Sunday, 26 February 2017 00:00

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለፉት 6 ወራት…

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በቀድሞ አትሌቶች በሚንቀሳቀስበት አዲስ ምዕራፍ ውስጥ ከገባ 6 ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ፌደሬሽኑ በኢትዮጵያ ስፖርት  ከሚንቀሳቀሱ መሰል ተቋማት በተሟላ በጀትና የገቢ አስተማማኝነት  ተጠቃሽ ነው፡፡ በስፖርቱ ያለፉ የቀድሞ አትሌቶች ወደ  አመራር መምጣታቸው ወደ የላቀ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ታምኖበት ነው።  በአደረጃጀትና በአሠራር የሚነሱት ጉድለቶች መሻሻላቸውም ተጠብቋል፡፡ ቀደም ሲል በአትሌቲክስ መሰረተልማቶች፤ በውድድሮች፤ በሆቴል፤ በሪል ስቴት እና ሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮች የሚንቀሳቀሱ  አትሌቶች  በስፖርቱ አስተዳደር ለውጥ ለመፍጠር እና ለማገልገል አቋም ይዘው መነሳታቸው ብዙ ተስፋዎችን ፈጥሯል።  ይህ የስፖርት አድማስ ሀተታ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ባለፉት 6 ወራት ያከናወናቸውን አበይት ተግባራት ይዳስሳል፡፡ ፌዴሬሽኑ የከፈታቸው አዳዲስ ምእራፎች፤ የብሄራዊ ቡድን ምርጫዎች፤ በተለያዩ ጊዜያት ከብሄራዊ ቡድን አትሌቶች እና አሰልጣኞች፤ ከሌሎች አትሌት ማናጀሮች፣ አሰልጣኞች፤ ክለቦች ተወካዮችና አትሌቶች ጋር ያካሄዳቸው የምክክር መድረኮች፤ የውይይት አጀንዳዎች ላይ ያተኩራል፡፡
የፌደሬሽኑ ታሪክና ያለበት ደረጃ
በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት ከ137 ዓመታት በፊት በትምህርት ቤቶችና በወታደራዊ ካምፖች በመዘውተር  እንደተጀመረ ይነገራል፡፡ ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው ተቋም ‹‹ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን›› በሚል መጠሪያ የተመሰረተው ከ68 ዓመታት በፊት ነው። በዓለም አቀፉ የስፖርት ህግ መሠረት በአንድ ሀገር በአንድ የስፖርት ዓይነት ሊኖር የሚችለው አንድ ሀገር አቀፍ ፌዴሬሽን ብቻ ነው፡፡ በፌደሬሽኑ ድረገፅ የተቀመጠው ታሪካዊ ዳራ እንደሚያወሳው ፌዴሬሽኑ የሀገሪቱን ሕግና ደንብ ጠብቆ በሕዝብ፣ በመንግስትና በድርጅቶች ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ሀገር አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ተግባራትን የሚያከናውንና ከአጠቃላይ የህብረተሰቡ አትሌቲክስ ስፖርት እንቅስቃሴ በመነሳት በተለይ የወጣቱን ትውልድ ግንዛቤና ተሳትፎ በማጠናከር የላቀ ችሎታ ያላቸው ምርጥ ስፖርተኞች እንዲፈሩ በማድረግ በአለም አቀፍ ደረጃ የአገራችንን ተወዳዳሪነትና ተጠቃሚነት ማስፋት በሚል አጠቃላይ ዓላማ የተቋቋመ ማህበር ነው፡፡
እንደፌደሬሽኑ ድረገፅ ሃተታ ከአህጉርና ዓለም አቀፍ ግንኙነት አኳያም  ፌዴሬሽኑ ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር፣ ከአዲዳስ ኩባንያ፣ ከአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን፣ ከምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅንና ከአቻ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት ጋር መልካም የሚባልና በአርዓያነት ሊጠቀስ የሚችል ግንኙነት ያደርጋል፡፡ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (IAAF) ፤በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን (CAA) እና በምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን (EAAR) አባልነቱ የሚንቀሳቀስም ነው፡፡
ፌዴሬሽኑ በየዓመቱ በሚያካሂዳቸው ከ10 በላይ የሃገር ውስጥ ውድድሮች ላይ የመላ ሃገሪቱ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች እንዲሳተፉ ያደርጋል። አትሌቶች ከሚያገኙት የቡድን ሽልማት፣ ከአትሌት ማናጀሮች ዓመታዊ ክፍያ፣ ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር፣ ከሕንፃ ኪራይ እና ከአዲዳስ ኩባንያ በድምሩ በየዓመቱ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሲኖረው፤ ከፌደሬሽኑ ገቢዎች ትልቁ ከአዲዳስ ኩባንያ ጋር ያለው የስፖንሰርሽፕ ስምምነት ሲሆን ለስምንት ዓመት በሚቆየው ውል፤ ለአንድ ዓመት 1.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያገኝ፤ ቦነሶችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ በሌላ በኩል በየውድድር ዘመኑ ውስጥ በፌደሬሽኑ ስር ለተካሄዱት ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች፣ በተለያዩ የመሰረተልማት ስራዎች፤ ለፌዴሬሽኑ ሰራተኞችና አሰልጣኞች ደመወዝና ስራ ማስኬጃ፣ ለትምህርትና ስልጠና፣ ለብሔራዊ ቡድን አትሌቶች ድጎማ፣ ለማርኬቲንግና ኮሚዩኒኬሽን፣ ለስፖርት ዕቃዎች ግዢ፣ ለሜዳና ለሕንፃ ጥገና፣ ለድጋፍ ለማበረታቻ እና ሽልማት እንዲሁም ሌሎች ለታቀዱ ስራዎች ማስፈፀሚያ እስከ 43 ሚሊዮን ብር ወጭ አለበት፡፡
የአዲሱ አመራር ልዩ አቅጣጫዎች
በሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ፕሬዝዳንትነት የሚመራው አዲሱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ሰራተኞች፣ ከአትሌት ተወካዮችና ከአትሌቲክስ አሰልጣኞች ጋር የትውውቅ መድረክ በማመቻቸት ስራውን ጀምሯል፡፡   በአትሌቲክሱ አጠቃላይ ጉዳዮች ዙሪያ ከአትሌት ተወካዮችና ከአሰልጣኞች ጋር ጥልቅና ጠቃሚ ውይይቶች በማድረግ ካለፉት አስተዳደሮች የተለየ ሆኗል፡፡ በቀጣይ 3 እና 4 አመታት በአትሌቲክሱ ኢትዮጵያን በተሻለ ውጤታማ ለማድረግ ያተኩሯል፡፡ ህፃናትን፣ ታዳጊዎችን፣ ወጣቶችንና አዋቂዎችን ከት/ቤቶች፣ ከፕሮጀክቶች፣ ከክለቦች፣ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር  ለማስተሳሰር የሚጥር ነው፡፡ በኢትየጵያ አትሌቲክስ የተዘበራረቀውን የስልጠና  የውድድር ሂደቶች ወጥ ማድረግ ይፈልጋል።  የአትሌቶችና የአሰልጣኞች - የአትሌቶችና የአትሌቶች - የአሰልጣኞችና የአሰልጣኞች የእርስ በርስ ግንኙነቶች በተሻለ ደረጃ ማስተካከል ይፈልጋል።  የእድሜ ማጭበርበር ለማስቀረትና በአትሌቲክስ ስፖርቶች ያለውን የተሳትፎ ውስንነት ለመለወጥም ተነስቷል። በአዲስ አበባ ላይ የሚታየውን የአትሌቶች ክምችትና ስልጠና ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲቀየር  ለአሰልጣኞች፣ ለክለቦች፣ ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ግንዛቤ በመፍጠር ተንቀሳቅሷል።  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ  ባንድ ወቅት እንደተናገረው ደግሞ … ሙያተኞች በየክልሎች ተዘዋውረው  ጥናቶችን የሰሩ ሲሆን፤ ከሩጫ ባሻገር ባሉ የአትሌቲክስ ስፖርቶች ከፍተኛ አቅም ያላቸው አካባቢዎች ተለይተው በመታወቃቸው፤ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ሊሰራበት ነው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና ሌሎች የስራ አስፈፃሚ አባላት በየጊዜው የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት እየተንቀሳቀሱም ናቸው። በእነዚህ መድረኮች የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችና አትሌቶች፣ የክለብ አትሌቶችና አሰልጣኞች፣ የአትሌቶች ማናጀሮችና ተወካዮች እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ናቸው፡፡  ፌዴሬሽኑ በየምክክር መድረኮች በተለያዩ የስፓርት አጀንዳዎች ዙርያ ግልፅ ውይይት በማድረግ ለማስተማር፣ ለማሳወቅ የሚሰራበት ሁኔታ ለስፖርቱ እድገትና ለውጥ ቅድሚያ ትኩረት መስጠቱን ያመለክታል፡፡ በየመድረኩ የአትሌቲክሱን ባለድርሻ አካላት የሚመራባቸውን አዳዲስ አሰራሮችና መመርያዎች በማስተዋወቅ እና በውይይት በማዳበር እየሰራ አዳዲስና ልዩ አቅጣጫዎችን ይዟል፡፡
የብሄራዊ ቡድኖች ምርጫና ከአዲስ አበባ ውጭ ዝግጅት
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የ2009 ዓ.ም የብሄራዊ ቡድን አትሌቶችና አሰልጣኞች ምርጫ በማካሄድ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያ ለሚኖራት ተሳትፎ የሚደረጉ ዝግጅቶችን አጠናክሯል፡፡ ብሄራዊ ቡድኖች ዝግጅቶቻቸውን ከአዲስ አበባ ውጭ እንዲደርጉ መወሰኑ ሌላው አዲስ አቅጣጫ ሲሆን፤ በዋናነትም አሰላ የሚገኘው የጥሩነሽ ዲባባ ማሠልጠኛ ማዕከል የመጀመርያው ተመራጭ ሆኖበታል፡፡ ፌደሬሽኑ  በስልጠና ፤ በዉድድር እና በእድገት ላይ በማተኮሩም ከ50 የማያንሱ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞችና ተያያዥነት ያላቸው ሙያተኞች በመፈፀም ወደ ስራ ገብቷል፡፡ ከከፍተኛ የአሰልጣኝነት ሹመቶቹም መካከከል ዶ/ር ይልማ በርታ የፕሮጄክቶች፣የማዕከላት፣የአካዳሚ፣ የክለቦች እንዲሁም የብሔራዊ ቡድን እና የማናጀሮች ስልጠና ዋና አስተባባሪ፤ መላኩ ደረሰ፤ የማዕከላት፣ የፕሮጄክቶች እና የአካዳሚ ስልጠና ክትትል፤ ትዕዛዙ ዉብሸት፤ የክለቦች ስልጠና ክትትል እንዲሁም መሰረት መንግስቱ፤ የማኑዋል ዝግጅት አስተባባሪ መሆናቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የብሄራዊ ቡድን  አትሌቶችን በተለያዩ የውድድር መደቦች የመረጠው ደግሞ መስፈርቶቹን በግልፅ በማሳወቅ ነበር፡፡ በ2009 ዓ.ም የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች የመምረጫ መስፈርት
በ2008 ዓ.ም በአህጉርና በዓለም ዓቀፍ ዉድድሮች የተሻለ ዉጤት ያስመዘገቡ፤ በ2008 ዓ.ም በአጭር ርቀት እና የሜዳ ተግባራት ከ1ኛ-2ኛ የወጡ፤ በ2008 ዓ.ም በመካከለኛ እና በረጅም ርቀት ስልጠና ምድቦች ከ1ኛ-3ኛ የወጡ፤ በአሰልጣኝ እይታ፤ ብቁ የሆኑት ተመልምለዋል፡፡
አክሳሪው የዶፒንግ ቀውስ
የዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገሮች ኤጀንሲ (ዋዳ) ኢትዮጵያን በዶፒንግ ቀውስ  ከሚገኙ አምስት አገራት ተርታ እንደፈረጃት ይታወቃል፡፡ አዲሱን ፌደሬሽን እየተፈታተኑ ከሚገኙ አሳሳቢ ሁኔታዎች ዋንኛው ነው፡፡ በአገር ደረጃ በተቋቋመው ብሔራዊ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገሮች ኤጀንሲ (ናዶ) አማካኝነት የመጀመርያው ግዙፍ ምርመራ የተካሄደው በቅርቡ ነው፡፡ ከአንድ መቶ በላይ አትሌቶች የደምና የሽንት ናሙና ሰጥተዋል፡፡ ናሙናዎቹ ወደ እውቅና ወደተሰጠው የኳታር  የምርመራ ማዕከል ቢላክም ተቋሙ ከጥራት ጋር በተያያዘ  በመታገዱ በፈረንሣይ የሚገኘው የምርመራ ማዕከል በምትኩ ተመርጦ ናሙናዎችን ተረክቦ እየመረመራቸው ነው፡፡ በዓለም አቀፉ ተቋም ዋዳ  በተሰጠው መመርያ  እስከ 200 ለሚደርሱ የኢትዮጵያ አትሌቶች ምርመራው በተያዘው የውድድር ዘመን ይቀጥላል፡፡ የዶፒንግ ምርመራዎቹ ሙሉ ወጪ የሚሸፈነው በኢትዮጵያ መሆኑ ቀውሱ ኪሳራ ሊያከትል እንደሚችል ያመለከተ ሲሆን፤  ለአንድ አትሌት የዶፒንግ ምርመራ እስከ 500 ዶላር እየተከፈለ ይገኛል፡፡ በፀረ - ዶፒንግ እንቅስቃሴ ዙሪያ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለውጭ ሃገርና ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አካላት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፕሬዝዳንቱ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ በአጠቃላይ እንዳመለከተው፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አትሌት ከአበረታች መድሃኒቶችና ቅመሞች አጠቃቀም እና ድርጊቶች ጋር ተያይዞ በIAAF 4 አመት እገዳ ከተጣለበትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባል ከሆነ ከአባልነት እስከ መጨረሻ ይታገዳል፡፡ አባል ካልሆነ ደግሞ እስከ መጨረሻ የብሔራዊ ቡድኑን አይቀላቀልም። በተጨማሪም ኢትዮጵያን ወክሎ በማንኛውም አይነት ሃገር አቀፍ፣ አህጉር፣ ዓለም አቀፍ እንዲሁም ማንኛውም ኢንተርናሽናል ውድድር መሳተፍ አይችልም፡፡ ዶፒንግን በተመለከተ ፌዴሬሽኑ ምንም አይነት ድርድር (ይቅርታ) ባይኖረውም፤ ለእውነተኛ እና ንፁህ አትሌቶቻችን መብት  በማንኛውም ሁኔታ እስከ መጨረሻ ድረስ ይሟገታልም ተብሏል፡፡
በዜግነት ቅየራ ላይ…
የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የሆነው አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ዜግነት ቀይረው ለማንኛውም አገር  እንዳይሮጡ ማገዱን አስታውቆ ነበር። ውሳኔው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረውን የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ስደት እና ዜግነት ቅየራ የሚከላከል መሆኑ ተገልጿል። የዜግነት ቅየራው የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በአገር አቋራጭ፤ በመካከለኛና በረጅም ርቀት የትራክ ውድድሮች እና በጎዳና ላይ ሩጫዎች የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች የበላይነት በማብዛት በውድድሮቹ ህልውና ላይ ተፅእኖዎች እየፈጠረ ቆይቷል፡፡
የማናጀሮች እና የአትሌቶች የስነምግባር ጉድለት፤ የስራ ውል
በተለያዩ ደረጃዎች በኢትዮጵያ አትሌቲክስ በአትሌት ማናጀርነትና ተወካይነት በመንቀሳቀስ ላይ በሚገኙት የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ፌደሬሽኑ ብዙ ችግሮች እየተፈጠሩበት ይገኛል፡፡ በርካታ ማናጀሮች በፌዴሬሽኑ በኩል የሚሰጣቸውን መመርያዎች ለማክበር እየተሳናቸው መቀጠሉ ፌደሬሽኑን አሳስቦታል።  ከሳምንት በፊት በተካሄደው 34ኛው የጃን ሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ የተከሰቱ ሁኔታዎች በናሙናት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ፌዴሬሽኑ በዚሁ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ክለቦችና ማናጀሮች አትሌቶቻቸውን በንቃት እንዲያሳትፉ ቢያሳስብም አትሌቶቻቸውን ወደተለያዩ የውጭ አገር ውድድሮች በመላክ ማሳሰቢያውን ያላከበሩት ጥቂት ማናጀሮች አይደሉም፡፡  ‹‹በፌዴሬሽኑ በኩል የቅጣት ርምጃዎችን መውሰድ ቀላል ነገር ነው፡፡››…የሚለው ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ፤ ‹‹ማናጀሮች የምናወጣቸውን መመርያዎች እና ደንቦች በተደጋጋሚ እየጣሱ በመሆናቸው ወደ ቅጣት ውሳኔዎች ለመግባት እያስገደደን ነው›› ብሏል። በአህጉራዊ ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ አገርን  ወክለው የሚሳተፉ የብሄራዊ ቡድን አባላት ሙያዊ ስነምግባሮችን ማክበር እንዳለባቸው፤ የተለያዩ የፌደሬሽኑ  መመርያዎችን የማያከብሩ አትሌቶች፣ አሰልጣኞችና ማናጀሮች በብሔራዊ ቡድን  ውስጥ ይዞ መቀጠል እንደማቻ እና በአትሌቲክሱ እንቅስቃሴ ህጋዊ እውቅና እንደማኖራቸው ስራ አስፈፃሚዎቹ በየመድረኮቹ እያሳሰቡ ናቸው፡፡
በአትሌቶችና በማናጀሮቻቸው መካከል በሚፈፀሙ የስራ ውሎች ላይም ችግሮች እየተፈጠሩ ናቸው፡፡ በሁሉም የአትሌቲክስ ባለድርሻ አካላት የሚፈፀሙ ውሎች ባለመኖራቸው ንትርኮች በዝተዋል፡፡ በአትሌቶችና በማናጀሮቻቸው መካከል በሚፈፀሙ የስራ ውሎች በአግባቡ እንደ ሰነድ ተዘጋጅተው፤ በሚመለከታቸው አካላት  የፀደቁ መሆን ነበረባቸው፡፡ ይሁንና ይህን ሂደት ባልተከተሉ ውሎች ለፌዴሬሽኑ የሚቀርቡ አቤቱታዎች እና ክሶች እየበዙ መጥተዋል፡፡ በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ የተመዘገቡ የአትሌቶች ማናጀሮች ብቻ ከአትሌቶች ጋር ለመስራት እና ውል ለመፈፀም የሚችሉበት እውቅና እንደሚያገኙ የሚገልፁት የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚዎች፤ ማናጀሮችና አትሌቶች ግልፅ የስራ ውል ፈርመው በማዘጋጀት ለፌደሬሽኑ ገቢ ማድረጋቸው በህጋዊነት ለመስራት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
የዶፒንግ ምርመራ መርሃ ግብሮች አለመከበር
በየዓመቱ የሚመረጡት የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ እና በዋዳ ክትትል እየተደረገባቸው በየጊዜው የዶፒንግ ምርመራ ውስጥ ይገባሉ። ስለሆነም በተለያዩ የውድድር መደቦች ለብሄራዊ ቡድን የተመረጡ አትሌቶች ይህን ወሳኝ መርሀ ግብር ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ ኃላፊዎች እንደሚገልፁት ግን ብዙዎቹ አትሌቶች፤ አሰልጣኞች እና ማናጀሮቻቸው ይህን ሁኔታ በቂ ትኩረት ባለመስጠታቸው አላስፈላጊ ጥፋቶች እየፈጠሩ መሆኑ አሳስቧቸዋል፡፡ በዶፒንግ ምርመራውና የክትትል መመርያ መሰረት ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡት አትሌቶች የ3 ወር መርኃ ግብራቸውን በዝርዝር በሚመዘግቡት ፎርም ያስታውቃሉ፡፡ ብዙ የኢትዮጵያ  አትሌቶች የመመዝገብ ችግር ባይኖርባቸውም በፎርም ላይ የመዘገቡትን መርሐ ግብር የማያከብሩ ሆነው ፌዴረሽኑን ለማያስፈልግ ትችት እያጋለጡት ናቸው፡፡  በቅርብ ጊዜ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ያጋጠመውን ሁኔታ በምሳሌነት ማንሣት ይቻላል፡፡  22 የብሔር ቡድን አትሌቶች ስለእለት መርሃ ግብራቸው በመዘገቡት መረጃ መሰረት የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ እና የዋዳ ተወካዮች ድንገተኛ ምርመራ ሊያካሄዱ ወስነው የገጠማቸው ነው፡፡ 22ቱ አትሌቶች በስታድዬም እንገኛለን ብለው ፎርም የሞሉ ቢሆንም በቦታው የተገኘው አንድ አትሌት ብቻ ነበር፡፡ በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍና ዋዳ የዶፒንግ ምርመራ እና ክትትል መመርያ ማንኛም አትሌት የ3 ወር መርሃግብሩን አለማክበሩ የሚያስቀጣው መሆኑን የሚያሳስበው ፌደሬሽኑ፤ ይህን ደንብ በተደጋጋሚ የሚተላለፉ አትሌቶች ቅጣት ሲወሰንባቸው ተዓማኒነት እያጎደለ የሚሄድ መሆኑ ያሳስበዋል፡፡
አሳሳቢዎች ውድድሮች በቻይና ምድር
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እጅግ ካሳሰቡት ሁኔታዎች ሌላኛው በቻይና በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በህገወጥ ዝውውር እና ግንኙነቶች የጉልበት እና የመብት ብዝበዛ ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ በቻይና በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ አትሌቶች በብዛት እየተሳተፉ መሆናቸው ለስፖርቱ እድገት ሳይሆን ውድቀት በር እየከፈተ ነው በማለት የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚዎች ይናገራሉ፡፡ አትሌቶች ከፌደሬሽኑ እውቅና ውጭ ቻይና ውስጥ በሚዘጋጁ ውድድሮች መሮጥ ማብዛታቸው ብቻ አይደለም። በህገወጥ ደላሎችና እውቅና በሌላቸው ማናጀሮች የጉልበት ብዝበዛ እየተደረገባቸው፤ ገንዘባቸው እየተመዘበረ እና ለዶፒንግ እግሮች እያጋለጣቸው መሆኑ በፌደሬሽኑ በኩል ተረጋግጧል፡፡
በቻይና የሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ  ለመሳተፍ የሚቻለው በፌደሬሽኑ ተመዝግቦ እውቅና ባገኘ ማናጀር ብቻ ነው፡፡ በህገወጥ ደላሎች እና የአትሌት ተወካዮች ነን በሚሉ ግለሰቦች ፌደሬሽኑ ሳያውቀው የሚደረጉ የውድድር ተሳትፎዎች ህገወጥ መሆናቸውን ፌደሬሽኑ አስገንዝቧል፡፡ ብዙሃነ እየተፈፀመ ነው ተብሏል፡፡ አትሌቶችን ለክፉ አደጋዎች ከሚያጋልጡ ሁኔታዎች የመጀመርያው በቻይና በሚደረጉ ውድድሮች የሚቀርቡት የ40ሺ እና የ60ሺ ዶላር የገንዘብ ሽልማቶች ሲሆኑ አትሌቶች  ስፖርቱ በማይፈቅደው መንገድ በ1 ወር ውስጥ ሁለት  ማራቶኖች ለመሮጥ፤ በ18 አመታቸው ውድድር ለማድረግና በዶፒንግ ቀውስ ውስጥ ለመግባት የሚዳርጋቸው ሆኗል፡፡ ፌዴሬሽን እንደሚያሳስበው ወደ ቻይና አትሌቶችን የሚልኩ ማናጀሮች የተመዘገቡና ህጋዊ እውቀና ያገኙ መሆን አለባቸው፡፡ ይህን ያልተገበረ ማንኛውም አትሌት ሆነ ማናጀር ኢትዮጵያ መወከል አይችልም፡፡ከወከለም የቅጣት እርምጃ ይጠብቀዋል፡፡

Read 2473 times