Monday, 06 March 2017 00:00

የሳምንቴ ትዝብትና ትንግርት!

Written by  አሰፋ ጫቦ Corpus Chirsti ,Texas USA
Rate this item
(2 votes)

አሜሪካ ዛሬም በሁለንተናው  ግንባር ቀደም ነኝ ስለምትል(“ያማ ያለፈ ወሬ ነው!” የሚሉ ሞልተዋል)  በፕሬዚዳንቱ፤ በዶናል ትራምፕ፤ ልጀምር። “የኔ ጠላት የአሜሪካን ህዝብ ጠላት ነው” (They are not my enemies but the enemy of the American people) ብሎ አረፈው።  
የፈረንሳይ ንጉሥ የነበረውን ልዊ 14ኛውን አስታወሰኝ። ”ፈረንሳይማለትእኔነኝ!” አለ!  (L’Etat Se Moi!) ትራምፕ ጠላቴ የሚለው የህዝብ መገናኛውን እንዳለ ነው። አንድ ሁለት በራሱ ቅጥረኛ የሚታተሙና አንድ የማይሆን ዜና አቀባይ የሆነ ቴሌቪዥን ጣቢያ፤ Fox፤ ከዚህ ውስጥ አስወጥቷል። “አርብ ማታ ስውዲን የደረሰው አደጋ!” አለ። ስውዲኖቹ፤ “እንዴት እኛ ሳናይ፣ ሳንሰማ ትራምፕ ሰማ !”አሉና አሽሟጠጡት። ይህንን ዜና ያገኘው ከFox ነበር።
ጠላቴ የሚለውን መገናኛ ብዙኅን  ነበር:: አሜሪካኖቹ አራተኛው የመንግስት ዘርፍ ይሏቸዋል። (The Fourth Branch of Government!) ሶስቱ ያው የታወቁት ህግ አመንጭ፤ ሕግ ተርጓሚና ህግ አስፈጻሚ የሚባሉት ናቸው፡፡ ትራምፕ እንግዲህ እልቅናው ለዚህ ለፈጻሚው ክፍል  ነው። ፈጽም ተብሎ የተሰጠውን!!
“አንድ እስላም ድርሽ አንዳይልብን!” ብሎ ያወጣውን ህግ፣ አንድ የፌዴራል ዳኛ አቀበው። የትራምፕ ሰዎች ይግባኝ ብለው ወደሚቀጥለው ፍርድ ቤት ሲሔድ፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት፤ “ይግባኝ አላችሁ እንጅ ለምን ይግባኝ እንዳላችሁ ልታስረዱን አልቻላችሁም “ብሎ ያንኑ የታችኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ አጸደቀ። ከዚያ  ትራምፕ ዳኞቹን፤ “ዳኛ ተብዬ!”  ብሎ ዘለፋቸው።
ትራምፕ እንደ ልቡ ተነጋሪ ነው!?  ዘረጦ ነው ማለት ሳይሻል አይቀርም! የአሜሪካንን መንግስት ሥርአት “ሀ ሁ” ሳያውቅ እንዴት እንደተመረጠ? አሁን መጠየቁ “ጅብ ከሔደ ውሻ ጮኸ!” እንደ ማለት ነው። ከሁለት ወር በፊት “በማግስቱ!” ብዬ በጻፍኩት ላይ በመጠኑ አንስቸዋለሁ። የአሜሪካን መንግስት ሥርአት “ሀ ሁ”፤ መንግስት በሶስት ቅርንጫፍ ይከፈላል የሚለውን ያልሰማ መሆኑ ነው። አራተኛው ቅርንጫፍ የሚባለው “የህዝብ መገናኛ” (Mass Media)  ሶስቱንም ሲያበጁ፤ “አበጀህ!” ሲያጠፉ፣ “አጠፋህ!”፤ ሲማግጡ “ማገጥክ!” የሚለው ነው።   ትራምፕ አልሰማ ሆኖ እንጅ፣ ይህ ነገር ወደ 300 አመት ሊሆነው ነው። የኢትዮጵያ ጠረን አለው ልበል?
“ኤረ ወየው ወየው! መጨረሻውን ላየው!”  ይላል፤ የኛ ሰው። የትራምፕ መጨረሻው ምን ይሆን?
    *   *   *
በቬትናም  ጦርነት ዘመን የተሰለፈውን ያክል የአሜሪካ ህዝብ  በየግዛቶቹና በየከተማዎቹ ሁሉ ይሰለፋል። ባለፈው ሳምንት  የፕሬዝዳንቶች ቀን (Presidents Day) ተብሎ በሚከበረው ለት ሕዝብ በገፍ ወጥቶ ተሰለፈ። የያዙት መፈክር ይናገራል! “Dump Trump!” ይላል፤ አብዛኛው። “ትራምፕን ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ወርውረው!” እንደ ማለት ነው። ሌላው “የኔ ፕሬዚዳንት አይደለም!” (Not My President!) የሚል ነው። ይህ እንግዲህ የአሜሪካ ህዝብ ነው። ትራምፕ ደግሞ የኔ ጠላት ሁሉ የአሜሪካ ህዝብ ጠላት ነው ብሏል። ቀረብ ብለው ሲተረጉሙት፤ የአሜሪካ ህዝብ ጠላቴ ነው እንዳለ የሚያስቆጥር አንድምታ ያለው ይመስለኛል። ሕዝቡ  ነዋ “ወግድልን!” የሚለው።
የትራምፕ መጨረሻን በተመለከተ፣ ተንታኞች ሁለት አማራጭ እይታ አሏቸው። አንዱ በቅርቡ ይወገዳል (Impeached) የሚል ነው። ይህ የተጧጧፈው የሕዝብ አመጽ ወደዚያ ያመራል በሚል መነሻ ነው። ሁለተኛው አማራጭ የመንፈቁን ምርጫ (Mid Term Election) መጠበቅ ነው። ለአሜሪካ ምክር ቤት በየሁለት አመቱ ምርጫ ይደረጋል፤ በዚህ ምርጫ ዴሞክራቶቹ የላይኛውንም የታችኛውንም ቤት (Senate and House) መቀመጫ ያሸንፋሉ።  በአሸነፉ ማግስት መጀመሪያ የሚያረቁት ሕግ የትራምፕን ማስወገጃ ሕግ (Impeacheament) ነው ይላሉ። የዚያ ሰው ይበለን!
ትራምፕ በእንግሊዝኛው ሲጻፍ ሁለት አጻጻፍ ለው። አንደኛው በu፣ ሌላው በa። በa የሚጻፈው ትራምፕ- Tramp አልባሌ፣ ማጋጣ እንደማለት ነው። “እርግጠኛ ስሙ ይኸኛው ይሆን?” የሚያሰኝ ነገር ይመጣብኛል። የአንጎል ጅምናስቲክ mental acrobatics መሆኑ ነው።
*   *   *
ከዚህ ከአለም ጉዳይ ሳንወጣ ግሬስ ሙጋቤ፤ የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት የሮበርት ሙጋቤ ባለቤት፣ ስለ ባለቤትዋ  የሰጠችው አስተያየትና በአደባባይ የተናገረችው ነው። “አይበለውና ሙጋቤ ሞቶ ተቀብሮ እንደገና ከመቃብሩ ተነስቶ ቢመጣም የዚምባቡዌ  ህዝብ በደስታ ይመርጠዋል!” አለች። ለሚቀጥለው የፕሬዝዳንትነት ምርጫ ሊገቡ ያሰቡትን “አትቋምጡ! አታገኟትም!” ለማለት ፈልጋ ነው።
ሙጋቤ አሁን 92  አመቱ ነው። ሥልጣን ላይ ደግሞ  37 አመት ሆኖታል። ባለቤቱ እድሜዋ 51 አመት ነው። ብዙ ነገር አሳሰበኝ። አንዱ ኦሪት ውስጥ የአይሁድ ንጉስ የነበረውን ዳዊትን ነው።  ከጠነዛ አልጋ ላይ ከዋለ በኋላ ወጣት ሚስት እየተፈለገ፣ አብሮት እንዲተኛና ሙቀት እንዲሰጠው ያደርግ ነበር ይላል፤ መጽሐፉ። ይህ ሁሉ ታስቦ ቅዱስ ዳዊትም ተብሏል።
ግሬስ ሙጋቤ “አትቋምጡ!” ስትል መልእክቱ፤ ዋንኛው መልእክት ፣ “አልጋ ወራሽ እኔ ነኝ!” ለማለት ነው።  ድፍረቱ፤ የሕዝብ ንቀቱ፤ ፕሬዚዳንት መባሉ፤ሬፑብሊክ መባሉ ሁሉ ይደንቀኛል።
*   *   *
ሶስተኛው፤ በሳምንቱ ውስጥ ከገረመኝ አንዱ የሰሜን ኮሪያው “ንጉስ “ሥራ ነበር። ንጉስ ያልኩት ማእረጉን ሁሌ መሪ (The Leader) ስለሚሉ ነው። በዚህ ላይ ከቀደመ-አያቱ ጀምሮ “ዘውዱ” ከዚያ ቤት አልወጣምና ነው። ማሌዥያ አውሮፕላን ማረፊያ  ትልቅ ወንድሙን ያስገድላል። አስተዳደሩ ኋላ ቀር ነው። አስገዳደሉ ግን ዘመናይ ነበር። ድሮ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ያየሁትን Candid Camera  አስታወሰኝ። ትንሽ ገንዘብ ይከፍሉና  ሰው ላይ ሳያስቡ ውሃ የሚረጩ ፤የሚያስረጩ፣ ያንኑ ቪዲዮ ሰርቶ የሚተዳደሩ አሉ። በዚህ አሠራር አንድ፤ ይህንኑ ስትሰራ የነበረች ሴትን “እዚህ ሰውዬ ላይ ውሀ እርጭበት !”ይሏትና ትራጫለች። የአሁኑ ውሃ ሳይሆን መርዝ ነውና ሰውዬው ይሞታል!
“VX’ በሚባል፣የደም ሥር ሰትሮ የሚገል መርዝ ነው የገደለው” አለ ፤የምርመራው ውጤት። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት VXን ሕዝብን በጅምላ መፍጃ መሳሪያ ነው -  Weapon of mass destruction   ነው፤ ብሎ መድቦታል።
*   *   *
 1984 አስታወሰኝ! Big Brother is Watching You! በየአውሮፕላን ማረፊያው የሚጠብቅ  CCTV  (Closed Circuit Telvision) ካሜራ አለና ሴትየዋም ተካፋዮችም ይያዛሉ። አገር ጥለው የፈረጠጡ አራት ሰሜን ኮርያውያንም እየታደኑ ነው።
ከዚያ በኋላ ያለው ትንሽ ትያትርነት ያለው ይመስላል። የሰሜን ኮሪያ አምባሳደር “አስከሬኑ ይሰጠን! መመርመርም የለበትም!” ይላል። “ የምርመራውንም ውጤት አንቀበልም!” ይላል። ትያትርነቱ እዚያ ላይ ነው። ሟቹ፤  “ምናችሁም አላማረኝም!” ብሎ ተሰዶ ይኖር የነበር ነው። እንደ ጠላት ያዩትም ስለነበር ነው፤ ያስገደሉት ማለት ይቻላል። አሁን ታዲያ ደርሶ “ቅቤ አንጓች!” መሆናቸው አይገርምም? ወይም የበለጠ አያስጠረጥርም? ከዚህ ሌላ የተገደለውን ሰው ሬሳው አይመርመርብን፤ ከተመረመረም ውጤቱን አንቀበልም ማለት የበለጠ አያስጠረጥርም? ወይስ የድንቁራንን ደረጃ መግለጫ ነው?
እንዳልኩት ኋላ ቀር ቢሆኑም አገዳደላቸው ዘመናይ ነው። ከዚያ በተረፈ ያለው እውነተኛነት፤ እርግጠኛ ኋላ ቀርነታቸውን መስካሪ ይመስለኛል። ምስኪን የሰሜን ኮርያ ሕዝብ!! ምኑን ሰጣቸው!! ይሰውረን!!
አሁን በመጨረሻ ገደማ የተደረሰበት መረጃ  እንደሚባለው፤ ይህ የተገደለው የመሪው ትልቅ ወንድም፤ ስደተኛው፤ የሰሜን ኮሪያ ስደተኛ መንግስት መሪ እንዲሆን በሌሎች ስደተኞች በተለይም አውሮጳና አሜሪካ በሚኖሩ ተጠይቆ ነበር። ይህ ይሆናል ቃታውን ለመሳብ፤ ይቅርታ መርዝ ለመርጨት ዋና ምክንያት የሆነው ይላሉ፤ ውስጥ አዋቂ ተንታኞች ነን የሚሉ።
*   *   *
አሁን ደግሞ ወደቤተሰብና ወደማሕበራዊ መገኛዎች በተለይም ወደ Facebook ልመለስ።
Facebook ትምህርት ቤት ሆኖኛል ያልኩኝ መሰለኝ። ጥሩውን፣ መጥፎውንና ጥፉውንም ለማየት መንገድ ይከፍታል።ጥሩ ሲገኝ በርግጥ መነጋገሪያችን ላይ ሐሳብ፤ ቃላት፤ አዝማሚያ  ሊሰጥ የሚችል ይሆናል። ያዳብራልም! ለዛሬ አንድ ካሳ አንበሳው የለጠፈውን እዚህ እንዳለ እለጥፈዋለሁ።
ተክሌ syndrome በሰፊው እያስተዋልኩ ያለሁበት ሁኔታ ነው ያለው፤ ወያኔ ተረስቷል፤ ፌስ-ቡክ በአጼ ሚኒሊክ፣ በቴጌ ጣይቱ እና በአባት አርበኞች ተጥለቅልቋል፤ አባቶቻችን ነጻነቷን የጠበቀች፣ የተፈራችና የተከበረች ሃገር አስረክበውናል፤ ይሄንን ጠብቆ ማቆየት እና እኛም ለልጅ ልጆቻችን የማስተላለፍ ታሪካዊ አደራ አለብን፤ ኑ ሃገራችንን ከወራሪው ወያኔ ነጻ እናውጣት! ዳይ!
*  *   *
የግርጌ ማስታወሻ:- “ተክሌ syndrome” እውነታን አሸሽቶ ታሪክ ውስጥ የሚያሸጉጥ የበሽታ ምልክት ነው፤ ይህ በሽታ ጎልቶ የታየው ተክሌ ይሻው ላይ በመሆኑ “ተክሌ syndrome” ተብሎ ተሰይሟል፡፡
እኔ ግርዳ ላይም አምጥቼ ለጥፌው ነበር። ያለምንም ተጨማሪ አስተያየትና ማዳበሪያ! ይህንን ያነበበ  አንድ ወዳጄ ከካናዳ ደውሎ ሳቅ በሳቅ ሆነ። ”ምነው?” ስለው “ስለዚህ የአማራ መሸጫ ሱቅ ስለአቋቋመው ተክሌ ይሻው እምለው አጥቼ ይህ ሰው አለልኝ” አለ። ሱቅ የሚለው ተክሌ  “ምጽአተ አማራ “ የሚል አንዳች የሚያክል መጽሐፍ ጽፏልና ነው። መጽሐፉን እየዞረ የሚሸጠውን ለማለትነው። መጽሐፉን አንድ ወዳጄ ከዋሽንግቶን ዲሲ ልኮልኝ ትንሽ አገላብጬ አስቀመጥኩ። ፈርቼ ያስቀመጥኩት የመጀመሪያው መጽሐፍ መሆን አለበት።
“የጋራ ቤታችን !ቅርሳችን! ውርሳችን!” የሚል ጽሁፍ ጀምሬ ነበር። አልሔድልኝ፣ አላልቅልኝ አለ። ውስጤ የቀረ ነገር አለ ማለቱ ነው ብዬ ተረጎምኩት። በዚያ ምክንያት ከኢትዮጵያ ታሪክ ውጭ ስለ ሰው ልጅ አብሮ የመኖር ታሪክ ማሰስ ጀመርኩ።
በዚህ አሰሳ Identity Politics የሚል አገኘሁ! “የማንነት ፖለቲክ!” ማለት ነው። በዚህ ምክንያት ያገኘዃቸውን 3 ጽሁፎች፡- 1. Identity Politics are Ripping Us Apart 2. Identity Politics Run A mak 3. Identity Politics/Philosophy Talk Facebook ላይ ለጠፍኩ።
ዛሬ አራተኛው ይሁን አምስተኛ ቀን ሆኖታል። ዞር ብሎ ያየው በጣት የሚቆጠር ነበር። እኔ ደግሞ ወደ 7,000 ወዳጆች (Friends) አሉኝ። “ወዳጆቼን ምን ነካቸው!” ማለቴ አልቀረም። ከወር በፊት ጣቴን በድል ምልክት (V) ቀስሬ የተነሳሁትን ፎቶግራፌን ለጥፌ እንኳን ወደ 700 የሚጠጋ ሰው ጎብኝቶታል።
ለዚህ መነሻ የሆነኝ ዛሬ በተለየ በዲያስፖራ የሚገኙ “የአማራና ኦሮሞ ሊቃውንት ነን” የሚሉ ከኢትዮጵያ ተፋተው ስለ መንደራቸውና “ነን!” ብለው ስለሚያስቡት ጎሳ (ሥራዬ ብዬ  ብሔረሰብ  አላልኩም) ብቻ ያወራሉ። የቀረነውን ኢትዮጵያውያንን “እኛ!” እና “እነሱ!” በሚል ፈርጀውታል። “እኛ!” የሚሉት “ብቸኛ ተጠቂ!” “እነሱ!” የሚሏቸው “አጥቂ!”፣ የኦሮሞ “ምሁራን ነን” የሚሉትማ ኢትዮጵያ የሚል ቃል ራሱ የሚያንገሸግሻቸው ያስመስሉታል።
ከኢትዮጵያ ውስጥ የሚጠሩት ቃል ቢኖር “አማራ!” የሚል ቃል ብቻ ይመስላል።
ዛሬ ደግሞ ይህንን First Peoples የሚል የPBS Utube ይኸው ለጥፊያለሁ። እባካችሁ እናድምጠው! አድምጡት! ይህኛው ክፍል 1 ስለ አፍሪቃ ብቻ የሚያወጋው ነው። ሌላ 4 ስለቀሩት አህጉራት የሚያወጋም አለ። እሱንም እናዳምጥ!
ዋናው ነገር፤ ለኔ ዋናው ነገር፣ ቆም ብለን “ነው እንዴ?!” እንድንል ነው። እይታችን ሰፋ እንዲል ነው! መነጽራችንን እንድንቀይር ነው! በተመዘገበ እውነት ላይ ተመስርተን እንድንወያይ ነው! “የጋራ ቤታችን!” ጉዳይ ስለሆነ፣ የጋራ ቤታችንን በአክብሮት ጭምር እንድናይ ነው። “ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ ባለ እዳ አይቀበለውም!” እንዲሉ በማነንት ፖለቲክ ላይ አንበቡ፤ እናንብብ  ለማለት ነው።
*   *   *
አሁን ስለ ቤተሰባችን ትንሽ:-
የካቲት 4 ቀን 2009፤ ድሬዳዋ ከተማ፤ ከዚህ አለም በሞት የተለየው የትልቁ ልጄ፤ ኤፍሬም አሰፋ፣ ልጅ ሊዲያና አብነት ገብረጊዮርጊስ ጋብቻቸውን ፈጽመዋል። እመቤት አሰፋ፤ እህቴ  ግምብነሽ ጫቦ፤ ባለቤትዋ ባልቻ ሙሊሳ ከልጆቻቸውና ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ከአዲስ አበባ ተጉዘዋል፡፡ ስለ ሰርጉ የሚነግሩኝን ማዳመጥ “አንድ ሺህ አንድ ለሊት”ን (The Arabian Night)  እንደ ማንበብ ነበር። የሊዲያ እናት ፣ተቀባሽ አንጣል፣ በስልክ ውስጥ ክንፍ አውጥታ የምትበር ነበር የመሰለችኝ። እመቤት “አሴ ብችል ድሬዳዋ መኖር እፈልጋለሁ!” አለች። “ምነው?” ስላት “ሰው ሁሉ እንደ ልጅ ግልጽና ፊት ለፊት ተናጋሪ ነው!” አለችኝ። ቅድመ አያትነት በሬን እያንኳኳ ነው ማለት ነው።
ሌላው ከሎንዶን ካትሪን ጫቦ Catherine Chabo  ደወለችልኝ። ቴዲ ባለፈው ወር  Sandhurst Military  Acadamy  ገብቷል ለማለት። ቴዲ ማለት ቴዎድሮስ፣ እሸቱ ጫቦ ማለት ነው። ካቲ የቴድ እናት ነች።
ቴዲ  Sanhurst Military Acadamy የገባው ሁለተኛ ድግሪውን (Masters) ከተቀበለ በኋላ ነበር። “አንዱ አይበቃም ነበር ወይ?” ስለው፤ “ሁለተኛው ሲኖር ጀኔራል ለመሆን ያፋጥናል (accelerate) ብዬ ነው” አለ።
እንግዲህ በጥቂት አመታት ውስጥ ቴዎድሮስ  የሚባል የእንግሊዝ ጀነራል ሊኖር ነው። ለእንግሊዝም፤ በተለየ ለኛ ታሪካዊ የሚሆን መሰለኝ። መቅደላ አፋፉ ላይ አንድ  ሐውልት ተከልን እንደማለት ይመስለኛል። አሁን 150 አመት ሆነው አይደል?
የተሻለ ሳምንት ይጠብቀን!

Read 2314 times