Saturday, 17 March 2012 10:42

“የሞት አምባሳደር” ሰው አልባ የጦር ጄቶች

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(0 votes)

በኢራን ሰማይ ላይ ሊያንዣብቡ እንደሚችሉ ተገለጸ

ኢራን በተለይ ከአሜሪካና ከእስራኤል እንዲሁም ከአውሮፓ አገራት ጋር ፊጥጫ ውስጥ ያስገባትን የኒኩሊየር ሃይል ግንባታ ጉዳይ በድርድር ካልፈታች የመጨረሻው አማራጭ   የጦር ጥቃት ሊሆን እንደሚችል በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡ አያድርገውና ድርድሩ ውጤት ካላመጣ አሜሪካና እስራኤል የኢራንን የኒኩሊየር ማብላያዎች ለማጥቃት የሚጠቀሙባቸውን ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች የተመለከቱ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡

የአሜሪካ አየር ሀይል ምክትል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሀርበርት ካርሊስሊን ጠቅሶ ዋሽንግተን ፖስት ባወጣው ዘገባ፤ አሜሪካ የኢራንን የኒኩሊየር ማብላያ ለማደባየት ከምትጥላቸው ቦንቦች አንዱ፣ እስከአሁን የጦር ግዳጅ ላይ ያልዋለ “በንከር በስተር” የተባለ ቦምብ እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡

“በንከር በስተር” የተባለው ቦምብ፤ 13600 ኪሎ ግራም ክብደት ያለው ሲሆን በብረት ኮንክሪት ውስጥ 65 ሜትር ሰርስሮ በመግባት የሚፈነዳ እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል፡፡ በሬዲዮ ጨረር እየተመራ በተፈለገው አቅጣጫ በመብረር፣ ከግማሽ የእግር ኳስ ሜዳ የሚበልጥ መሬት ውስጥ የተቀበረ ኮንክሪት ሰርስሮ በመግባት ኢራን በድብቅ የገነባችውን የኒኩሊየር ማብላያዎች የሚደረማምሰው ይኼ ቦንብ የሚወነጨፈው ከኢራን የሆርሙዝ የባሕር ዳርቻ፣ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ አምስተኛ ዕዝ ከተባለ የአሜሪካ የባህር ኃይል መርከብ ነው - ተብሏል፡፡

አሜሪካ በቅርቡ ወደ አካባቢው ያሰማራችው “ሊንከን 2” የተባለ ዘመናዊ የባህር ሃይል መርከብ እነዚህን አውዳሚ ቦምቦች እንደያዘ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

የኢራንን ተወንጫፊ ሚሳይሎች ለማደባየት ጥቅም ላይ ይውላሉ የተባሉት ሰው አልባ ጀቶች በፔንታጐን በጀት ሳንዲያጐ በሚገኘው “ጀነራል አቶሚክስ ካምፓኒ” የተሰሩ እንደኑ ታውቋል፡፡

ከነዚህ ሰው አልባ ጄቶች ወይም “ድሮንስ” መካከል “ፕሪዴተር” የተባለው ጄት  የሚገኝበት ሲሆን ጀቱ “ሄል ፋየር” የተባለውን ሚሳኤልና 225 ኪ.ግ የሚመዝኑ ቦምቦችን ተሸክሞ በመብረር በታለመው ዒላማ ላይ ያስወነጭፋል፡፡

ላስቬጋስ አቅራቢያ ከሚገኘው የአሜሪካ አየር ኃይል ጣቢያ በሳተላይት የሚደርሰውን መረጃ አንድ ሰከንድ ከ20 ሚሊ ሰከንድ ባልበለጠ ፍጥነት የሚቀበለው ሰው አልባ ጄት፤ በኢራን ሰማይ ላይ ለ40 ሰዓት ያለማቋረጥ ያንዣብባል፡፡

ከ”ፕሬዴተር” ጐን የሚሰለፉት “ሪፐር ግሎባል ሃውክ” እና “ዋሪየር አልፋ” የተባሉት ሰው አልባ ጄቶች ይሆናሉ ተብሏል፡፡

ድሮንስ የጐን ስፋቱና ርዝመቱ ቴኒስ መጫወቻ ሜዳ ያህል ነው፡፡ ከዋና ዋና ክፍሎቹ አንዱ አንገቱ ስር የተለጠፈው ክብ ቆብ የመሰለ “መልቲ ስፔክትራል ሴንሰር” ሲሆን ይኼ ክፍል ከ6,500 ጫማ  ከፍታና በ1,600 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ምድር ላይ በተረጩ ማይክሮ ቺፕሶች የሚተላለፈውን መረጃ ይቀበላል፡፡ ጄቱ ከአሜሪካ በሬዲዮ የሚደርሰውን ትዕዛዝ ተቀብሎ ዒላማውን የሚመታው በሰዓት 463 ኪ.ሜ እየከነፈ ሲሆን ትዕዛዙን  ከ1-2 ሰከንድ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይፈጽማል፡፡

ጥቁር ወለል ከሚመስለው ደረቱ ፊት ለፊት የተገጠመለት “ሊንክስ ራዳር ሲስተም” የተባለ የመገናኛ መሣሪያ ደግሞ ጥቃት የሚሰነዘርበትን ዒላማ በተመለከተ የምስል መረጃ ይቀበላል፡፡ የሬዲዮ ግንኙነቱ ቢቋረጥ ጄቱ ሰማይ ላይ እያንዣበበ ለመቆየት የሚያስችል ቴክኖሎጂም አለው፡፡

ጄቱ በክንፉ ሥር በስተቀኝ ከተደረደሩ አውዳሚ ሚሳኤሎች መካከል የመጀመሪያው “ኤም 9 ሳይድ ዋይንደር” በመባል የሚጠራ ሲሆን ሚሳይሉ ሙቀት እያመነጨ በአጭር ርቀት ተጠግቶ የታለመውን ጥቃት የሚፈጽም ነው፡፡ “ሳይድ ዋይንደር” የሚል ስም የተሰጠው ሙቀት እያነፈነፈ ከሚነድፈው “ሳይድ ዋይንደር” ከተባለ እባብ ባህርይ ጋር ስለሚመሳሰል ነው፡፡

ጄቱ በስተግራ ብብቱ ሥር የተሸጐጡ “ሄል ፋየር 2” የተባሉት ሶስት ሚሳይሎች የተገጠሙለት ሲሆን ሚሳይሎቹ ተራራና ህንፃ ቦርቡረው የሚያፈራርሱ፣ ተቀጣጣይ የፈንጂ ሐሩር የተሸከሙ ሲሆን፣ “ጂቢዩ 12 ፔቭ ዌይ 2” የተሰኘው ሚሳይል ደግሞ የታዘዘውን ዒላማ የሚመታው እንደ መብረቅ ነው፡፡

እያንዳንዱን ሰው አልባ ጄት ለመስራት 10 ሚሊዮን ዶላር የሚፈጅ ሲሆን ጄቱ 40 ሰዓታት ያለማቋረጥ በአየር ላይ ለማንዣበብ የሚያስችለውን ነዳጅ የሚሸከመው በክንፎቹ ውስጥ ነው፡፡

ከላይ በመጠኑ የቴክኖሎጂ አወቃቀሩንና ብቃቱን ለማሳየት የተሞከረው የድሮንስ ጥቃት ጐልቶ የተደመጠው እ.ኤ.አ በ2005 በፓኪስታን ግዛት ዳማዶላ በተባለ ቦታ የአልቃይዳ ሁለተኛ መሪ የነበረው ዶክተር አይመን አልዛዋሃሪ (በአሁኑ ወቅት የአልቃይዳ ዋነኛው መሪ) ተደብቆበታል በተባለ ህንፃ ላይ በፈፀመው ጥቃት ነበር፡፡ ነገር ግን ጥቃቱ እርሱን ሳያገኝ ስድስት የአልቃይዳ መሪዎችና 18 ንፁሀንን ገድሏል፡፡ በዚህ ጥቃት ወደ አቧራ ብናኝ ከተለወጡት ሬሳዎች ውስጥ የምዕራብ የአልቃይዳ ክንፍ መሪና የኬሚካል መሣሪያ ኤክስፐርት ሸሪፍ መሀመድ እንደሚገኝበት የታወቀው ከዓመታት በኋላ ነው፡፡

ከዚህ ጥቃት በኋላ ከ20 የአልቃይዳ አመራሮች ውስጥ ዘጠኙ መገደላቸውን የሚገልፀው ዜና ለፓኪስታን የደህንነት መሥሪያ ቤት የሚዋጥ አልነበረም፡፡ ይህንን አስመልክቶ ዘኒውስ የተባለው የፓኪስታን ዕለታዊ ጋዜጣ በጥቃቱ የተገደሉት የአልቃይዳ መሪዎችን 14 ያህል ሲሆኑ፣ ዒላማውን ስቶ 687 ንፁሀንን ፈጅቷል የሚል ወቀሳ ሰንዝሮ ነበር፡፡

አሜሪካ አሁን ብሏት 183 ሰው አልባ ጄቶች በተጨማሪ 387 ጄቶችን ከሚያመርቱ በ42 ግዛቶች ከሚገኙ የጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያዎች ጋር ኮንትራት የተፈራረመችው ኦባማ ሥልጣን በያዙ አመት ሳይሞላቸው መሆኑን ጄኔራል ዋርተን ሸዋርትዝ የተባሉ የቀድሞ አየር ኃይል አዛዥ ለዋሽንግተን ፓስት የሰጡት መረጃ አመልክቷል፡፡

አሜሪካ እነዚህን ሰው አልባ ጄቶች በኢራን አየር ላይ በማሠማራት ስለላ ከጀመረች ረጅም ጊዜ እንዳስቆጠረች ኢራን ከጥቂት ወራት በፊት በግዛቷ የወደቀውን አንድ ድሮንስ በቪዲዮ አስደግፋ ያቀረበችው መረጃ አመልክቷል፡፡

ከአሜሪካ ጋር እጅና ጓንት ሆና የመጨረሻው አማራጭ የተባለው የመሣሪያ ጥቃት በኢራን ላይ ለመፈፀም ዝግጅት እያደረገች የምትገኘው እሥራኤል “በንከር በስተር” የተባለውን 36 ሺህ ኪሎ የሚመዝን ቦምብ አሜሪካ እንድትሸጥላት ጥያቄ ያቀረበችው ባለፈው ሳምንት የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በዋሽንግተን ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር ባደረጉት ውይይት ነበር፡፡

ምንም እንኳ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሊዮን ፓኔታ የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ለኦባማ ጥያቄውን ማቅረባቸውን አላውቅም ቢሉም እሥራኤል ጠየቀችም አልጠየቀች የእሥራኤልን ህዝብ ከጥቃት ለመጠበቅ የተጣለብንን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የምንቆጥበው ኃይል የለም ማለታቸው የመረጃውን ዕውነታ የሚያመለክት ነው፡፡ ካለፉት 10 ዓመታት ወዲህ ሰው አልባ ጄቶች ድሮንስ የተባሉት እነዚህ ሰው አልባ ጄቶች በርካታ ጥቃቶችን አድርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2001 ዓ.ም መሀመድ አታፍ የተባለው የአልቃይዳ ከፍተኛ አመራር በአፍጋኒስታን፣ እንዲሁም በ2011 ዓ.ም ሌላኛው የአልቃይዳ አባል እና የአሜሪካ ዜግነት የነበረው አንዋር አል-አዋሊክ የተገደለው በየመን የተገደሉት በድሮንስ ነበር፡፡ እነዚህ ጄቶች እስካሁን አሸባሪዎችን ከማደንና የጦር ካምፖቻቸውን ከማፈራረስ በስተቀር ሉዓላዊ በሆነ አገር ላይ አልዋሉም፡፡ ይሁንና እነዚህ ጄቶች በእስራአል እጅ መግባታቸውን እስራኤል ኢራንን ለመምታት የሚያስችላትን አስተማማኝ ኃይል የሚያቀዳጇት በመሆኑ እስራኤል ጄቶቹን ከመጠቀም ወደ ኋላ እንደማትል ተገልጿል፡፡ የኒውክሊየር ጠበብቶች ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኢራን ላይ የመሣሪያ ጥቃት ቢሰነዘር የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪና ዕጥረት ይደርሳል የሚል ማስተባበያ ቢያቀርቡም ዋናው ፍራቻቸው የኒኩሊየር ማብላያዎቹ ላይ ሲሰነዘር አፈትልከው የሚወጡ የኒውክሊየር ጨረሮች ሚሊዮኖችን ሊፈጅ የሚችል አደጋ ያስከትላል የሚል ነው፡፡ በሩሲያ ከቼርኖቤል የኒውክሊየር ሀይል ማመንጫ አፈትልኮ በወጣ ጨረር እንዲሁም በጃፓን ፋክሹማ ግዛር በርዕደ መሬት የተናወጡ የኒውክሊየር ሀይል ማመንጫዎች ያፈተለከ ጨረር ያስከተለው አደጋን ለዚህ አካላቸው በዋቢነት ይጠቅሳሉ፡፡ የኒኩሊየር ጨረሮች በንፋስ ሞገድ እየተመሩ የሚሄዱበት አቅጣጫ መዳረሻቸው የማይታወቅ በመሆኑ አሜሪካ በጃፓን ላይ በሰነዘረችው የኒኩሊየር ቦምብ ጥቃት ለውግዘት ካበቋት ጥቁር የታሪክ አሻራ የባሰ መጥፎ ዕልቀትና ውግዘት ሊያስከትል ይችላል፡

 

 

Read 6002 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 10:48