Sunday, 26 February 2017 00:00

የቱሉ ዲምቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ገመና

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(28 votes)

    በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወረዳ ዘጠኝ በ2007 ተመርቆ ለእድለኞች የተሰጠ 408 ብሎክና 10608 አባወራ የያዘው የቱሉ ዲምቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነዋሪዎች፤ በውሃ፣ በመብራት፣ በጤና እና ሌሎች መሰረተ ልማት እጥረቶች መማረራቸውን ገለፁ፡፡ የአዲስ አድማስ ሪፖርተሮች ከትላንት በስቲያ በስፍራው ተገኝተው ለመታዘብ እንደቻሉት፤ ነዋሪው በውሃ፣ በመብራት፣ በመፀዳጃ ቤትና በጤና ጣቢያ እጦት ችግር ውስጥ መውደቃቸውን መታዘብ ችለዋል፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሚያዚያ 2007 ዓ.ም ያወጣው ‹‹ፍኖተ አዲስ›› የተባለ ልዩ ዕትም መፅሄት፣ በቱሉ ዲምቱ ሳይት 10608 አባወራዎች የቤት ባለ ዕድል መሆናቸውን ጠቅሶ፤ በዚህ ሳይት 7130 ሜትር መንገድ መገንባቱን፣ ከዚህም ውስጥ 4700 ሜትሩ የኮብል ስቶን ንጣፍ መልበሱንና ቀሪው 2430 ሜትር መንገድ አስፓልት መደረጉን ይገልፃል። ይህን መሰረተ ልማት ለማሟላት ለኮብል ስቶን ንጣፍ 213 ሚ. 531 ሺ 1023 ብር ወጪ ማድረጉን የገለፀው ባለስልጣኑ፤ የአስፓልት መንገድ ለመሥራት 103 ሚ. 081 ሺህ 136 ብር ከ60 ሳንቲም ለመብራትና ለስልክ አገልግሎት፤ 105 ሚ. 409 ሺህ 201 ብር ከ36 ሳንቲም በማውጣት መሰረት ልማቱ መሟላቱን የገለፀ ሲሆን አዲስ አድማስ በቦታው ተገኝቶ ባደረገው ቅኝት በሳይቱ አንድም የአስፓልት ንጣፍ መንገድ መመልከት አልቻለም፡፡ መብራትም ቢሆን በአነስተኛና ጥቃቅን ለተደራጁ ብሎኬት አምራቾች የገባ እንጂ ለነዋሪዎች እንዳልገባ ለመገንዘብ ችለናል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች እነዚህ ድርጅቶች መስመር ዘርግተው ሲጠቀሙ መቆየታቸውን ገልፀው፤  የወረዳ ዘጠኝ አስተዳደር ግን፤ ‹‹ድርጅቶቹ የገባላቸውን መብራት ለሶስተኛ ወገን አሳልፈው መስጠታቸውን በተለይ ወንጀል እንደሆነ በመጥቀስ በሶስት ቀን ውስጥ ካላቋረጡ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድም ማስጠንቀቂያ ፅፎላቸዋል›› ያሉት የአካባቢው ነዋሪዎች የመፀዳጃ፣ የጤና ጣቢያ፣ የት/ቤት፣ የቆሻሻ ክምር፣ ያማረረን ሳያንስ የወረዳ አስተዳደሩ ጨለማ ውስጥ ሊጥለን ነው በማለት ለብሎኬት አምራቾቹ የተፃፈውን ደብዳቤ በመያዝ አቤቱታ እያሰሙ ነው፡፡
‹‹መንግስት ሁሉን አሟልቻለሁ ቢልም ‹‹ጤና ጣቢያ፣ ውሃና መብራት የለንም›› ያሉት ነዋሪዎቹ፤ የመጠጥ ውሃ ሣይቀር በጋሪ ሩቅ ሄደው ከወንዝ እንደሚቀዱ ገልፀው፤ የሽንት ቤት መስመሮች ከዋናው መስመር ጋር ባለመገናኘታቸው ለመፀዳጃ ችግር መጋለጣቸውን ጠቁመው፤ በተለይ ብሎክ 83ትን  በዋቢነት ጠቅሰዋል፡፡ በG7 ቤት ከላይ የሚኖሩት ነዋሪዎች ተጠቅመው የሚለቁት ዐይነ ምድር በኩሬ መልክ ምድር ቤት ላይ የተራቀመ ሲሆን፤ ሽታው ለአካባቢው የጤና ችግር ሆኗል፡፡ በዚህ ብሎክ ላይ ገና ሰው ያልገባባቸው  በርካታ ክፍሎች ለመፀዳጃ ቤትነት  ውለዋል፡፡ በሳይቱ 480 ብሎክ የተሰራ ሲሆን፤ አንዱ ተደርምሶ፤ ፍርስራሹ ተወግዶ ካርቶን ለብሶ ተመልክተዋል። በወረዳው በጨረታ ቤት ገዝተው ንግድ ላይ የተሰማሩ ወደ 300 የሚጠጉ ነጋዴዎች በበኩላቸው ንግድ ቤቶቻቸውን ለማልማት ጥያቄ አቅርበው የነበረ ሲሆን‹‹ወረዳው አዲስ በመሆኑ ባለሙያ የለንም ማልማት ትችላላችሁ›› እንደተባሉ የገለፁ ሲሆን፣ አሁን ግን እስከ 250 ሺህ ብር ወጪ የተደረገበት በረንዳ ግሪልና ቴራዞ ያለ አግባብ እየፈረሰ ሳይቱ ውበቱን ከማጣቱም በላይ፤ ነጋዴው ለፍተኛ ኪሳራ እየተዳረገ ነው ሲሉ አማርረዋል፡፡
በጀሞ፣ በልደታና በሌሎች ሳይቶች በጨረታ ተገዝተው የለሙ ንግድ ቤቶችን በማየት በከፍተኛ የጨረታ ዋጋ ቤቶቹን መግዛታቸውን የተናገሩት ነጋዴዎቹ፤ የወረዳው አስተዳደር ለሳይቱ ፅዳት፣ መብራት ውሃና መሰል መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ሳይተጋ፤ የለማን ለማፍረስ ሩጫ ላይ ነው›› ብለዋል፤ ነጋዴዎቹ። ‹‹አንዳንዶቻችን ፍ/ቤት ሄደን እግድ ባናወጣ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ኪሳራ ይደርስብን ነበር›› ያሉት ባለሀብቶች፤ ያላሳገዱትን የወረዳ መስተዳደሩ እንዴት እንዳፈረሰውና ሳይቱን ለተጨማሪ ጉስቁልና እንደዳረገው ተናግረዋል። በዚህ ሁኔታ የንግድ ቦታቸው ሲፈርስ ያለቀሱ፣ መሬት ላይ የተንከባለሉ ነጋዴዎች እንደነበሩ ‹‹ወረዳው ይህን ለምን አደረግህ›› በሚል በፖሊስ ሲያስደበድቡ የሚያሳይ ቪዲዮ በዋቢነት አቅርበዋል፡፡  እነዚህ ተበዳይ ነን የሚሉ ባለሀብቶች፣ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንዲገባ ተማፅነዋል፡፡

Read 7826 times