Print this page
Monday, 27 February 2017 08:17

ዘሌማን

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

    “ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከብቁ ባለሙያ ጋር አደራጅተናል
                • አትሌት ኃይሌ፤ከሮቦቱ ጋር የሚሮጥበት የቶታል ማስታወቂያ የእኛ ፈጠራ ነው
                • ሰራተኞች ውጤታማ እንዲሆኑ በሚወዱት ስራ ላይ ይመደባሉ፤ ጥሩ ይከፈላቸዋል
                • የውጭ ኤጀንሲዎች ይሰሩት የነበረውን ፕሮዳክሽን፣ እኛ በብቃት እየሰራነው ነው
                • ለህጻናት መጫወቻዎችና ሞግዚት፣ ድካም ለተሰማቸው ሰራተኞች ጆተኒ

        ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ነው፡፡ምንም እንኳን በማርኬቲንግ ማኔጅመንት ቢመረቅም ነፍሱ ለፈጠራ ጥበብ እንደምታደለ ይናገራል፡፡ በሴልስ ማናጀርነትና በማርኬቲንግ ማናጀርነት ለተወሰነ ጊዜ ተቀጥሮ ከሰራ በኋላ የዛሬ 11 ዓመት ዘሌማንን አቋቁሞ “11ኛው ሰዓት›› የተሰኘውን ፊልም በመስራት የራሱን ኩባንያ መምራት ጀመረ - ዘላለም ወ/ማሪያም፡፡
    በቀጥታም ወደ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ማስታወቂያዎች፣ የቴሊቪዥን ድራማዎችና ዘጋቢ
ፊልሞች ሥራ መግባቱን ይገልጻል፡፡ የዛሬው እንግዳችን የዘሌማን አድቨርታይዚንግ፣ ፕሮዳክሽንና ኮሚዩኒኬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚና ቺፍ ክርኤቲቭ ዳይሬክተር አቶ ዘላለም ወ/ ማሪያም፤ በስፋት ስለተሰማራበት የፕሮዳክሽን፣አድቨርታይዚንግና ኮሚዩኒኬሽን ስራው፣ድርጅቱ ከትልልቅ ብራንድ ኩባንያዎች ጋር ስላለው የሥራ ግንኙነት፣ ስለ ደርጅቱ አወቃቀርና የቴክኖሎጂ አቅም --- ወዘተ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ስናፕ ፕላዛ ህንፃ ላይ በሚገኘው ቢሮው ተገኝታ አነጋግራዋለች፡፡ በፎቁ ሁለት ወለል ላይ የተደራጀውን ዘመናዊ የፕሮዳክሽን ስቱዲዮና
ማራኪ ቢሮዎች ጎብኝታለች፡፡ ቃለምልልሱ እነሆ።

      መጀመሪያ በፊቸር ፊልሞች ላይ ነበር አተኩረህ የምትሰራው፡፡ ከ‹‹11ኛው ሰዓት›› በኋላ የፊልም ስራ አቆምክ ልበል?
ከ‹‹11ኛው ሰዓት›› በኋላ ሁለት ፊልሞችን ሰርቻለሁ ‹‹ለዛሬ›› እና ‹‹አዳምጥ›› የተሰኙ አጫጭር ፊልሞች ናቸው፡፡ ‹‹ለዛሬ›› የተሰኘው ፊልም እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም የተሰራ ነው፡፡ በአገር ውስጥ በበርካታ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ታይቶ፣‹‹ቤስት ፊልም›› ተብሏል፡፡ በዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ተወዳድሮም፣ከዘጠኝ በላይ ዓለም አቀፍ ሽልማቶች አግኝቷል፡፡ ‹‹አዳምጥ›› በ2013 ነው የተሰራው፡፡ ፕሮዱዩስ ያደረገልኝ ‹‹ፎከስ ፊቸርስ›› የተሰኘ ትልቅ የሆሊውድ ስቱዲዮ ነው፡፡ ስቱዲዮው እንደ እነ ‹‹ዘ ፒያኒስት››፣ ብሮክን ፍላወርስ›› እና የመሳሰሉ ትልልቅ ፊልሞችን የሰራ ነው፡፡ ከአፍሪካ አምስት ፊልም ሰሪዎችን መርጦ ነበር፤አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ይህ ፊልም እስካሁን እየታየ ሲሆን ወደ ሰባት ያህል ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ አሁንም ፊልሞችን እንሰራለን፡፡
በአሁኑ ወቅት በዋናነት የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ማስታወቂያዎችን እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የኮሚዩኒኬሽንና የማስታወቂያ ስራዎችን እየሰራችሁ ነው፡፡ እስቲ አንድ ማስታወቂያ ስትሰሩ ያለውን ቅድመ ተከተል አስረዳኝ?
ስራው እንግዲህ ወደ ዘሌማን ሲመጣ ---- ምርት ሊሆን ይችላል ወይም ካምፔይን (ዘመቻ) ሊሆን ይችላል፡፡ ዘመቻው የባህሪ ለውጥ ማምጣት ሊሆን ይችላል፡፡ የባህሪ ለውጡ ደግሞ በአመጋገብ፣ በአኗኗር ዘይቤ አሊያም በልጆች አስተዳደግና እንክብካቤ ዙሪያ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መሸጥ የሚፈልጉት ምርት ይኖራል፤ያንን  እንድንሰራ ሲያመጡልን፣ መጀመሪያ ጥናትና ምርምር (Research) ይደረግበታል፤ ስለዚያ ነገር ለማወቅ ጥናቱ ይካሄዳል። ይህን የሚሰሩ በዕውቀት የላቁ ተመራማሪዎችን የያዘ የጥናትና ምርምር ዲፓርትመንት አለ፡፡ ከዚህ ዲፓርትመንት የጥናትና ምርምር ግኝቶች ይመጣሉ፡፡ እነዚህን ግኝቶች ይዘን ወደ ስትራቴጂ ዲፓርትመንቱ እንሄዳለን፡፡
የስትራቴጂ ዲፓርትመንቱ ስራ ምንድነው ነው?
የስትራቴጂ ዲፓርትመንት ለምርቱ ወይም ለሚሰራው ዘመቻ ስትራቴጂ ያወጣል፡፡ የጥናት ግኝቶቹን መሰረት አድርጎ ነው ስትራቴጂ የሚያወጣው፡፡ ስትራቴጂው ከወጣለት በኋላ ወደ ክርኤቲቭ ዲፓርትመንት ይሄዳል፡፡ ይህ ዲፓርትመንት በምን አይነት ፈጠራ ይሰራ፣ እንዴት ስለ ምርቱ ማህበረሰቡን ማሳመን እንችላለን፣ የሚለውን ነገር ያወጣል ያወርዳል፡፡ ከዚያ ፈጠራው በጥሩ ሁኔታ ከተፈጠረ በኋላ፣ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ ከሆነ ማስታወቂያው ይሰራል። ምርቱን ቀጥታ ወስዶ ስለ ምርቱ ለህብረተሰቡ ማስተማር፣ ማስቀመስ ወይም ምርቱን ዳስሰው እንዲያዩት የማድረግ (ኤክስፕሪዬንሽያል) ስራም ይወጣል። የህዝብ ግንኙነት ስራም ከሆነ ለምሳሌ የሚዲያ ስትራቴጂ ከሆነ፣ ወደ ሚዲያ ይሄዳል ማለት ነው። በጉብኝትሽ እንዳየሽው ሁሉም የተሟላ ነው፤ ፕሮዳክሽኑ የቴሌቪዥንም የሬዲዮም ማስታወቂያ ለመስራት በበቂ ሁኔታ የተሟላ ነው፡፡
ምን ያህል ዲፓርትመንቶች አሏችሁ? ከእነ ሥራቸው ልትነግረኝ ትችላለህ?
ብዙ ናቸው፡፡ ከደንበኞች አገልግሎት (Client service department) ጀምሮ --- በርካታ ዲፓርትመንቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ በፕሮዳክሽን እንኳን ፕሮዳክሽን ዲፓርትመንት፣ ፖስት ፕሮዳክሽን ዲፓርትመንት---- የሚባሉ አሉ፡፡ በአድቨርታይዝመንት ደግሞ ሁለት ነገሮች አሉ፡- ‹‹Above the line›› እና ‹‹Below the line››  የሚባሉ ናቸው፡፡ ‹‹Above the line›› ማለት  አንድን ምርት አምርተሽ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ፣ የሬዲዮ ማስታወቂያና ቢል ቦርድ ላይ ይተዋወቃል። ለምሳሌ እናቶች ላይ የሚሰራ ስራ ከሆነና ከላይ በጠቀስኩልሽ መንገዶች  ካስተዋወቅሽ፣ አዋቂም ልጆችም፣ ማንኛውም አካል ያንን ነገር ያየዋል፤ ያውቀዋል፡፡
መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች  (NGos) ጋር እናቶች እስከ ስድስት ወር ያለ ምንም ተጨማሪ ምግብ ጡት እንዲያጠቡ፣ ህፃናቱ ተጨማሪ ምግብ ሲፈልጉ እንዴት ማዘጋጀት እንዳለባቸው ለማስተማር እናቶቹ ያሉበት ድረስ እንሄዳለን፡፡ ይሄ ‹‹Below the line›› የምንለው አሰራር ነው ማለት ነው፡፡ ሌላው ዲጂታል ማርኬቲንግ የምንለው አለ፡፡ ትልልቅ ብራንድ ኩባንያዎችን፣ዘመቻዎችን በማህበራዊ ትስስር ሚዲያዎች የማስተዋወቅ ስራ እንሰራለን። በእነዚህ ሶሻል ሚዲያዎች የማስተዋወቅ ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ እያደገ የመጣ ዘርፍ ነው፡፡  እሱም ራሱን የቻለ ዲፓርትመንት አለው፡፡ ሌላው ህዝብ ግንኙነት - public Relation ዲፓርትመንት ነው፡፡ በዚህ ዲፓርትመንት ለትልልቅ ኩባንያዎች፣ ለዓለም አቀፍና አገር በቀል ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ስራ እንሰራለን፡፡ የሚዲያ ስራዎችን የምንሰራበት ሚዲያ ዲፓርትመንት አለን፤ ይህ ዲፓርትመንት ደንበኞቻችን በሚዲያ ማስተላለፍ የሚፈልጓቸው ጉዳዮች ሲኖሩ በየትኛው ሚዲያ፣ መቼ ቢያስተላልፉ ውጤታማ እንደሚሆኑ እናማክራለን፡፡ የሚዲያ ሞኒተሪንግ እንሰራለን፡፡ የሚዲያ ዲፓርትመንቱም የተዋጣለትና በብቁ የሰው ሀይል የተደራጀ ነው፡፡
ከሰራችኋቸው ሥራዎች ጥቂቶቹን ልትጠቅስልኝ ትችላለህ ?
ለምሳሌ ‹‹አላይቭ ኤንድ ትራይቭ›› የሚል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አለ፡፡ ይህ ድርጅት የሬዲዮ ፕሮግራም አለው፡፡ አውትሪች ወይም ጉዳዩ በሚፈለግበት ቦታ እየተገኘ ጥናት ወይም ትምህርት የሚሰጥበት አሰራር ይተገብራል፡፡ ከወርልድ ባንክ ጋር በአይኤፍ ሲ ፕሮጀክት ላይቲንግ ኢትዮጲያ የተባለ የፀሐይ ብርሀን አጠቃቀም (solar light) ላይ የሚሰራ ‹‹lighting Ethiopia›› የተባለ ዘመቻ አለው፡ ይህ ዘመቻ ሰዎች ጥራት ያለው solar light መሳሪያ በመግዛት፣ ኩራዝ መጠቀም እንዲያቆሙና በፀሀይ ብርሀን እንዲጠቀሙ ለማድረግ የተጀመረ እንቅስቃሴ ሲሆን፣‹‹አላይቭ ኤንድ ትራይቭ›› በየገጠሩ እያስተማረና እየሰራ ይገኛል፡፡ ኩራዝ ከሰዎች ጤናም ሆነ ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚሰራ ስራ ነው፡፡ እኛም ይህን ስራ ከድርጅቱ ጋር አብረን እየሰራን እንገኛለን፡፡
ሌሎችም በርካታ ስራዎች ሰርተናል፡፡ ለምሳሌ ከዩኒሴፍ ጋር ብዙ ሰርተናል፡፡ ከብራንድ ኩባንያዎች - ከኮካ ኮላ ጋር እንሰራለን፡፡ ከአንከር ወተት ጋርም እየሰራን ነው፡፡ የአንከርን በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በቢል ቦርድ---- ወተቱን በማስቀመስ፣ በማስተማር ጭምር የምንሰራው እኛ ነን፡፡ በአንድ አመት ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነትና እውቅናን እንዲያገኙ አግዘናቸዋል፡፡ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ከሮቦቱ ጋር የሚሮጥበት የቶታል ማስታወቂያ የእኛ ፈጠራ ነው፡፡ እጅግ በርካታ አለም አቀፍ ደንበኞችን አሉን፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ ስኬታማ የሆነው፤ በቅጡ በተደራጁ  ዲፓርትመንቶች፣በየዲፓርትመንቱ ባሉ ብቁ ሰራተኞች፣ ሰራተኛው ባለው የእርስ በእርስ የጠበቀ የስራ ግንኙነት፣ ባለን ብቁ አመራርና በምንጠቀማቸው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ድምር ውጤት ነው፡፡
ለትላልቅ አለም አቀፍ ኩባንያዎች የኮሚዩኒኬሽን፣ የማስታወቂያና የፕሮዳክሽን----ስራዎችን እንደምትሰሩ ነግረኸኛል፡፡ የእነዚህን ትላልቅ ኩባንያዎች ሥራዎች በጥራት ለመሥራትና ፍላጎታቸውን ለማርካት የምትጠቀሟቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ምን ይመስላሉ?
ቴክኖሎጂውን በተመለከተ በየዲፓርትመንቱ አሉ የተባሉ ቴክኖሎጂዎችን እንጠቀማለን፡፡ ዋናው ነገር ግን ቴክኖሎጂው አይደለም፤ ቴክኖሎጂውን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ጠንቅቀው የሚያውቁ ብቁ ባለሙያዎች ያስፈልጉሻል፡፡ ለምሳሌ አንድ ዘመኑ ያፈራው ምርጥ መኪና ተገዝቶ ለአንድ ሰው ቢሰጥ፣ አነዳዱንና መኪናው ምን እንደሚፈልግ ያ ሰው ካላወቀ፣ መኪናው ብቻውን ምን ይፈጥራል? ምንም! እኛ አሉ የተባሉ ቴክኖሎጂዎችን፣ አሉ በተባሉ ብቁ ባለሙያዎችን እንጠቀማለን፡፡ ለምሳሌ እኔና አንቺ አንድ አይነት ስማርት ስልኮች ቢኖሩን ምናልባት እኔ ስልኩን ስልክ ለመደዋወልና መልዕክት ለመለዋወጥ ብቻ ልጠቀምበት እችላለሁ። አንቺ ደግሞ አለምን የምትፈትሺበት፣ ብዙ ስራሽን የምትሰሪበት ቢሮሽ ልታደርጊው ትችያለሽ፡፡ አየሽ ሌላው ቴክኖሎጂም እንደዚህ ነው፡፡ በአጠቃላይ ብቁ ቴክኖሎጂ ከብቁ ባለሙያ ጋር በማደራጀታችን በፊት ትልልቅ ብራንድ ኩባንያዎች የአድቨርታይዚንግ፣የኮሚዩኒኬሽንና የፕሮዳክሽን ስራ ለማሰራት ኤጀንሲዎችን ከውጭ አገር ያስመጡ ነበር፡፡ እኛ ራሳችንን በማደራጀታችን ከውጭ የሚመጡት ቀርተው፣ እኛ በብቃት እየሰራነው እንገኛለን።
በእርግጥ በዚህ የብቃትና ጥንካሬ ደረጃ ላይ ለመገኘት ብዙ ጥረት፣ ብዙ ልፋት፣ ብዙ ውጣ ወረድ ታልፏል፡፡ ይህንንም አልፈን እዚህ የደረስነው ‹‹If your dreams don’t scare you they are not BIG enough›› በሚል መርህ ነው፡፡ በቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የቢሮ መሳሪያዎች አደረጃጀትም ዓለም አቀፍ ኤጀንሲ ሊያሰኝ የሚችል አቅም ገንብተናል፡፡ ሁሉንም ጎብኝተሻል፡- የቢሮ ወንበርና ጠረጴዛዎች፣ የቢሮ ስፋትና አጋጊያጥ፣ ሁሉም ሴትአፕ የተሰራው ‹‹ቦልድ ዲዛይን›› በተባለ ፕሮፌሽናል ኢንቴሪር ዲኮሬሽን ድርጅት ነው፡፡ ይህን ድርጅት የሚመሩት ሁለት ሴቶች ናቸው፡፡ እጅግ በጣም ጎበዞችና የማደንቃቸው ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ለሰራተኛውም ሆነ ለሚመጡ ደንበኞች ምቹ የስራ ከባቢን የሚፈጥር ዲዛይን ነው የሰሩት፡፡ ከጉግልና ሊንክዶን ከተባለ ድርጅት ለስራ ጉብኝት የመጡ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ዜጎች፣ ቢሯችን የጉግል ዓይነት እንደሆነና ኢትዮጵያ ውስጥ ያልጠበቁት ትልቅ ተቋም መሆኑን መስክረዋል፡፡ በሴትአፕም ሆነ በቴክኖሎጂው፣ በብቁ ባለሙያም ሆነ በማንኛውም ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ “ቁጥር 1” ነን ማለት ይቻላል፡፡ ይሄ ጉራ አይደለም፤ የሚታይ የሚዳሰስ እውነት ነው፡፡
ዘሌማን ሰራተኞቹ ላይ ብዙ ኢንቨስት ያደርጋል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ በምን መልኩ ነው ኢንቨስት የሚያደርገው?
በመጀመሪያ ሰራተኞቻችንን የምንመርጥበት ሂደት በጣም ከባድ ነው፡፡ በየዘርፉ በጣም የሰለጠኑ፣ልምድ ያላቸውና ተወዳዳሪ የሆኑትን ነው የምንመርጠው። ከ105 በላይ ናቸው፤ የአቅም ግንባታ ስልጠና፣ አነቃቂ ንግግሮችንና ልምዶችን የሚያካፍሏቸው እውቅ ምሁራን፣ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ድርጅታችን ድረስ ይመጣሉ፤ ስልጠናውም በየወሩ ይሰጣል፡፡ ጥሩ የስራ ግንኙነትና ባህል አለን፡፡ አብረን የምናሳልፍባቸው ጥሩ ጊዜዎች አሉን፡፡ ሌላው ሰራተኛው ውጤታማ እንዲሆን የሚወደው ስራ ላይ ይመደባል፤ምቹ የስራ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው፣ በሚያምርና በደንብ በተደራጀ ቢሮ ነው የሚሰሩት፤ ጥሩ ደሞዝ ተከፋይም ናቸው፡፡
በጉብኝቴ ወቅት ጆተኒ ያየሁ መሰለኝ፡፡ መቼም የሥራው አካል አይደለም?
አንድ ሰው እየሰራ ሊደክመው ወይ ሊደብረው ይችላል፤ ያን ጊዜ ብድግ ብሎ ከፈለገ ካፍቴሪያው ውስጥ ሻይ ቡና ይላል፤ ያለበለዚያም ጆተኒ ሊጫወት ይችላል። ሰራተኞቹ ሁሌ ስራ ስለሚበዛ በስራ ይጠመዳሉ፤ ነገር ግን ደክሟቸው አረፍ ማለት ከፈለጉ በሚመቻቸው መንገድ ራሳቸውን ዘና እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ክርኤቲቭ ዲፓርትመንቱ፡፡ ሌላው ‹‹ዘሌማን ጎት ታለንት›› የሚባል አለ፡፡ እዚህ የተለያዩ ክርኤቲቭ ልጆች አሉ፤ ታለንት ሾው ያሳያሉ፡፡ ይህን የምናደርግበት ፕሮግራም አለን፡፡ የውይይት ፕሮግራምም እንዲሁ እናካሂዳለን፡፡ አነቃቂ ቪዲዮዎችን የምናይበት ሰአት አለ፡፡ በዚህ መንገድ  ከሌላው ዓለም ልምድ እንቀስማለን፡፡
ዘሌማን ከብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ስላለው፣ ሰራተኞቻችን የተለያዩ አገራት ሄደው እንዲጎበኙ፣ እንዲማሩና እንዲሰለጥኑ እናደርጋለን። የተለያዩ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ወርክሾፖች ላይ ተልከው የሰለጠኑ፣ እየሰለጠኑ የሚገኙም አሉ፤ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡
እናቶች፤ ህፃናት ልጆቻቸውን የሚያቆዩበት ክፍልና ሞግዚትም አዘጋጀታችኋል----የውጭ ኩባንያዎች ተሞክሮ ይመስላል፡፡ እስቲ ዓላማውን አብራራልኝ-----
እናቶች ሞግዚት ሲሄድባቸው፣ ቤተሰቦቻቸው ሳይመቻቸው ሲቀር፣ ልጆቻቸውን ለሰራተኛ ጥለው መምጣት በጣም ይከብዳቸዋል፤ በዚህ ምክንያት ከስራቸው ሲስተጓጎሉ ማየት የተለመደ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እናቶች፤ ልጆች ባያመጡም የጡት ወተታቸውን አልበው የሚሰጡ አሉ፤ ይህን ለማድረግ የሆነ ጥግ ላይ፣ወይም መፀዳጃ ቤት ሲገቡና ሲቸገሩ ይታያሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች በእኛ ድርጅት ውስጥ የሉም፤ ምቹ የራሳቸው ክፍል አለ፡፡ መጫወቻ፣ የልጆች መኝታ ከብቁ ሞግዚት ጋር ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ እናቶች ልጆቻቸውን እየገቡ ያያሉ፣ ያጠባሉ፤ ሁሉም ምቹ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በጥሩ መንፈስ ስራቸውን ይሰራሉ ማለት ነው፡፡ ከ100 በላይ ሠራተኞች አሉን፤ ከነዚህ መካከል ብዙ ሴቶች ስላሉን ነው የህፃናት መንከባከቢያ ክፍሉን ያዘጋጀነው፡፡ ሌላው እናቶች እስከ ስድስት ወር ያለ ምንም ተጨማሪ ምግብ ልጆቻቸውን ጡት ብቻ እንዲያጠቡ እናስተምራለን፡፡ ድርጅታችን ይህን በተግባር ማሳየት ስላለበት ነው፡፡
በአገራችን የኮሙኒኬሽን፣ አድቨርታይዚንግና ፕሮዳክሽን ሥራ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል ትላለህ ?
እኛ እዚህ ደርሰናል፤አለም አቀፍ ብራንድ ኩባንያዎች ኤጀንቶችን ከውጭ ማስመጣታቸውን አስቀርተናል፡፡ ጨረታ ሲወጣ እየተወዳደርን እያሸነፍን እየሰራን ነው። ሌላውስ ካልሽኝ--- ሁሉም የአቅሙን እየሰራ ነው፡፡ ለምሳሌ በዩኒቨርስቲ ደረጃ ጆርናሊዝምና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት በስፋት ይሰጣል፤ አድቨርታይዚንግ ላይ የሚሰጥ ትምህርት ግን የለም፡፡ የፊልም ትምህርት ቤትም እንዲሁ ከአንዳንድ የስልጠና ማዕከላት በስተቀር የለም። ይህ አማራጭና እድል በሌለበት ሁሉም በግል ጥረት የኮሚዩኒኬሽንና የአድቨርታዚንግ ስራ እየሰራ ነው፡፡ ይህንን በእውነቱ ማድነቅ ያስፈልጋል፡፡ ነገ ደግሞ በጥረታቸው ትልቅ ይሆናሉ፤ እኛም በግል ጥረታችን ይህንን ገፅታ መገንባት እንደቻልነው ማለት ነው፡፡ እኔ ራሴ የዚህ ነገር አካል ነኝ፤ እዚህ ተወልጂ እዚህ አድጌ፣ እዚህ ተምሬ እዚህ ደርሻለሁ፤ ከሰራተኞቼ ጋር ለእዚህ በቅቻለሁ፡፡
በዚህ ሂደት እኛ ቀድመን ባቡሩ ላይ ተሳፍረን ከሆነ፣ ሌላው ደግሞ ሊሳፈር ቀርቦ ይሆናል፤ ነገር ግን ሁሉም ህልሙ ላይ ይደርሳል ባይ ነኝ፡፡ አደገኛ የሚሆነው ባለበት የሚረግጥ፣ ህልሙ ላይ ለመድረስ የማይጥር ከሆነ ብቻ ነው፡፡ አሁን ግን በተለያየ ዘርፍ ብዙ ለውጦች እየታዩ ነው። በሌላ በኩል በቀላሉ የሚኖሩ፣ ብዙ ህልም የሌላቸው አሉ፡፡ እነዚህን ሰዎች ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ሌት ተቀን የሚሰሩ የሚጥሩ፣ የሚያነቡ የሚጠይቁ አሉ፡፡ እነሱ በግል ጥረት እያደጉ ነው፤ ለዚህ ማሳያው ዘሌማን ነው፡፡
ዘሌማን እስካሁን በሥራው ላይ ኢንቨስት ያደረገው በገንዘብ ምን ያህል ይገመታል?
ዘሌማን ኢንቨስት ያደረገው በገንዘብ ቢተመን፣ ለብዙ አመት ያወጣውን ላይመልስ ይችላል፤ ግን ለዘርፉ ባለን ፍቅር፣ በምንሰራው ስራ፣ በውጤታችን ነው የምንለካው። ለውጥ ማምጣት ለእኛ ክፍያችን ነው። ይህንን ያህል መሰረት ልማት፣ ይህን ያህል ተፅዕኖ መፍጠር---- 105 ያህል  ጥልቅ የሙያ ፍቅር ያላቸው ብቁ ፕሮፌሽናል ሰራተኞች ይዞ መጓዝ-----በገንዘብ ሊተመን አይችልም፡፡ ኢንቨስትመንቱ ህዝቡ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያክላል፤ ትልልቅ ኩባንያዎች ደንበኞቻችን ያመጡትን ስኬት ያክላል፤ በገንዘብ መለካት አንችልም፡፡
ባለፈው ሳምንት የአርቲስት ሙላቱ አስታጥቄን ኮንሰርት ያዘጋጀው ዘሌማን ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ሥራ የመቀጠል ዕቅድ አላችሁ?
እንግዲህ ሙላቱ ለ52 ዓመት ኢትዮ ጃዝ በመፍጠር ለዓለም ያስተዋወቀ ሳይንቲስት ነው፡፡ እሱ ሳይንቲስቶቹ ብሄር ብሄረሰቦች ናቸው ይላል፡፡ የሆነ ሆኖ የእሱን ስራዎች ስሰማ እነቃቃለሁ፡፡ ሙላቱ ብዙ ለፍቷል፤ ደክሟል፤ እኛ ያደረግነው ለእሱ እውቅና መስጠትና ከአድናቂዎቹ ጋር ማገናኘት ነው፡፡
ይሄን ለማሳካት ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፈናል፤ ብዙ ወጪ አለው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጆኒ ዎከርን፣ አሜሪካ ኤምባሲን፣አውሮፓ ህብረትን፣ ዮድ አቢሲኒያን ሆቴል፣ ኤርሚያስ አድቨርታይዚንግ ክላስ ፕላስ ኤቨንትና ሌሎችንም ተባባሪ አካላት አመሰግናለሁ፡፡ ስራው ያማረና የተሳካ እንዲሆን የእነሱ ትብብር ትልቅ ነበር፡፡ በዚህ ትቀጥላላችሁ ወይ ለተባለው፣ ከባድ ነው፡፡ በእርግጥ በየዘርፉ ሊከበሩ፣ ሊሸለሙ የሚገባቸው ብዙ ትልልቅ ሰዎች አሉ፡፡ ባለው ውጣ ውረድ በዓመት በስድስት ወር እንሰራለን ባንልም፣ ሁኔታዎች ሲመቹ፣ እግዜር እንደፈቀደ ወደፊት እናስብበታለን፡፡
እስቲ በጥቂቱ ስለ ግል ህይወትህ ንገረኝ ----?
ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነኝ፡፡ ከልጆቼና ከሚስቴ ጋር የሰመረ የትዳር ህይወት አለኝ፡፡ ባለቤቴ በጣም የስራ ሰው ናት፡፡ ድርጅቱ ለውጤት እንዲበቃ ያደረገች፣ የተማረችና የበቃች ናት፡፡ በድርጅቱ ውስጥም ቺፍ ኦፕሬሽን ማናጀር ሆና፣ በበቂ ሁኔታ እየመራች  ትገኛለች፡፡

Read 4799 times