ የምለው…”
ይህን ሰው ከአገር ውስጥ የትኞቹን ደራስያን ሥራዎች አንብበሀል ብትሉት… እዚህ አገር ደራሲ እንደሌለ ይነግራችኋል፡፡
ሰውየው ‘ከወንዝ ማዶ አሻግረን እንውሰድህ’ ቢሉት… “እዚሁ ጋብዙኝ…ባይሆን እኔ የማሩን እከፍላለሁ፣” ያለው ቢቸግረው ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4799 times