Sunday, 26 February 2017 00:00

የዛፉ ፀሎት

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(10 votes)

  እኔ ዛፍ ነኝ፡፡ የምተነፍስ፣ የምወለድ፣ የማድግ፣ የምራባና የምሞት ነኝ፡፡ ህይወት ያለኝ የፈጣሪ ፍጡር ነኝ፡፡ አሁን ግን ልሞት ነው፡፡ አሳዳሪዬ ሊያስቆርጠኝ ወስኗል፡፡ ይሄን እንዴት እንደማውቅ መጠየቅ የለብኝም፡፡ በቃ አውቃለሁ፡፡
የተከለኝ የአሳዳሪዬ ቅድመ አያት ነበር፤ ልጁ ደግሞ ተንከባክቦ አሳደገኝ፡፡ የልጅ ልጅ፣ ልጁን አይቻለሁ፡፡ እድሜዬ መቶ ዓመት አልፎታል። አሁን ግን ልሞት ነው፡፡ አሳዳሪዬ ሊቆርጠኝ ወስኗል። ለሱ፣ ለአባቱና ለአያቱ የህይወት ምንጭ ነበርኩ። የተቃጠለ አየራቸውን ወስጄ ንፁህ እስትንፋስ በምትኩ እሰጣቸው ነበር፡፡ ልጆቻቸው በዙሪያዬ ይጫወቱ ነበር፡፡ ከጠራራውና ከሚያቃጥለው ፀሐይ በጥላዬ እከልላቸው ነበር፡፡ አሁን ግን ልሞት ነው፡፡ አሳዳሪዬ እንድሞት ወስኗል፡፡ ያልገባው ነገር፤ ከኔ መሞት በኋላ የሱ ሞት እንደሚመጣ ነው፡፡
አገልግሎቴ በዚህ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ከጠራራጊው ጎርፍ ለሙን አፈር በጠንካራ ስሮቼ ይዤ አቆይቼዋለሁ፡፡ እኔ ስለነበርኩ አፈሩ ተጠራርጎ አልተወሰደም፡፡ አሳዳሪዬ እህል ዘርቶ፣ ቡቃያ አፍርቶና ምርቱን አጭዶ እርሱንና ቤተሰቦቹን የሚመግበውም እኔ በጠበቅኩት ለም አፈር እንደሆነ አላወቀም፡፡ ስለዚህ ሊያስቆርጠኝ ወስኗል፡፡
አሳዳሪዬ በፍቅረ ንዋይ ልቡ ታውሯል፡፡ እኔን ካስቆረጠኝ በኋላ ግንዴ፣ ቅርንጫፌና ቅጠሎቼ የሚያወጡትን ገንዘብ እያሰላ ነው፡፡ ትናንትና አንድ ዛፍ ቆራጭ ይዞ መጣ፡፡ ቆራጩ መንፈሱ የጠቆረ፣ የብዙ የኔን መሳይ ዛፎች ግብአተ መሬት የፈፀመ ጨካኝ ሰው ነው፡፡ ከአሳዳሪዬ ጋር በገንዘብ ተስማማና በነጋታው እንደሚመጣ ነግሮት ሄደ፡፡
አሳዳሪዬ እኔን የመግደል መብት አልነበረውም። በዚች ምድር ላይ የመኖር መብታችን ለኔም ለሱም እኩል ነው፡፡ ምክንያቱም፤እኔም እሱም የፈጣሪ ፍጡሮች ነን፡፡ ዛፍ በመሆኔ የተፈጥሮን ሚዛን አጠብቃለሁ፡፡ አስፈላጊ ባልሆን ኖሮ ባልተፈጠርኩኝ ነበር፡፡ እግዜር የፈጠረኝ ለተፈጥሮ፣ ለምድርና ለሰው ልጅ ጠቃሚ ስለሆንኩኝ ነበር፡፡
ይሄ የመጨረሻ ፀሎቴ ነው፡፡ እግዜሩ ባንዳች ተአምር የአሳዳሪዬን ልብ እንዲያራራልኝ እፀልያለሁ፡፡ የማዝነው ለራሴ ብቻ ሳይሆን … ለእራሱ ለአሳዳሪዬ፣ ለልጆቹና ለልጅ ልጆቹ ጭምር ነው፡፡
እነሆ አሳዳሪዬ ከአራት ዛፍ ቆራጮችና ከሁለት ሌሎች ሰዎች ጋር ወደኔ እየመጣ ነው፡፡ ሁለቱን ሰዎች አውቃቸዋለሁ፡፡ አንደኛው፤ የመንደሩ አናጢ ሲሆን ሁለተኛው የመንደሩ ሬሳ ሳጥን ሻጭ ነው፡፡ አሳዳሪዬ፤ግንዴንና ቅርንጫፎቼን ለነዚህ ሰዎች ሊሸጥላቸው አስቧል፡፡ እኔ ግን በረጃጅም ቅርንጫፎቼና ቅጠላ ቅጠሎቼ፣ ዝናብን ወደ ምድር እስብ ነበር፡፡ ዝናቡ በስሮቼ የያዝኩትን ለም አፈር ያርስና … የተዘራውን ዘር ቡቃያ ሆኖ እንዲያብብ ያደርጋል፡፡ አሳዳሪዬና ቤተሰቡ አመቱን ሙሉ የሚመገቡትንና ለትርፍ የሚሸጡትን እህል ያመርቱ ነበር፡፡ አሁን ግን ልሞት ነው፡፡ አሳዳሪዬ ሊያስቆርጠኝ ወስኗል፡፡ እኔም የመጨረሻ ፀሎቴን አድርሻለሁ፡፡
                  *          *        *
ጉልቴ ይመር ዛሬ በለስ ቀንቶታል፡፡ ዛፉን ቆርጦ ለመገንደስ ግማሽ ቀን ቢፈጅም ጠቀም ያለ ገንዘብ ስላተረፈ ብዙ አልተከፋም፡፡ ለቆራጮቹ ሁለት መቶ ብር ቢከፍልም፣ ከአናጢው ሶስት ሺህ ብር ስለተቀበለ፣ ወጪው እምብዛም አልከበደውም። ይህ ሁሉ ሲሆን፤ የተሸጠው የዛፉ አንድ አራተኛ የሚሆነው ግንድና ቅርንጫፍ ብቻ ነው፡፡ ገና ሲሶው የሚሆነው የዛፉ እንጨት በእጁ ነው። ጉልቴ ገንዘብ ላይ ቀልድ አያውቅም። ደፋሩ የሬሳ ሳጥን ሰሪ፣ ዛፉ እንደሚቆረጥ ሲሰማ፣ ለምን አብሮት እንደመጣ ገብቶታል፡፡ ለምን አጥብቆ ሰላምታ እንደሰጠውና የዘር ማንዘሩን ጤንነት እንደጠየቀም አልጠፋውም። ሰውየውን በቅርበት ቢያውቀውም፣ ገንዘብ ላይ ግን የለየለት ቆጥቋጣ እንደሆነም ሰምቷል፡፡ አሁን የሚፈልገው ያንን ግንድ በርካሽ እንዲሸጥለት ወይም በዱቤ እንዲሰጠው ነው፡፡
“አይሞከርም!” ሲል ለራሱ መለሰ፤ጉልቴ ብሩን ኪሱ እየከተተ፡፡ ወዲያውኑም ፊቱን ወደ ቆራጮቹ አዙሮ፤ “ጠባቂ እስክልክ ድረስ እዚህ ቆዩ” አለና ወደ መንደሩ የሚወስደውን መንገድ ተያያዘው፡፡ ሰፈሩ እንደደረሰ፣ ዛፉን የሚጠብቁ ሰዎች ወደ ቦታው ከላከ በኋላ አረቄ ለመቀማመስ ወደ አሰገደች ቤት አመራ፡፡ ሶስት መለኪያ አጋብቶ አራተኛውን እንዳስቀዳ፣የሬሳ ሳጥን ሰሪው አሰገደች ቤት ሲገባ ተመለከተው፡፡
አጠገቡ ሄዶ ተቀመጠ፤ባርኔጣውን አንስቶም ሰላምታ ሰጠው፡፡ ጉልቴ አፀፋውን መለሰ፡፡ ሰውየው ጠላ አስቀዳ፡፡
‹‹ደፈርከኝ አይበሉኝና አያ ጉልቴ፤ እንጨቱን ለመውሰድ ፈልጌ ነበር›› አለና ጉዳዩን አፈረጠው፡፡
‹‹ይቻላል፡፡ ገንዘብ ከከፈሉኝ ምን ገዶኝ›› አለ ጉልቴ፤ ሰውየውን ለመገላገል፡፡
‹‹ስንት ነው የሚሉት?››
‹‹ምን ያህል ነው የፈለጉት?››
‹‹ከሲሶው አንዱን እጅ››
‹‹ሶስት ሺህ ብር››
‹‹በጣም በዛ!››
‹‹ከዚህ ድምቡሉ አልቀንስም፡፡ አናጢውም የወሰደው በዛው ዋጋ ነው››
‹‹እኛና እነሱን ማን አንድ አደረገን? እኛ እኮ ስራ የለንም፤ ከየት እናመጣለን?›› አለ ሬሳ ሳጥን ሰሪው፡፡
‹‹ስራ የለንም ይላሉ?›› አለው ጉልቴ፤በሰውየው አነጋገር እየተገረመ፡፡
‹‹መቼም ሳንበላ አላደርንም፡፡ ከስንት አንዴ ለኛም ይጥልልናል … ይመስገን››
‹‹እውነት ነው፤ እሱ ሁሉንም ያያል” አለ ጉልቴ።
‹‹ሁለት ሺህ ብር፣ቀሪው አንድ ሺህ እዳ ይሁንብኝ፤ሰርቼ ልከፍል›› አለ ሰውየው፤ሁለት ሺህ ብሩን ከኪሱ እያወጣ፡፡
ጉልቴ ትንሽ አሰበ፡፡ ምንም ወጪ ሳያወጣ ሁለት ሺህ ብር ቢያገኝ ምን ይጎዳል? በዚያ ላይ ሰውየው ሰርቶ ይከፍላል፡፡
‹‹ማለፊያ!› አለና ብሩን ተቀበለ፡፡
‹‹ሐሳብ አይግባዎት …. አያ ጉልቴ፡፡ እዳዬን በፍጹም አልረሳም››
ሬሳ ሳጥን ሰሪው፣ባርኔጣውን አንስቶ አመሰገነና ሂሳቡን ከፍሎ ወጣ፡፡
ይህ ከሆነ አስር አመታት ተቆጠሩ፤ነገሮች እንደ ድሮ አይደሉም፡፡ በአገሩ ድርቅ ከገባ አራት አመታት አለፉ፡፡ ዝናብ ከእነ አካቴው ጠፋ፡፡ ዛፎቹ በሙሉ ተቆርጠው አልቀዋል፤አፈሩ እየተሸረሸረና ለምነቱን እያጣ፣ አገሩ በንዳድና በሐሩር ወደ በረሃ ተለውጧል፡፡ በድርቁ ምክንያት ሰው ሁሉ ቀዬውን ለቆ ወደ ሌላ ቦታ ተሰዷል፡፡
ጉልቴ የአልጋ ቁራኛ ከሆነ አመት አልፎታል፡፡ ገንዘቡና ጥሪቱ ባለፉት አመታት ንፋስ እንደበተነው አቧራ ብን ብሎ ጠፍቶበታል፡፡ ቤተሰቡና ልጆቹ የሚላስ የሚቀመስ አጥተው፣ነፍሳቸውን ለማዳን ሲሰደዱ ‹‹ከአገሬ አልወጣም›› ብሎ የቀረው እሱ ብቻ ነበር፡፡ አጥንቱ ሞግጎ አልጋ ላይ ተንጋሏል፡፡ ላለመሞት ለረጅም ግዜ ሲታገል ቆይቷል፡፡ አሁን ግን እጅ ሰጠ፡፡ በሽታው ከረሃቡ ጋር አንድ ሌሊት እንደማያሳድረው አወቀ፡፡ በደህና ጊዜ ፊደልም ቢሆን ትንሽ ቆጥሮ ነበረና … በሰለለ እጁ ቢክ እስክሪፕቶ ይዞ፣ብጣሽ ወረቀት ላይ አንድ አረፍተ ነገር ፃፈ፡፡
ከድርቅ የተረፉትንና ሞታቸውን የሚጠብቁ ጎረቤቶቹን ጠርቶ ወረቀቱን ሰጣቸው፡፡ ከእነሱ ደህና ጉልበት ያለው ወረቀቱን ይዞ ወደተላከበት ተፈተለከ፡፡ ሬሳ ሳጥን ሰሪው ወረቀቱን ካነበበ በኋላ ወደ ጉልቴ ቤት አመራ፡፡ እዚያ ሲደርስ ግን ጉልቴ ህይወቱ አልፏል፡፡
ለሬሳ ሳጥን ሰሪው የደረሰው መልእክት፡- ‹‹እዳህን የምትከፍልበት ሰአት አሁን ነው፤ቀኔ ስለደረሰ የሬሳ ሳጥን ያስፈልገኛል›› የሚል ነበር፡፡
ጉልቴ የተቀበረበት የሬሳ ሳጥን የተሰራው ከተቆረጠው ዛፍ መሆኑን ግን ከሬሳ ሳጥን ሰሪው በስተቀር ማንም አያውቅም፡፡

Read 3620 times