Monday, 27 February 2017 08:02

25% እናቶች ... በደም መርጋት... በድንገት ይሞታሉ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

• እንደኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች በሆስፒታል ውስጥ ከሚሞቱ እናቶች በሚወሰደው መረጃ መሰረት እስከ 20% የሚሆነው የእናቶች ሞት በደም መርጋት በሽታ ነው።
 ዶ/ር ሙህዲን አብዶ
የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት
ደም በሰውነት ውስጥ ትልቅ ተግባር ያለው ተፈጥሮ ነው። ደም በሰውነት ውስጥ በሕይወት ዘመን ሁሉ ካለምንም ችግር መመላለስ መቻል አለበት። ነገር ግን ጉዳት በሚደርስበት ገዜ ከሰውነት ውጭ እንይፈስ እና ተጎጂው ከጉዳት እንዳይወድቅ እራሱን ማዳን መቻል አለበት። ይህም የደም ስሩ በተቆረጠበት በኩል ካለአግባብ እንዳይፈስ በአካባቢው በመርጋት እና የተከፈተውን የደም ስር በመዝጋት ነው። ስለዚህም የደም መርጋት ጤናማ እና ሕይወት አድን ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው። ነገር ግን ባልተፈለገ ሁኔታ ማለትም ከልብ ሕመም፣ ስትሮክ እና ከመድሀኒት ጋር በተያያዘ በሚደርስ ችግር የደም መርጋት ከተከሰተ ጠቃሚነቱ ቀርቶ ጎጂ ይሆናል።
በሰውነት ውስጥ የደም መርጋት ተከሰተ ሊባል የሚችለው የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲስተዋሉ ነው።
• የደም ዝውውሩ በትክክለኛው መንገድ መሆን ሲገባው ነገር ግን ሲገታ፣
• በደም ውስጥ የደም መርጋትን አጋጣሚ የሚጨምሩ ነገሮች በሚጨምሩበት ጊዜ፣
• በደም ስር ውስጥ ያሉ ተፈጥሮአዊ አካላት በሚጎዱበት ወይንም አደጋ በሚደርስባቸው ጊዜ፣ ነው።
ከዚህ ውጭ ግን በተለያዩ ባእድ አካላት ሰውነት ሲመታ ወይንም ሲቆረጥ የሚኖረውን ደም መፍሰስ ለማስቆም የሚረዳው ደም መርጋት እንደችግር ሳይሆን እንደነፍስ አድን ይቆጠራል። ምክንያቱም በዚያ በተቆረጠው የደም ስር ጫፍ ላይ ተከስቶ የደም ፍሰቱን ስለሚገታ ነው። ነገር ግን ደም የሚያቀጥን መድሀኒት የሚወስዱ ሰዎች ከሌሎች በተለየ በአደጋ ጊዜ የደም ስራቸው በራሱ የሚያደርገውን የደም መርጋት ሂደት ሊያስተጉዋጉልበት ይችላል። የደም መርጋትን ሊያመጡ የሚችሉ ከሚባሉት ውስጥ የደም ግፊት፣ ኮሎስትሮል፣የልብ ሕመም፣የስኩዋር ሕመም፣ማጨስ እና በቤተሰብ ውስጥ የደም መርጋት ሕመም የነበረ ከሆነ ተጠቃሾች ናቸው። ከልብ ሕመም፣ስትሮክ እና ከደም ስሮች መዘጋጋት ጋር የሚያያዘውን የደም መርጋትን ለመከላከል የደም ግፊትን የስኩዋር ሕመምን እና ኮለስትሮልን መቆጣጠር ተገቢ ነው።
አንዲት ሴት በእርግዝና ላይ እና በወሊድ ወቅት ሊያጋጥሙዋት ከሚችሉ የጤና እክሎች አንዱ የደም መርጋት ነው። በዚህ ወቅት የደም መርጋት በሽታ እንዲከሰት የሚያደርጉ የተለያዩ አጋጣሚዎች በመኖራቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። በእርግዝና ጊዜ የሚከሰተው የደም መርጋት ጽንሱን አደጋ ላይ የመጣል አዝማሚያው ከፍተኛ ነው። እንደመረጃዎቹ ጥቆማ ለዚህ ደረጃ የሚያደርስበት ምክንያትም የደም መርጋቱ በእንግዴ ልጅ ውስጥ ስለሚፈጠር ወደልጁ የሚሄደውን የደም ፍሰት ሊዘጋ ስለሚችል ነው።
• በእርግዝና ጊዜ ሰውነት በራሱ ደም እንዳይፈስ ለመከላከል ሲል የሚያዘጋጃቸው የደም መርጋት ተፈጥሮአዊ ሂደቶች ይጨምራሉ።
• እርግዝናው ጊዜውን እየጨመረ በሚመጣበት ጊዜ ጽንሱ በማደጉ ምክንያት በሚፈጠረው ጭነት ምክንያት ደም መልስ የሚባለው አካል በትክክል ስራውን እንዳይሰራ የሚሆንበት አጋጣሚ ይኖራል።
• በእርግዝና ወቅት በምጥ ሰአት ወይንም በውርጃ ጊዜ በተለይም ደግሞ ከወሊድ በሁዋላ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የደም መርጋት ሂደቱን የሚያባብሱ ነገሮች አሉ። በተለይም...
o ከምጥ ጋር በተያያዘ የደም ስሮች መጎዳት፣
o በኦፕራሲዮን መውለድ፣
o የሰውነት ውፍረት፣
o ተገቢውን አካላዊ እንቅስቃሴ ካለማድረግ ...ወዘተ ጋር በተያያዘ ወላድዋ የደም መርጋት ሕመም ሊገጥማት ይችላል።
• የደም መርጋት ምልክት ደም መርጋቱ እንደተከሰተበት የስውነት ክፍል ወይንም አርተሪ እና ቬይን በተባሉ የደም ክፍሎች ይለያያል። ስለዚህም የልብ ሕመም ወይንም መጠነኛ ስትሮክ ሊያጋጥም ይችላል። የደም መርጋትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ምክንያቶች ተብለው ከሚጠቀ ሱት መካከል ውፍረት፣እንቅስቃሴ አለማድረግ፣መተኛት የመሳሰሉት ይገኙበታል። አንዲት ሴት በተለይም በኢትዮጵያ ስትወልድ ከሚደረግላት እንክብካቤ መካከል ምግብ ከለመደችው መጠንና አይነት በላይ መስጠት እና ለእረፍት መተኛት እንዳለባት ታዋቂ ነው።ይህ ግን በባለሙያዎች ዘንድ ተቀባይነት የለውም።
• .....እንደጥሩ ልማዳዊ ድርጊት ተደርገው ከሚወሰዱ መካከል ሴቶች ሲወልዱ የሚደረግላቸው እንክብካቤ ይገኝበታል። ነገር ግን የእንክብንቤው መንገዱ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። የወለደች ሴት መታረስ አለባት ከሚል አስተሳሰብ ብዙ እንድትተኛ ቅባት ያላቸውን ምግቦች ከመጠን በላይ እንድትመገብ ይደረጋል። በተለይም መኝታው እንደእረፍት የሚቆጠርበት መንገድ ትክክል አለመሆኑን መረዳት ይገባል። እረፍት ማለት መኝታ አይደለም። ማረፍ ማለት ሰውነት እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ ለተለያዩ በሽታዎች እንዲጋለጥ ማድረግ ተብሎ ሊተረጎም አይገባም። ማረፍ ማለት ቀደም ሲል ከነበረው አስጨናቂ ነገር አእምሮን ገለል አድርጎ ጥሩ ጥሩ ነገር እያሰቡ አዲስ ስላገኙት ነገር በተለይም ስለወለዱት ልጅ ምቹ ነገርን እያሰቡ ቀድሞ ከነበረው ውጥረት የበዛበት የኑሮ እንቅስቃሴ እራስን ገለል አድርጎ በመጠኑ እየተንቀሳቀሱ ለተወሰነ ጊዜ እራስን ማደስ ተብሎ ቢታሰብ ይበጃል። ከወለዱ በሁዋላ መተኛት የሚለው እጅግ ጎጂ የሆነና የተሳሳተ አስተሳሰብ መሆኑን ሁሉም ቢረዳው መልካም ነው። ስለዚህ አንዲት ሴት ከወለደች በሁዋላ ለተወሰነ ጊዜ እረፍት አድርጋ በየአንድ እና ሁለት ሰአቱ ልዩነት ለአስራ አምስት እና ሰላሳ ደቂቃ ያህል ከአልጋ እየተነሳች ብዙ ሳትርቅ ከክፍል ክፍል ዞር ዞር ማለት እና አቅሙዋም በጨመረ ጊዜ በደንብ በቤቷ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ማለት ይጠበቅባታል። ወደምግቡ ሁኔታ ስንመለስም... በወለዱ ጊዜ የሚመገቡት ምግቦች ስብ እና ጣፋጭ የበዛባቸው እንዲሆኑ አይመከርም። ይልቁንም በፈሳሽ መልክ የተዘጋጁ ምግቦችን እንዲሁም መጠጦችን እየወሰዱ በወለዱ ጊዜ የሚሰሩ የአካል እንቅስቃሴዎችን በየደረጃው በባለሙያ ምክር መስራት ሊከሰት የሚችለውን የደም መርጋት ሊያስቀር ይችላል። በተለይም ኦፕራሲዮን ሆነው የወለዱ ሴቶች ከቁስሉ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ምክንያቶችን ለራሳቸው እየፈጠሩ ፍርሀት ሰለሚያድርባቸው እራሳቸውን ከእንቅስቃሴ ሊገድቡ ስለሚችሉ የደም መርጋት ክስተቱን ሊያባብሱ ይችላሉ። ስለዚህ ማንኛዋም ወላድ የመጀመሪያዎቹን ስምንት ሰአታት ካረፈች በሁዋላ በየደረጃው የሰውነት ክፍሉዋን ማንቀሳቀስ ይጠበቅባታል.....
• እርግዝናና መውለድ የደም መርጋትን ከሚያባብሱ ነገሮች መካከል ናቸው። የደም መርጋት ችግር በሕይወት ዘመኑዋ አንድ ጊዜ ማለትም በእርግዝና ወይም ወሊድ ወቅት ብቻ የተከሰተባት ሴት እና በሌሎች የጤና ሁኔታዎች ወይንም በዘር ምክንያት ችግሩ የተሰከተባት ሴት በእኩል አይን አይታዩም። ስለዚህ ከእርግዝናው ወይንም ከመውለድ ጋር በተያያዘ ብቻ የደም መርጋት ሕመም የገጠማት ሴት ለዚህ ሕመም የዳረጉዋት ምክንያቶች ከተስተካከሉና ሕክምናውን በተገቢው መንገድ ወስዳ ለሚቀጥለው እርግዝና ብቁ መሆንዋን ሐኪም ካረጋገጠላት የሚቀጥለውን ልጅ ብዙም ሳትቆይ ማርገዝ ትችላለች። የደም መርጋት ችግር በተለያዩ ምክንያቶች እና በዘር የወረሱ ወይንም በተደ ጋጋሚ የሚከሰትባት እናት ከሆነች ግን በቀላሉ ወደ እርግዝናው እንድትገባ አይፈቀድም። ተከታታይ የሆነ የህክምና ክትትል አድርጋ የደም መርጋቱ ችግር በከፍተኛ ሁኔታ መወገዱ ሲረጋገጥ እና ሐኪሞች ሲወስኑላት ግን ልጅ መውለድ ትችላለች። (ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ - የጽንስና ማህጸን ሕክምና)
• በአጠቃላይ ግን በደም መርጋቱ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት የታማሚው የጤንነት ሁኔታ ፣የደም መርጋቱ የተከሰተበት ቦታ እና በምን ያህል ፍጥነት ሕክምና እንዳገኘ የመሳሰሉት ሁኔታዎች ደረጃውን ይለያዩታል። ብዙ ሰዎች በተለይም በእግራቸው ላይ የደም መርጋት ሕመም እንደደረሰባቸው ላያውቁ ይችላሉ። ምናልባትም ምልክቱ በግልጽ የማይታይ ሆኖ ወይንም ችላ ተብሎ ሊሆን ይችላል። በዚህም የተነሳ ወደ 25% የሚሆኑ ታማሚዎች የደም ቡዋንቡዋቸው በደም መርጋት ስለሚዘጋ በድንገት ይሞታሉ።
• የደረት ሕመም፣ የሆድ እቃ የላይኛው ክፍል ሕመም፣ ክንድ፣አንገት ወይንም መንጋጋ አካባቢ ሕመምና ስቃይ፣የምግብ አለመፈጨት፣ የትንፋሽ ማጠር፣ላብ ማላብ፣የማቅለሽለሽ ወይንም የማስመለስ እና የመሳሰሉት ሕመሞች ሲከሰቱ በፍጥነት ወደህክምና መሔድ ይገባል። ነገር ግን እነዚህ ምልክቶች ታዩ ማለት ሁልጊዜ የደም መርጋት ምልክቶች ናቸው ማለት አይደለም።

Read 12022 times